የአንድ ፈረስ ግልቢያ

0
85

የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ በአውሮፓ ካሉ ሊጐች በብዙ መልኩ ይለያል ቢባል ስህተት  አይሆንም፡፡ ለዚሁ አባባል አስረጂ ይሆን ዘንድ አብነቶችን መጥቀስ ካስፈለገም በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ በዓለም ዙሪያ በርካታ ተከታዮች እና ደጋፊዎች ያሏቸው ክለቦች መኖራቸውን እንደ አንድ አብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

አብነቱ ግን ይህ ብቻ አይደለም፤ በእንግሊዝ  ፕሪምየር ሊግ መጫወት የሚፈልጉ በርካታ እግር ኳሰኞች መኖራቸው፣ በሊጉ ዋንጫ ለመሳም የሚደረገው ትንቅንቅ ከባድ መሆኑ፣ እንግሊዝ የእግር ኳስን ፈጣሪ ነኝ ከማለቷ በተጨማሪ የእንግሊዝ የመገናኛ ብዙኃን ለሊጋቸው የሚሰጡት መጠነ ሰፊ ሽፋን፣ በፕሪምየር ሊጉ ላለመውረድ የሚደረጉት ትንቅንቆች፣ የአህጉራዊ ጨዋታን ለማግኘት የሚደረገው ፍልሚያ እና ሌሎችም እግር ኳሳዊ ሁነቶች የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግን በዓለም ላይ  ተወዳጅ ሊግ እንዲሆን አድርጐታል ብንል መረጃ ጥቀሱ የሚለን አይኖርም፡፡

የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ እ.አ.አ በ2024/25 የውድድር ዘመን ግን ብዙ አጓጊ ፋክክሮችን አጥቶ ይገኛል፡፡ እዚህም ጋር አብነት ለመጥቀስ ያህል ዘንድሮ ፕሪምየር ሊጉን የተቀላቀሉት ሳውዝ አምፕተን፣ ሌስተር ሲቲ እና ኤፕሲዊች ታውን በፕሪምየር ሊጉ ለመቆየት መፎካከር ተስኗቸው በመጡበት እግራቸው ወደ ሻምፒዮን ሺፑ ሊመለሱ መሆኑን መጥቀስ ይቻላል፡፡

በፔፕ ጋርዲዮላ የሚመሩት ውኃ ሰማያዊ ለባሾቹ ማንቸስተር ሲቲዎች በአረቦች ረብጣ ዶላር እና በስፔናዊው የእግር ኳስ ሊቅ ፔፕ ጋርዲዮላ እየተመሩ ለአራት ተከታታይ ዓመታት የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ወደ መደርደሪያቸው ሲወስዱ ተፎካካሪ አልነበራቸውም ማለት አይቻልም፡፡ በተለይ የሰሜን ለንደኑ አርሴናል በሌላኛው ስፔናዊ የቀድሞ ተጨዋቹ ሚኬል አርቴታ እየተመራ ያለፉትን ሁለት ዓመታት ከማንቸስተር ሲቲዎች ጋር እስከ ውድድሩ ማብቂያ ድረስ ፍልሚያ አድርጎ ዋንጫውን ለሲቲ አስረክቧል፡፡

በስፔን ላሊጋ እስከ 30ኛው ሳምንት ባርሴሎና በ67፣ ሪያል ማድሪድ 63 እና አትሌቲኮ ማድሪድ 60 ነጥቦችን ይዘው ለዋንጫው አጓጊ ፍልሚያ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ በጣሊያን ሴሪኤም እስከ 31 ኛው ሳምንት ኢንተር ሚላን 68፣ ናፓሊ 65 እና አታላንታ 58 ነጥቦችን አስመዝግበው የሴሪኤውን ዋንጫ ከፍ ለማድረግ እየተፎካከሩ ይገኛሉ፡፡

የጀርመኑ ቡንደስ ሊጋም በ28ኛው ሳምንት ባየር ሙኒክ 68 እና ባየር ሊቨርኩሰን 62 ነጥቦችን ይዘው ለድል እየተፎካከሩበት ይገኛሉ፡፡ የፈረንሳዩ ሊግ አንድ ግን ፒኤስጂ አራት ጨዋታዎች እየቀሩት ለአራተኛ ተከታታይ ዓመታት ሻምፒዮን እንዲሆን አድርጐት ተጠናቋል፡፡

ዘንድሮ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ለዋንጫ የሚደረገው ፉክክር “የተበላ ዕቁብ” የሚባለው ዓይነት ሆኗል፡፡ በእርግጥ ይህንን ዘገባ ስናዘጋጅ 31ኛ ሳምንቱ ላይ የሚገኘው ፕሪምየር ሊጉ ሊቨርፑልን በ73 ነጥቦች በደረጃው አናት ላይ አስቀምጦ አርሴናል በ62 ነጥቦችና ከመሪው ሊቨርፑል በ11 ነጥቦች አንሶ በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ አስገድዶታል፡፡

ኖቲንግሀም ፎረስት 57፣ ቼልሲ 53፣ ኒውካስል ዩናይትድ 53 እና የአምናው ሻምፒዮና ማንቸስተር ሲቲ ደግሞ 52 ነጥቦች ይዘው ለአውሮፖ ጨዋታዎች ተሳትፎ መፎካከር እንጂ ከዋንጫው በጣም ርቀዋል፡፡

የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ቀሪ ሰባት ጨዋታዎችን እና 21 ነጥቦችን ይዞ ለዋንጫ የሚደረገውን ፉክክር “አልተጠናቀቀም” የሚል ቢሆንም ኔዘርላንዳዊው አርኔ ስሎት ከጀርመናዊው ጀርገን ክሎፕ፣ የተረከቡትን ሊቨርፑል በመጀመሪያ ዓመታቸው የዋንጫ ባለቤት ሊያደርጉት ከቀሪ ሰባት ጨዋታዎች ማሸነፍ የሚጠበቅባቸው አራት ጨዋታዎችን ብቻ ሆኗል፡፡ ይህም የሚሆነው ሊቨርፑልን በሁለተኛነት የሚከተለው አርሴናል በቀሪ ጨዋታዎች የማይሸነፍ እና ነጥብ የማይጥል ከሆነ ብቻ ነው፡፡

ሚስተር “ሁለተኛ” የሚል ቅፅል ስም ሊያገኝ እየተንደረደረ የሚገኘው የሰሜን ለንደኑ አርሴናል ዘንድሮም የሦስተኛነት ደረጃን በመያዝ ሦስታታ (ሀትሪከ) የሚሠራ ይመስላል፡፡ ያለፉትን ሁለት ዓመታት በሚያስቆጭ መልኩ ዋንጫውን ለማንቸስተር ሲቲ ያስረከቡት መድፈኞቹ ዘንድሮም በሚያስቆጭ ወይም በማያስቆጭ መልኩ ዋንጫውን ለሊቨርፑሎች እንደሚያስረክቡ ግምቶች በዝተዋል፡፡

ቀዮቹ እስከ ቅርብ ጊዜያት ድረስ ለሦስት ዋንጫዎች ይጫወቱ የነበረ ቢሆንም በሻምፒዮንስ ሊጉ በፈረንሳዩ ፒኤስጂ እና በሊግ (ካራባው) ዋንጫ ደግሞ በኒውካስል ተሸንፈው አሁን ለብቸኛው ዋንጫቸው (ለፕሪምየር ሊጉ) በመፋለም ላይ ይገኛሉ፡፡

በ31ኛው ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት አርሴናሎች ከኤቨርተኖች ጋር ያደረጉትን ጨዋታ በአንድ አቻ አጠናቀው ከዋንጫ ፉክክሩ በ14 ነጥቦች ሊርቁ ነው ሲባል፣ በማግስቱ እሁድ በክራቨን  ከቴጅ ከፉልሀም ጋር ጨዋታቸውን ያደረጉት ሊቨርፑሎች የ3 ለ 2 ሽንፈት ስለገጠማቸው ከአርሲናል ጋር የነበራቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ 14 ከማሳደግ ይልቅ ወደ 11 ዝቅ እንዲል ተገደዋል፡፡

መድፈኞቹ ማክሰኞ ምሽት በሻምፒዮንስ ሊጉ የቫምፒዮንስ ሊግ ንጉሡን ሪያል ማድሪድን በሜዳቸው አስተናግደው  ሦስት ለ ዜሮ በማሸነፍ በታሪክ የማይዘነጋ ድልን ለራሳቸው እና ለደጋፊዎቻቸው ጽፈዋል፡፡ ምንም እንኳን ይህ ድል እና መድፈኞቹ በሻምፒዮንስ ሊግ ለማያውቁት ዋንጫ የሚያደርጉት ግስጋሴ በጥሩ የሚነሳ ቢሆንም የሚኖርባቸው የጨዋታ  መደራረብ በፕሪምየር ሊጉ ላይ ያላቸውን ተፎካካሪነት እንዳያሳጣቸው ያሰጋል፡፡

በአንፃራዊነት ሲታይ በቀሪ ሰባት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ሊቨርፑሎች ከአርሴናሎች በባሰ ፈተናዎች የሚገጥሟቸው ይመስላል፤ ሊቨርፑሎች በቀሪ ሰባት ጨዋታዎች ኮዌስትሃም፣ ከሌስተር ከቶተንሀም፣ ከቼልሲ፣ ከአርሴናል፣ ከብራይተን እና ከክሪስታል ፓላስ ጋር የሚጫወቱ ይሆናል፡፡

ከእነዚህ ሰባት ጨዋታዎች ውስጥ ደግሞ ከሌስተር፣ ከቼልሲ  እና ከብራይተን ጋር የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ከሜዳቸው ውጪ የሚደረጉ ፍልሚያዎች ናቸው፡፡

አርሴናል ከብሬንት ፎርድ፣ ከኤፕስዊች ታውን፣ ከክሪስታል ፓላስ፣ ከበርን ማውዝ፣ ከሊቨርፑል፣ ከኒውካስል እና ከሳውዝ አምፕተን ጋር ጨዋታዎችን ያደርጋል፡፡ ከእነዚህ ጨዋታዎች ውስጥ አርሴናል ከሜዳው ውጪ የሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ከወራጆቹ ኤፕስዊች እና ሳውዝ  አምፕተን ጋር መሆኑ ከሊቨርፑል የተሻለ ቀለል ያሉ መርሃ ግብሮች ይሆኑለታል፡፡በአንፊልድ ሊቨርፑል እና አርሴናል እርስ በራሳቸው የሚያደርጉት ጨዋታ ደግሞ ከምንም በላይ አጓጊ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አሁን ላይ በሊቨርፑል እና በአርሴናል መካከል ያለው የነጥብ ልዩነት 11 መሆኑ ብቻ ሳይሆን የሚቀሩት ጨዋታዎችም ሰባት ብቻ መሆናቸው ኦፕታን ጨምሮ ሌሎች የጨዋታ ውጤት ገማቾችን “ፕሪምየር ሊጉ የተበላ ዕቁብ ነው” እንዲሉ አስገድዷቸዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ሊቨርፑል ቀድሞ በሰበሰባቸው ነጥቦች ታግዞ የዘንድሮው የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮን እንደሚሆን 90 በመቶ ግምት ተሰጥቶታል፡፡ በእግር ኳስ የሚፈጠረው ነገር አይታወቅም የሚለውን መላ ምት ይዘን በቀሪ ሰባት ጨዋታዎች የሚመዘገቡትን ውጤቶች አብረን የምንከታተላቸው ይሆናል፡፡

ቀዮቹ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ አንድ ጆሮ ጨብጠዋል፣ የዘንድሮው የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የአንድ ፈረስ ግልቢያ ብቻ ነው ቢባልም እና ሌሎች የተባሉ ግምቶችንም ደምረን የዋንጫ ግምቱን ለሊቨርፑል ብናደርገውም በቀጣይ ሳምንታት የሚደረጉት ጨዋታዎች የዋንጫውን መዳረሻ በቅርቡ ወይም ዘግየት ብሎ እንደሚሆን ፍንጭ ይሰጡናል፡፡ የእናንተስ ግምት ምን ይሆን?

(እሱባለው ይርጋ)

በኲር የሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here