የአውሮፓው ክስተት ክለብ

0
177

ይህ ክለብ ከአንጋፋዎቹ የጀርመን ክለቦች አንዱ ነው። 119 ዓመታት እድሜን አስቆጥሯል። ነገር ግን የቡንደስሊጋውን ዋንጫ ዓይቶት አያውቅም:: የዲኤፍቢ ፖካል (DFB POKAL) ዋንጫ ካነሳም 31 ዓመታትን አስቆጥሯል። በ1988 እ.ኤ.አ የአውሮፓ ዋንጫ( የኢሮፓ ሊግን) ከማንሳቱ ውጪ ደጋፊዎቹ የሚኮሩበት እና የሚያወሩለት ታሪክ የለውም።ይህንን መጥፎ ታሪኩን ለመሰረዝም ዘንድሮ በታሪኩ እና በቡንደስሊጋው ታሪክ ምርጥ የተባለውን ጅማሮ አድርጓል- ባየርሊቨርኩሰን።
ባየርሊቨርኩሰን እግር ኳስ ክለብ በሊቨርኩሰን ከተማ የሚገኝ ክለብ ነው። ባየርሊቨርኩሰን ስፖርት ክለብ በባየር ኤጅ(Bayer AG) የመድሀኒት አምራች ድርጅት ሠራተኞች አማካኝነት በ1904 እ.አ.አ ተመሰረተ። የስፖርት ክለቡ ሲመሰረት ከእግር ኳስ በተጨማሪ የአትሌቲክስ ፣የጅምናስቲክ ፣የቅርጫት ኳስ ፣የጠረጴዛ ቴኒስ እና የገና ጨዋታ ክለቦችንም በውስጡ ይዞ ነው የተመሰረተው።
በፈረንጆቹ ሚሊኒየም ዋዜማ በ1999 እ.አ.አ ግን የእግር ኳስ ክለቡ ለብቻው ተለይቶ በመውጣት ራሱን ችሏል።በቀይ እና ጥቁር መለያ የሚታወቀው የጀርመኑ ክለብ የቡንደስሊጋውን ዋንጫ ለማንሳት ባይቀናውም አምስት ጊዜ ግን ተፎካካሪ በመሆን ሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።ይህም በጀርመን እግር ኳስ ታሪክ ክብረ ወሰን ሆኖ ተቀምጧል።በፈረንጆቹ ሚሊኒየም ማግስትም በታላቁ መድረክ በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ተፋላሚ እንደነበር ይታወሳል።ክለቡ ሲቀርበው የሚሸሸውን የቡንደስሊጋ ዋንጫ ለማንሳትም በዚህ ዓመት ትክክለኛ ጉዞ እያደረገ ይገኛል።
የጀርመኑ ኃያል ክለብ ባየርሙኒክ የ11ዓመታት የበላይነት ጉዞም ዘንድሮ በባየርሊቨርኩሰን የሚገታ ይመስላል። ባየርሊቨርኩሰን በ2021/22 እ.አ.አ የውድድር ዘመን ስዊዘርላንዳዊውን አሰልጣኝ ጄራርዶ ሲኦኒን በማሰናበት ስፔናዊውን የቀድሞ የመሀል ሜዳ ኮከብ ዣቢ አሎንሶን በአሰልጣኝነት ቀጥሮ ድንቅ የውድድር ጊዜ እያሳለፈ ነው። ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድርስ የዣቢ አሎንሶው ቡድን በሁሉም ውድድሮች በአውሮፓ ሽንፈትን ያላየ ብቸኛው ክለብ ነው። ካደረጋቸው 22 መርሀ ግብሮች 20ውን ሲረታ በሁለቱ ነጥብ ተጋርቷል::በቡንደስሊጋው ገና ከወዲሁ በክብረ ወሰን የታጀበ አስደናቂ አጀማመር ነው እያደረገ ያለው።
ከዚህ ውጤት በስተጀርባ የቀድሞው የሊቨርፑል፣ የሪያል ማድሪድ እና የባየርሙኒኩ የመሀል ሜዳ ተጫዋች ዣቢ አሎንሶ ሚና ላቅ ያለ መሆኑን የኦፕታ አናሊስት (OPTA ANALYST) መረጃ ያመለክታል። የ41 ዓመቱ ስፔናዊ አሰልጣኝ በአሰልጣኝነት ሙያው የሪያል ሶሲዳድን ቢ ቡድን እና የሪያል ማድሪድን የወጣቶች ቡድን በማሰልጠን ሙያውን አጎልብቶ ነው የጀርመኑን ክለብ የተረከበው። የፔፕ ጋርዲዮላው ደቀ መዝሙር በዚህ ዓመት በቡንደስሊጋው ክስተት የሆነ ቡድንም ገንብቷል።
ቡንደስሊጋው ከተጀመረበት 1963 እ.አ.አ ጀምሮ በተከታታይ አስራ አንድ የቡንደስሊጋ ጨዋታዎችን በማሸነፍም አዲስ ክብረ ወሰን አስመዝግቧል። ካደረጋቸው አጠቃላይ 13 ጨዋታዎች ደግሞ አስራ አንዱን አሸንፏል። በሁለቱ ብቻ ነጥብ ተጋርቶ የእግር ኳስ ቤተሰቡን አጃኢብ አሰኝቷል። በተጋጣሚዎቹ ላይ 38 ግቦችን ሲያስቆጥር አስራ አንድ ግብ ብቻ ነው የተቆጠረበት:: ከኃያሉ ክለብ ባየርሙኒክ ቀጥሎ በሊጉ ከፍተኛ ግብ ያስቆጠረ እና አነስተኛ ግብ የተቆጠረበት ክለብም ነው ባየርሊቨርኩሰን። በሊጉ እያሳየ ባለው ድንቅ አቋምም ከ31 ዓመታት በኋላ ዘንድሮ ከዋንጫ ጋር ሊያገናኛቸው እንደሚችል ደጋፊዎቹ እምነትን አሳድረዋል።ባየርሊቨርኩሰን በመጀመሪያዎቹ ሦስት የሊግ ጨዋታዎች ሲያሸንፍ አስራ አንድ ግቦችን ከመረብ በማገናኘት ጭምር ነው። ይህ ደግሞ በቡንደስሊጋው ታሪክ አዲስ ታሪክ ሆኖ ተመዝግቧል።
ዣቢ አሎንሶ በ2016 እ.አ.አ የቀድሞ አሰልጣኙ ፔፕ ጓርዲዮላ ያስመዘገበውን ታሪክም መጋራት ችሏል። ጓርዲዮላ በወቅቱ በባቫሪያኑ ክለብ ቤት፣ አስራ አንድ ጨዋታዎችን አድርጎ ማግኘት ከነበረበት 33 ነጥብ ሰላሳ አንዱን ማሳካቱ ይታወሳል።በወቅቱም በሊጉ ታሪክ አዲስ ክብረ ወስን ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን ዣቢ አሎንሶ የባየርሙኒክ ተጫዋች ሆኖ የመሀል ሜዳውን ሲመራ እንደነበረም ይታወሳል።
ባሳለፍነው የክረምቱ የዝውውር ወቅት በርካታ የቡድኑ ተጫዋቾች ክለቡን ሲለቁ በበርካታ የጀርመን መገናኛ አውታሮች መነጋገሪያ ሆኖ እንደነበረ ይታወሳል። ነገር ግን የዝውውር ወቅቱ ሳይጠናቀቅ አሰልጣኝ ዣቢ አሎንሶ ቡድኑን ለማጠናከር ጥቂት የማይባሉ ተጫዋቾችን በማስፈረም ቡድኑን የመገንባት ሥራ ሠርቷል።የፈረሙት አዲሶቹ ተጫዋቾችም የቡድኑ ወሳኝ እና ቁልፍ ተጫዋች በመሆን የጀርመን ጋዜጦችን ግምት ፉርሽ አድርገዋል።
ግራኒት ዣካ ፣ቪክተር ቦኒፌስ ፣አልሀንድሮ ግሪማልዶ እና ፍሎሪያን ዊርትዝ በክረምቱ የዝውውር ወቅት የፈረሙ እና የቡድኑ መሪ ተዋናይ ከሆኑት ተጫዋቾች መካክል ይገኙበታል።
የቀድሞው የአርሴናሉ ተጫዋች ግራኒት ዣካ ከሰባት ዓመታት በኋላ ነው ወደ ቡንደስሊጋው የተመለሰው።የመሀል ሜዳ ሞተሩ ለዣቢ አሎንሶው ቡድን ወሳኝ እና መሪ ተጫዋች ነው። በ3-4-2-1 አሰላለፍ ስልት በግራ በኩል የመሀል አማካኝ ሆኖ ለአሎንሶው ቡድን እያገለገለ ይገኛል። ዣካ ወደ ፊት በመጠጋት አጥቂዎችንም ያግዛል፤ ታጋይነቱና አልሸነፍ ባይነቱም የቡድኑን ሚዛን እንዲጠብቅ ረድቶታል።ባየርሊቨርኩስን አሁን ላለበት የስኬት ደረጃም የግራኒት ዣካ አስተዋጽኦ ላቅ ያለ መሆኑን የቡንደስሊጋው ድረገጽ መረጃ ያሳያል።
ባየርሊቨርኩሰን ተጋጣሚን ለማጥቃት ከሚጠቀምበት ትልቁ መሳሪያው ናይጄሪያዊው አጥቂ ቪክተር ቦኒፌስ ዋነኛው ነው።ወጣቱ ፊት አውራሪ ለዣቢ አሎንሶው ቡድን በቀላሉ ግቦችን ያስቆጥራል። የተጋጣሚ ቡድን ተከላካይ እንዲረበሽ በማድረግ ፣ክፍተቶችን በመፍጠር አደጋ የመፍጠር ክህሎትም አለው።ናይጀሪያዊው ኮከብ በሦስት ጨዋታዎች፣ በስድስት ግቦች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ በማድረግ በቡንደስሊጋው አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል።
ሌላኛው የፊት መስመር ተሰላፊ ፍሎሪያን ዊርትዝም ለባየርሊቨርኩሰን ቁልፍ ተጫዋች ከሆኑት መካከል ይጠቀሳል።ጀርመናዊው ተጫዋች ግቦችን ያስቆጥራል፣የግብ ዕድሎችንም ይፈጥራል። እንዲሁም በቀኝ ክንፍ በኩል አስቶንቪላን በተቀላቀለው ሙሳ ዲያቢ ምትክ ጆናስ ሆፍ ማን ነው በክረምቱ የዝውውር ወቅት ባየርሊቨርኩሰንን የተቀላቀለው። ትክክለኛው የሙሳ ዲያቢ ተተኪ ተብሎ የተዘመረለት ተጫዋቹ በአዲሱ ክለቡ ድንቅ የውድድር ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል።ክለቡ በሚያስቆጥራቸው ግቦች ላይም ቀጥተኛ ተሳትፎ እያደረገ ነው።
የአሰልጣኝ ዣቢ አሎንሶ አዲሱ የእግር ኳስ ፍልስፍና ለእነዚህ ቁልፍ ተጫዋች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ተጫዋቾች ምቾትን በመፍጠር ቡድኑን ለውጤት አብቅቶታል።
የስፔናዊው አሰልጣኝ አሎንሶ የእግር ኳስ ፍልስፍናም የክለቡ መለያ የሆነውን የእግር ኳስ ባህል የጠበቀ ነው ።በጥብቅ መከላከል እና ኳስን ይዞ መጫወት በቀይ እና ጥቁር ለባሾቹ ዘንድ በትኩረት ተግባራዊ የሚደረግ የታክቲክ ሀሳብ ነው።ኳስን ከኋላ መስርተው በመጫወት በፈጣን አጥቂዎቻቸው በመስመር ላይ ተጋጣሚን በቀጥታ ፋታ ማሳጣት ይችላሉ።እንደ ሁኔታው የሚለዋወጥ በተጋጣሚ ቡድን ላይ ያልታሰበ አደጋ የሚጥል ፈጣን የመልሶ ማጥቃት ስልትም በውድድር ዘመኑ በስፔናዊው አሰልጣኝ ሜዳ ላይ የሚተገበሩ ታክቲኮች እንደሆኑ የኦፕታ አናሊስት (OPTA ANALYST)መረጃ ያመለክታል።
ዣቢ አሎንሶ በተጫዋችነት ዘመኑ አስደናቂ ዕይታ የነበረው፣በጥልቀት እግር ኳስን የሚረዳ እና የሚገነዘብ ሀሳባዊ ተጫዋች እንደነበረ ይነገራል። ኦፕታ አናሊስትም ዣቢ አሎንሶ በአንድ ጨዋታ ከ200 በላይ ቅብብሎችን ካደረጉ ሦስት ተጫዋቾች መካከል አንዱ እንደነበር ጠቅሶ ኳስ ይዞ የሚጫወት ፣ ትንፋሽን የሚያስውጥ ፣ልብን የሚያሞቅ እንቅስቃሴዎችን የሚያደርግ ቡድን ለመገንባት ነገሮቹን ቀላል እንዳደረገለት ነው መረጃው የሚያመለክተው።
ነገር ግን ባየርሙኒክም በቡንደስ ሊጋው አንድም ጨዋታ አለመሸነፉ ዋንጫውን ለማንሳት ከባቫሪያኑ ክለብ የሚያደረገው ፍክክር ቀላል አይሆንም።ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ዋንጫውን ካነሳበት ከ2011እ.አ.አ በኋላ ዘንድሮ በውድድር ዓመቱ መጨረሻ አዲስ የቡንደስሊጋ ሻምፒዮን እንመለከት ይሆን የብዙዎቹ ጥያቄ ነው?
በኢሮፓ ሊግ አንድም ጨዋታ ያልተሸፈው ክለቡ የት ድረስ ሊጓዝ ይችላል? የሚለውም አጓጊ ሆናል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር ታኀሣሥ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here