የአዕምሮ ጤና አጠባበቅ

0
129

የዓለም ጤና ድርጅት ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት በዓለም ላይ ከአራት ሰዎች መካከል አንዱ የአዕምሮ መታወክ አለበት:: በመጭው እ.አ.አ 2030ም በርካታ ሰዎች ከአዕምሮ ሕመም መገለጫ አንዱ በሆነው ድባቴ ይጠቃሉ:: በዚህም ደስተኛነታቸውን ያጣሉ:: ከላይ የተነሳውን ዓለም አቀፍ መረጃ ዋቢ አድርገው ከአዕምሮ ጤና ጋር በተያያዘ ሙያዊ ሐሳብ የሰጡን በባሕር ዳር ጥበብ ጊዮን ሆስፒታል እና በሜሎስ ስፔሻሊቲ ሳይካትሪስት ክሊኒክ የስነ ልቦና ሐኪም ዶ/ር ሚካኤል በቃ ናቸው::

 

ዶ/ር ሚካኤል በቃ እንደሚገልጹት አዕምሮ ስንል በእንግሊዘኛ “ማይንድ” የሚለውን የሚገልጽ ሲሆን ሥራውም መረጃን፣ ሀሳብን እና ድርጊትን ማቀናጀት ነው:: አንድ ሰው አዕምሮው ጤነኛ ነው የሚባለው ካለማንም አጋዥ በራሱ ነጻ ሆኖ መወሰን እና ሕይዎቱን መምራት ሲችል ነው:: እንዲሁም ከሰዎች ጋር ተግባብቶ መኖር ሲችል፣ ለራሱ በጎ አመለካከት ሲኖረው፣ የደስተኝነት ስሜት ሲያዳበር፣ ለወደፊቱም ማቀድና ማገናዘብ ሲችል አዕምሮው ጤነኛ ነው ይባላል::

 

አንድ ሰው የአዕምሮ ጤናው ታወከ የሚባለው ደግሞ ለራሱ የሚሰጠው አመለካከት ወይም ግምት ሲዛባ (ትክክል ሳይሆን ሲቀር)፣ በራሱ መወሰን ሲሳነው፣ በኑሮው ደስተኛ ሳይሆን ሲቀር፣ በዙሪያው ካሉ ሰዎች ጋር መግባባት ሲያቅተው፣ ብስጩ ሲሆን፣ ስለወደፊቱ ማሰብ እና ማቀድ ሲያቆም (ተስፋ ሲቆርጥ)፣ … ነው::

ባለሙያው እንዳሉት አንድ ሰው በተፈጥሮው መልካም እና መጥፎ ዝንባሌዎች ይኖሩታል:: እነዚህ ዝንባሌዎች ከአካባቢያዊ ወይም ከቤተሰባዊ መስተጋብር ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ ይችላሉ::

አዕምሮን ለሕመም የሚዳርጉ መንስኤዎች በሦስት እንደሚከፈሉ የተናገሩት ባለሙያው እነሱም ስነ ሕይዎታዊ (ባዮሎጂካል)፣ ስነ ልቦናዊ (psychological) እና ማሕበራዊ ናቸው::

 

ስነ ሕይዎታዊው (ባዮሎጂካል) መንስኤ የሚባለው አንድ ሰው በተፈጥሮው ችግርን ከመቋቋም አቅም ጋር ተያይዞ ቶሎ ስሜታዊ ሲሆን፣ የነርቭ ቅንጀት ሲዛባ፣ በአዕምሯችን የሚለቀቀው ኬሚካል አለመመጣጠን፣ ከቤተሰብ ዘረመል (ጀነቲክስ) ጋር ተያይዞ የአዕምሮ ሕመም ያለበት የቅርብ የቤተሰብ አባል መኖር በአዕምሮ ሕመም የመያዝ ዕድልን ይጨምራል። ነገር ግን አንድ የቤተሰብ አባል የአዕምሮ ሕመም አለበት ማለት ሌሎችም ያጋጥማቸዋል ማለት አይደለም።  የመድኃኒቶች አለመስማማት፣ የእንቅልፍ እጥረት፣ አንጎል ሲጎዳ፣ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት (ኦቲዝም)፣ እርጅና፣ በቅድመ ወሊድ ጊዜ መጎዳት ሲኖር) እና አደንዛዥ ዕጽ መጠቀም ለአዕምሮ ሕመም ሊዳርግ ይችላል::

ስነ ልቦናዊ መንስኤዎች  የሚከሰቱት በተለምዶ ቤተሰብም ይሁን ማሕበረሰቡ ሰዎችን  በንግግር ሲጎዷቸው ነው:: ለአብነትም ወላጆች አውቀውም ይሁን ሳያውቁ በሚናገሩት ነገር ልጆች ላይ የስነ ልቦና ችግር ያጋጥማል:: በተለይም በአንተ ምክንያት ነው እኔ እንደዚህ የሆንኩት፣ አንተ ሰነፍ ነህ፣ አንተ ጥሩ ልጅ አይደለህም ሲባሉ፤ እንዲሁም  በመልካቸው እና በቁመታቸው መሸማቀቅ ሲደርስባቸው ለስነ ልቦና ቀውስ ይዳረጋሉ::

 

ማሕበራዊ የአዕምሮ ጤና መንስኤ ደግሞ ጦርነቶች፣ የኢኮኖሚ ሁኔታዎች፣ ማህበራዊ ሚዲያ፣ ስልክ (ዘመናዊ ስልኮችን ከመጠን በላይ መጠቀም እንቅልፍን ሊያስተጓጉል ይችላል) ይጠቀሳሉ:: እነዚህ ሁኔታዎች አንድን ሰው የአዕምሮ ጤናው እንዲታወክ አጋላጭ ምክንያቶች ሊሆኑ ይችላሉ ያሉት ዶ/ር ሚካኤል  ከዛ በኋላ የሚፈጠሩ ተጽዕኖዎች ማለትም የትምህርት ውጤት መቀነስ፣ የቤተሰብ መበተን፣ የፍቅር ግንኙነት መበላሸት እና የገንዘብ ማጣት በጋራ የአዕምሮ ጤና እንዲቃወስ ያደርጋሉ::

 

የአእምሮ ጤና መዛባት ማንኛውም ሰው ላይ ሊከሰት ቢችልም ከዕድሜ ጋር ተያይዞ በምናይበት ጊዜ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት (ኦቲዝም) በሕጻናት ላይ እንደሚከሰት አንስተዋል:: የመርሳት ችግር የሚያስከትለው ዲይሜንሽያ (dementia) የሚባለው  ደግሞ እድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ በሆኑ ሰዎች የመከሰቱ ዕድል ሰፊ ነው:: ሌላው ደግሞ ከባድ የሚባለው የአዕምሮ ሕመም ጭንቀት (depression) የሚከሰተው በጉርምስና ጊዜ ነው:: ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 25 ያሉ ወጣቶችም ተጠቂ ይሆናሉ:: እንደ ዶ/ር ሚካኤል ማብራሪያ ከሰው ፊት  ቆሞ የመናገር ፍርሃት  በጉርምስና ዕድሜ ላይ ሊከሰት ይችላል:: ድባቴ ግን በማንኛውም የዕድሜ ክልል ላይ ሊከሰት የሚችል ነው:: በአጠቃላይ የአዕምሮ ሕመም ከጾታ አንጻር  ሴቶች ላይ የመከሰቱ ዕድል ከፍተኛ ነው:: በተለይም ድባቴ ከ20 እስከ 30 ዕድሜ በሚገኙ ሴቶች ላይ ከፍተኛ እንደሆነ ነው የተናገሩት::

 

ጦርነት በባህርይው የሰዎችን ችግርን የመቋቋም አቅምን በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚጠይቅ ለአዕምሮ ሕመም ይዳርጋል:: ከጦርነት እና ግጭት ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ መደፈሮች፣ መፈናቀል እና የኢኮኖሚ ችግሮች ለጭንቀት ሕመም ይዳርጋሉ:: የተኩስ ድምጽ መስማት እና ‘የሞት አደጋ ሊደርስብኝ’ ነው የሚለው ስሜት የሚያመጣው የፍርሃት ስሜት እንቅልፍ ማጣትን ያስከትላል:: ይህ ደግሞ ተስፋ እንዲቆርጡ እና ራሳቸው ላይ መጥፎ ነገር እንዲፈጽሙ ያደርጋቸዋል::

የዓለም ጤና ድርጅት እንደገለጸው ከዋና ዋናዎቹ የአዕምሮ ጤና መታወክ መገለጫዎች  መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል። የስሜት መዛባት (እንደ ድብርት ወይም ባይፖላር ዲስኦርደር)፣ የጭንቀት እና የባህርይ መዛባት፣ ስነ ልቦናዊ በሽታዎች (እንደ ሲዞፈሪንያ ያሉ)፣ የአመጋገብ መዛባት፣ ከአሰቃቂ ሁኔታ ጋር የተዛመዱ በሽታዎች፣ የዕፅ ሱሰኝነት፣ … ዋናዋናዎቹ ሲሆኑ እያንዳንዱ ዓይነት የአዕምሮ ሕመምም የተለያዩ ምልክቶች አሉት::

 

የአዕምሮ ጤናን ለመጠበቅ ግንዛቤው ሊኖር ይገባል የሚሉት ባለሙያው አብዛኛው ሰው ወደ ሕክምና የሚመጣው በጣም ዘግይቶ በመሆኑ ለከፋ ችግር ያጋልጣቸዋል ነው የሚሉት:: በፍጥነት ከመጡ ግን ወዲያው መፍትሔ እንደሚያገኙ ነው የጠቆሙት::

የእንቅልፍ ማጣት፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ከስራ ባልደረቦች ጋር ያለመግባባት በሚኖርበት ጊዜ የአዕምሮ ጤና ችግር አለብኝ ብሎ ወደ ባለሙያ በመሄድ አዕምሮ ጤንነትን ዕለት በዕለት መጠበቅ እንደሚቻል ነው ዶ/ር ሚካኤል የተናገሩት::

 

ናሽናል ሜንታል ሄልዝ ኢንስቲትዩት (National institute of mental health) ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ የእንቅልፍ እጦት፣ የምግብ ፍላጎት ማጣት፣   ያልታቀደ የክብደት ለውጥ፣ በስሜት መዋዠቅ ምክንያት ጠዋት ላይ ከአልጋ ለመውረድ አለመፈለግ፣ ትኩረት ለማድረግ መቸገር፣ ቀደም ሲል አስደሳች ሆነው በሚያገኟቸው ነገሮች ላይ ፍላጎት ማጣት፣ የተለመዱ ተግባራትን እና እንቅስቃሴዎችን ማጠናቀቅ አለመቻል፣ የብስጭት ወይም ከልክ ያለፈ የመረጋጋት ስሜቶች የአዕምሮ ጤና መስተጓጎል እንዳለ ሊያመላክቱ እንደሚችሉ ያትታል::

 

የአዕምሮ ሕመም ሁሉም አንድ አይነት እንዳልሆኑ (ከ300 በላይ የአዕምሮ እክሎች እንዳሉ ልብ ይሏል) ነገር ግን ሰዎች ወደ ሕክምና ተቋም ሲመጡ እንደየ ሕመማቸው ታክመው ሊድኑ እንደሚችሉ ማወቅ አለባቸው ነው ያሉት ባለሙያው ዶክተር ሚካኤል በቃ::

አክለውም አንዳንድ ሰዎች የአዕምሮ ሕመምን የፈጣሪ ቁጣ አድርገው እንደሚያስቡ እና ወደ ሕክምና ቦታ ቢሄዱ ሰዎች የሚያገልሏቸው ስለሚመስላቸው ከሕክምና እንደሚርቁ ነው የጠቆሙት:: ታዲያ  ይህ ነገር ተገቢ እንዳልሆነ ነው የገለጹት:: የአዕምሮ ሕመም ማንኛውንም ሰው ሊያጋጥም እንደሚችል ማወቅ አለባቸውም ነው ያሉት::

 

ወደ ሕክምና ቦታ ሲመጡም መድኃኒት እንደሚታዘዝላቸው እና አስፈላጊውን የባለሙያ ምክር አግኝተው ጤናቸው እንደሚመለስ ማወቅ እንደሚገባ መክረዋል:: በተለምዶ ‘መድሃኒቱ ይለምድብኛል፤ ዕድሜ ልኬን ነው የምወስደው’ የሚል አመለካከትን ማስወገድ እንደሚገባ ጠቅሰው የተለያዩ አይነት የአዕምሮ ሕመሞች በመኖራቸው ለሁሉም አንድ አይነት ሕክምና እንደማይሰጥ አስገንዝበዋል::

ዶ/ር ሚካኤል መንፈሳዊ መሆን፣ በቂ እንቅልፍ ማግኘት፣ የሚያስደስትን ነገር ማከናወን፣ በቂ ረፍት ማድረግ፣ ለራስ በጎ አመለካከት መኖር፣ ከሰዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት (ተግባቦት) መፍጠር እና ድባቴ ውስጥ ከሚያስገቡ ነገሮች መራቅ ለአዕምሮ ጤና አስፈላጊ እንደሆኑ ነው የመከሩት::

 

ባለሙያው የአዕምሮ ጤናን ከሚጎዱ ተግባራት በመራቅ፣ ማሕበራዊ ግንኙነትን የሚያዳብሩ ተግባራትን በማከናወን፣ ችግሮች ሲያጋጥሙ ለሰዎች በማማከር እና ግጭቶችን በመፍታት የአዕምሮ ጤናን ቀድሞ መከላከል እንደሚቻልም ጠቁመዋል::

ሰዎች ጦርነት ወይም ግጭት ያለበት አካባቢ የሚኖሩ ከሆነ ከአካባቢው በመራቅ፣ ወደ ጦርነት ሊያመሩ የሚችሉ ጉዳዮችን አስቀድሞ በንግግር እና በውይይት በመፍታት ጦርነት ከሚያደርሰው የአዕምሮ ጤና ችግር መጠበቅ ይችላሉም ብለዋል::

 

ጦርነት በሚኖርበት ጊዜ የሰው ልጅ ትኩረቱ ይጨምራል፣ እንቅልፍ አይተኛም፣ ቶሎ ይበሳጫል:: ነገር ግን ይህ የሚሆነው በጊዜያዊነት ነው:: ሞት የማይቀር ነገር ነው፣ ጦርነት ሲኖር ይተኮሳል፤ ከባድ ድምጽ ይኖራል የሚለውን ማሰብ እና አምኖ መቀበል እንደሚገባም መክረዋል::

ዶ/ር ሚካኤል እንዳብራሩት መልካም የሆኑ ማሕበራዊ ግንኙነቶች አዕምሮ ላይ ከፍተኛ በጎ ተጽዕኖ አላቸው፤  የአዕምሮ ንጥረ ነገሮች ቅንብር እንዲስተካከል ያደርጋሉ:: በየዕለቱ ከሰዎች ጋር የሚኖረን መስተጋብር የአዕምሮ ጤናን ያዛባሉ ወይም ያስተካክላሉ:: ታዲያ ይህንን ታሳቢ ያደረጉ ግንኙነቶች መመሥረት ተገቢ ነው::

 

የድባቴ ስሜትን  የሚወዱትን ነገር በማድረግ ወይም በመሥራት መከላከል ይቻላል:: በስነ ሕይወታዊ ምክንያት የሚመጣን የአዕምሮ ችግር ደግሞ መድኃኒት በመውሰድ እና ማሕበራዊ ሕይወትን በማስተካከል የሚለቀቁ ኬሚካሎችን ማስተካከል ይቻላል ሲሉ ነው ሙያዊ ምክራቸውን የለገሱት፡፡

ጤና አዳም

የአዕምሮ ጤናዎትን ለማሻሻል የሚረዱ ወሳኝ ነጥቦች

* በየቀኑ ለ30 ደቂቃ መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያድርጉ።

*ጤናማ ምግቦችን ይመገቡ፤ በቂ ውኃ ይጠጡ፡፡ የካፌይን እና የአልኮል ፍጆታዎን ይቀንሱ፡፡

* በቂ እንቅልፍ እያገኙ መሆኑን ያረጋግጡ።

* ዘና የሚያደርግ እንቅስቃሴን ይሞክሩ።

* ሙዚቃ ያድምጡ፣ ያንብቡ፡፡

* በዕቀድ መመራትን ይለማመዱ፡፡

* አዎንታዊ ነገሮችዎ ላይ ያተኩሩ።

* ለስሜትዎ የሚጠነቀቁ ድጋፍ እና ተግባራዊ እርዳታ ሊሰጡ የሚችሉ ጓደኞችዎን ወይም የቤተሰብዎን አባል ያግኙ።

ምንጭ፡- www.nimh.nih.gov

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የሐምሌ 21  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here