የአየር ንብረት ለውጥ እና ተጽዕኖዎቹ

0
74

ዓለም ልዩ ትኩረት እና አፋጣኝ እርምጃ የሚሹ በርካታ አሳሳቢ የአካባቢ ተግዳሮቶችን እየታገለች ነው። የአየር ንብረት ለውጥ እና ያስከተላቸው አደጋዎች፣ የብዝኃ ሕይወት መጥፋት እና የፕላስቲክ ብክለት ዋናዎቹ ፈተናዎች ናቸው::

ቢቢሲ እንዳስነበበው አየር ንብረት ማለት በአንድ ሥፍራ ያለው የአየር ጸባይ በዓመታት የሚያሳየው አማካይ ውጤት ነው:: የአየር ንብረት ለውጥ ደግሞ የዚህ አማካይ አየር ጸባይ መቀየር ማለት ነው:: ለአብነትም ከዚህ በፊት ከዓመት ዓመት የበረዶ ብናኝ ያስተናግድ የነበረ ስፍራ ከዓመታት በኋላ ተቀይሮ ጸሐያማ ሲሆን የአየር ንብረት ለውጥ ተከሰተ ይባላል::  ለአየር ንብረት ለውጥ መከሰትም የሰው ልጅ ተጠያቂ ነው::

ታዲያ በአሁኑ ወቅት የሙቀት ማዕበል፣ ድርቅ፣ ጎርፍ እና አውሎ ነፋስ እየተለመዱ እና እየጠነከሩ በመምጣታቸው ሞት፣ የአካል ጉዳት እና የመሠረተ ልማት ውድመት እያደረሱ ነው። የግብርና ምርትን እያስተጓጎለ ነው:: ይህም የምግብ እጥረትን እና የዋጋ ጭማሪን በማስከተል ሰዎችን ለረሃብ ዳርጓል::

በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የውኃ እጥረትን ሲያስከትል በሌሎች ቦታዎች ደግሞ ከመጠን በላይ ዝናብ እንዲኖር በማድረግ  የጎርፍ መጥለቅለቅ እንዲኖር አድርጓል:: የአየር ንብረት ለውጥ ከበሽታዎች ስርጭት፣ ከመተንፈሻ አካላት እና ከሙቀት ነክ ሕመሞች ጋር የተቆራኘ በመሆኑ በጤና አጠባበቅ ስርዓቶች ላይም ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል።

ከአየር ንብረት ጋር ተያይዘው በሚደርሱ አደጋዎች ሰዎች ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡ እየተገደዱ ነው:: ይህም  መፈናቀልን እና ስደትን በማስከተል ለተፈናቀሉ ሕዝቦች እና ለተቀባይ ማሕበረሰቦች በርካታ ፈተናዎችን እንዲጋፈጡ አድርጓል።

የዓለም ጤና ድርጅት እንዳስታወቀው የአየር ንብረት ለውጥ በተለያዩ መንገዶች በሰው ሕይወት እና ጤና ላይ ከባድ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳረፈ ነው። ንፁህ አየር፣ ንጹህ የመጠጥ ውኃ፣ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት እና ደኅንነቱ የተጠበቀ መጠለያ ለማግኘት የሚደረገውን ትግል ከባድ አድርጎታል::

እ.አ.አ በ2030 እና በ2050 መካከል የአየር ንብረት ለውጥ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ በወባ፣ በተቅማጥ እና በከፍተኛ ሙቀት ብቻ ወደ 250 ሺህ የሚጠጋ ተጨማሪ ሞት ሊከሰት እንደሚችል የድርጅቱ መረጃ ያመላክታል።

እ.አ.አ በ2030 በጤና ላይ የሚደርሰው ቀጥተኛ ጉዳት በዓመት ከሁለት እስከ አራት ቢሊዮን ዶላር  ይገመታል። ደካማ የጤና መሠረተ ልማት ባላቸው አካባቢዎች (በአብዛኛው በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች) የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት እንዳያደርስ ለመዘጋጀት እና ምላሽ ለመስጠት እርዳታ ካልተደረገላቸው ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገቡ ነው የተገለጸው::

ፐብሊክ ሄልዝ ኢንሳይደር ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ለመተንፈሻ አካላት በሽታ የመጋለጥ ዕድል  ከፍተኛ ነው።

የአየር ንብረት ለውጥ በሳንባ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድርባቸው መንገዶች በርካታ  ናቸው።  እንደ አስም ያሉ ሥር የሰደዱ በሽታዎችን ሊያባብስ ይችላል። በሞቃታማና ደረቅ የበጋ ወቅት እየበዛ የሚሄደው የሰደድ እሳት የአተነፋፈስ ሥርዓትን ያዛባል። ሞቃታማ የአየር ሁኔታ በነፍሳት እና በተሸከሙት በሽታ አምጪ ወኪሎች (በሺታውን መንስኤ ተሸካሚዎች) ምክንያት የበሽታዎችን ስርጭት የበለጠ እንዲባባስ ያደርጋል።

ሞቃታማ እና ደረቅ የአየር ጠባይ ብዙውን ጊዜ ጎጂ ባክቴሪያዎችን፣ ቫይረሶችን ወይም በሽታ አምጪ ወኪሎች እንዲራቡ ምቹ ነው።

እንደ አውሎ ነፋስ፣ ጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተት እና የሰደድ እሳት ያሉ ከፍተኛ የአየር ሁኔታ ክስተቶች  ረጅም ጭንቀትን ሊያስከትሉ ይችላሉ። ይህም ለአዕምሮ ጤና እክል ይዳርጋል። እነዚህ ክስተቶች ሰዎችን ሀብት ንብረታቸውን በማውደም ባዷቸውን ያስቀራል።  ይህም በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ሀገራት እና ሕዝቦች ፈታኝ ነው። ሕጻናት፣ አረጋዊያን እና የታመሙ ሰዎች በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ችግሩ የበለጠ ያርፍባቸዋል ሲል ነው የመረጃ ምንጩ (ፐብሊክ ኸልዝ) ያብራራው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ እአ.አ 2024 በታሪክ ሞቃታማው ዓመት መሆኑን በአየር ንብረት ዙሪያ መረጃ የሚሰጠው ኧርዝ ዶት ኦርግ (www.earth.org) ድረ ገጽ ላይ የሰፈረ መረጃ ይጠቁማል::

የያዝነው የአውሮፓዊያኑ ዘመን 2025 ከገባ ስምንት ወራትን አስቆጥሯል:: ታዲያ ይህ ዓመት ባይጠናቀቅም ከፍተኛ የአየር ብክለት ለውጥ የሚያስከትሉት መዘዞች ጎልተው እየታዩበት ነው::

መረጃው እንደሚያትተው ዋና ዋና የፕላኔታችን ሙቀት እንዲጨምር የሚያደርጉ ጋዞች ካርቦን ዳይኦክሳይድ (CO2)፣ ሚቴን እና ናይትረስ ኦክሳይድ ጋዞች ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱት እ.አ.አ በ2023 ነበር:: ይህ በመሆኑም በፕላኔታችን ላይ ለመጪዎቹ ዓመታት የሙቀት መጠን ከፍተኛ የመሆን ዕድሉ አጠያያቂ አይደለም::

የግሪን ሀውስ ጋዝ ልቀቶች ምድርን ሲሸፍኑ የፀሐይ ሙቀት ይጨምራል፤ የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት መጨመር ደግሞ ፈጣን እና ተከታታይነት ያለው የዓለም ሙቀት እንዲጨምር አድርጓል:: ይህም በተራው  በመላው ዓለም አስከፊ ክስተቶችን አስከትሏል:: ከአውስትራሊያ እስከ አሜሪካ እስከ አሁን ከተመዘገቡት በላይ እጅግ አስከፊ የደን ቃጠሎዎች እየተመዘገቡ ነው:: የአንበጣ መንጋ በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በእስያ እየተዘዋወሩ ሰብሎችን እያወደሙ ናቸው::

የአየር ንብረት ቀውሱ ሞቃታማ አውሎ ነፋሶች፣ የሙቀት ማዕበል እና የጎርፍ መጥለቅለቅ የመሳሰሉ ከበፊቱ የበለጠ ኃይለኛ እና ተደጋጋሚ እንዲሆኑ እያደረገ ነው።

ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ በሰው ልጅ ፍጆታ፣ በሕዝብ ብዛት፣ በዓለም ንግድ እና በከተሞች መስፋፋት ፈጣን ዕድገት ታይቷል፤ በዚህም የሰው ልጅ ብዙ የምድር ሃብቶችን እንዲጠቀም አድርጓል። በሕይዎት ለመኖር ካለው ጉጉቱ የተነሳ የምድርን ሀብት አሟጦ እየተጠቀመ ነው:: ኑሮውን ዘመናዊ እና ቅንጡ ለማድረግ በወሰዳቸው እርምጃዎች ተፈጥሮን አውቆም ይሁን ሳያውቅ በመጉዳቱ ዋጋ እየከፈለ ነው::

ኧርዝ ዶት ኦርግ (www.earth.org) ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያስረዳው ዘርፈ ብዙ ችግር በሚያደርሰው የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እ.አ.አ በ2021 በተደረገ ጥናት ከ500 በላይ የሚሆኑ ዓለም ላይ የሚገኙ የእንስሳት ዝርያዎች በመጥፋት ላይ ናቸው::  እንዲሁም ቀሪዎቹ በ20 ዓመታት ውስጥ ሊጠፉ ይችላሉ::

የጥናቱ ባለቤት ሳይንቲስቶቹ እንደሚናገሩት የሰው ልጅ ጥፋት ባይኖር ኖሮ ከዚህ የኪሳራ መጠን ለመድረስ በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት ሊወስድ ይችል ነበር።

እ.አ.አ በ1950 ዓለም በዓመት ከሁለት ሚሊዮን ቶን በላይ ፕላስቲክን አምርታለች። እ.አ.አ በ2015 ይህ ዓመታዊ ምርት ወደ 419 ሚሊዮን ቶን በመድረስ  የፕላስቲክ ብክለትን አባብሷል።

በአሁኑ ጊዜ ወደ 14 ሚሊዮን ቶን የሚጠጋ ፕላስቲክ በየዓመቱ ወደ ውቅያኖሶች ይገባል:: ይህም በውቅያኖሶች ውስጥ የሚኖሩ እንስሳትን ይጎዳል። አስፈላጊው ርምጃ ካልተወሰደ እ.አ.አ በ2040 የፕላስቲክ ቀውሱ ወደ 29 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን እንደሚያድግ ጥናቱ አመላክቷል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ጥቃቅን የፕላስቲክ ቁርጥራጮች (ማይክሮ ፕላስቲኮችን) ቢካተቱ በውቅያኖስ ውስጥ ያለው የፕላስቲክ ድምር መጠን 600 ሚሊዮን ቶን ሊደርስ ይችላል።

እስካሁን ከተሠሩት ፕላስቲኮች 91 በመቶው ዳግም አገልግሎት (Recycled and Reused) ላይ ያልዋሉ ናቸው። ይህም በሕይወታችን ውስጥ ካሉት የአካባቢ ችግሮች ዋናው ያደርገዋል። ፕላስቲክ ለመበስበስ 400 ዓመታት እንደሚወስድ ግምት ውስጥ በማስገባት ሕልውናው እስኪያበቃ ድረስ ብዙ ትውልድ የችግሩ ሰለባ ይሆናል::

ሌላው የአየር ንብረትን እየጎዳ የሚገኘው የደን ጭፍጨፋ ነው:: በየሰዓቱ 300 የእግር ኳስ ሜዳዎች የሚያክሉ ደኖች ይቆረጣሉ። በዚህም እ.አ.አ በ2030 ዓለም የሚኖራት የደን ሽፋን 10 በመቶ ብቻ ሊሆን ይችላል። (አሁናዊ የዓለም ደን ሽፋን 31 በመቶ ገደማ መሆኑን ልብ ይሏል)።

የደን ጭፍጨፋ ካልተገታ ቀሪው የደን ሽፋን ከመቶ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሊጠፉ ይችላሉ። ከፍተኛ የደን ጭፍጨፋ የደረሰባቸው ሦስቱ ሀገራት ብራዚል፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ኢንዶኔዥያ ናቸው።

የዓለማችን ትልቁ የዝናብ ደን ስድስት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትር (ሁለት ነጥብ 72 ሚሊዮን ስኩዌር ማይል) የሚሆነው እና 40 በመቶውን የደቡብ አሜሪካ አህጉር የሚሸፍነው፣ እንዲሁም እጅግ  ልዩ ልዩ ሥነ ምሕዳሮች ባለቤት የሆነው አማዞን ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ የዕፅዋት እና የእንስሳት ዝርያዎች መገኛ ነው። ሆኖም ይህን ደን ለመጠበቅ ጥረቶች ቢደረጉም የደን ጭፍጨፋ አሁንም ተስፋፍቷል:: አንድ ሦስተኛው የዓለም ሞቃታማ የደን ጭፍጨፋ በብራዚል የአማዞን ደን ውስጥ የሚካሄድ ሲሆን በየዓመቱ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር ይደርሳል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው አስከፊ የአየር ጠባይ ክስተት ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እያስከተለ ነው። ከነዚህም መካከል በመሠረተ ልማት ላይ ውድመት፣ የግብርና ምርት መቀነስ እና የአቅርቦት ሰንሰለት መቆራረጥን ይጠቀሳሉ::

በቻይና እና በታይላንድ የሚከሰቱ ጎርፎች ለአየር ንብረት ለውጥ ማሳያዎች ናቸው:: ፈረንሣይ እ.አ.አ ከ1949 ወዲህ አጋጥሟት የማያውቅ ሰደድ እሳት ነሐሴ 5 ቀን 2025 (እ.እ.አ) ተከስቷል። ሰደድ እሳቱ በድርቅ፣ በኃይለኛ ነፋስ ታጅቦ  ከ15 ሺህ ሔክታር በላይ ደን አቃጥሏል:: ይህም ከዋና ከተማዋ ከፓሪስ የቆዳ ስፋት በላይ ነው::

የአየር ሙቀት እና የእርጥበት መጠን መጨመር አንዳንድ ክልሎችን ለሰዎች መኖሪያ እንዳይሆኑ እያደረጋቸው ነው። አፍሪካ ሲ ዲ ሲ ማዕከል የአየር ንብረት ለውጥ እና ጤና ስትራቴጂያዊ ማዕቀፍ ባወጣው መረጃ የአየር ንብረት ለውጥ በአፍሪካ አህጉር ላይ ያለውን ያልተመጣጠነ ተፅዕኖ አጉልቶ ያሳያል:: በአህጉሪቱ የበሽታ መበራከትን  እና የምግብ ዋስትና እጦትን እያባባሰ ነው ብሏል።

ሀገራችን ኢትዮጵያም የአየር ንብረት ለውጥ ባስከተለው ችግር የዝናብ እጥረት በመከሰቱ በርካታ ዜጎቿ ችግር ላይ ይገኛሉ::

በአፍሪካ ሕብረት እና በኢትዮጵያ መንግሥት የተጠራው ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ በአዲስ አበባ ጳጉሜ 05 ቀን 2017 ዓ.ም (እ.አ.አ መስከረም 10 ቀን 2025) ይካሄዳል። የአፍሪካን የአየር ንብረት አጀንዳ እና የዘላቂ ልማትን በተመለከት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ለማራመድ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ባለሙያዎች፣ የቢዝነስ ስዎች እና ሲቪል ማሕበራት የሚሳተፉበት መድረክ ነው።

(ሳባ ሙሉጌታ )

በኲር የነሐሴ 5  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here