አሮጌው ዓመት በአዲስ ሊተካ ከወር ያነሰ ጊዜ ቀርቶታል:: ደብረ ታቦር (ቡሄ) ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ የእንግጫ ነቀላ እና የከሴ አጨዳ በዓላት እና ክዋኔዎች ደግሞ የአዲስ ዓመት መቃረብን የሚያበስሩ ናቸው:: የዝናባማው ወራት ማብቂያ ነጋሪት፣ የአዝመራው መድረስ ምልክት ተደርገውም ይወሰዳሉ::
በየዓመቱ በቡሄ ተጀምሮ በእንግጫ ነቀላ የሚጠናቀቀው የነሐሴ ወር በዓላት ዘንድሮም በተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ ክዋኔዎች ይከበራሉ:: ለመሆኑ የበዓላቱ አከባበር እና ፋይዳ ምንድን ነው? የትንታኔያችን አንኳር ጉዳይ ነው::
ቡሄ
የክረምቱ ጨለማ ተገፎ የብርሐን ወጋገን ሲፈነጥቅ፣ ሰማይ ከጭጋጋማነት ወደ ብሩሀማነት ሲለወጥ ከሚከበሩ በዓላት መካከል የቡሄ በዓል ይገኝበታል:: ቡሄ በአማራ ክልል አብዛኛው አካባቢዎች በሙልሙል ዳቦ እና በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበር ቢሆንም በደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ግን በልዩነት ይከበራል:: ሙል ሙል ዳቦ መድፋት፣ ጅራፍ መገመድ እና ማጮኽ፣ ችቦ ማብራት የበዓሉ ድምቀቶች ናቸው::
የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ዓመታዊ የቡሄ በዓልን በድምቀት ለማክበር መዘጋጀቱን የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊው አቶ አለበል ደመላሽ ለበኵር ጋዜጣ በስልክ አስታውቀዋል:: ቡሄን ጨምሮ ሌሎች ሃይማኖታዊ እና ሕዝባዊ በዓላት በየዓመቱ እንደሚከበሩ የገለጹት አቶ አለበል፣ እነዚህም ለቱሪዝሙ ዘርፉ መነቃቃት ጉልህ ሚና ማበርከታቸውን ተናግረዋል:: የአካባቢውን ነዋሪ የገቢ ምንጭ የማነቃቃት ሚናውም ከፍተኛ ነው:: ማኅበራዊ መስተጋብር እንዲጠናከርም የማድረግ አጋጣሚ ከፍ ያለ መሆኑን ተናግረዋል:: ይህም በዓሉን ለመታደም ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ደብረ ታቦር በርካታ ሕዝብ የሚገባ በመሆኑ ነው ይላሉ::
የዘንድሮው የቡሄ በዓልም ሳይበረዝ እና ሳይከለስ ታሪካዊ አከባበሩን ተከትሎ በድምቀት እንደሚከበር ተናግረዋል:: ለዚህም አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅትም መጠናቀቁን ጠቁመዋል:: የበዓሉ መነሻ ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው መሆኑ ከደብረ ታቦር ርእስ አድባራት ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ጋር በጋራ ለማዘጋጀት መታቀዱንም ተናግረዋል:: ከዋናው የቡሄ ክብረ በዓል ቀደም ብሎ የፓናል ውይይት እና የጎዳና ላይ ትርኢት እንደሚካሄድም ታውቋል:: ከቡሄ በዓል አንድ ቀን ቀደም ብሎ ደግሞ የእቴጌ ጣይቱ የልደት ቀን በመሆኑ ታስቦ እንደሚውል አስታውቀዋል:: በዓሉም በሰላም እንዲከበር ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው ያሉት አቶ አለበል፣ ሕዝቡም የሚታወቅበትን እንግዳ ተቀባይነት በተግባር እንዲያሳይ ጥሪ አቅርበዋል::
ሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል
ሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል በዋግ ኸምራ ብሄረሰብ አስተዳደር እና በሰሜን ወሎ ዞን በድምቀት የሚከበሩ በዓላት ናቸው:: እነዚህ በዓላት ሃይማኖታዊ መሠረትነት ያላቸው በወንዶች ታጅበው በልጃገረዶች ብቻ የሚከወኑ በዓላት ናቸው:: ሁሉም በዓላት በሀገር ውስጥ አልባሳት እና ጌጣጌጦች ተውበው የሚከወኑ በዓላት ናቸው:: ልጃገረዶች በዓላቱን የሚያከብሩት ጸጉራቸውን ሹሩባ ተሠርተው፣ አካባቢያቸውን የሚገልጹ ነጫጭ አልባሳትን ለብሰው እና ጫማዎችን ተጫምተው፣ ከአንገታቸው ላይ የተለያዩ ጌጣ ጌጦችን አጥልቀው፣ ከወገባቸውም ለምለም ሳር (ቄጤማ) አስረው ነው:: የተለያዩ ጣዕመ ዜማዎች የበዓላቱ ሌላው ድምቀት ናቸው::
በዋግ ኸምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የሚከበረውን የሻደይ በዓል ጨምሮ አሸንድዬ እና ሶለል በዓላት የፍልሰታ ጾምን መገባደጃ ተከትሎ የሚከበሩ በዓላት ናቸው:: በአጸደ ተፈራ (ዶ/ር) በተሰናዳው የሻደይ መጽሔት ላይ “ፍልሰታ” የቅድስት ድንግል ማርያም ስጋ ከጌቴሰማኒ ወደ ገነት መፍለሱን፣ በኋላም በገነት በእፀ ሕይዎት ስር ከነበረበት መነሳቱን የሚያመላክት እንደሆነ ተጠቁሟል::
ሻደይ በልጃገረዶች ብቻ የሚከወን ሲሆን የወንዶች ሚና ልጃገረዶችን ከበው ጥበቃ ማድረግ ነው:: የቀድሞው የዋግ ኽምራ ሀገረ ስብከት የስብከት ወንጌል መምሪያ ኃላፊ የነበሩት መጋቤ ምስጢር ገብረሕይዎት ኪዳነማርያም “በዓሉ በልጃገረዶች የሚከበረው በሔዋን ምክንያት የተዘጋው ገነት በእመቤታችን አማካኝነት በመክፈቱ ነው” ማለታቸውን የዋግ ኸምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያሳያል:: ይህም የበዓሉ ሃይማኖታዊ መሠረትነት ማሳያ ነው::
በሻደይ በዓል ቀሚስ፣ መቀነት፣ ጫማ እና ሻሽ ይለበሳል:: የፀጉር ሥሬቱም ግልብጭ፣ አንድ እግራ፣ ግጫ፣ አልባሶ፣ ሳዱላ፣ ጋሜ እና ቁንጮ፣ ጐፈሬ እና ከእንጨት የተሠራ ማበጠሪያን ያጠቃልላል:: እንደ ኩል፣ ድሪ፣ ድኮት፣ አልቦ፣ ዛጎል፣ ጠልሰም፣ መስቀል፣ አምባር፣ ማርዳ፣ ድባ፣ አሸን ክታብ፣ ስቃጫ… የመሳሰሉት ጌጣጌጦችም የበዓሉ ድምቀቶች ናቸው::
ሻደይ በዋግ ኸምራ ብሄረሰብ አስተዳደር በሚገኙ አካባቢዎች ለሚኖረው ሕዝብ የሚፈጥረው ማኅበራዊ መስተጋብር ከፍተኛ መሆኑን ያስታወቁት ደግሞ የብሄረሰብ አስተዳደሩ ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ እዮብ ዘውዴ ናቸው:: ሻደይ ዘንድሮም ባሕላዊ ገጽታውን ሳይለቅ ለማክበር ከወረዳ ጀምሮ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ሲከናወን መቆየቱን አቶ እዮብ አስታውቀዋል:: በዓሉን በተሳካ ሁኔታ ለማክበር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው ብለዋል::
ሕዝቡም ባህሉን እና ወጉን ጠብቆ እንዲያከብረው ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን መምሪያ ኃላፊው ጠቁመዋል:: ”ሻደይ ከድንግል ማርያም ማረግ ጋርም የተያያዘ በመሆኑ በዓሉ በቤተ ክርስቲያናትም በድምቀት ይከበራል” ያሉት አቶ እዮብ የሃይማኖት አባቶችም አከባበሩን አስመልክተው ምክረ ሐሳቦችን እንዲሰጡ እየተደረገ ነው ብለዋል::
እንግጫ ነቀላ እና ከሴ አጨዳ
የአዲስ ዓመት መቃረብ ዋናው ምልክት እንግጫ ነቀላ እና ከሴ አጨዳ ነው:: ይህ ባሕላዊ ክዋኔ በምዕራብ እና ምሥራቅ ጎጃም ዞኖች በሚገኙ ወረዳዎች በስፋት የሚዘወተር እንደሆነ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ መረጃ ያሳያል::
የእንግጫ ነቀላ በዓል ልክ እንደ ሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል ሁሉ በወንዶች ጠባቂነት በልጃገረዶች የሚከወን በዓል ነው:: ልጃገረዶች በየመንደራቸው ቡድን በመመስረት እንግጫ ለመንቀል በሀገር ባህል አልባሳት ተውበው እንግጫው ወደሚገኝበት መስክ ይወርዳሉ፤ እንግጫም ይነቅላሉ፤ ከሶሪት እና አደይ አበባ ጋር በመጎንጎን ለስጦታ ያዘጋጃሉ:: በበዓሉ ቀንም የተጎነጎነውን እንግጫ ይዘው በየቤቱ በመሄድ “እንኳን አደረሳችሁ!” በማለት በስጦታ መልክ ያበረክቱታል:: በስጦታ የተበረከተው የእንግጫ ጉንጉንም በየቤቱ ምሰሶ ወይም አጥር ላይ የመልካም ዘመን መምጣት ምሳሌ ተደርጎ ይታሰራል:: ይህ የሕዝቡን የእርስ በእርስ የመጠያቅ ባሕል በእጅጉ እንደሚያሳድገው ይታመናል::
የድንቅ ባህል ማሳያዎቻች እንዴት ይከበሩ?
የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ በነሐሴ እና ጳጉሜ ወራት የሚከበሩ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓላትን ምክንያት በማድረግ ነሐሴ 02 ቀን 2017 ዓ.ም መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫውን የሰጡት የቢሮ ኃላፊው መልካሙ ጸጋዬ ናቸው:: በመግለጫቸውም “ባሕላዊ ዕሴቶቻችን ለዘላቂ ሰላማችን የነበርንበት፣ ያለንበት እና የምንደርስበት” በሚል መሪ መልዕክት በዓላቱ እንደሚከበሩ አስታውቀዋል:: የመሪ ቃሉ መልዕክትም በዓላቱ አስቀድመው የነበሩን፣ አሁንም እየተከወኑ ያሉ እና ወደፊትም ተጠብቀው ለትውልድ የሚተላለፉ መሆናቸውን የሚገልጽ መሆኑን ተናግረዋል::
ክልሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጎብኝዎች መዳረሻ መሆኑን ጠቁመዋል:: የሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ ቡሔ፣ እንግጫ ነቀላ እና የከሴ አጨዳ ክብረ በዓላት ደግሞ የክልሉ ሕዝብ ባሕል፣ ታሪክ፣ ትውፊት እና ቅርስ ማሳያ እና ማስመስከሪያ መሆናቸውን አስታውቀዋል::
ከቡሄ ጀምሮ መከበር የሚጀምሩት የነሐሴ ወር ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓላትም በታሪክ ሂደት በተቀረጹበት የተለየ እና ተወዳጅ ክዋኔ ምክንያት ሚሊዮኖች በጉጉት እና በፍቅር የሚጠብቋቸው እና በቦታው ተገኝተው የሚያከብሯቸው ድንቅ ሀብቶች መሆናቸውን ተናግረዋል::
የሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ ቡሔ፣ እንግጫ ነቀላ እና የከሴ አጨዳ ክብረ በዓላት ላይ የሚታደሙ የኅብረተሰብ ክፍሎች በዕድሜ ወይም በጾታ የተገደቡ ቢሆነም ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የሚያከብራቸው በዓላት መሆናቸውን ተናግረዋል:: ማጀብ፣ ማስተናገድ እና መመረቅ ከእያንዳንዱ የኅብረተሰብ ክፍል የሚጠበቅ መሆኑን አንስተዋል::
የሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ እንግጫ ነቀላ እና የከሴ አጨዳ ክዋኔዎች ልጃገረዶች ባሕላቸውን እና ትውፊታዊ አደራቸውን በአደባባይ ለተተኪዎች የሚያጋሩበት ነው:: ነፃነታቸውን የሚያውጁበትም እንደሆነ ተናግረዋል:: አስደናቂ ባሕላዊ ትዕይንቶችን ለዓለም ለማሳየት፣ የየአካባቢው ባህላዊ ምግብ እና መጠጥ የሚገለጥባቸው በዓላት ናቸው::
ቡሔ በደብረ ታቦር፣ ሻደይ በዋግ ኽምራ፣ አሸንድዬ እና ሶለል በሰሜን ወሎ፣ የከሴ አጨዳ እና እንግጫ ነቀላ በምሥራቅ ጎጃም በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበሩ አስታውቀዋል:: የበዓላቱ የማጠቃለያ ዝግጅትም እንደ ክልል በባሕር ዳር ከተማ እንደሚከናወን አስታውቀዋል :: ለበዓላቱ በድምቀት መከበርም ከሐምሌ ጀምሮ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ገልጸዋል:: ለዝግጅቱም ቢሮው የተቀናጀ የግብዓት እና ሙያዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል::
እንደ ቢሮ ኃላፊው መግለጫ በዓላቱ የክልሉን ሕዝብ ባሕል እና እሴት በመጠበቅ ትውልዱ በጠንካራ ማንነት ላይ እንዲቆም ያግዛሉ:: በዓላቱ ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት ከሚያበረክቱት አስተዋጽኦ በተጨማሪም ምጣኔ ሀብታዊ መነቃቃት ይፈጥራሉ:: ይህም የበዓሉ ቀጥተኛ ባለቤት የሆነውን ማኅበረሰብ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ያደርጋል::
ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ በሚፈለገው ልክ እንዲለሙ እና እንዲጠበቁ ሠፊ ሥራዎች መሥራቱን አቶ መልካሙ ተናግረዋል:: ይህም በዓላቱ ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፉ እና ወደ ቱሪዝም ገበያው እንዲገቡ ያግዛል:: ክብረ በዓላቱ በሚከናወኑባቸው አካባቢ ብቻ ተወስነው የቆዩትን የቡሔ፣ የሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል እና የእንግጫ ነቀላ በክልል ደረጃ በማክበር እና በማስተዋወቅ ከፍተኛ ተቀባይነትን እንዲያገኙ መደረጉን ለተሠራው ሥራ አብነት አድርገው አንስተዋል::
የክልሉ ሕዝብ እና በየደረጃው ያለው የመንግሥት መዋቅር በዓላቱ በድምቀት እንዲከበሩ እና ለበዓሉ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ እንግዶችን በማስተናገድ የተለመደ እንግዳ ተቀባይነቱን በተግባር እንዲገልጥ ጥሪ ቀርቧል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የነሐሴ 12 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም