ተመራማሪዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ለማይችሉ አልጋ ላይ ለዋሉ አረጋውያን፣ ለአጥንት ስብራት ተጋላጭ ለሆኑ እና ሥር የሰደደ በሽታ ላለባቸው ሰዎች አጥንትን የሚያጠናክር መድሃኒት ለማግኘት መቃረባቸውን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡
የሆንግ ኮንግ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች እንቅስቃሴ አጥንትን እንዴት እና ለምን ጠንካራ እንደሚያደርገው በአካል ውስጥ በተተከለ መለያ (ሴንሰር) መረዳት መቻላቸውን እና ለችግሩ ተጠቂዎች መድሃኒት ለመሻት መቃረባቸውን አስታውቀዋል፡፡ይህም ግኝት ለአረጋውያን፣ አልጋ ላይ ለዋሉ ህሙማን ወይም ታካሚዎች እንዲሁም ለአጥንት ስብራት ተጋላጭ ለሆኑ ስር የሰደደ በሽታ ላለባቸው ሰዎች አዲስ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ነው ያሰመሩበት፡፡
አሁን ላይ ያሉት ህክምናዎች በእንቅስቃሴ ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውን የገለጹት ተመራማሪዎቹ ይህንን በቀላሉ ተግባራዊ ለማድረግ ህሙማኑ እንደሚቸገሩም ነው የደረሱበት፡፡የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በህዋሳት ደረጃ አጥንትን እንዴት የሚጠነክርበትን መንገድ በመኮረጅ የሚፈለገው ግብ ላይ መድረስ እንደሚቻል ደርሰውበታል፡፡
በሆንግ ኮንግ የአጥንት መድከም ወይም መሳሳት እና ለስብራት መዳረግ 45 በመቶ ሴቶችን እና እድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆናቸው ወንዶችን 13 በመቶ ይጐዳል ነው ያሉት፡፡
ተመራማሪዎቹ ስብ በአጥንት መቅኒ ውስጥ ሲከማች ጤናማ ህዋሳትን እንደሚያጨናንቅ ጠቁመዋል፡፡ ይህም አጥንትን እንዲሰንፍ እና እንዲደክም አድርጐ ችግሩን መግታት ወደ ማይቻልበት ደረጃ እንደሚያሸጋግር ደርሰውበታል፡፡
በመጨረሻም “ፒኢዞ1” የሚሰኝ ኘሮቲን ወይም ገንቢን ለይተዋል – ተመራማሪዎቹ፡፡ ይህ ገንቢ ኘሮቲንም የአጥንት መቅኒ የስብ ክምችትን ገድቦ የአጥንት ጥንካሬን መመለስ ያስችላል ነው ያሉት -ተመራማሪዎቹ፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የካቲት 2 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


