የአጭር ርቀት ሯጭ ለምን አጣን?

0
217

ኢትዮጵያ ለአትሌቲክስ ስፖርት ተስማሚ የአየር ፀባይ ፣ምቹ የመሬት አቀማመጥ ያላት ተፈጥሮ ፀጋውን አብዝቶ የሰጣት ሀገር ናት። ይሄንን ፀጋ በመጠቀም እ.አ.አ በ1960 የሮም ኦሎምፒክ አበበ ቢቂላ ታላቅ ገድል ከፈፀመ በኋላ በሀገራችን እና በአህጉራችን በአትሌቲክሱ ዘርፍ ትልቅ መነቃቃት ተፈጥሯል። ከዛን ጊዜ ጀምሮ በሁሉም መድረኮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በረዥም እና በመካከለኛ ርቀት የሚቀድማቸው አልተገኝም። በተለይ ርዥም ርቀት በሁለቱም ፆታዎች የኢትዮጵያውያን ባህል ከሆነ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ተቆጥሯል።
ይሁን እንጂ ሀገራችን በተለያዩ የአህጉር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች በአጭር ርቀት እና በሜዳ ተግባራት ግን ውጤታማ መሆን አልቻለችም። የአትሌቲክስ ስፖርት አፍቃሪም “ችግሩ ምንድነው? “ሲል ይጠይቃል። በዚህ ጉዳይ ላይ አሚኮ በኩር ዝግጅት ክፍል ከመምህር እና አሰልጣኝ መሰረት መንግስቱ ጋር ቆይታ አድርጋለች። መምህር እና አሰልጣኝ መሰረት ፣ በአሰላ ዩንቨርሲቲ በስፖርት ሳይንስ የትምህርት ክፍል በመምህርነት እያገለገለ ሲሆን በአሰላ የጥሩነሽ ዲባባ አትሌቲክስ አካዳሚም በአሰልጣኝነት እየሰራ ይገኛል። ለመሆኑ አጭር ርቀት የሚባሉት የትኞቹ ናቸው? የአጭር ርቀት (sprinting) ሩጫ ከረዥም ጊዜ በላይ ሳይሆን ወደ መጨረሻው መስመር ለመድረስ ትልቅ ፍጥነት እና ጉልበት የሚጠይቅ ነው። በኦሎምፒክ የአትሌቲክስ ዘርፍ በርካታ የተለያዩ የአጭር ጊዜ ውድድሮች ያሉ ሲሆን በሦስት የተለያዩ ርቀቶች የተከፋፈሉ ናቸው። መቶ ሜትር ፣ሁለት መቶ ሜትር እና አራት መቶ ሜትርን እንደሚያካትት የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ መረጃ ያመለክታል።
እንደ መምህር እና አሰልጣኝ መሰረት ገለፃ በሀገራችን በሁሉም የአትሌቲክስ ሰፖርት ዘርፎች በኦሎምፒክ ስፖርት ውጤት ማስመዝገብ የሚችል (Olompian athletes) እንዳለ ያምናል። ጥናቶችም የሚያስረዱት ይህ እንደሆነ ባለሙያው ያስገነዝባል። እንደ ኢትዮጵያ በመልክአ ምድር አቀማመጥ የታደለ ሀገር የለም። ኢትዮጵያ ለስፖርቱ ተስማሚ የሆነ ደጋ ፣ ወይናደጋ እና ቆላማ የአየር ፀባይ ቢኖራትም በአጭር ርቀት እና በሜዳ ተግባራት በልዩነት በሚጠበቀው ያህል ውጤት ማስመዝገብ አልተቻለም ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ፣ ቦትስዋና ፣ናሚቢያ ፣ ናይጀሪያ እና ደቡብ አፍሪካን የመሳሰሉ ሀገራት በዓለም አቀፍ መድረክ በአጭር ርቀት እየተሳካላቸው ያሉ ሀገራት ናቸው።
በኢትዮጵያ ለምንድነው ከሌሎቹ በተለየ በአጭር ርቀት እና በሜዳ ተግባራት ውጤት ማስመዝገብ ያልተቻለቸው? የተሰጥኦ አለመኖር? ተፈጥሯዊ ዘረመል፣ አመጋገባችን፣ ተፈጥሯዊ የሰውነት ቅርፃችን ወይስ የስነ ልቦና ችግር ? የሚለው በተደጋጋሚ የሚነሳ ጥያቄ ነው። የዘርፉ ባለሙያው መምህር እና አሰልጣኝ መሰረት መንግስቱ ችግሩ ከላይ የተጠቀሰው ሳይሆን የአጭር ርቀት እና የሜዳ ተግባራት አትሌቶችን ከታች ጀምሮ የምናሳድግበት መንገድ (developmental process) ደካማ መሆኑን ያነሳል።
ከአጭር ርቀት ሩጫ በተጨማሪ ፍጥነት እና ኃይል የሚያስፈልጋቸው እግር ኳስ እና ቅርጫት ኳስ በመሳሰሉ ሌሎች ስፖርቶች ላይም ደካማ መሆናችን ተፈጥሯዊ ተሰጥኦን ተንከባክበን የምናሳድግበት መንገድ አነስተኛ ስለመሆኑ ማሳያዎች እንደ ሆኑ ተጠቅሷል። ስለ አጭር ርቀት እና የሜዳ ተግባራት በቂ ግንዛቤ አለመኖርም ሌላኛው ችግር ነው። በሀገራችን ውስጥ እንደ ረዥም ርቀት በአጭር ርቀት እና ሜዳ ተግባራት ምልክት የሆኑ አትሌቶች አለመኖራቸው ባለተሰጥኦዎች እንዳይወጡም አድርጓል።
ለእነዚህ ስፖርቶች የሚሆን በቂ መሰረተ ልማት አለመሟላቱም እንደ ምክንያት ሲነሳ ሌላው እና ዋነኛው ዘርፉን ለማሻሻል የሚተጋ ቁርጠኛ አመራር አለመኖሩም እንደ ችግር ይነሳል። ፍጥነት፣ ጥንካሬን ፣ቴክኒክን መቼ እና እንዴት ማሰልጠን እንዳለበት ጠንቅቆ የሚረዳ ብቁ፣ የሰለጠነ እና አቅም ያለው አሰልጣኝ እጥረትም አለ ብሏል ባለሙያው። ከተሰራበት ኢትዮጵያውያን ውጤታማ የሚሆኑበት ለአጭር ርቀት የሚሆን የጡንቻ ድር መኖሩንም በህክምና ሳይንሱ ተረጋግጧል። በሀገራችን ለአጭር ርቀት እና ለሜዳ ተግባራት የሚሆን ተሰጥኦ ፣ የአየር ፀባይ ፣ የመሬት አቀማመጥ የለም የሚባለውም የተሳሳተ አስተሳሰብ መሆኑን ጭምር ባለሙያው አጽንኦት ሰጥቶታል።
ታዲያ በምን መንገድ ይሠራ?
የአጭር ርቀት እና የሜዳ ተግባራት ስልጠናዎችን ለመስጠት ለዘርፉ ተስማሚ የአየር ፀባይ እና የመሬት አቀማመጥ መለየት ያስፈልጋል። ለእነዚህ ስፖርቶች ከባህር ጠለል ወለል በላይ ከስድስት መቶ ሜትር ከፍታ በታች መሆን እንደሚኖርበት ባለሙያው ያብራራል። የሜዳ ተግባራት ለሆኑት ለጦር እና ለመዶሻ ውርወራ፣ ለዝላይ ስፖርቶችም ከአጭር ርቀት ስፖርቶች ጋር ተመሳሳይ የአየር ፀባይ እና የመሬት አቀማመጥ ያስፈልጋል።
በቆላማ አካባቢዎች ከፍተኛ የአየር መጠን ፣ ሙቀት ስለሚኖር እና የአየር ግፊቱም ከባድ ስለሆነ አየሩን ሰንጥቆ ለማለፍም ብዙ ጉልበት ፣ ብዙ ኃይል ያስፈልጋል እና ብቁ ስፖርተኞችን ለማፍራት ይሄ ሀሳብ ግምት ውስጥ መግባት እንዳለበት መምህር እና አሰልጣኝ መሰረት ይመክራል። ከባህር ጠለል በላይ ዝቅተኛ ከፍታ ካላቸው የአውሮፓ ሀገራት ጋር ለመፎካከር ተመጣጣኝ በሆነ ከፍታ እና በተጠና መንገድ መስራት እንደሚጠይቅም ባለሙያው ያሳስባል። “ኢትዮጵያ ውስጥ ለአጭር ርቀት እና ለሜዳ ተግባራት ተብሎ በቆላማ(በዝቅተኛ ቦታ) አካባቢ የተቋቋመ ክለብ የለም።ስልጠናዎች የሚሰጡትም ለረዥም ርቀት ተብለው ከተቋቋሙ ክለቦች ጋር በአንድ ቦታ ነው። ከባህር ዳር ወደ አሰላ ስዘዋወር የመጀመሪያ ጥያቄዬ አጭር ርቀት እና የሜዳ ተግባራት ከዚህ መሆን የለበትም ይልቁንም ዝቅተኛ ቦታዎች ላይ ነው መሆን ያለበት የሚል ነበር ነገር ግን የሰማኝ አልነበርም።” ያለው ባለሙያው እስካሁንም ስልጠናው በተመሳሳይ መንገድ እየተሰጠ መሆኑን ከበኩር ዝግጅት ክፍል ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል።
ቦታዎች ተለይተው ታዳጊዎች ከታች ከአምስት ዓመታቸው ጀምሮ ፣ ክህሎታቸውን ተረድቶ መስራት ይጠይቃል። የፍጥነት እና የኃይል ስፖርት ነው የሚባለው አጭር ርቀት ከጡንቻ፣ ከነርቭ ሥርዓት ጋር የሚገናኝ በመሆኑ ከሌሎች በተለየ ሳይንሳዊ ዕውቀት የሚጠይቅም ነው። ይሄ ደግሞ በታዳጊዎች ላይ መሰራት ያለበት ከታች ዕድሜ መሆኑን ያስረዳው ባለሙያው በዚህ መንገድ ካልሆነ ግን የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት አዳጋች ነው ይላል። በረዥም ርቀትም ቢሆን እየተገኘ ያለው ውጤት በአትሌቶቹ ጥረት እና ድካም እንጂ የባለሙያ፣ የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የአትሌቲክስ ፌደሬሽን እገዛ እንዳልሆነ ጭምር ባለሙያው ያብራራል። መምህሩና አሰልጣኙ፣ ለዚህም ነው ለሚመጣው ውጤት ተገቢውን ዋጋ እና ክብር ያልተሰጠው ብሏል።
ዘርፉም በአጠቃላይ ስልጠና እና ምልመላ ተኮር ሳይሆን ውድድር ተኮር መሆኑ የተሻለ ሥራ እንዳይሰራ አድርጓል። በትምህርት ቤት በሥርዓት ትምህርት ተቀርጾ መሰጠት እንዳለበት የዘርፉ ባለሙያ ያስረዳል። ተሰጥኦ የምንለይበት እና የምናሳድግበት ሥርዓት መዘርጋትም ይኖርበታል፣ በአትሌቲክስ የረዥም ርቀት ባህል ተጽእኖንም ማስወገድ ይገባል። “በሜዳ ተግባራት ፣ በውርወራም ሆነ በዝላይ ስፖርት ከዓለም ግማሽ ርቀት ላይ ነው ያለነው፣ አሎሎ ውርወራ ዓለም ሃያ ሁለት ሜትር ሲወረውር እኛ ገና አስራ አንድ ሜትር ብቻ ነው የምንወረውረው፣ በጦር ውርወራም ዓለም ሰማንያ ሜትር ሲወረውር እኛ ግን ስድሳ ሜትር ገደማ ነው የምንወረውረው” ይህ የሚያሳየውም መሰረታዊ ለውጥ እንደሚያስፈልግ ነው ብሏል መምህር እና አሰልጣኙ።
የትኞቹ አጭር ርቀቶች እና የሜዳ ተግባራት ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሰሩ ውጤታማ እንሆናለን?
በዘርፉ ቶሎ ውጤታማ ለመሆን እና በኦሎምፒክ መድረክ ውጤት ለማስመዝገብ መቶ ሜትር መሰናክል፣ መቶ አስር ሜትር መሰናክል ፣ አራት መቶ ሜትር እና አራት መቶ ሜትር መሰናክል አጭር ርቀቶች በደንብ ቢሰሩ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል የባዮ ሜካኒሱን ጥናቶች ጠቅሶ አሰልጣኝ እና መምህር መሰረት ያስረዳል። ለእነዚህ ስፖርቶችም ባህር ዳር አካባቢ ፣ ደሴ ሀይቅ፣ ደቡብ ኮንሶ እና ሌሎችንም መጠቀም ከተቻለ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ተሰጥኦ መኖሩን ገልጿል። አትሌቶቹ መሰናክሉን የሚዘሉበትን የጊዜ እርዝማኔ ማሳጠር ከተቻለ በቀላሉ ለውጤት ይበቃሉም ነው የተባለው። በመቶ ሜትር ሩጫ ውጤት ለማምጣት ግን በጣም ብዙ ሥራ መስራት እንደሚጠይቅ ተጠቁሟል። ከሜዳ ተግባራት ደግሞ በጦር ፣ በአሎሎ እና በመዶሻ ውርወራ ከተሰራ ውጤታማ መሆን ይቻላል የመምህር እና አሰልጣኝ መሰረት አስተያየት ነው።
የጦር፣ መዶሻ እና አሎሎ ውርወራ ጎንደር፣ ደሴ፣ ጋምቤላ ቢሆን ይመረጣል። የክብደት ስፖርትን ባህሉ ያደርገ አካባቢ መሆን እንዳለበት ይታመናል። ለአብነት ከጎንደር አካባቢ ከዚህ በፊት በርካታ ስፖርተኞች በመቻል ስፖርት ክለብ ከተጫዋችነት እስከ አስልጣኝነት ደረጃ መድረሳቸውም ይታወሳል። በዚህ መንገድ ሁሉም በየደረጃው ከሰራ በዘርፉ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደ ቦትስዋና ወጤታማ መሆን ይቻላል የባለሙያው ምክረ ሀሳብ ነው፡፡
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር ታኀሣሥ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኲር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ
በhttp:// www.ameco.et/Bekur
በቴሌግራም – https://t.me/bekur123 ላይ ማግኘት ይችላሉ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here