የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዓመት ሲጀምር ብዙዎች የሚጠበቁት የተለመዱትን የዋንጫ ተፎካካሪዎች ስም ነበር። ይሁን እንጂ ባለፉት ሁለት ዓመታት ተዳክመው የነበሩት አፄዎቹ በሊጉ የመጀመሪያ ስድስት ሳምንታት ውስጥ ዳግም ወደ ቀድሞ ግርማቸው እየተመለሱ መሆናቸውን አብስረዋል። ፋሲል ከነማ በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ እየተመራ ዘንድሮ ገና ከወዲሁ ለዋንጫ ተፎካካሪ መሆኑን እያሳየ ይገኛል::
ከአሚኮ ስፖርት ጋር ቆይታ ያደረገው የእግር ኳስ ባለሙያው አቶ አብርሃም መላኩ እንደገለጸው የአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ወደ ቡድኑ መምጣት በክለቡ ውስጥ የነበረውን “ያለመረጋጋት መንፈስ” (Instability) በማስወገድ የአሸናፊነት ስነ ልቦና እንዲገነባ ምክንያት ሆኗል ይላል::
አሰልጣኙ ቡድኑን ሲረከቡ ያገኙት ስብስብ በተጫዋቾች ስነ-ልቦና እና በታክቲክ አተገባበር ላይ ክፍተቶች ነበሩበት:: ዮሐንስ ሳህሌ ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ የመልበሻ ቤት መንፈሱን በማደስ ሜዳ ላይ ምን ማድረግ እንዳለባቸው በውል የሚያውቁ እና በራስ መተማመናቸው ከፍ ያሉ ተጫዋቾችን መፍጠር ችለዋል::
ቡድኑ አሁን የሚታይበት የታክቲክ ዲሲፕሊን እና የመናበብ አቅም የአሰልጣኙ ፍልስፍና በቡድኑ ውስጥ በፍጥነት መስረፁን እንደሚያመለክት የእግር ኳስ ባለሙያው ያስረዳል:: ባለፉት ዓመታት የነበረው የአቋም መዋዠቅ እና የተሸናፊነት ስሜት ጠፍቶ አሁን ላይ ከፍተኛ የማንሸነፍ ስነ-ልቦና ያለው ቡድን ተገንብቷል:: “በእግር ኳስ ዓለም ማጥቃት ጨዋታን አሸናፊ ያደርጋል፤ መከላከል ደግሞ ዋንጫን አሸናፊ ያደርጋል“ የሚል የሰር አሌክስ ፈርጉሰን ዝነኛ አባባል አለ::
የዘንድሮው ፋሲል ከነማ አቋም የታላቁን አሰልጣኝ ንግግር በተግባር ያረጋገጠ ነው ማለት ይቻላል:: ፋሲል ከነማ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ነው የተቆጠረበት:: ይህ ቁጥር በሊጉ ካሉ 20 ክለቦች የበለጠ የመከላከል ብቃት ያለው መሆኑን ያሳያል::
ታዲያ የዘንድሮው የፋሲል ከነማ የኋላ ክፍል ጥንካሬ የመጣው ከየት ነው? የመጀመሪያው ምክንያት ግብ ጠባቂው ሞይስ ፖውቲ ያሳየው ድንቅ ብቃት እንደሆነ ባለሙያው ያብራራል:: ፖውቲ በወሳኝ ሰዓት ክለቡ ግብ እንዳይቆጠርበት በመከላከል ለቡድኑ ትልቅ ዋስትና ሆኗል::
አሰልጣኝ ዮሐንስ የፈጠሩት “የቡድን መከላከል” (Collective Defending) ስልት ከተጋጣሚ ሳጥን ጀምሮ ኳስን በመቀማት እና የተጋጣሚን ቡድን በማስጨነቅ የተመሰረተ ነው:: የተከላካይ መስመሩ እና አማካይ ክፍሉ ያላቸው መናበብም ለተጋጣሚ አጥቂዎች ክፍተት እንዳይገኝ አድርገዋል:: ይህ ጥንካሬው ነው ዘንድሮ ገና ከወዲሁ ክለቡ ለዋንጫ ተጠባቂ ያደረገው::
ምንም እንኳን የፋሲል ከነማ ዋናው የጥንካሬ ምንጭ መከላከሉ ቢሆንም የቡድኑን የማጥቃት አቅም መዘንጋት ግን አይቻልም:: ምንም እንኳ የፊት መስመሩ አስፈሪ ባይሆንም ውጤት ቀልባሽ (Efficient) የመሆን ባህሪን ግን አዳብሯል:: በስድስት ጨዋታዎች አምስት ግቦችን ከመረብ አገናኝቷል:: እነዚህ ግቦችም ከፍ ያለ ዋጋ ያላቸው 12 ነጥቦችን አስገኝተዋል::
በዚህ ረገድ የአጥቂው በረከት ግዛው ሚና እጅግ የጎላ ነው:: ሦስት ግቦችንም ከመረብ አገኝቷል:: ፋሲል ከነማ የሚያገኛቸውን ውስን የግብ እድሎች ወደ ውጤት በመቀየር በረከት ያሳየው ብቃት ቡድኑን ከነጥብ መጋራት ወደ አሸናፊነት በተደጋጋሚ ሲያሸጋግር ተመልክተናል:: እስካሁን በተመለከትነው የአጼዎቹ የአጨዋወት ስልት ብዙ ግቦችን ከማስቆጠር ይልቅ አነስተኛ ግብ በማስቆጠር ውጤቱን አስጠብቆ ከሜዳ ሲወጣ ዐይተናል:: አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ እስካሁን ባለው የጨዋታ ዘይቤ ውጤትን መሰረት ያደረገ (ፕራግማቲክ) አካሄድን መምረጡን ሜዳ ውስጥ ተመልክተናል::
አጼዎቹ ከሊጉ ጠንካራ እና በገንዘብ አቅም ከተገነባው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ነጥብ መጋራቱ ቡድኑ ገና ከወዲሁ ጠንካራ ተፎካካሪ መሆኑን ያሳየበት ነበር:: ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን ሁለት ለባዶ በማሸነፍ ድንቅ የማጥቃት አቅሙን ያሳየበት እና በራስ መተማመኑን ያሳደገበት ድል እንደነበር የሚታወስ ነው::
ሲዳማ ቡና እና ሽረ እንዳስላሴን በተመሳሳይ አንድ ለባዶ በማሸነፍ የአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌው ቡድን ጠንካራ ተከላካይ እና ታክቲካዊ ብልጥነት የታየበት፣ በትንሽ ልዩነት አሸንፎ የመውጣት ብቃት እና ወጥነቱን (Consistency) ያስመሰከረበት እንደነበር አይዘነጋም:: በሊጉ ጠንካራ ከሆነው መቻል ጋር የዋንጫ ግብ ሳይቆጠርበት ነጥብ መጋራቱ የቡድኑን የኋላ ክፍል ጥንካሬ ይበልጥ አረጋግጧል::
የባለፉት ስድስት መርሀግብሮች ውጤት እንደሚያሳዩት ፋሲል ከነማ የገጠማቸው ቡድኖች ቀላል የሚባሉ አይደሉም::ነገር ግን ሁሉንም ፈተናዎች በብቃት በመወጣት አንድም ሽንፈት ሳይገጥመው በወጥነት እየተጓዘ ነው:: እግር ኳስ በስሜት ብቻ ሳይሆን በቁጥርም ይተነተናል። የፋሲል ከነማን የዘንድሮ እድገት ለመረዳት ካለፉት ዓመታት ተመሳሳይ አምስት ሳምንታት ብቻ ጋር ስናነጻጽረው ዘንድሮ የተሻለ ሆኖ እናገኘዋለን::
በ2016 ዓ.ም የመጀመሪያዎቹ አምስት ሳምንታት ቡድኑ ዘጠኝ ነጥብ ነበር የሰበሰበው:: 2017 ዓ.ም ደግሞ ሰባት ነጥብ እንደሰበሰበ ቁጥራዊ መረጃዎች ያመለክታሉ:: ዘንድሮ በአምስት ጨዋታዎች 11 ነጥብ መሰብሰቡ አይዘነጋም:: በዚህ ዓመት ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ድረስ እስካሁን ሽንፈትን አለማወቁ የቡድኑን ስነ-ልቦና ከፍ አድርጎታል::
ፋሲል ከነማ ከዚህ በፊት ነጥብ ይጥልባቸው የነበሩትን ጨዋታዎች ዘንድሮ በድል እየወጣ መሆኑን ስንመለከት ወደ ሻምፒዮንነት አስተሳሰብ (Championship Mentality) መመለሱን ያሳያል ብሏል የእግር ኳስ ባለሙያው አቶ አብርሃም::
ሌላው የአማራ ክልል ክለብ ባሕር ዳር ከነማ ከባለፉት ጥቂት ዓመታት ሲነጻጸር በመጀመሪያዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ደካማ ውጤት አስመዝግቧል:: በተጨማሪም ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡናን የመሳሰሉ ክለቦች አጀማመራቸው ያን ያህል ጥሩ የሚባል አይደለም:: ከእነዚህ ጠንካራ ክለቦች በተቃራኒ ፋሲል ከነማ እያሳየ ያለው ወጥነት ለሊጉ ዋንጫ ያለውን ተስፋ ያረጋግጣል::
ፋሲል ከነማ ድንቅ አጀማመር ቢያደርግም የውድድር ዘመኑ ገና እየተጀመረ በመሆኑ ብዙ የቤት ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅበት አቶ አብርሃም ተናግሯል:: ሊጉ በተለያዩ ከተሞች የሚደረግ በመሆኑ የአየር ፀባይ ለውጡ ቡድኑን ሊፈትን እንደሚችል የዘርፉ ባለሙያ አቶ አብርሃም ይጠቁማል::
በተለይ ሊጉ ለብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎች ወይም ለኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታዎች ሲቋረጥ ያለውን የእርፍት ጊዜ ተጠቅሞ የተጫዋቾችን አካላዊ ብቃት መጠበቅ እንደሚያስፈልግም ባለሙያው ያስረዳል:: እንዲሁም ክለቡ ለሁሉም ክለቦች ተመሳሳይ ግምት በመስጠት ለማሸነፍ ሜዳ ውስጥ መግባት አለበትም ተብሏል::
የ2018 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች አፄዎቹ ተመልሰዋል! ብለው በልበ ሙሉነት የሚናገሩበት ዓመት የሆነ ይመስላል:: ጠንካራ የኋላ ክፍል፣ ብልህ አሰልጣኝ እና ውጤት ቀልባሽ የፊት መስመር የያዘው የአጼዎቹ ስብስብ ዘንድሮው ሻምፒዮን ለመሆን የሚያስችሉ ግብአቶች ሁሉ እንዳሉት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ሳምንታት ምስክር ናቸው::
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የህዳር 22 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


