የአፈር ለምነትን ለማሻሻል እየተሠራ መሆኑን ቢሮው አስታወቀ

0
77

የአፈር አሲዳማነትን በመከላከል የአፈር ለምነትን ለመጨመር የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል፤ ሐሳባቸውን በስልክ ያካፈሉን አርሶ አደሮችም የአፈር አሲዳማት መስፋፋቱን ገልጸው ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

በግብርናው ዘርፍ በትርፍ አምራችነቱ የሚታወቀው አማራ ክልል በምርታማነቱ እንዳይቀጥል ከገጠሙት እንቅፋቶች መካከል የአፈር አሲዳማነት ተጠቃሽ ነው። ይህን ችግር በዘላቂነት ለመከላከል ደግሞ የተለያዩ ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባ ተጠቁሟል።

 

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ዙሪያ ወረዳ ወይንማ አምባየ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ምንባለ ታየ ለበኩር በስልክ እንደተናገሩት የመሬታቸውን ለምነት ለመጠበቅ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ ነው። የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) ማዘጋጀት እና መጠቀም ቀዳሚ ሥራቸው ነው። በአሲድ የተጠቃ መሬታቸውን በኖራ ማከም ደግሞ ሌላው ተግባራቸው እንደሆነ ነግረውናል።

 

እንደ አርሶ አደሩ ማብራሪያ ሦስት ጥማድ መሬታቸውን በኖራ በማከም እና የተፈጥሮ ማዳበሪያን በመጠቀም የአፈር ለምነቱ እንዲመለስ አድርገዋል። በዚህም ማሳቸው ከፍተኛ የምርት ጭማሪ ማሳየቱን ነው ተሞክሯቸውን ያጋሩን።

 

የአፈር አሲዳማነት ችግሩ አሳሳቢ እንደነበር ያስታወሱት አርሶ አደሩ በኖራ በማከም እና የተፈጥሮ ማዳበሪያ አቀናጅተው በመጠቀም በፊት ይገኝ ከነበረው ምርት በእጥፍ ጭማሪ ማሳየቱን ገልጸዋል።

 

አርሶ አደር አምባየ እንዳሉት መሬታቸው በአሲዳማ አፈር በመጠቃቱ ምርታማነቱ ቀንሶ ነበር። ይሁን እንጂ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ የአፈር ናሙና በግብርና ባለሙያ አስመርምረው ኖራ መጠቀም እንደጀመሩ ነግረውናል። በ2017/18 የምርት ዘመን 15 ኩንታል ኖራ በመግዛት መሬታቸውን እያከሙ ነው። ሌሎች አርሶ አደሮችም የተፈጥሮ ማዳበሪያ እና ኮምፖስት በመጠቀም በአሲድ የተጠቃ መሬታቸውን ማከም እንዳለባቸው ተሞክሯቸውን አካፍለዋል።

በኖራ ማከም የአፈር ለምነቱን በማሻሻል እንዲሁም ምርታማነቱን የመጨመር አቅሙ ከፍተኛ በመሆኑ የተጎዳውን መሬት ማከም እንዲቻል መንግሥት በቂ ኖራ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል።

 

የምዕራብ ጎጃም ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አጉማሴ አንተነህ የአፈር ለምነትን ለማሻሻል በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል። ከነዚህ ተግባራት መካከልም የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) ማዘጋጀት እና ኖራ ማቅረብ እንደሆኑ ጠቅሰዋል። አርሶ አደሩ ኖራን የመጠቀም ፍላጎቱ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መምጣቱንም ተናግረዋል። ሆኖም በወቅቱ እና በበቂ መጠን ኖራ እንደማይቀርብ አመላክተዋል።

 

በዞኑ አሲዳማ አፈርን ለመከላከል 48 ሺህ 103 ኩንታል ኖራ በመግዛት አንድ ሺህ 603 ሄክታር መሬት በኖራ ለማከም እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት (ሐምሌ ወር 2ኛ ሳምንት መጨረሻ) ድረስ ስምንት ሺህ 275 ኩንታል ኖራ ለአርሶ አደሩ በማሰራጨት 413 ሄክታር መሬት ማከም እንደተቻለ ተናግረዋል። በተጨማሪም የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ቨርሚ ኮምፖስት፣ ባዮ ሳላሪ ኮምፖስት፣ መደበኛ ኮምፖስት እና አረንጓዴ ማዳበሪያን) በመጠቀም የአፈርን ለምነት ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ መሆኑን  አስረድተዋል።

 

በአማራ ክልል ከሚታረሰው አምስት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 36 በመቶው በአፈር አሲዳማነት የተጠቃ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ የአፈር ለምነት ማሻሻያ ባለሙያ አምሳሉ አድማስ አስታውቀዋል። የሰብል ምርታማነትን በከፍተኛ መጠን እንዲቀንስ ብሎም ከምርት ውጪ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል የአፈር አሲዳማነት አንዱ መሆኑንም ለበኩር ጋዜጣ ተናግረዋል። በክልሉ የአፈር አሲዳማነት የሚያጠቃቸው ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ አካባቢዎችን መሆኑ ደግሞ ችግሩን አሳሳቢ አድርጎታል ነው ያሉት።

 

የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት መፍትሔ የሚሆኑ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ግብርና ቢሮ የግብርና ግብዓት እና ገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ ሙሽራ ሲሳይ ናቸው። እንደ ወ/ሮ ሙሽራ ማብራሪያ በአሲድ የተጠቃን መሬት የተለያዩ ዘዴዎችን በመተግበር ለምነቱን መመለስ ካልተቻለ በክልሉም ሆነ በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል።

 

በመሆኑም በአማራ ክልል በአሲዳማ አፈር የተጎዳውን መሬት ለማከም የፌዴራል መንግሥት 556 ሚሊዮን ብር መድቦ ግዥ በመፈፀም ለአርሶ አደሩ ኖራ የማቅረብ ተግባር እያከናወነ ነው ብለዋል። በምርት ዘመኑ (2017/18) 199 ሺህ ኩንታል ኖራ ገዝቶ ለማሰራጨት ታቅዶ 160 ሺህ ኩንታል ኖራ መገዛቱን ገልፀዋል። 149 ሺህ 614 ኩንታል የሚሆን ኖራ መሰራጨቱንም አክለዋል።

 

ዳይሬክተሯ አያይዘውም የአፈር አሲዳማነትን በኖራ ከማከም ባሻገር የተፈጥሮ ማዳበሪያን (ኮምፖስት) መጠቀም፣ ሰብልን በፈረቃ መዝራት፣  የተቀናጀ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ማከናወን እንደሚገባ አሳስበዋል።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የሐምሌ 21 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here