በአማራ ክልል በ2017/18 የምርት ዘመን አምስት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማረስ 187 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የዕቅድ ዝግጅት፣ ክትትል እና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ጌትነት እንደተናገሩት በመኸር በሰብል ለመሸፈን በዕቅድ ከተያዘው ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ታርሷል። ምርታማነቱን በሄክታር ከ32 ኩንታል ወደ 34 ኩንታል ለማድረስ ታልሞ እየተሠራ ነው።
በክልሉ ለ2017/18 የመኸር ምርት ዘመን የሚውል ስምንት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዷል። ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ ከሦስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደብ ደርሷል። እስካሁን ባለው መረጃ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቷል።
የዘር ወቅት ቀድሞ በሚጀምርባቸው አካባቢዎች ቅድሚያ በመስጠት የማዳበሪያ ሥርጭቱ እየተከናወነ መሆኑን እና ለአርሶ አደሩ ለማድረስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት ለምርት ዘመኑ የሚያገለግል በሁሉም የሰብል ዓይነቶች በቂ ምርጥ ዘር ተባዝቷል። እስካሁንም 280 ሺህ 897 ኩንታል የዘር ብዜት እንደተሰበሰበም ተናግረዋል።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም