የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ አርሶ አደሩን ከምርት ውጪ እንዳያደርገው በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፤ በአማራ ክልል በ2017/18 የምርት ዘመን ከአምስት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ይሸፈናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ቢሮው አስታውቋል:: 187 ሚሊዮን ኩንታል ምርትም ይጠበቃል:: ለስኬቱ ደግሞ የምርታማነት ማረጋገጫ አማራጮችን አሟጦ መጠቀም ይገባል ተብሏል::
የክልሉ ግብርና ቢሮ ከአጋር አካላት ጋር የምርታማነት ማሳደጊያ ስልቶችን በተመለከተ ውይይት አካሂዷል፤ በውይይቱ የተገኙት ምክትል ቢሮ ኃላፊዉ አጀበ ስንሻው በመኸር ዘመኑ ለሚጠበቀው ምርት ስምንት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሟል:: ከዚህ ውስጥ አራት ነጥብ አንድ ሚሊዮኑ ወደብ ላይ ደርሷል:: ወደ ክልሉ የገባው ደግሞ ሦስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል የሚሆነው ነው:: ወደ አርሶ አደሩ የተሰራጨውም ከሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ይልቃል:: ይህም ቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎች በቂ መሆኑን አቶ አጀበ ጠቁመዋል::
ቀሪዉን የአፈር ማዳበሪያ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ወደ ክልሉ ለማስገባት እየተሠራ መሆኑን ምክትል ቢሮ ኃላፊው አስታውቀዋል:: እንደ አቶ አጀበ ማብራሪያ በዚህ ዓመት የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ችግር አያጋጥምም፤ ምክንያቱ ደግሞ ግዢው ቀድሞ መከናወኑ ነው::
የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ ከለፉት ሁለት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር በዚህ ዓመት ጭማሪ መታየቱን አቶ አጀበ ገልጸዋል:: መሠረታዊ ምክንያቱም ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖ ስለመሆኑ ነው ያነሱት::
የአፈር ማዳበሪያ በተገዛበት ዋጋ ያለምንም ድጎማ ቀጥታ ቢሸጥ አርሶ አደሩ የአፈር ማዳበሪያ በበቂ መጠን እንዳይጠቀም በማድረግ በምርታማነት ላይ አሉታዊ ጫና ሊፈጥር እንደሚችል አቶ አጀበ ተናግረዋል:: በመሆኑም መንግሥት ተጽዕኖውን በመረዳት ከአንድ ኩንታል ሦስት ሺህ 700 ብር በድምሩ 87 ቢሊዮን ብር ድጎማ አድርጎ የአፈር ማዳበሪያን ለአርሶ አደሩ እያቀረበ መሆኑን ምላሽ ሰጥተዋል::
የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ ጨምሮ እያለ የሰብል ምርቶች ዋጋ በእጅጉ መቀነሱ ሌላው በክፍተት የሚነሳ ጉዳይ እንደሆነ አቶ አጀበ አንስተዋል:: ክልሉ ካጋጠመው የሰላም መደፍረስ ጋር ተገናኝቶ አርሶ አደሩ ያመረተውን ከቦታ ቦታ አዘዋውሮ መሸጥ ባለመቻሉ የሰብል ምርቶች ላይ የዋጋ ዝቅ ማለት መከሰቱን አንስተዋል:: አቶ አጀበ አርሶ አደሩ የግብርና ግብዓትን መግዛት ያለበት ሰብል በመሸጥ ብቻ መሆን የለበትም ብለዋል:: “የእኛ የግብርና ሥርዓት ድብልቅ ግብርና ነው፤ አርሶ አደሩ ከሰብል ምርት ባለፈ ከእንስሳት፣ ከደን ልማት፣ … ገቢ ያገኛል:: ይህንን ገቢውን አጠራቅሞ አፈር ማዳበሪያ በመግዛት ለተሻለ ተጠቃሚነት መዘጋጀት እና ራሱን ማሳመን ይኖርበታል” ብለዋል::
ከዚህ ባሻገር የአርሶ አደሩ የመግዛት አቅም እየተዳከመ ሲሄድ ተግባራዊ ሊደረግ የሚችለው የአፈር ማዳበሪያን በብድር ማሰራጨት ነው:: እንደ ቢሮ የተያዘው ዕቅድ አርሶ አደሮች ቢያንስ የመጀመሪያውን ዙር ገዝተው እንዲጠቀሙ ነው ብለዋል:: በቀጣይ የአርሶ አደሩን ነባራዊ ሁኔታ መሠረት ያደረገ የአፈር ማዳበሪያ ሥርጭት (ብድር) ሊመቻች እንደሚችል አስታውቀዋል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም