የአፈር አሲዳማነትን መከላከል እንደሚገባ ተገለፀ

0
67

የሰብል ምርታማነትን በከፍተኛ መጠን እንዲቀንስ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል የአፈር አሲዳማነት አንዱ ነው። የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳትም ለችግሩ መፍትሔ የሚሆኑ ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባም ተገልጿል።

በአማራ ክልል የአፈር አሲዳማነት ከተከሰተባቸው አካባቢዎች መካከል የምሥራቅ ጎጃም ዞን አንዱ ነው። በምሥራቅ ጎጃም ዞን የሁለት እጁ እነሴ ወረዳ ሀገረ ብርሐን ቀበሌ ነዋሪው የኔዓለም መኮንን ለበኩር ጋዜጣ እንደተናገሩት የአፈር አሲዳማነት መሬታቸውን ከምርት ውጪ አድርጎት ነበር። ሆኖም አሁን ላይ ሶስት ጥማድ መሬታቸውን በኖራ በማከም እና የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) በመጠቀም የአፈር ለምነቱ እንዲመለስ አድርገዋል። የአፈር አሲዳማነት ችግሩ አሳሳቢ እንደነበር የተናገሩት አርሶ አደር የኔዓለም ከኖራ በተጨማሪ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ጭምር አቀናጅተው ከመጠቀማቸው በፊት ይገኝ ከነበረው ምርት የሶስት እጥፍ ጭማሪ ማሳየቱን ተናግረዋል። ከዘጠኝ ዓመት በፊት መሬታቸውን በኖራ ማከም የጀመሩት አርሶ አደሩ አሁን ላይ መሬታቸው ሙሉ ለሙሉ ለምነቱ እንደተመለሰ ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ በስልክ እንደገለፁት የአፈር አሲዳማነትን በኖራ ማከም “የታመመን ሰው መድኃኒት ሰጥቶ እንደማዳን ነው”። አሲዳማ አፈርን በኖራ ለማከም የግብርና ባለሙያ ምክረ ሐሳብ በመቀበል በጥንቃቄ ከአፈር ጋር እንደሚቀላቅሉ ነግረውናል።

አርሶ አደሮች በአፈር አሲዳማ የሚጠረጠር መሬታቸውን የአፈር ናሙና በባለሙያ በማስወሰድ የአፈሩ ጤንነት እንዲመረመር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከሚታረሰው 642 ሺህ 585 ሄክታር መሬት ውስጥ 25 በመቶ የሚሆነው በአፈር አሲዳማነት የተጠቃ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበበ መኮንን ለበኩር ጋዜጣ በስልክ ተናግረዋል። ይህንን የተጎዳ መሬት ለምነቱን ለመመለስ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን በኖራ ማከም አንዱ ተግባር መሆኑን ነው የተናገሩት። በመሆኑም በምርት ዘመኑ 61 ሺህ 440 ኩንታል ኖራ ለማቅረብ ታቅዶ  20 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ ኖራ ወደ ዞኑ ገብቷል። ከዚህ ውስጥ 16 ሺህ 615 ኩንታል ኖራ ለአርሶ አደሩ ተሠራጭቷል።

አርሶ አደሩ ኖራን ከአፈር ጋር መቀላቀል ያለበት ዘር ከመዘራቱ ቀደም ብሎ መሆን እንዳለበት አቶ አበበ አሳስበዉ  ከኖራ አቅርቦቱ ባሻገር አርሶ አደሩ መደበኛ ኮምፖስት፣ ቨርሚ ኮምፖስት እና ባዮ ሳላሪ ኮምፖስት እንዲያዘጋጅ ግንዛቤ እየተፈጠረ ነው ብለዋል። በመሆኑም አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) በመጠቀም በአፈር አሲዳማ የተጠቃውን መሬት ለምነቱ እንዲመለስ ጥረት እንዲያደርግ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በአማራ ክልል የአፈር አሲዳማነት በተለያዩ አካባቢዎች የአፈሩን ለምነት በእጅጉ እየጎዳው መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ የግብርና ግብዓትና ገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ ሙሽራ ሲሳይ ለበኩር ጋዜጣ ተናግረዋል። በክልሉ የአፈር አሲዳማነት የሚያጠቃቸው ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ አካባቢዎች መሆኑ ደግሞ ችግሩን አሳሳቢ አድርጎታል ነው ያሉት።  ካለው የችግሩ ስፋት እና አሳሳቢነት አኳያ አስቸኳይ መፍትሔ እና የሁሉንም ርብርብ እንደሚጠይቅም ተናግረዋል።

በመሆኑም በ2017/18 የምርት ዘመን በአማራ ክልል በአሲዳማ አፈር የተጎዳውን መሬት ለማከም መንግሥት 556 ሚሊዮን ብር መድቦ ግዥ በመፈፀም ለአርሶ አደሩ ኖራ የማቅረብ ተግባሩን እያከናወነ ነው ብለዋል። እስካሁንም 85 ሺህ ኩንታል የሚሆን ኖራ ችግሩ በስፋት በተከሰተባቸው ዞኖች መሠራጨቱን ገልፀዋል። ዳይሬክተሯ አክለውም አሲዳማ መሬት ላይ ዘር ከመዘራቱ አንድ ወር እና ሁለት ወር ቀድሞ ኖራውን ከአፈር ጋር መቀላቀል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የአፈር አሲዳማነትን በኖራ ከማከም ባሻገር የተፈጥሮ ማዳበሪያን (ኮምፖስት) መጠቀም፣ ሰብልን በፈረቃ መዝራት፣  የተቀናጀ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ማከናወን እንደሚገባ አሳስበዋል። (መልካም ከፋለ)

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የሚያዝያ 27 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here