የአፈር አሲዳማነት አደጋ ደቅኗል

0
336

የአፈር አሲዳማነት በተለያዩ የኢትዮጵያ  አካባቢዎች የአፈርን ለምነት በእጅጉ እየጎዳዉ ይገኛል:: በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ከሚታረሰው ከ15 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የእርሻ መሬት ውስጥ 43 በመቶው በአሲዳማነት መጠቃቱን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል፤ ከዚህም ውስጥ ሦስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ወይም 28 በመቶ በጠንካራ አሲዳማነት ተጠቅቷል። የአፈር አሲዳማነቱ ሽፋንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።  በኢትዮጵያ የአፈር አሲዳማነት የሚያጠቃቸው ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ አካባቢዎችን መሆኑ ደግሞ ችግሩን አሳሳቢ አድርጎታል:: የአፈር አሲዳማነት አሳሳቢ ከሆነባቸው መካከል እንደ ሀገር ከ33 በመቶ በላይ ምርት ድርሻ የሚይዘዉ የአማራ ክልል አንዱ ነዉ።

በክልሉ ከሚታረሰው አምስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በአሲዳማነት መጠቃቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያመለክታል:: ከዚህ ውስጥ ደግሞ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታሩ በከፍተኛ አሲዳማነት የተጠቃ ነው። ይህን አሳሳቢ ችግር ለመፍታት ታዲያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ  ተካሂዷል። በመድረኩ ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል። በዚህም በሰብል ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያስከተሉ ከሚገኙ ችግሮች መካከል አንዱና ዋናው የአፈር አሲዳማነት መሆኑን በማንሳት በትኩረት መሠራት እንዳለበት ተመላክቷል።

የአፈር አሲዳማነት ችግር ከተስፋፋባቸው መካከል ሰሜን  ሸዋ ዞን አንዱ ሲሆን ተስፋየ ግዛው ደግሞ በዞኑ የአንጎለላ እና ጠራ ወረዳ ጠንገጎ ቀበሌ አርሶ አደር ናቸው። እርሳቸው ለበኩር እንደተናገሩት ችግሩ አሳሳቢ ቢሆንም ከታከመ ግን ምርታማነቱ ይሻሻላል። በባለሙያ ከመሬታቸዉ ናሙና ተወስዶ ካስመረመሩ በኋላ የአሲዳማነት አፈር በመገኘቱ ኖራ መጠቀም ጀምረዋል::

አርሶ አደር ተስፋየ እንዳሉት ሁለት ጥማድ  የእርሻ መሬት በአሲዳማነት በመጠቃቱ ምርት መስጠት አቁሞ ነበር። ይሁን እንጅ ባለፈዉ ዓመት መሬታቸዉን በኖራ ከማከማቸው በፊት ያገኙት ከነበረዉ ምርት በእጥፍ ማግኘት ችለዋል:: ኖራ ምርታማነትን የመጨመር አቅሙ ከፍተኛ መሆኑን ያነሱት አርሶ አደሩ በአቅርቦት ምክንያት የተጎዳውን መሬት ማከም እንዲቻል በቂ ኖራ ለአርሶ አደሩ እንዲቀርብ ጠይቀዋል። በቀጣይም በአሲዳማነት የሚጠረጠር መሬታቸዉን የአፈር ናሙና በመዉሰድ እንዲታይ ለማድረግ ተዘጋጅተዋል::

መሰረት ቀፀላ በሰሜን ሸዋ ዞን የአንጎለላና ጠራ ወረዳ የሰብል ልማት ቡድን መሪ ናቸው። በወረዳው ያለው የእርሻ መሬት በስፋት በአሲዳማነት እየተጠቃ መሆኑን ለበኩር በስልክ በሰጡት መረጃ አስታውቀዋል። የችግሩን አሳሳቢነት በማንሳትም በተያዘው በጀት ዓመት በኖራ የማከም ሥራ በትኩረት እንደሚሠራ አስረድተዋል።

ቡድን መሪዋ ለበኩር እንዳሉት በወረዳው ናሙና ከተወሰደባቸው መሬቶች ውስጥ ከአራት መቶ ሄክታር በላይ መሬት በአሲዳማ አፈር ተጠቅቷል። የአፈሩን አሲዳማነት ለማከም ደግሞ 12 ሺህ ኩንታል ኖራ እንደሚያስፈልግ በዕቅድ መያዙን አስረድተዋል።

የአፈር አሲዳማነት ምርታማነትን እየቀነሰው መሆኑን የተናገሩት ወ/ሮ መሰረት፣ ለአብነትም ካሁን በፊት በአንድ ሄክታር ከ12 እስከ 15 ኩንታል የገብስ ምርት ይገኝ እንደነበር አንስተዋል። መሬቱ በኖራ ከታከመ በኋላ ግን እስከ 44 ኩንታል ምርት በሄክታር ማግኘት ተችሏል ብለዋል። በቀጣይ   በኖራ ከማከም ጎን ለጎን አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያን በመጠቀም የአፈር አሲዳማነትን መከላከል እንዳለበት አስገንዝበዋል። አርሶ አደሩ በስፋት እና በጥራት የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) እንዲያዘጋጅ የባለሙያ እገዛ እየተሰጠ ነው ብለዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ አበበ ጌታቸው በዞኑ ሰፊ መሬት በአሲዳማ አፈር መጠቃቱን ገልጸዋል:: ግብርና ሚኒስቴር ያጠናውን ጥናት መሰረት አድርገዉ ለበኩር እንደገለጹት ከ73 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በአሲድ መጠቃቱን አስረድተዋል:: የኖራ አቅርቦት ችግር በዞኑ አሳሳቢ መሆኑንም አንስተዋል::

አቶ አበበ እንዳሉት በበጀት ዓመቱ ሁለት ሺህ 723 ሄክታር አሲዳማ አፈር ያለበትን መሬት ለመለየት በዕቅድ ተይዞ ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ  አንድ ሺህ 790 ሄክታር መሬት ተለይቷል::

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፉት አራት ዓመታት በሚፈለገው መጠን አሲዳማነትን የማከም ሥራ መሥራት እንዳልተቻለ ነው ያስታወቁት::

ለዞን፣ ለወረዳ፣ ለቀበሌ ባለሙያዎች እና ለአርሶ አደሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሂዷል ብለዋል:: ለአብነትም ለ494 የወረዳ እና የቀበሌ ባለሙያዎች እንዲሁም ከሰባት ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ መሰጠቱን አንስተዋል::

በዞኑ እስካሁን ያለው ኖራ ከሁለት ሺህ ኩንታል  እንደማይበልጥ የተናገሩት አቶ አበበ የፌደራሉ እና የክልሉ መንግሥት እንዲያቀርብላቸው የሚፈልገዉ ግን  82 ሺህ ኩንታል ያህል  ነው ብለዋል::

ቡድን መሪው እንዳሉት አርሶ አደሩ አሲዳማ አፈርን ሳያክም የሰው ሠራሽ መዳበሪያን የሚጠቀም ከሆነ የአሲዳማነት መጠኑ ይጨምራል ወይም ያባብሰዋል:: ከዚህ በተጨማሪም ለማዳበሪያ ግዥ የወጣዉ ወጭ ኪሳራ ይሆናል ብለዋል::

በሌላ በኩል ይመጣል ተብሎ የታሰበው የኖራ አቅርቦት ሳይመጣ ቢቀር እንኳን አርሶ አደሩ የተፈጥሮ መዳበሪያን (ኮምፖስት)  እንዲጠቀም ግንዛቤ መፈጠሩን ገልጸዋል:: አርሶ አደሩ የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ከመጠቀም ይልቅ የተፈጥሮ አፈር ማዳበሪያን የመጠቀም ልምዱን ማዳበር እንዳለበትም መክረዋል::

ምንም እንኳን የኖራ እጥረት ቢኖርም ያለውን በባለሙያ ምክረ ሐሳብ መሠረት መጠቀም እንደሚገባ ጠቁመዋል። አሲዳማ መሬት ላይ ዘር ከመዘራቱ አንድ ወር አስቀድሞ ኖራውን መጨመር እንደሚያስፈልግ አስረድዋል:: አርሶ አደሩ ኖራው በእጁ ከገባ በኋላ ጥቅም ላይ እስከሚውል እርጥበት እንዳይነካው በጥንቃቄ ማስቀመጥ አለበት ብለዋል::

የክልሉን የእርሻ መሬት የአሲዳማነት ችግር ለመፍታት እና ምርታማነትን ለማሳደግ የክልሉ መንግሥት በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች ተጀምረው የተቋረጡ የኖራ ፋብሪካዎችን ወደ ሥራ በማስገባት  ችግሩን መፍታት ይጠበቅበታል ብለዋል::

የአፈር  አሲዳማነት  እንዲከሰት  በምክንያትነት የሚጠቀሱት  በዋነኝነት በተደጋጋሚ ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ያለምክረ ሀሳብ ከመጠን በላይ መጠቀም፣ የአፈር መሸርሸር፣ ለብዙ ዓመታት ማረስ፣ አርሶ አደሩ የሰብል ተረፈ ምርትን ከማሳው ላይ አለማስቀረት ወይም ሙሉ በሙሉ ከማሳ ማንሳት፣ ፍግ አለመጠቀም እንዲሁም  አፈር ውስጥ ያሉ ለተክሉ እድገት ጠቃሚ የሆኑ ንጥረ ነገሮች መሟጠጥ  ዋናዎቹ ናቸው:: ይህ ሲሆን ደግሞ በአፈር ውስጥ የሚገኙ እንደ ካልሺየም፣ ሶዲየም፣ ማግኒዝየም እና ፖታሽየም የመሳሰሉ ጠቃሚ ንጥረ ነገሮች ስለሚታጠቡ ችግሩ ይፈጠራል:: በመሆኑም ሀገሪቱ ማግኘት የሚገባትን ምርት እንድታገኝ እና በአሲዳማ አፈር ምክንያት የምታወጣውን ያልተገባ ወጪ ለመቀነስ ማሕበረሰቡ የአፈር አንክብካቤና ጥበቃ ሥራ ላይ ትኩረት ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት በአማራ ክልል 21 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ማከም የሚያስችል ከ623 ሺህ በላይ  ኩንታል ኖራ  ለማቅረብ  የቅድመ ዝግጅት ሥራ አየተሠራ እንደሚገኝ የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ይጠቁማል። በ762 ቀበሌዎችም ጥቅም ላይ ይውላል ነው የተባለው።  ይህንን ችግር ለማቃለል አርሶ አደሩን በማሳተፍ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑ ተገልጿል።

በሌላ በኩል በተለያዩ አካባቢዎች ሕብረተሰቡን በማሳተፍ እየተከናወኑ ያሉ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች የአፈር አሲዳማነትን ለመከላከልና ለመቀነስ ሚናቸው የጎላ ነው ተብሏል።

በ2016/2017 ዓ.ም የምርት ዘመን በከፍተኛ አሲድ የተጠቃ የእርሻ መሬትን በኖራ

ለማከም፣ መንግሥት 50 በመቶ ወጪ ለአርሶ አደሮች ለመሸፈን አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ለክልሎች በድጎማ መስጠቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታዉቋል:: ኢትዮጵያ በአሲዳማ አፈር ምክንያት በየዓመቱ ከፍተኛ ምርት እንደምታጣ ሚኒስቴሩ አክሏል:: የግብርና ሚኒስቴር ለጊዜው አሲዳማ መሬትን ለማከም እየሠራሁ ነው ቢልም ውጤታማ ለመሆን ግን ጊዜ ይፈጅብኛል ብሏል።

ለግብርና ሥራ ትልቁ ግብዓት በሆነው አፈር ላይ የሚያጋጥመው አሲዳማነትና ጨዋማነት በምርታማነት መጨመር ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል:: ጉዳቱ ቦታ ሳይሰጠው ቢቆይም በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መንግስት ለችግሩ መፍትሄ የሚሆኑ እርምጃዎችን እየተወሰደ መሆኑ ተመላክታል።

በበጀት ዓመቱ ክልሎችን ጨምሮ እንደ ሀገር 200 ሺህ ሄክታር መሬት አሲዳማ መሬትን በኖራ ለማከም፤ የግብርና ሚኒስቴር ኖራ አቅርቦት ሥርዓቱን በማሻሻልና ተደራሽነቱን በማስፋት ከክልሎች ጋር እየሠራሁ ነው ብሏል። ይሁን እንጂ ከችግሩ ስፋት አኳያ በርካታ ቀሪ ሥራዎች መኖራቸው ተጠቅሷል።

በሌላ በኩል አሲዳማ አፈርን መቋቋም የሚችሉ የሰብል አይነቶችን በመዝራት በምርታማነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳይፈጥር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑ ነው የተነገረው።  የተቀናጀ የተፈጥሮ ሀብትና አካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን በመሥራት የአፈር ለምነትን ለመጠበቅና አሲዳማነትን ለመከላከል እየተሠራ መሆኑም ተጠቁሟል።

የግብርና ሚንስቴር ሚንስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በአሲዳማ አፈር ምክንያት ኢትዮጵያ ከፍተኛ ምርት ይባክንባታል ሲሉ አስረድተዋል። አሲዳማ አፈር በአብዛኛው የሚከሰተው በደጋ እና ወይና ደጋ የኢትዮጵያ ክፍል አካባቢ ነው ያሉት ሚንስትሩ ለዚህም ምክንያቱ መሬቱ፤ በዝናብ ስለሚታጠብና  የአፈር ማዳበርያ አጠቃቀም ችግር እንደሆነም ተናግረዋል:: አሲዳማ አፈር ኢትዮጵያ ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል የሚሉት ሚንስትሩ መሬቱን ለማከም ኖራ እየተጠቀምን ነው ብለዋል።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here