የአፋልጉኝ ማስታወቂያ

0
123

ይሄንን ማስታወቂያ በፌስ ቡክ ገጼ ላይ ተለጥፎ ሳገኘው ያነበብኩት በጣም ተገርሜ እና ውስጤ በሀዘን ተነክቶ ነው፡፡ በኣማራ ክልል ብቻ ሳይሆን በሁሉም ግጭት ባለባቸው የዓለማችን ክፍሎች ውስጥ የብዙ እናቶችን እንባ በእኚህ እናት ዓይኖች ውስጥ ማየት አይቸግረንም፡፡

የእኚህ እናት እና መሰሎቻቸው የሀዘን እንባ እንዲታበስ የሁሉም ጥረት ያስፈልጋል እያልኩኝ የአፋልጉኝ ማስታወቂያውን እናንተም ታነቡት ዘንድ አጋርቼያችኋለሁ፡፡

ስሜ ኢትዮጵያ ይባላል፡፡ ዕድሜዬ ብዙ ሺህ ዓመታትን ተሻግሯል፡፡ በዚህ ሁሉ የህይወት ዘመኔ የማላውቀው የኢትዮጵያ አከባቢ የለም፡፡ የማላውቀው የሀገሬ ዓየር ንብረትም የለም፡፡

ዛሬ በዚህ የማሕበራዊ ገጽ በኩል ብቅ ያልኩት እናንተ ኢትዮጵያውያንን አንድ ነገር ልለምናችሁ ነው፡፡ ልጄ ሰላም ድንገት ከቤት ወጥታ ቀርታለች፡፡ ስለ ልጄ ሰላም ጥቂት መለያዎችን (ምልክቶችን) ልንገራችሁና ያያችኋት እንድትጠቁሙኝ በፈጣሪ ስም አደራ እላችኋለሁ፡፡

ልጄ ሰላም ከቤት ስትወጣ የለበሰችው በጥበበኞች የሽመና ጥበብ የተሠራ ነጭ የጎንደር ጉብሎች የሚዋቡበትን ቀሚስ ነው፡፡

ሰላም ከቤት በወጣች ቀን የተሠራችው የጸጉር ስሪት የወሎዎችን ይመስላል፡፡ በአንገቷ እና በጆሮዎቿ ላይ ያጠለቀቻቸው ጌጣ ጌጦችም በሰሜኑ ኢትዮጵያ ሴቶች የሚያዘወትሯቸውን ዓይነት ጌጣ ጌጦች ናቸው፡፡

በእጆቿ እና በእግሮቿ ላይ እንደ አምባር፣ አሸንክታብ እና የመሳሰሉ ጌጦችን ያደረገች እጅግ ውብ ልጅ ካያችሁም እሷ የኔዋ ሰላም ልትሆን ስለምትችል እባካችሁ ከታች በምተውላችሁ አድራሻ ጥቆማችሁን አድርሱኝ፡፡

ውዷ ልጄ ሰላም ውልደቷ እና እድገቷ በአማራ ክልል ውስጥ ነው፡፡ ልጄ ሰላምን ከአራት ዓመታት በፊት ብታውቋት እንዴት ያለች ሳቂታ እና ውብ ልጅ መሰለቻችሁ… ከአራት ዓመታት ወዲህ ግን በክልላችን ውስጥ በጠፋው ሰላም ምክንያት  የኔዋ ልጅ ሰላምም ሰላሟን አጥታ ፊቷ ላይ ትካዜና መከራ ብቻ ይነበብባት ጀምሯል፡፡

ሰላም በትምህርቷ በጣም ጎበዝ እና እኛ ወላጆቿም ብዙ ተስፋ ያደረግንባት ቢሆንም በክልሉ ውስጥ ባለው ግጭት ምክንያት የምትወደውን ትምህርቷን አቋርጣ እቤት መዋል ጀምራ ነበር፡፡

ሰላም በትምህርቷ ላይ የነበራትን ጉልህ ተስፋ ባኮሰመነባት የክልሉ ሰላም ማጣት በጣም ታዝን ነበር፤ እኔንም «እማዬ፣ የቀድሞው ሰላማችን መቼ ነው የሚመለሰው?» ብላ ጠይቃኛለች፡፡

እኔም፣ «እግዚያብሔር የፈቀደ ዕለት እና ሁላችንም ሰዎች ቅን ስንሆን» እያልሁ እመልስላት ነበር፡፡

ሰላም አባቷን ያጣችውም በዚሁ የክልሉ ሰላም ማጣት ምክንያት በመሆኑ የሰላም እጦታችን ያሳጣን ብዙ ነገሮችን ነው፡፡

የሰላም አባት በትልቅ ሆስፒታል ታክመው የሚድኑትን ሕመም በመጓጓዣ እና በሕክምና ዕጦት ምክንያት በአልጋቸው ላይ ተኝተው እስከወዲያኛው እንዲያሸልቡ አስገድዷቸዋል፡፡

የሰላም አባት መምህር ስለነበሩ በክልሉ የተለያዩ አከባቢዎች እሳቸው አስተምረዋቸው ለቁም ነገር የበቁ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ እንዳለመታደል ሆኖ ግን በክልሉ ውስጥ ያለው የመጓጓዣ እንቅስቃሴ ብዙም አስተማማኝ ስላልነበረ የሰላምን አባት መቅበር እየፈለጉ መቅበር ያልቻሉ ዘመዶቻቸው እና ወዳጆቻቸው ብዙ ናቸው፡፡

በክልሉ ውስጥ የጠፋው ሰላም የጎዳው ሁሉንም የክልሉን ነዋሪ ነው፤ መንግሥትንም ጭምር፡፡ ሲጀመር ሰላም ከሌለ ምንም ነገር እንደማይኖር መናገሬ ለቀባሪው የማርዳት ያህል ነው፡፡

የኔዋን ሰላም መጥፋት እና አፋልጉኝ ለማለት የጀመርኩትን ሃሳብ ወደ ክልሉ ሰላም መጥፋት ወስጃችሁ ብዙ ነገር ቀባጠርኩባችሁ አይደል? የኔዋ ሰላም መጥፋት እኔን ያን ያህል ካንገበገበኝ የክልሉ ሰላም መጥፋት ደግሞ እናንተንም እንደ እግር እሳት ለብልቧችሁ ሰላሜን ከልባችሁ እንድትፈልጉልኝ ፈልጌ ነው፡፡

እባካችሁን፣ ከምንም በላይ አብልጬ የምወዳትን ሰላሜን ፈልጉልኝ፡፡ ሰላምን አይቻታለሁ ወይም አግኝቻታለሁ የሚል ማንኛውም የመንግሥት አካል፣ መንግሥትን በመቃወም ትጥቅ ይዞ የወጣ አካል፣ የሀገር ሽማግሌ፣ የሃይማኖት መሪ፣ የሲቪል ተቋም ወይም ሌላ ማንኛውም ሰላምን የሚወድ ግለሰብ እና ተቋም በሚከተለው አድራሻ ሰላሜ ያለችበትን ቦታ እንዲጠቁመኝ አደራ እላለሁ፡፡

እኔ የሰላም እናት አድራሻዬ በአማራ ክልል የትኛውም አከባቢ እገኛለሁ፡፡ አዘውትሬ የምለብሰው አረንጓዴ ሻሽ፣ ቢጫ ሹራብ እና ቀይ ቀሚስ ሲሆን ከሰሞኑ ግን በደረሰብኝ ተደጋጋሚ ሀዘን ምክንያት ጥቁር የሀዘን ልብስ ለብሻለሁ፡፡ መልኬ ቁርጥ ሀገራችንን የሚመስል ነው፡፡

ውድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ፣ ልጄ ሰላም ድንገት ከምትኖርበት የአማራ ክልል ወጥታ በመቅረቷ ሀዘን በርትቶብኛል፡፡ ልጄን አየኋት ወይም አገኘኋት ብሎ ለሚመልስልኝ ሰው፣ መንግሥት ወይም ሌላ አካል በኑሮ ውድነቱ ምክንያት የምከፍለው ጥሪት ባይኖረኝም ልብን የሚያርስ ምርቃት እቸረዋለሁና ሰላሜን መልሱልኝ ስል  ልባዊ እንባን ባጋቱ ዓይኖቼ እማጸናችኋለሁ፡፡

እባካችሁ ሰላሜን አፋልጉኝ!

 

( እሱባለው ይርጋ)

በኲር የካቲት 2 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here