የአፍሪካ ቀዳሚዉ የሩጫ መድረክ

0
179

የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም

ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ በፈረንጆች ሚሊኒየም በሲድኒ ኦሎምፒክ ተሳትፎ ወደ ሀገሩ ሲገባ ለሀገራችን የወርቅ ሜዳሊያ ብቻ ሳይሆን አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ደርጃ ዝነኛ የሆነውን ዝግጅት ጭምር በልቡ ጠንስሶ ነው። “እኛ ኢትዮጵያውያን ብዙ ጊዜ ከሀገራችን ወጥተን ስለምንሮጥ በሀገር ውስጥ አንድ ትልቅ የአትሌቲክስ መድረክ እንዲኖር እመኝ ነበር፤ እናም ዛሬ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስሙ የናኘውን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለመጀመር በቃሁ” ሲል በአንድ ወቅት ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር በነበረው ቃለ ምልልስ ተናግሯል።

ይበልጥ ነገሩን አልጋ በአልጋ ያደረገው ደግሞ በእንግሊዝ “የሰሜን ታላቁ ሩጫ”  ግብዣ ሲቀርብለት ነው። በወቅቱ የሰሜን ታላቁ ሩጫ አዘጋጆች ለሻለቃ ኃይሌ በውድድሩ እንዲገኝ የክብር ተጋባዥ ያደርጉታል። ኢትዮጵያዊው ጀግናም በውድድሩ እንደሚገኝ በመግለጽ፣  በኢትዮጵያ ታላቁ ሩጫን ለማዘጋጀት እገዛ እንዲያደርጉለት አዘጋጆችን ቃል ያስገባቸዋል። ህዳር 16 በ1993 ዓ.ም በሁለቱ እንግሊዛውያን እገዛ ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ የመጀሪያውን የታላቁ ሩጫ ውድድር አስጀመረ።

በወቅቱ ዐስር ሺህ ሰዎች በውድድሩ እንደተካፈሉ መረጃዎች አመልክተዋል።  ለአትሌቲክስ ስፖርት የተትረፈረፈ ጸጋን አብዝቶ የቸራት ሀገራችንም ሁሌም የሰው ድግስ አድማቂ ብቻ ሳትሆን ደጋሽ መሆን እንደምትችል አስመስክራለች። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በየዓመቱ የልጆችን እና የአካል ጉዳተኞችን ጨምሮ በሁለቱም ጾታዎች ከስድስት በላይ የሩጫ ውድድሮችን ያስተናግዳል።

ቀደምት እና ትልቁ የአፍሪካ የጎዳና ሩጫ ሲሆን በዓለም ላይ ካሉት ኒውዮርክ፣ ለንደን፣ ፓሪስ እና የበርሊንን ከመሳሰሉ ታላላቅ ውድድሮች መካከል አንደኛው ነው። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከዓለም አትሌቲክስ ባሳለፍነው ጥቅምት ወር እውቅና ማግኝቱ አይዘነጋም። የዓለም አትሌቲክስ የ2017 ዓ.ም ሶፊ ማልት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ የሌብል ደረጃ( label road race) ያለው ውድድር ነው ሲል እውቅና ሰጥቶታል።

በዓለም አትሌቲክስ ጥራታቸውን የጠበቁ፣ ደህንነታቸው የተጠበቀ፣ ተሳታፊዎች በውድድሩ ላይ በነበራቸው ቆይታ፣ ዝግጅቱ በአበረታች መድሃኒት ዘርፍ ላይ እየሠራ ያለው ሥራ እና  ከተማ አስተዳደሮች ለዝግጅቱ ያላቸው ድጋፍ የውድድሩ መመዘኛ ነው። በተጨማሪም የመሮጫ ኮርስ ልኬት፣ የውድድር ሰዓት ምዝገባ እና የታላላቅ አትሌቶች ተሳትፎ ከግምት ውስጥ እንደሚገባ የዓለም አትሌቲክስ መረጃ አስነብቧል።

በዓለማችን እጅግ በርካታ ውድድሮች ባሉበት ዓለም የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ አስተዳዳሪ እውቅና ማግኝቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ መድረኩ እያደገና እየተሻሻለ መምጣቱን ያሳያል። በተሳታፊ ቁጥርም ቢሆን በዐስር ሺህ የተጀመረው ውድድር አሁን ላይ ከ50 ሺህ በላይ ደርሷል። ውድድሩ ከተጀመረ ከአራት ዓመታት በኋላ በ1997 ዓ.ም የተሳታፊዎች ቁጥር 25 ሺህ እንደደረሰ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ግዙፉ የአትሌቲክስ መድረክ  የውድድር ዕድል ያላገኙ አትሌቶች የሚመለመሉበት በመሆኑ ለሩብ ምዕተ ዓመት ያህል ለብዙ አትሌቶች ዋነኛ የውድድር ምንጭ ሆኖ ቆይቷል፤ አሁንም እየሆነ ነው። ባለፉት 24 ዓመታትም በሁለቱም ፆታ ህጻናት፣ ወጣቶች፣ አዛውንቶች፣ አካል ጉዳተኞች እና የውጪ ሀገር ዜጎች በመድረኩ ተሳትፈዋል፤ እየተሳተፉም ነው።

ታላቁ ሩጫ በአጠቃላይ በአትሌቲክስ ስፖርት የአመለካከት ለውጥ ያመጣ በተለይ ሩጫን በተግባር የለወጠ መድረክ ነው። በኦሎምፒክ እና በዓለም ሻምፒዮና ላይ በመሳተፍ ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡ አትሌቶች ወጥተውበታል። ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ ያሉትን እንኳ ብንመለከት ታምራት ቶላ፣ ሰለሞን ባረጋ፣ ሀጎስ ገብረ ህይወት፣ በሪሁ አረጋዊ፣ ያለምዘርፍ የኋላው፣ ጽጌ ገብረ ሰላማ እና ትዕግስት ከተማን የመሳሰሉት በዚህ ውድድር መታየታቸው አይዘነጋም።

ለስፖርተኞች የውድድር ዕድል ከመፍጠሩ ባሻገር የቱሪዝም ስፖርትን ለማሳደግ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተም ይገኛል። የውጪ ሀገር ስፖርተኞች፣ ጎብኚዎች እና የሚዲያ ባለሙያዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ በር ይከፍታል። ለአብነት ከዚህ በፊት ኬኒያዊው የቀድሞ አትሌት ፖል ቴርጋት እና  ደቡብ አፍሪካዊቷ የቀድሞ ሯጯ ኤለና ሜየር በውድድሩ መገኘታቸው አይዘነጋም።

ዘንድሮ ደግሞ ኬኒያዊቷ አትሌት ሩት ቺፐንግ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የክብር እንግዳ ሆና ተገኝታለች።  ውድድሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመዘገበ በመሆኑ የኢትዮጵያን በጎ ገጽታ ለዓለም ያስተዋውቃል። በርካታ የውጪ ሚዲያዎች ውድድሩን ለመዘገብ ወደ ሀገራችን ይገባሉ፤ ይህ ደግሞ የሀገራችንን ትክክለኛ ገጽታ ምን እንደሚመስል ዓለም እንዲገነዘብ ያደርጋል።

የአትሌቲክስ መድረኩ የኢትዮጵያውያን ባህል የሚታይበት በመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገራችንን ለማስተዋወቅ ያግዛል። ውድድሩ በተለያዩ ቀለማት ያሸበረቁ ተሳታፊዎች በመካፈል ያደምቁታል። ሀገራችን በየዓመቱ በሚሊዬን ዶላር የሚቆጠር የውጪ ምንዛሬ እንድታገኝም ያስችላታል። የ2017 የሶፊ ማልት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ህዳር ሰባት 2017 ዓ.ም ተከናውኗል። በአጠቃላይ ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች እንደተሳተፉም አዘጋጆቹ አሳውቀዋል። ከተለያዩ 15 ሀገራት የተውጣጡ 200 ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪዎችም በሩጫው ላይ ተስትፈዋል።

የ2017 ዓ.ም የሶፊ ማልት ታላቁ ሩጫ ውድድርን በወንዶች የአምናው አሸናፊ ቢኒያም መሀሪ በተከታታይ አሸንፏል። በሴቶች ደግሞ አሳየች አይቼው አሸንፋለች። የመጀመሪያውን የመድረኩ ምዕራፍ መስራቹ ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ስላሴ ማሸነፉን ታሪክ ያወሳል። ሀጎስ ገብረ ህይወት፣ በሪሁ አረጋዊ እና አቤ ጋሻው እኩል ሦስት ጊዜ በማሸነፍ ክብረወስኑ ተጋርተዋል።

ከሴቶች ያለምዘርፍ የኋላው ሁለት ጊዜ በማሸነፍ ክብረወሰን ማስመዝገብ ችላለች። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጽንሰ ሀሳብ በመከተል በተለያዩ ክልሎች እና ቦታዎች ውድድሮች መደረግ ተጀምሯል። ይህን ግዙፍ የአትሌቲክ መድረክ በቀጣይ አምስት ዓመታት በዓለም ቀዳሚው የጎዳና ላይ ውድድር እንዲሆን የውድድሩ ማርኬቲንግ ዳይሬክተር እና የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ወ/ሮ ህሊና ንጉሴ ተናግረዋል።።

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የህዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here