… ካለፈው የቀጠለ
በጀርመኗ በርሊን ከተማ አፍሪካን እንደ ቅርጫት ለመቀራመት ለወራት የዶለቱትን በምድር ላይ አሳርፈው አፍሪካን የወረሯት አውሮፓውያን ለዓመታት በቅኝ ግዛት ቀንበር አማቀቋት። ነገር ግን አፍሪካውያን በተለይ የአድዋን ድል ተመርኩዘው ለነፃነታቸው የመታገል መነቃቃት አቅም አግኝተው በተለያየ መንገድ ከባእዳኑ አገዛዝ ራሳቸውን ነፃ ለማውጣት ብዙ ትግል በማድረግ የማታ ማታ ማሳካት እንደቻሉ ጀምረን ቀጣዩን ለማቅረብ ቃል ገብተን ነበር ያቆምነው፤ የቀጣዩን እነሆ።
አፍሪካ ከአውሮፓውያኑ ቅኝ አገዛዝ ነፃ እንድትወጣ የተጀመረው የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ በተለይ በአምስተኛ ጉባኤው ላይ ታላቅ ውሳኔ አሳልፎ ነበር። አፍሪካ ሙሉ ለሙሉ ነፃነቷን ማረጋገጥ እንዳለባት እና የተጀመሩ የነፃነት ትግሎች እንዲጠናከሩ እርስ በርስ መተጋገዝ እንደሚገባ ተነጋግረው መለያየታቸውን ታሪክ ያሳያል። ስለሆነም የነፃነት ታጋዮችን የተለያየ የትግል ስልትን ተከትለው ነፃነታቸውን ተቀዳጅተዋል። በትጥቅ እና በሰላማዊ ትግል መንገድ የተጓዙ ለአብነት ከሚጠቀሱት መካከል እንደ ኬኒያ፣ ካሜሩን አይነቶች ግንባር ቀደም ናቸው።
የማኦ ማኦ አመፅ
ኬኒያ ለአያሌ ዓመታት በእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ስር ቆይተለች። አገዛዙ በኬኒያውያን ላይ የጫነው ጨቋኝ አገዛዝ እና በዘር ከፋፍሎ የመግዛት መሰሪ ስልት ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል። የሀገሪቱን ሀብት መዝብረዋል። እናም ገበሬውን በገዛ ርስቱ ገባር ያደረገውን ይህን ስርዓት በመቃወም ከባድ ደም አፋሳሽ ትግል የተደረገበት ነው። ከጀሞ ኬንያታ በፊት የነበረው ሀሪ ቱኩ የተባለ የኬኒያውያኑ የነፃነት ታጋይ ፓን የኬኒያን ናሽናሊስት ንቅናቄ ፓርቲ መስርቶ ነበር። ሀሪ ቱኩ የወቅቱ የእንግሊዝ ነጮች የመሰረቱት የኬኒያ መንግሥት ፓርላማ ሙሉ ለሙሉ በነጮች ብቻ መሟላቱን ተቃውሞ አመፅ አስተባብሮ ነበር። ይሁን እንጂ በኃይል ተበልጦ በእንግሊዝ ቁጥጥር ሲወድቅ ያኔ 23 ወጣቶች በግፍ ተገድለው ነበር።
በ1930 ዓ.ም የኬኒያ አባት ከሚባሉት ግንባር ቀደሙ ጆሞ ኬንያታ ከአውሮፓ ቆይታው ወደ ሀገሩ ከተመለሰ ከአንድ ዓመት በኋላ የኬንያ አፍሪካን ዩኒየን የተሰኘ አፍሪካዊ ድርጅት አቋቁሞ የዩኒየኑ የመጀመሪያ መሪ ሆነ። ምንም እንኳ በአፍሪካዊ የሚመራ ራሱን የቻለ የኬኒያ መንግሥት የመመስረት ህልሙ እና ጥረቱ ኃይልን ይጠቀም በነበረው የእንግሊዝ መንግሥት ባይሳካም በኬንያ የነጭ ሰፋሪዎችን የበላይነት ለማስቆም የተደረገው ጥረት ባይሳካም ሁለቱን ነጭ እና ጥቁር ሰፋሪዎች ሁልጊዜ ለግጭት መዳረጉን ቀጥሏል።
ጊኪዩ በሚባል አንድ ማህበረሰብ ውስጥ አሳሳቢ የመሬት እጥረት ተፈጥሮ ነበር። ቅኝ ገዢው ስርዓት የጥቁሮችን መሬት እየቀማ ነጮች እንዲሰፍሩ የማድረጉ ተደጋጋሚ ተግባር ጥቁሮቹን አፈናቅሏል። ታዲያ ከእነዚህ በጎሳዎች ተፈንቅሎ የወጣው ምሬት ነበር ታዋቂውን የማኦ ማኦ አመፅ የወለደው። ኬንያታ እና የኬንያ አፍሪካውያን ዩኒየን ፓርቲ አመራሮች በ1944 ዓ.ም ግጭት ቀስቅሰዋል፤ የማኦ ማኦን አመፅ አካልም ናቸው በሚል በሀሰት ክስ ተመስርቶባቸው ለእስር ተዳርገዋል። ይሁን እንጂ ማኦ ማኦ ንቅናቄ የትጥቅ ትግሉን አጠናክሮ ገፋበት። በማውንት ኬንያ እና ናኩሩ አውራጃ ውስጥ አብዛኛዎቹን ውጊያዎች ተዋግቷል። ይህም ቅኝ ገዥውን አስጨንቆ ለኬንያ ነፃነቷን እንዲመልስ አስገድዷል። በሌላ በኩል ከምስራቅ አፍሪካ የነፃነት ትግሎች መካከል በኡጋንዳ ሚልተን ኦቦቴ፣ በታንዛኒያ ጁሊየስ ኔሬሬ የመሯቸው የነፃነት ትግሎች ረጅም እና መራር ቢሆኑም የማታ ማታ ፍሬያቸው ያማረ ነበር።
የጋና ፈር መቅደድ
በምእራብ አፍሪካ የነበረው ትግል ደግሞ ሌላ መልክ ያለው ሲሆን ለሁሉ ቀድማ ነፃነቷን ከተቀዳጀችው ጋና እና መሪዋ ኩዋሜ ንክሩማ አቋም እና የትግል ስልት አንፃር የተከወነ ነበር። በአፍሪካ የነፃነት ታሪክ ውስጥ ግንባር ቀደም በሆነው ክዋሜ ንክሩማህ ከአውሮፓ መልስ ባቋቋመው የዩናይትድ ጎልድ ኮስት ኮንቬንሽን ፓርቲን ከሕዝቡ ጋር በማስተባበር ምእራብ አፍሪካን ወደ ነፃነት መርቷል። በተለይ ኩዋሜ ንክሩማህ ንክሩማኒዝም የሚል መጠሪያ የተሰጠውን አፍሪካን በሶሺያሊዝም አስተሳሰብ ቀርፆ የአፍሪካን አንድነት የመፍጠር ርእይ ጠንሳሽ ከቀደምት የአፍሪካ ባለውለታዎች አንዱ ነበር። ንክሩማህ እጅግ ፈታኝ የትግል መስመር በመከተል ጋናን የመጀመሪያዋን የምእራብ አፍሪካ ነፃ ሀገር አድርጓል። ታዲያ ጋናን ተከትሎ በርካታ የቀጠናው ሀገራት ነፃነታቸውን እንዲቀዳጁ የንከሩማህ አስተዋፅኦ ትልቅ ነበር። ጋናን ተከትለው በኮትዲቮር ሀውፌት ቡዋኜ፣ በሴኔጋል ሴኩ ቱሬ፣ እና ሌሎቹም የሚመሯቸው የምእራብ አፍሪካ ሀገሮች የነፃነት ትግሎች በስኬት ተጠናቀዋል።
የዘገየው የደቡብ አፍሪካ ነፃነት
መላው አፍሪካ ነፃነቱን ባረጋገጠበት በዚህ ወቅት በደቡብ አፍሪካ ያለው ሁኔታ ግን የተለየ መልክ ያዘ ። እድለ ቢሷ ደቡብ አፍሪካ እና ጎረቤቶቿ በአፓርታይድ ቀንበር የነፃነት ቀናቸው ተራዘመ። ይሁን እንጂ እንደ ማንዴላ ያሉ ደቡብ አፍሪካውያን የአፓርታይድን ቀንበር ሰብረው ነፃነታቸውን ለማረጋገጥ ረጅም የትግል መንገድ ገና መጓዝ ነበረባቸው። ትግሉ የብዙ ደቡብ አፍሪካውያንን መስዋእትነት አስከፍሏል። በኤ ኤን ሲ ፓርቲ አስተባባሪነት በርካታ የጎዳና ላይ አመፆችን አለፍ ሲል የትጥቅ ትግሎችን በማድረግ ለነፃነት በመታገል አፓርታይድን አስጨንቀዋል። በመጨረሻም ማንዴላ በነጭ እና በጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን መካከል የተፈጠረውን ክፍተት የሚያጣብ ስልትን በመከተል በይቅርታ መንፈስ ደቡብ አፍሪካን ወደ ነፃነት መርቶ አሳክቷል።
የፖርቹጋል ቅኝ ግዛቶች አንጎላ፣ ሞዛምቢክ እና ጊኒ ቢሳው ለነፃነት የጀመሯቸው ትግሎች ውጤታማ ነበሩ።
ትግሉ በመላው የአህጉሪቱ አካባቢዎች እየተጠናከረ ቀጥሎ በተለይ በ1952 ዓ.ም እና ከዚያ በኋላ በርካታ አፍሪካውያን ነፃነታቸውን አረጋግጠዋል። የአፍሪካውያኑን የነፃነት ትግሎች በማገዝ ረገድ ኢትዮጵያ ሚናዋ የጎላ ነበር። በተለይ ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የነፃነት አባቶች የወር ደመወዝ ከመክፈል እና ቤተሰቦቻቸውን ከማገዝ ጀምሮ ወታደራዊ ስልጠናዎችን እንዲሁም የሞራል ድጋፍ በመስጠት ያደረገቸው ተሳትፎ እና የተጫወተችው ሚና በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ አለው። የወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ አፍሪካውያን የነፃነት የታጋዮችን አመራሮች በማስተባበር የአታጋይነት ሚናቸውን ተወጥተው ነበር።
አፍሪካ ምንም እንኳ በቆራጥ አባቶቿ የነፃነት ታጋዮችን የትግል ፅናትና ቅኝ ግዛትን ከአህጉሪቱ ምድረ ገፅ ማስወገድ ቢችሉም የነፃነቱን መልካም ትሩፋት ሊያጣጥሙ አልቻሉም። ጨርሶ ያልተነቀለው የቅኝ አገዛዝ ሸንኮፍ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ አለመረጋጋትን ተክሎባት አልፏል። ከአካል እንጅ ከአእምሮ ቅኝ ግዛት ነፃነት ያልወጣላቸው አፍሪካ ሕይወት ከድጡ ወደ ማጡ ሆኖባታል። የአፍሪካ አይኖች ሙሉ ለሙሉ ተገልጠው ማየት እስኪችሉ ድረስ አፍሪካ እና ልጆቿ ድህነት፣ ረሀብ፣ ስደት እና ጦርነት መገለጫቸው እንደሆነ ቀጥሏል።
(መሠረት ቸኮል)
በኲር የታህሳስ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም