የአፍሪካ ዓመት

0
17

“የአፍሪካ ዓመት” የሚባለው የፈረንጆቹ 1960 ከዛሬ 65 ዓመታት በፊት 17 የአፍሪካ ሀገራት ከአውሮፓውያን ቅኝ አገዛዝ ነፃነታቸውን ያገኙበት ልዩ ዓመት ነው። ነሐሴ ወር ደግሞ አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት የነፃነት በዓላቸውን የሚያበሩበት ወር መሆኑን በተመለከተ አጭር ዳሰሳ ለማድረግ የዚህ ሳምንት የበኩር የታሪክ ማህደራችን ትኩረት አድርጓል፤ አብራችሁን ቆዩ።

የጀርመኗ መዲና በርሊን፤ በአፍሪካ ላይ ሴራ የሚጎነጉኑ አሜሪካን ጨምሮ አስራ አራት የአውሮፓ ኃያላን ያዘጋጁትን ታሪካዊ ኮንፈረንስ   ከሕዳር 15 እስከ የካቲት 26 ቀን 1877 ዓ.ም አስተናግዳ ነበር። ኃያላኑ በዘመኑ እያበበ የነበረው የኢንዱስትሪ አብዮት የጠየቃቸውን የግብአት አቅርቦት ፍላጎት፤ አፍሪካን በመውረር ለማርካት ለሦስት ወራት ያህል በርሊን ውስጥ ዶለቱ።  ዱለታው አፍሪካን ለመቀራመት የተስማሙበት ነበር። ሳይውል ሳያድር መጠነ ሰፊ ወረራ በመላው የአፍሪካ ምድር ላይ በተግባር ፈፀሙ። ወረራው ዱብ እዳ የሆነባቸው አፍሪካውያን የቻሉትን ያህል ለመከላከል ቢሞክሩም ተዘጋጅቶበት የመጣውን ወራሪ መመከት አልቻሉም። በመሆኑም እስከ 1897 ዓ.ም ድረስ ከኢትዮጵያ እና ከላይቤሪያ በስተቀር ሁሉም የአፍሪካ ምድር በአውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎች እጅ መውደቁን ሮላንድ ኦሊቨር እና አንቶኒ አትሞር “አፍሪካ ሲንስ 1800” በተሰኘው የጋራ መፅሃፋቸው ላይ አስፍረውት ይገኛል።

አፍሪካ በመሰሪዎቹ ቅኝ ገዥዎች የሴራ መረብ ተጠልፋ እጃቸው ከመግባቷ በፊት የአፍሪካ ምድር በራሱ አፍሪካዊ አስተዳደር፣ በጥቁር መሪዎቹ፣ እንደራሱ ወግ እና ባህል ይተዳደር ነበር። ይህም እስከ 19ኛው ክፍለዘመን የመጨረሻዎቹ ሩብ ዓመታት ድረስ በአፍሪካ ምድር ምንም የነጮች አስተዳደር አልነበረም ማለት ነው።  ነገር ግን አውሮፓውያኑ አፍሪካን በይፋ በወረሩበት ጊዜ በኢትዮጵያ ከገጠማቸው አንገት አስደፊው የአድዋ አሳፋሪ ሽንፈት ውጭ አህጉሪቷን በቀላሉ መቆጣጠር እና በጥቁሮች ምድር የነጭ ቅኝ ግዛታዊ አስተዳደርን መስርተው አፍሪካን እና ሕዝቧን ለበርካታ አስርት ዓመታት ያህል ሲበዘብዙ ኖሩ።

ምንም እንኳ አፍሪካውያን ራሳቸውን ለመከላከል ያደረጉት ጥረት በወራሪዎቹ የበላይነት ቢጠናቀቅም፣ ከአድዋ ድል አድራጊ ወንድሞቻቸው የአሸናፊነት መንፈስን ወርሰው ለነፃነታቸው እየተፋለሙ ቅኝ ገዢውን ኃይል ሲፈትኑት ኖረዋል። ታዲያ መራር ትግላቸው አይሎ አስከፊውን የቅኝ አገዛዝ ዘመን አንኮታኩተው ነፃነታቸውን ማስመለስ የቻሉበት ዘመን ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ ከአስርት ዓመት በኋላ እውን ሆነ። በተለይ ከ17 በላይ የአፍሪካ ሀገራት ከአውሮፓውያኑ የቅኝ አገዛዝ ቀንበር የተላቀቁበት ‘የአፍሪካ ዓመት’ በመባል የሚታወቀው የፈረንጆቹ 1960 በአፍሪካ የነፃነት ታሪክ ውስጥ ሰፊ ስፍራ ይዞ እናገኘዋለን። ከዚሁ ዓመት ውስጥ ደግሞ ከዘጠኝ በላይ የሆኑ የአፍሪካ ሀገሮች ነፃ የሆኑበት ነሐሴ ወር 1960 ጎልቶ ይታያል። ታሪኩን ለመንገር እንዲያመች ከዚህ ቀጥሎ ያሉትን ዓመተ ምህረቶች በፈረንጆቹ ቀመር ተጠቅመናል።

በአፍሪካ እና በሕዝቦቿ ላይ የተጫነው የቅኝ አገዛዝ አስከፊ ዘመን ከግማሽ ክፍለዘመን በላይ በአህጉሪቱ ቆይቷል። በአፍሪካውያን የተጀመሩት የነፃነት ትግሎች አብዛኛዎቹ ለፍሬ የበቁት በፈረንጆቹ 1960 በመሆኑ የአፍሪካ ዓመት እየተባለ ይጠራ እንጂ ከዚያ በፊት ነፃ የወጡ የአፍሪካ ሀገራት አልነበሩም ማለት ግን አይደለም። ቁጥራቸው ጥቂት ይሁን እንጂ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ ዓስርት ዓመት ጀምሮ በተለያዩ ዓመታት ነፃነታቸውን የተቀዳጁ ሀገራት ነበሩ። እስኪ  አስቀድመን ከ1960 በፊት የነበሩትን የታሪክ ኩነቶች በአጭሩ እንመልከት።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃት ማግስት ጀምሮ ለአፍሪካ ነፃነት የተፈጠረውን መልካም አጋጣሚ እየተጠቀሙ ነፃነታቸውን ማረጋገጥ የጀመሩ ሀገራት ነበሩ። እ.ኤ.አ በ1922 ግብፅ ከእንግሊዝ ነፃነቷን ተረክባ በሀገሯ ልጅ ንጉስ ፉአድ መመራት በመቻሏ ሌሎች ሀገራትም ተከትለዋል። የጣሊያን አገዛዝ አብቅቶ በንጉሥ እድሪስ መመራት የጀመረችው ሊቢያ በ1951 ነፃነቷን አገኘች። ሱዳን፣ ቱኒዚያ፣ ሞሮኮ፣ ሁሉም በ1956 በተለያዩ ወራት ነፃነታቸውን ተቀዳጅተዋል።

ለምእራብ አፍሪካ ነፃነት ፈር ቀዳጁ የሚባልለት የነፃነት ቀን ደግሞ ጋና ከእንግሊዝ ነፃነቷን ተቀብላ በመጀመሪያው ጥቁር መሪዋ ኩዋሜ ንክሩማህ መመራት የጀመረችበት ማርች 6 ቀን 1957 የተበሰረበት ታሪካዊ ዓመት በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ ይዟል። የጋና ቀድማ ከምእራቡ የአፍሪካ ሀገራት ነፃነቷን ማረጋገጥ ለቀሪዎቹ ሰፊ በር ከፈተ። ጋናን ተከትሎ በ1958 ጊኒ ከ1960 በፊት ነፃነታቸውን ካወጁ ዘጠኙ የአፍሪካ ሀገራት ጋር ተደመረች። በአጠቃላይ ከ1960 በፊት በመላው አፍሪካ ነፃ የሆኑ ሀገራት ዘጠኝ ከሆኑ በአጠቃላይ በአህጉሪቱ ከአውሮፓ ቅኝ አገዛዝ ነፃ የወጡት 98 ሚሊዮን የሚሆኑ አፍሪካውያን ብቻ ነበሩ። ነገር ግን ይህ አኃዝ በ1960 ብቻ በእጥፍ ጨምሮ 180 ሚሊዮን አፍሪካውያን ነፃ መውጣት የቻሉበት አስደናቂ ታሪክ በአፍሪካ ተመዘገበ። እስከዚህ ዓመት ከአውሮፓውያኑ አገዛዝ ነፃ የወጡ ሀገራት ቁጥር 26 ደርሶ እንደነበርም ታሪክ ያስታውሳል።

በ1960 ነፃ ከወጡት 17 ከሚሆኑ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ዘጠኙ በነሐሴ ወር ያረጋገጡ ነበሩ። በዚሁ ወር መባቻ ነሐሴ 1 ቀን 1960 በቤኒን ሰማይ ስር የወጣችው ፀሀይ ለ60 ዓመታት አሳር ስቃይ ያበላት የፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ዘመን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማክተሙን አበሰረች። ከሁለት ዓመታት በፊት በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ መሰረት ነፃነትን ከፈረንሳይ እጅ ስትረከብ ዳሆሜ በሚለው የቀድሞ ስሟ ሲሆን፤ የመጀመሪያ መሪ ሆኖ በተሾመው ጥቁር ፕሬዚዳንቷ ሁበርት ማጋ ነፃነቷን ጀምራለች። ቢኒን የተባለችው ደግሞ ከ1975 በኋላ መሆኑን የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ።

‘ኢንሳይክሎፒዲያ ኦፍ አፍሪካን ሒስትሪ’ በተሰኘ የታሪክ ሰነድ ላይ እንደተቀመጠው ከቤኒን ሁለት ቀን ዘግይታ ነሐሴ 3 ቀን 1960 ላይ ኒጀር ሌላዋ የነሐሴ ትሩፋት ሆነች። ኒጀር የፈረንሳይ ወራሪዎችን ላለማስገባት በጀግንነት ከተከለከሉ  የምእራብ አፍሪካ ሀገራት አንዷ ናት። ይሁን እንጂ ቆራጥ ትግሏ ወራሪዎችን ቢያዘገያቸውም ፈፅሞ ግን አላቆማቸውም። እናም ከ1883 ጀምሮ በፈረንሳይ ስር ሆና ከቆየች በኋላ ነፃነቷን ስታረጋግጥ፤ ሐማኒ ዲዮሪ የተባለ የሀገሯን ልጅ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንቷ አድርጋ በመሾም ነበር። ፕሬዚደንት ሐማኒ ለ14 ዓመታት ኒጀርን መርቶ በ1975 በተካሄደ መፈንቅለ መንግሥት  ከስልጣን ተወግዷል።

ነሐሴ 5 ቀን 1960 ለቶማስ ሳንካራ ሀገር፤ ለምእራብ አፍሪካዊቷ ቦርኪናፋሶ  ልዩ ቀን ነበረች። ቦርኪናቤዎቹ የፈረንሳይ የግማሽ ክፍለ ዘመን የቅኝ ግዛት ቀንበር መሰበሩን በፌሽታ የተቀበሉበት ልዩ እለት ነው። ማውሪስ ያሚዮጎ የመጀመሪያ ጥቁር የቦርኪናቤዎቹ ፕሬዝደንት ሆነው ተመረጡ፤ ለስድስት  ዓመታት ካስተዳደሩ በኋላ በመፈንቅለ መንግሥት ከስልጣን ወርደዋል። በተለይ ተደጋጋሚ መፈንቅለ መንግሥት በተካሄዱባት ቦርኪናፋሶ የ1984ቱ መፈንቅለ መንግሥት ድንቅ ወጣት አብዮተኛ መሪ አስገኝቶላት ነበር፤ ወጣቱን አብዮተኛ ቶማስ ሳንካራ። ሳንካራ በፈረንሳይ አስከፊ አገዛዝ መቀመቅ ወርዶ የነበረውን የሀገሩን ኢኮኖሚ በአራት አመታት ሀቀኛ አብዮታዊ ስር ነቀል እርምጃዎችን  በመውሰድ የሕዝቡን ሕይወት መቀየር የቻለ፣ ለቦርኪናፋሶ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ መኩሪያ የሆነ ድንቅ መሪ ነበር።

ለበርካታ የምእራብ አፍሪካ ስደተኞች መጠለያ በመሆን በምትታወቀው የአይቮሪ ኮስት ምድር እንደ ነሐሴ 7 ቀን 1960 ያለ የፌሽታ ቀን አልታየም። በሌላ ስሟ ኮትዲቯር የምትባለውን በተፈጥሮ ሀብት የታደለችው ሀገር በ1893 በፈረንሳይ እጅ ከወደቀች ጀምሮ እስከ 1960 በአስከፊ ሁኔታ የማቀቀችበት፣ ሀብቷን የተዘረፈችበት አስቀያሚው የባእዳን ስርአት አበቃ። ኮትዲቯር ይህን ልዩ ቀን የሀገሯን ልጅ ፊሊክስ ሀውፌት የመጀመሪያ ፕሬዚዳንቷ አድርጋ በመሾም  የነጭ የቀድሞ ጌቶቿን ፊት የማታይበትን ታሪክ ፃፈች።

ፕሬዝደንት ፍራንኮይስ ቶምበልባየ  የመካከለኛው አፍሪካዊት ሀገር የቻድ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዚደንት በመሆን የሀገሪቱ ነፃነት የተበሰረበት ነሐሴ 11 ቀን 1960 ሌላው በአፍሪካ የተሰማው ድንቅ ዜና ነበር። እንደ አለመታደል ሆኖ ይህ የነፃነት ፌሽታ ብዙም ሳይቆይ ቻድ በከፋ የርስ በርስ ጦርነት አዘቅት ውስጥ ወድቃለች።

በመሀከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ነሐሴ 13 ቀን 1960 የተበሰረው የነፃነት ቀን በዚሁ ዓመት ነፃነታቸውን ካገኙ ሀገራት 11ኛዋ ያደርጋታል። ዳቪድ ዳኮ የመጀመሪያ ጥቁር ፕሬዝደንት በመሆን ሀገሪቱን መርቷል። ዴቪድ ዳኮ ሀገሪቱ በብሔራዊ ጀግና የምትዘክረው የባርቶሎሜ ቦጋንዳ የአጎት ልጅ ነው። ባርቶሎሜ ቦጋንዳ ለመሀከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ እና ለመላ አፍሪካ ነፃነት በቁርጠኝነት ሲታገል የኖረ፣ ነገር ግን የሀገሩን ነፃነት ከማየቱ አንድ ዓመት በፊት በደረሰበት የአውሮፕላን አደጋ ሕይወቱ በማለፉ ምክንያት ከነፃነት በኋላ የሀገር መሪነቱ ቦታ ለአጎቱ ልጅ መሰጠቱን የሀገሪቱ ታሪክ ያስረዳል። በ1905 በፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ስር የወደቀችው ኡባንጊ ቻሪ እየተባለች የምትጠራበትን ስሟን አሁን ወደምትታወቅበት ማእከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ የለወጠችው በ1958 እ.ኤ.አ መሆኑን ልብ ይሏል።

ቤልጅየም ከብዙ ማቅማማት በኋላ ሳትወድ በግዷ የኮንጎን ነፃነት ለባለቤቶቹ በይፋ ያስረከበችው ነሐሴ 15 ቀን 1960 ነበር። ለሀያ ዓመታት ያክል ለቤልጅየሙ ንጉሥ ዳግማዊ ሊዮፖልድ እንደ ግል ርስት፤ ከዚያም ለ60 ያህል ዓመታት በቤልጅየም መንግሥት ቅኝ ግዛት ስር በአጠቃላይ ከ80 በላይ ዓመታት በባእዳን አገዛዝ ስር አሰቃቂ ሕይወት የመራው የኮንጎ ሕዝብ በዚህ እለት የሰማውን ዜና ማመን እስኪቸገር ደስታውን በየጎዳናው በነቂስ ወጥቶ በፌሽታ ሲያከብር ዉሎ አምሽቷል። በተለይ ደግሞ በነፃነቷ ማብሰሪያ ስነስርአት ላይ የቁርጥ ቀን ልጇ ፓትሪስ ሉሙምባ ያደረገው ንግግር መላውን ዓለም ያነጋገረ ታሪካዊ ክስተት ሆኖ እለቱን አድምቆት ነበር። ነገር ግን ቤልጅየሞች የፓትሪስ ሉሙምባን ንግግር ክብራቸውን የነካ ያህል ቆጥረው ቂም ቋጠሩበት። እናም ቤልጅየም ከፈረንሳይ እና ከአሜሪካ ጋር በማሴር መቃብሩን ይቆፍሩ ያዙ። የኮንጎ ደስታ አንድ ዓመት ሳይዘልቅ ሴረኞቹ ኮንጎን ለሦስት ሀገርነት በጣጠሷት። ቆራጡን ታጋይ ፓትሪስ ልሙምባንም ከንፈራቸውን እንደነከሱበት በሴራቸው ጠልፈው አስቀያሚ በሆነ መንገድ ሕይወቱን ቀሙት።

ተአምረኛው ነሐሴ ሳያልቅ ሌሎች የምስራች ዜና ከሰሙ ሀገራት መካከል የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት የነበረችው ሴኔጋል ትጠጠሳቃለች። ሊዮፖልድ ሴንጎር የመጀመሪያ ፕሬዝዳንቷ ነበር። በነገራችን ላይ ሴኔጋልና እና ማሊ ተጣምረው “የማሊ ፌዴሬሽን” የሚል አንድ ሀገር በፈጠሩ አንድ ዓመት በኋላ በተፈጠረ አለመግባባት ተለያይተው ሴኔጋል እና ማሊ የተባሉ ሁለት ሉዓላዊ ሀገሮች ሊፈጠሩ እንደቻለ በታሪክ ተዘግቧል። ብቻ ትኩረታችን ነሐሴ 1960 ሆነና ሁሉንም የዚህን ድንቅ ዓመት ትሩፋቶች ለማካተት አልቻልንም፣ ሆኖም ማሳረጊያችንን በታዋቂው ኬኒያዊ የስነ ፅሁፍ ሰው ንጉጊ ስለኬንያ የነፃነት ቀንን በተመለከተ በፃፈው ድንቅ ፅሁፉ እድርገን እናብቃ።

“እኩለ ሌሊት ሊሆን ከአንድ ደቂቃ በፊት፣ መብራት ጠፍቶ ነበር።…ጨለማው ውስጥ  የእንግሊዝ ሰንደቅዓላማ በፍጥነት ወረደ። በመቀጠል መብራቶች ሁሉ እንዲበሩ በተደረገ ጊዜ የአዲሷ ኬንያ ሰንደቅዓላማ …እየተውለበለበ ነበር።” –ሲል ታዋቂው የኬንያ የስነፅሁፍ የዓለም ሎሬት ንጉጊ ዋ ቶንግ’ኦ፣ በመዲናዋ ናይሮቢ የነፃነት ብስራቱን ክስተት  ጽፎታል።

ኬኒያ በዚሁ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት አስርት ዓመት በኋላ ከአውሮፓውያኑ ቅኝ አገዛዝ ነፃነታቸውን ካገኙ ከ40 በላይ የአፍሪካ ሀገራት አንዷ በመሆን የተደመረችበት ታሪካዊ ቀን ነበር።

ሳምንቱ በታሪክ

ዝብስት

በሱዳን በኩል ወደ ኢትዮጵያ እየገባ የነበረው የኢትዮጵያ ነፃ አውጭ ወደ ጎጃም የገባው ጳጉሜ 5 ቀን 1932 ዓ.ም ነበር።

በዳንግላ የነበረው የጠላት ጦር አዛዥ ኮሎኔል ቶሬሊ  ከእነ ጦሩ ከዳንግላ አቸፈር ዝብስት ከተባለው ቀበሌ የገባው በዚሁ ዕለት ነበር።   የአቸፈር አርበኛ የሆኑት ፊታውራሪ አያሌው መኮንን በመጀመሪያ መጥተው ተገናኝተው የተወያዩትም ጳጉሜ 5 ቀን 1932 ዓ.ም ነበር። በዚህ ወቅት አውሮፕላን በላያቸው  ይመላለሰ ነበር።

ምንጭ፦ የታሪክ ማስታዎሻ በከበደ ተሰማ

ጥቁር መስከረም

ጳጉሜን 1 እና 2 ቀን 1964 ዓ.ም – ሙኒክ ላይ በተካሄደው የበጋ ኦሊምፒክ ውድድር ላይ “ጥቁር መስከረም” (“Black September”) የተባለ የፍልስጥኤም ሽብርተኛ ቡድን የእስራኤልን ተወዳዳሪዎች እና አሰልጣኞች በአፈና ከያዘ በኋላ አሥራ አንዱን ገደላቸው።

በአፀፋውም የእስራኤል ተዋጊ ጀቶች በሊባኖስ እና ሶሪያን በቦምብ የፍልስጥኤማውያንን ይዞታ ደበደበች።

ምንጭ፦ ሂሰቶሪፕሌስ

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የነሐሴ 26   ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here