ኢትዮጵያ መፍትሄ በራቃቸው ግጭት እና ጦርነቶች እያለፈች ነው:: እነዚህም ግጭት እና ጦርነቶች የሕዝቡ ማኅበራዊ መስተጋብር እንዲላላ እና ምጣኔ ሐብቱ እንዲዳከም እያደረጉ መጥተዋል:: ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ መልካቸውን እየቀያየሩ የመጡ የጸጥታ መናጋቶች ለዚህ አብነት ሆነው ይነሳሉ::
በተደጋጋሚ እያጋጠሙ ላሉ የሰላም እና ደኅንነት መናጋት ምክንያቶችን መረዳት ደግሞ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ያስችላል:: የመጀመሪያው እና ክፍተት እንዳለበትም ታምኖበት በመንግሥት በኩል ለማሻሻል ትኩረት የተሰጠው የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት ነው:: ሕገ መንግሥቱ በ1987 ዓ.ም ሲረቀቅ በኢትዮጵያ የሚገኙ ሁሉንም ብሄር ብሄረሰቦች ሳያሳትፍ የተረቀቀ ነው በሚል በብዙኃኑ ዘንድ እንዲሻሻል ሲጠየቅ ቆይቷል:: በፍጥነት ምላሽ አለማግኘቱ ግን ሀገሪቱ አሁን ለገባችበት ቀውስ ገዥ ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል::
ሰላማዊ የሆነ የስልጣን ሽግግር አለመኖርም ሌላው ግጭቶች እንዳይበርዱ ያደረገ ክስተት ነው:: ለዚህ የሰሜኑ ጦርነት ዋና አስረጂ ይሆናል:: ኢትዮጵያን ለ27 ዓመታት ሲያስተዳድር የነበረው ሥርዓት ተወግዶ በሌላ መተካቱ ያልተዋጠለት ኢህዴግ ጦርነትን በመቀስቀስ ሀገሪቱን ለበርካታ ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ… ምስቅልቅል ዳርጓል::
የወሰን እና የማንነት ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎች ምላሽ አለማግኘትም ዛሬም ድረስ ዋና ያለመረጋጋት ምክንያት ሆኖ ይስተዋላል:: እንደ ራያ እና ወልቃይትን በመሰሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ማንነታቸው በጉልበት መነጠቁን እያነሱ ቢሆንም በመንግሥት በኩል አሁንም ፈጣን ምላሽ አለመሰጠታቸው በርካቶች ተረጋግተው ለመኖር እንዳይችሉ አድርጓል:: ዛሬም የራያ አካባቢ ሕዝብ በትግራይ ኀይሎች ዳግም መወረራቸውን ሲስታውቁ፣ የአማራ ክልል መንግሥትም በቅርቡ ማስጠንቀቂ ዘል መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል::
ከአማራ ክልል ውጪ የሚኖረው አማራ ሕገ መንግሥታዊ ውክልና ተነጥቆ፣ ተጋብቶ እና ተዋልዶ፣ ሐብት አፍርቶ ከሚኖርበት አካባቢ እንዲፈናቀል መደረጉ ሌላው ሀገሪቱ ለገጠማት የሰላም መናጋት ዋና ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል:: በእርግጥ መንግሥት አሁንም ከሌሎች ክልሎች የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቋል:: ይሁን እንጂ ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት አሁንም ባልቆመበት ዜጎች በሚመለሱበት አካባቢ የተረጋጋ ሕይወትን መምራት ይችላሉ? የሚለው ጥያቄ የብዙኃኑ ሆኖ አሁንም እየተስተጋባ ነው:: በእነዚህ እና በኢኮኖሚ እኩል ተጠቃሚነት ችግሮች ምክንያት የተፈጠሩ እና እየተፈጠሩ ያሉ ጦርነቶች እና ግጭቶች የበርካቶችን ሕይወት ነጥቋል፤ ለአካል ጉዳት ዳርጓል፤ ምጣኔ ሐብታዊ ጉዳቱም ከፍተኛ ሆኗል፤ የሕዝብ ለሕዝብ መስተጋብር እንዲላላ፣ ኢትዮጵያዊ አንድነት እንዲዳከም እያደረጉ ይገኛሉ:: መፍትሄ ያልተሰጣቸው ግጭቶች የሕዳሴ ግድቡ እና ሌሎች ምጣኔ ሐብታዊ ፋይዳቸው ከፍተኛ የሆኑ የልማት ሥራዎች እንዳይጀመሩ እና እንዳይጠናቀቁ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ሲደረግም ቆይቷል::
የኢትዮጵያን የቀደመ አንድነት በመመለስ ዓለም አቀፋዊ ተሰሚነቷን አጽንቶ ለመቆየት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተፈጠሩ ላሉ የሰላም መናጋቶች ዘላቂ መፍትሄ መስጠት ይገባል:: መንግሥት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጠሩ ያሉ በትጥቅ የታገዙ ግጭቶችን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቋጨት በሚል ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ የሕግ ማስከበር ዘመቻ እያከናወነ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ አስታውቋል:: በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት የነጠቀው የሰሜኑ ጦርነት ምንም እንኳ በሰላም ስምምነት ቢቋጭም ከባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ በአማራ ክልል የተቀሰቀሰውን ግጭት ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች አሁንም ግጭቶች እንደቀጠሉ ናቸው:: ግጭቶችን በአጭር ጊዜ ለመቋጨት በሚልም መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ከአንድም ሁለት ጊዜ በማራዘም የተጠናከረ የሕግ ማስከበር ዘመቻ እያከናወነ ይገኛል:: በአማራ ክልል ከአሥር ወራት በላይ የዘለቀውን በትጥቅ የታገዘ ግጭት መንግሥት በበላይነት ለመቋጨት የሕግ ማስከበር ዘመቻ እያከናወነ ቢገኝም የክልሉን ሰላም ወደ ዘላቂነት ማሸጋገር አልቻለም::
ክልሉ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ እንዲያልፍ በማድረግ እየተከናወነ ካለው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በተጨማሪ በትጥቅ ትግል ውስጥ የሚገኙ ወገኖች ወደ ሰላም እንዲመጡ መንግሥት ተደጋጋሚ ጥሪ ማድረጉም ይታወሳል:: የዓባይ ወንዝ ድልድይ ግንቦት 4 ቀን 2016 ዓ.ም በተመረቀበት ወቅት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለአማራ ሕዝብ መብት እና ጥቅም መከበር የሚታገል ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ቡድን ከክልሉ መንግሥት ጋር በመነጋገር ለክልሉ ሠላም እና ልማት ሊሠሩ እንደሚገባ መናገራቸው ይታወሳል:: በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉ የሰላም ጥሪዎች የክልሉ ሰላም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ እንዲመጣ አድርጓል በሚል በተለያዩ የመንግሥት አካላት በተደጋጋሚ ቢገለጽም፣ ግጭቶች እና የመንገድ መዘጋቶች ግን አሁንም እንደቀጠሉ ናቸው::
በትጥቅ ግጭት ውስጥ ያሉ ወገኖች እንታገልለታለን ለሚሉት ሕዝብ ፍላጎት መሳካት ሰላማዊ አማራጮችን ብቸኛ መንገድ እንዲያደርጉ ከማድረግ በተጨማሪ ብሄራዊ ምክክር እና የሽግግር ፍትህ ሀገሪቱን ከግጭት አዙሪት ለማውጣት ዋና መፍትሄ ሆነው እየተሠራባቸውም ይገኛሉ:: በተለይ ሀገራዊ ምክክር በርካታ በግጭት ውስጥ የነበሩ ሀገራት ችግሮቻቸውን ፈትተው ዛሬ ላይ ተምሳሌታዊ ሰላምን አስፍነዋል፤ ሀገራዊ ዕድገታቸውንም የተሻለ ደረጃ ላይ አድርሰውበታል:: ኢትዮጵያም በተደጋጋሚ እያጋጠሟት የሚገኙ የሰላም መደፍረሶችን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ይፈታልኛል ያለችውን ሀገራዊ ምክክር ተግባራዊ እያደረገች ነው::
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በአሁኑ አብዛኛዎችን ሥራዎች እያጠናቀቀ ወደ አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት እየገባ መሆኑን አስታውቋል:: የመጀመሪያ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራውንም በአዲስ አበባ አካሂዷል:: በዚህ ወቅት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ኮሚሽኑ የዝግጅት ምዕራፉን አገባዶ የአጀንዳ መሰብሰብ ሥራውን በይፋ መጀመሩን አስታውቀዋል:: እስካሁንም በአሥር ክልሎች እና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች ከ1ሺ በላይ ወረዳዎች በአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ የሚሳተፉ ተወካዮችን ማስመረጥ እንደቻሉ አስታውቀዋል:: በቀጣይም የተሳታፊዎች መረጣ በተካሄደባቸው ክልሎች እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራው እንደሚቀጥል ተናግረዋል:: በአማራ እና በትግራይ ክልሎች ደግሞ የተሳታፊዎች ልየታ እና መረጣ እንደሚከናወን ጠቁመዋል::
በአዲስ አበባ በተካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት 11 የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ እንደሆኑ ተገልጿል:: በሀገሪቱ ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው የምክክር ሂደት የተሳትፎ ጥሪ አልተደረገልንም በሚል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅሬታዋን አሰምታለች::
ቤተክርስቲያኒቱ የ2016 ዓ.ም የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ማጠናቀቋን ተከትሎ ባወጣችው መግለጫ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የሰላም ችግሮችን በውይይት እና ንግግር ለመፍታት በሚደርገው ሀገራዊ ምክክር ሂደት ለቤተክርስቲያኒቱ ይፋዊ የተሳትፎ ጥሪ እንዳልተደረገላት አስታውቃለች:: በዚህም ማዘኗን ገልጻለች:: “የቤተ ክርስቲያኒቱን ተሳትፎ እና አጀንዳ የማቅረብ መብቷ እንዲረጋገጥ ከኮሚሽኑ ጋር በመነጋገር ጉዳዩን ተከታትሎ ለማስፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስ ኮሚቴ መሰየሙን ከጉባኤው መግለጫ መረዳት ተችሏል::
ኮሚሽኑ የሚያካሂደው የምክክር ሂደት የአካታችነት መርህ ከሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ጋር በእኩልነት የሚተገበር መሆኑን ከሚሽኑ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የተሳትፎ ጥሪ አልደረሰኝም በሚል ለደረሰበት ወቀሳ ምላሽ በሰጠበት መግለለጫ ለመረዳት ተችሏል:: ኮሚሽኑም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዱስ ጋር ለመወያየት ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል::
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች አሁንም ጦርነቶች አለመቆማቸው የምክክር ሂደቱ ውጤታማነት እንዳይሆን ሊያደርግ ይችላል የሚሉ ወገኖች ደግሞ አልታጡም:: ለአብነት የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) እና እናት ፓርቲዎች ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ በሆነችበት፣ የታሰሩ ንቁ ሰዎች ባልተፈቱበት እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባልተነሳበት ሁኔታ በምክክር መሳተፉ ትርጉም የለውም በሚል ራሳቸውን ከምክክሩ እንደሚያገሉ እየገለጹ ይገኛሉ:: በአንጻሩ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ተወካይ ግርማ ሰይፉ ሀገር በዘላቂ መሰረት ላይ እንድትቆም እና በማያግባቡን ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ከስምምነት እንድንደርስ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራዊ ምክክሩ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጠይቀዋል::
ኮሚሽኑ በበኩሉ ኢትዮጵያዊ መቀራረብን እና መግባባትን ለማምጣት በትጋት እየሠራ እንደሚገኝ ፕሮፌሰር መስፍን አስታውቀዋል:: ምክክሩ አካታች፣ ሂደቱም ግልፅ እና ተዓማኒ በሆነ መንገድ እንዲከናወን ይደረጋል ብለዋል:: በመሆኑም በተጀመረው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ አጀንዳውን በግልም ሆነ በጋራ በማፍለቅ ኢትዮጵያዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል::
ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ኮሚሽኑ በየትኛውም ቦታ ላሉ ወገኖች የሰላም በር ለማመቻቸት ትኩረት መስጠቱንም ለጥርጣሬው መልስ አድርገው ተናግረዋል::
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ጥቅምት 1 ቀን 2015 ዓ.ም የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች እና ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ስትራቴጂክ ዕቅዱ በማቅረብ ውይይት ማድረጉ ይታወሳል:: በዚህ ወቅት ዋና ኮሚሽነሩ ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን የመንግስት ድጋፍ፣ ጠንካራ አመራርነት መስጠት፣ የውጭ ሀገራትን ጣልቃ ገብነት መከላከል እና ሕዝባዊ ተሣትፎ እንዲኖር ማመቻቸት ሰላም የማስፈን ግቡ እንዲሳካ ጉልህ አበርክቶ እንደሚኖረው በመግለጽ ሁሉም የኮሚሽኑን ሥራ ሊደግፍ እንደሚገባ አሳስበዋል::
ብሄራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ግንቦት 24 ቀን 2016 ዓ.ም የአጀንዳ መሰብሰብ ሥራውን በአዲስ አበባ በጀመረበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ተገኝተው ነበር:: በምክክሩ መግባባት ላይ የተደረሰባቸውን ድምዳሜዎች ለማስፈፀም መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል:: ከኮሚሽኑ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው ዘገባ እንደሚያመለክተው ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የማንስማማባቸው አጀንዳዎች የሚገጥሙን ከሆነም በህዝበ ውሳኔ (ሪፈረንደም) እልባት ያገኛሉ” ብለዋል። ሕዝብ ከወሰነ በኋላ ማናችንም ብንሆን የሕዝቡን ውሳኔ ማክበር ይኖርብናል ሲሉም አክለዋል::
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኮሚሽኑ ለሰላም በሚያደርገው ጥረት የመንግሥትም ሆነ የፓርቲ ጣልቃ ገብነት እንደማይኖር ከገለጹ በኋላ “በኢትኢዮጵያ የሽግግር መንግሥት አይኖርም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖረው በምርጫ የተመረጠ መንግሥት ብቻ ነው” ማለታቸው ደግሞ ብዙዎች ምክክሩ ግቡን አያሳካም ወደሚል ሐሳብ እንዲገቡ አድርጓቸዋል::
ሰላምን በብሄራዊ የምክክር መድረክ ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት የተሳካ ሆኖ ኢትዮጵያም ትንሳኤዋ እውን እንዲሆን በሂደቱ ካለፉ ሀገራት ተሞክሮ መውሰድ ሌላው ለስኬታማነቱ ውጤታማነት አስተዋጽኦ ይኖረዋል:: ብዙኃኑን አሳትፎ የሰላም መንገድን ለመቀየስ የታመነበትን የምክክር ኮሚሽን በማቋቋም በርካታ የዓለም ሀገራት ከሰላም እጦት የመውጫ መንገድ አድርገው ተጠቅመውበታል:: የአካሄድ ልዩነት ግን አንዳንዶች የነበረባቸውን የሰላም ስብራት አስወግደው ለዓለም ሀገራት ተምሳሌት የሚሆን ሰላም እንዲያሰፍኑ ሲያደርጋቸው ውስኖች ከተዘፈቁበት የሰላም እጦት እንዳይወጡ አድርጓቸዋል::
የምክክሩ ሂደቱ ግልፅ፣ ተአማኒነት ያለው እና አካታች በሆነባቸው ሀገራት ውጤቱ ያማረ ሆኖ በተምሳሌትነት ዛሬም ተነስቷል:: በሌላ በኩል ደግሞ የመሪዎች አምባገነንነት እና የገዢ ፓርቲ እና የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነት እና ስውር ተልዕኮ በተስተዋለባቸው የመን፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ባሉ ሀገራት የሰላም ምክክሩ አልሰመረም::
ኢትዮጵያ በምክክር፣ ውይይት እና ንግግር ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር የምታደርገው ጥረት እንደ አንዳንድ ሀገራት እንዳይከስም፣ ይልቁንም ግቡን እንዲያሳካ በሂደቱ ተሻጋሪ ሰላምን ከገነቡ ሀገራት ተሞክሮን ልትወስድ ይገባል:: ለአብነት ለበርካታ ዓመታት በከፍተኛ ሃይማኖታዊ ግጭት ውስጥ ያለፈችው አየርላንድ ለዚህ ተጠቃሽ ናት:: ግጭቱ በዋናነት በካቶሊክ እና በፕሮቴስታንት እምነት መካከል የተፈጠረ እንደነበር መረጃዎች ሲያሳዩ የነበረው ሁኔታ ዘሬ ላይ የኋሊት ሲታሰብ አየርላንድ እንደ ሀገር ትቀጥላለች ብሎ ያሰበ አልነበረም:: በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ አስተማማኝ ሰላምን ካሰፈኑ አሥር ሀገራት ውስጥ በሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው አየርላንድ የዛሬ ሰላሟን ያረጋገጠችው በሀገራዊ ምክክር እንደሆነ ቪዥን ኡፍ ሂውማኒቲ ድረ ገጽ አስታውቋል::
በነጭ እና በጥቁር ሕዝብ መካከል በደቡብ አፍሪካ የተፈጠረው የሰላም ችግርም በሰላም ስምምነት የተፈታ፣ ዛሬም ተሞክሮው ለብዙዎች ተርፏል:: ኢትዮጵያም እንደ አየር ላንድ፣ ቤኒን፣ ቱኒዚያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ሌሎች ስኬታማ ምክክር አድርገው የሰላም ችግሮቻቸውን የፈቱባቸውን መልካም ተሞክሮዎች በመቅሰም የሀገሪቱን ሰላም እና ደኅንነት ማረጋገጥ ይገባል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም