ታላቁ የአክሱም ሥርወ መንግሥት መዳከምን ተከትሎ ለሺህ ዘመናት በዙፋኑ ላይ ሳይቆራረጥ የቆየው የሰሎሞናዊው ስርወ መንግሥት የስልጣን መስመር ተቋረጠ። የመጨረሻው የአክሱም ስርዎ መንግሥት ንጉሥ አንበሳ ውድም ወደ ሸዋ በማቅናት ከጠላቶቹ ጥቃት በየአካባቢው እየተዘዋወረ ራሱን ጠብቋል። በዚህም ዙፋን ያልጫኑ የሰለሞናዊው ስርወ መንግሥት አስር ነገሥታት እየተተካኩ የንግሥና መስመሩን እንዳይቋረጥ አድርገዋል። ይሁን እንጅ በሰሎሞናዊው እግር ተተክቶ በኢትዮጵያ ዙፋን ላይ የወጣው የዛግዌ ሥርወ መንግሥት ነገሥታት ለሦስት መቶ ዓመታት ያህል የራሳቸውን አሻራ አኑረዋል። ይሁን እንጅ ዘውድ ባይጭኑም እየተተካኩ በመንገሥ ሰሎሞናዊውን መሥመር ያስቀጠሉት ነገሥታት ለሰሎሞናዊው ስርወ መንግሥት ትንሳኤ የየራሳቸውን ጥረት ቢያደርጉም የተሳካው በ1263 ዓ.ም በዐፄ ይኩኖ አምላክ ነበር። እስከ 1277 ዓ.ም ድረስ ቆይቷል።
የሰሎሞናውያኑ መመለስ
በ1263 ዓ.ም ከሶስት መቶ ዓመታት በላይ የኢትዮጵያን ዙፋን ተቆጣጥሮ የቆየው የዛግዌ ስርወ መንግሥት ከሰሎሞናዊው የዘር ሀረግ በሆነው ይኩኖ አምላክ ተሸነፈ። ይኩኖ አምላክ የሸዋ ልዑል ነበር። በንጉሥ ነአኩቶ ለአብ እና በይኩኖ አምላክ የተደረገው የስልጣን ሽግግር በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ወሳኝ የተባለለት ክስተት ነበር። ታሪካዊው የስልጣን ሽግግር የሀይል ማእከሉን ከትግሬ እና ላስታ ወደ ሸዋ አዛውሯል።
ሰሎሞናዊውን የንጉሣዊ ስርዓት ወደ ቀደመው የታላቅነት ዘመኑ የመለሰው ዐፄ ዮክኖ አምላክ ለአስራ አምስት ያህል ዓመታት ያህል ኢትዮጵያን በድንቅ ብቃት መርቶ ለተተኪዎቹ አስረከበ። ከእርሱ በኋላም እስከ አምደ ጽዮን ድረስ ሰባት ነገሥታት እየተቀባበሉ ሰሎሞናዊውን ስርዓት ለማጠናከር ተግተዋል። ከእነዚህ መካከል ግን ታላቅ ከሚባሉት የኢትዮጵያ ነገሥታት ተርታ የሚሰለፈው በዘመኑ ታላቅ ታሪክ ሰሪዎች መካከል አንዱ የሆነውን ንጉሥ አምደ ጽዮንን ለዚህ ሳምንት የታሪክ ማህደር ልናስነብባችሁ መርጠነዋል። መልካም ንባብ።
የይኩኖ አምላክ የልጅ ልጅ የሆነው የውድም አርዕድ ልጅ አምደ ጽዮን በ1298 ዓ.ም የአባቱን ዙፋን ወርሶ ነገሠ። በየዘመኑ ከተነሱ ድንቅ ኢትዮጵያውያን ነገሥታት ውስጥ አንዱ የነበረ እና በአፍሪካ ቀንድ ገንኖ የገዛ ወደር የለሽ መሪ ነበር። አምደ ጽዮን ውጤታማ በሆነ አግባብ ባካሄዳቸው ዘመቻዎች ሰለሞናዊውን ሥርወ መንግሥት ያጠናከረ እና ግዛቱን ያስፋፋ እውነተኛው የኢትዮጵያ ሀገረመንግስት ገንቢ ነው ይሉለታል።
እርሱ የተረከባት ኢትዮጵያ በዙሪያዋ በተለይም የቀይ ባህር ጠረፋማ ክልሏ ባእዳን ወራሪዎች የመከበብ እና ከአለማቀፉ ማህበረሰብ ጋር ግንኙነቷ ተቋርጦ ተዘግቶባት የተገለለች ነበረች። በዚህ ላይ ደግሞ ውስጣዊ የፖለቲካ አለመረጋጋት ውስጥ የተቆለፈባት ሀገር ነበረች። ሆኖም ከእርሱ በፊት የነበሩት ነገሥታት ይህን አለመረጋጋት ለማስተካከል ያደርጉት የነበረ ጥረት እየበረደ ባለበት ፣ ነገር ግን ድንበሮቿን ወርረው የተቀመጡት ባእዳን ጠላቶቿ ከድንበር አልፈው ወደ መሃል ዘልቀው የመውረር ሙከራ እያደረጉ በነበረበት ነበር ታላቁ እና በጀግንነቱ የሚወሳው አምደ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ ዙፋን የተከሰተው።
ሣልሳዊ ገብረ መስቀል በሚል ስመ መንግሥት ዘውድ የጫነው ንጉሠ ነገሥት አምደ ጽዮን ሰሎሞናዊውን የአገዛዝ መስመር በማጠናከር ወደ ኃያልነት የመራ እና ዳግም ሀይለኛ ያደረገ ትልቅ ሰው ነው፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ። በምስራቃዊው የቀይ ባህር ጠረፍ በአባቶቹ ታላቅ ተጋድሎ ባሉበት ተወስነው ለዘመናት የቆዩት ወራሪ የውጭ ጠላቶች በኢትዮጵያ ላይ የተጋረጡትን አደገኛ ስጋት የማስወገድ ኃላፊነቱ በአምደ ጽዮን ትከሻ ላይ ወድቆ ነበር። ስለሆነም ወሳኝ እና ድል አጎናፃፊ ወታደራዊ ዘመቻዎችን በሀገሪቱ የተለያዩ አቅጣጫዎች አድርጓል። በተዳከመው የሰለሞናዊው ስርወ መንግሥት ደካማ ጎን ተጠቅመው ምእራባውያን እና አረቦች ያወደሙትን የታላቅነት አሻራ እንደገና የማደስ እና ኢትዮጵያን ወደ ከፍታዋ መመለስ በአምደ ጽዮን ልብ ውስጥ ይመላለስ ነበር።
የስነ ፅሁፍ ትንሳኤ
ንጉሠ ነገሥት አምደ ጽዮን በስልጣን ዘመኑ መጀመሪያ ላይ ከፈፀማቸው ስኬታማ ስራዎች መካከል የተዳከመውን የስነ ፅሁፍ ስራ እንዲያንሰራራ ያደረገው በታሪክ ከሚያስወሱት ከታላላቅ ስራዎቹ መካከል አንዱ ነበር። የአክሱም ስርወ መንግሥት ሲዳከም የሰለሞናዊው ነገሥታት ታሪክ ለማጥፋት ሮማውያን እና አረቦቹ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ የታሪክ እና መንፈሳዊ መፃህፍትን አውድማው፤ አቃጥለዋቸው ነበር። እናም አምደ ጽዮን ወደ ስልጣን እንደመጣ ወዲያውኑ እነዚህን የነገስታት ታሪክ እና መንፈሳዊ መፃህፍትን የሚፅፉትን እና መተርጎም የሚችሉትን ሊቃውንት ከሀገሪቱ የተለያዬ አቅጣጫ እንዲመጡ ጥሪ አቅርቦላቸው ነበር። አስፈላጊ ነገሮች ተሟልተውላቸው ስራቸውን አስጀመሯቸው። በርካታ መፃህፍትንም እንደገና በመፃፍ እና በመተርጎም ማዘጋጀት ችለዋል። በእርሱ ዘመን የስነፅሁፍ ፍላጎት በሕዝቡ ዘንድ ጨምሮ እንደነበርም ታሪኩ ያስረዳል።
ታላቅ ዘመቻዎች
ዐፄ አምደ ጽዮን በአፍሪካ ቀንድ ተፅእኖ ፈጣሪ እና ተፈሪ መሪ ነበሩ። የሀገራቸውን ጥቅም እና ክብር በሚያረጋግጥ ዲፕሎማሲያቸው ይታወቃሉ። በ1317 ዓ.ም ለግብፁ የማምሉክ ሱልጣን አል ናስር ሙሃመድ የፃፉት መልእክት አንዱ ማሳያ ነው። አምደ ጽዮን የግብፁ የፈጣን በሀገሩ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን እና ግብፃውያን ክርስትያኖች በአረቦች ይደርስባቸው የነበረን በደል በመቃወም ማስፈራሪያ አዘል መልእክት አድርሶታል። ይህን ድርጊት ሱልጣኑ ካላስቆመ ተመሳሳይ እርምጃ በኢትዮጵያ በሚኖሩ አረቦች ላይ እንደሚወስድ እና ወደ ግብፅ የሚሄደውን የአባይ ወንዝ እንደሚገድበው ማስፈራሪያ እንደላከ በታሪክ ተፅፏል።
ከዚህ በኋላ ወታደራዊ ዘመቻዎችን እና አስደማሚ ድሎችን አምደ ጽዮን ማስመዝገቡን ልብ ይሏል። ኢትዮጵያ ሰሎሞናዊውን ስርወ መንግሥት የሚገዳደሩ ሱልጣኖች ተነስተው አምደ ጽዮንን ፈተኑት። በምስራቅ ሸዋ በኩል የነበረው የይፋት ሱልጣን የመጀመሪያው የኢትዮጵያ አደጋ ሆኖ ተከሰተ። ስለዚህ አምደ ጽዮን የገነባውን ጠንካራ ሰራዊት ወደ ይፋት ሱልጣን ሳብር አድ ላዲን አዘመተ። አምደ ጽዮን በ1321 ዓ.ም ላይ ከተደረጉ ተከታታይ ፍልሚያዎች በኋላ የኢፋትን ስልጣን አሸነፈ እና ይፋትን እና ፋጠጋርን ተቆጣጥሯል። በሰብር አድ ዲን ፋንታ ወንድሙን ጀማል አድ አዲንን ባለሥልጣን አድርጎ በመሾም በድል ተመልሷል።
(መሠረት ቸኮል)
በኲር የካታቲ 3 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም