የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እና ፋይዳዉ

0
94

የኢንቨስትመንት ችግሮችን ለይቶ በመፍታት ምርታማነትን ማሳደግ የመንግሥት ዋነኛ ትኩረት መሆኑ ተገለጸ፡፡

የኢንዱስትሪዎችን የሥራ ማነቆዎች በመፍታት ወደ ምርት እንዲገቡ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ታምኖበት በ2014 ዓ.ም የተጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በጎንደር ከተማ ተካሂዷል፡፡ “ኢትዮጵያ ታምርት፤ እኛም እንሸምት!” የንቅናቄው መሪ መልዕክት ነው፡፡ ከተለያዩ አካባቢዎች  የተውጣጡ አምራች ኢንዱስትሪዎችም ምርቶቻቸውን ይዘው በመቅረብ ለሸማቹ ማኅበረሰብ ማስተዋወቅ ችለዋል፡፡

 

እንደ ሀገር ከሦስት ዓመታት በፊት የተጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአማራ ክልልም  የአምራች ዘርፉ እንዲነቃቃ፣ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እንዲጨምር እና በርካታ ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩ ማድረጉ በወቅቱ ተገልጿል፡፡

 

የአማራ ክልል በግብርናው ዘርፍ ጠንካራ ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ፣ ይህም ለኢንዱስትሪው ትልቅ አቅም እንደሚሆን የገለጹት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ናቸው፡፡ አሁንም ክልሉ ባለው የመልማት ጸጋ ልክ እንዲለማ መንግሥት፣ ባለሃብቶች እና ሕዝቡ በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

 

ጎንደር እና አካባቢው የካበተ የእደ ጥበብ እና የኢንጅነሪንግ ጥበብ ቀድሞ የተጀመረበት ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያጋሙ የመጡ ግጭቶች ግን ይህ ገናናነት እንዳይቀጥል ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡ አሁንም ያለው የመልማት እንቅስቃሴ እንዳይገታ ከተደጋጋሚ ግጭት እና አልባሌ አስተሳሰብ መውጣት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ለዚህም ልዩነትን ተቀራርቦ በሐሳብ የበላይነት መፍታት ይገባል ብለዋል፡፡

 

ክልሉን ወደ ቀደመ ሰላሙ ከመመለስ ባሻገር ባለሃብቶች በነጻነት በሙሉ አቅማቸው እንዲሠሩ መደገፍ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ ባለሐብቶች ከራሳቸው አልፈው ለክልሉ እና  ለሀገር የሚጠበቅባቸውን ኢኮኖሚያዊ አበርክቶ እንዲወጡ በመንግሥት በኩል የሚደረገው ድጋፍ ጠንካራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ልማት ባንክ አስፈላጊውን የፋይናንስ አቅርቦት እንደሚያመቻች አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ባለሃብቶች የወሰዱትን መሬት በጊዜ አልምተው ተገቢውን የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ እና ኢኮኖሚ እንዲያመነጩ አሳስበዋል፡፡

በአጠቃላይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን አቶ መላኩ አስታውቀዋል፡፡

 

ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ “የኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት” ንቅናቄ ላለፉት ሦስት ዓመታት በክልሉ ሁሉም ዞኖች እና ወረዳዎች ሲካሄድ መቆየቱን አስታውቀዋል፡፡

ይህም በክልሉ ያለው የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ በፍሰትም ሆነ በጥራት ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጣ ማስቻሉን አስታውቀዋል፡፡ ተኪ ምርቶች በመጠን እና በሚያስገኙት ኢኮኖሚ ከፍ ማለታቸውንም ገልጸዋል። የሥራ ዕድል እና የቴክኖሎጂ ሽግግር የተገኘበት መሆኑንም አንስተዋል፡፡

 

ተቋማዊ የመምራት ብቃት ውስንነት እና የቅንጅት መጓደል፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍና እና የጥራት ውስንነት እንዲሁም የመሬት፣ የፋይናንስ፣ የመሠረተ ልማት እና የሠለጠነ የሰው ኀይል አቅርቦት ማነስ አሁንም የኢንዱስትሪ ዘርፉ ፈተናዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

“ኢንዱስትሪ የሕዝባችን ዋነኛ የኢኮኖሚ መረባረቢያ ዘርፍ ሊሆን ይገባል” ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ፣ የኢንቨስትመንት ችግሮችን ሁሉ በመቅረፍ ምርትን  ማሳደግ የመንግሥት ዋነኛ አቅጣጫ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢትዮጵያን ማንሰራራት ከሚያሳዩ ሁነቶች ውስጥ አንዱ መሆኑን ያስታወቁት ደግሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ ናቸው፡፡ እየሠራን ያለነው “ኢትዮጵያ በገፍ አምርታ በብዙ የምትሸጥ፤ ከውጭ ግን በጥቂቱ የምትሸምት ሀገር እንድትሆን ነው” ያሉት አቶ ተመስገን፣ ለዚህም ንቅናቄው ዋና መፍትሔ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የኢንዱስትሪዎችን ችግር እያቃለለ ለምርት ዕድገት ከፍተኛ ሚና መጫወቱን አብነት አድርገው ተናግረዋል፡፡

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here