የኢትዮጵያ የባሕር በር የማስመለስ ጥያቄ እና አግባብነት

0
42

የዓለም ንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ከ12 እስከ 15 በመቶ ይከናወንበታል፤ ከኮንቴይነር ጭነቶች መካከል ደግሞ 30 በመቶ ዓመታዊ የንግድ እንቅስቃሴ የሚስተናገድበት የባሕር ላይ የንግድ መስመር ነው – ቀይ ባሕር:: በእስያ፣ በአፍሪካ እና በአውሮፓ መካከል በቀይ ባሕር ላይ በሚደረግ የንግድ እንቅስቃሴ በዓመት አንድ ትሪሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶች ዝውውርም ይደረግበታል:: ግዝፍ ኢኮኖሚ የሚያንቀሳቅሱ ኀያላን ሀገራት ሳይቀር ቀይ ባሕርን የብሔራዊ ጥቅማቸው አካል እና የሉዓላዊነታቸው መከበር ዋና መናኸሪያ አድርገውታል::

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰው ዘር መገኛ እና የጥቁር ሕዝብ የነጻነት አርማ፣ ከቀይ ባሕር ከ60 ኪሎ ሜት ባነሰ ርቀት የምትገኘው፣ የሕዝብ ቁጥሯም ከ130 ሚሊዮን በላይ የተሻገረው ኢትዮጵያ ያለፉትን 36 ዓመታት ከቀሪው የዓለም ክፍል ጋር በባሕር ላይ ለመገናኘት በር ከተዘጋባቸው 44 ሀገራት ተርታ ተሰልፋለች:: ይህም የወጪ እና ገቢ ንግድ ዋጋ ከፍተኛ እንዲሆን ያደርገዋል:: ዛሬ ላይ ግን ኢትዮጵያን ቀድሞ ወደነበራት ገናናነት ለመመለስ ጥያቄው በመንግሥት ተነስቶ ሕዝባዊ አጀንዳ ከሆነ ውሎ አድሯል::

የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዋ ዘሪቱ አለባቸው ዓለም ውድድር ውስጥ በገባችበት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ከቀሪው የዓለም ክፍል ጋር ተወዳዳሪ ሆና የምትወጣው፣ የንግድ እና የግንኙነት መረቧን የምታሰፋው የባሕር በር ሲኖራት ነው ይላሉ:: በታሪክ የባሕር በር የነበራት ኢትዮጵያ ባልተገባ እና ባልታመነበት መንገድ በሯ እንዲዘጋባት ሆና ከ30 ዓመታት በላይ መሻገሯ ሁሉንም ቁጭት ውስጥ ሊያስገባ ይገባልም ብላዋል::

አሁናዊ ጥያቄ የነበረን ማስመለስ እንጂ የሌላን ሀገር ሉዓላዊነት መጫን አይደለም የሚሉት አስተያየት ሰጪዋ፣ በጉዳዩ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የጋራ አስተሳሰብ ሊኖረው እንደሚገባ ጠይቀዋል:: ምክንያቱም ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት ስትሆን በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርገው እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ነው:: አለፍ ሲልም ሀገሪቱ በምጣኔ ሐብት ከሌላው ሀገር ጋር ተወዳዳሪ እና ወደ ቀደመ ኀያልነቷ እንድትመለስ ያስችላታል:: በመሆኑም መንግሥት ያመነባቸውን የማስመለሻ አማራጮች ሁሉ መቀበል እና መደገፍ ይገባል ብለዋል::

የባሕር በር ጥያቄው ኢትዮጵያን ወደ ቀድሞ ገናናነቷ የሚመልስ ነው ያሉት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ ዘላለም ጌታሁን ናቸው:: የፖለቲካ፣ የብሔር እና የእርስ በእርስ ቁርሾ ደግሞ ታሪካዊ ገናናነቷን ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት የሚያሰናክል እንደሆነ ያምናሉ:: ሁሉም ነገር የሚኖረው ሀገር ሲኖር በመሆኑ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አንድነቱን አጠናክሮ የባሕር በር ጥያቄውን ቀዳሚ አጀንዳ እንዲያደርግ ጠይቀዋል:: አንድነትን ማጠናከር ኢትዮጵያን ለሌላ አሸናፊነት  ማሸጋገር እንደሆነም ተናግረዋል::

የታሪክ ምሁራንም ኢትዮጵያ ያለፉትን ከ30 ዓመታት በላይ ከቀይ ባሕር ቀጣና ብትርቅም የቀደመ ታሪኳ የሚናገረው ግን የዓለም ትልቁ የውኃ ላይ የንግድ መስመር ቀዳሚ ተዋናይ መሆኗን ነው:: የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አደም ካሚል ለአሚኮ በሰጡት አስተያየት የቀይ ባሕር የቀድሞ ስም የሐበሻ ባሕር (ባሕረ ነጃሽ) ይባል እንደ ነበር አስታውሰዋል:: በተጨማሪም በአክሱም ዘመነ መንግሥት የነበሩ የሐበሻ ነገሥታት ቀይ ባሕር ላይ ለሚፈጠር ውዝግብ እና አለመግባባት መፍትሔ ይሰጡ የነበረበትን ጊዜም የኢትዮጵያ ገናናነት ማሳያ አድርገው ያነሳሉ:: እነዚህም ሁለት ምክንያቶች ኢትዮጵያ በዓለም የንግድ መስመር ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ ፈጣሪ እንደነበረች የሚያረጋግጥ ነው::

ቀይ ባሕር ከኢትዮጵያ ስልጣኔ፣ ንግድ፣ ዕድገት እና እምነት ጋር ያለው ቁርኝት ከፍተኛ መሆኑን የታሪክ ተመራማሪው አስገንዝበዋል:: ምሁሩ እንዳብራሩት የአይሁድ እና የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች መሠረታቸውን ኢትዮጵያ ያደረጉት ቀይ ባሕርን መሸጋገሪያቸው አድርገው ነው:: በአዶሊስ ወደብ ላይ ከ100 በላይ መርከቦችን አሠማርታ ምርቶችን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ በስፋት ታስተላልፍም የነበረች ሀገር ናት::

ያለፉትን ከ30 ዓመታት በላይ ግን ከቀጣናው መራቋ የሚያስቆጭ ስለመሆኑ ነው የታሪክ ምሁሩ የገለጹት:: ለምን? በማን? እና እንዴት ራቀች? የሚለውን መረዳት በታሪክ ወደነበራት ባለቤትነት ለመመለስ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል::

ፕሮፌሰር አደም ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር እንድትነጠል የግብጽን ሴራ ትልቅ ትርጉም ይሰጣሉ:: በተለያዩ ዘመናት ግብጽን ያስተዳደሩ መሪዎች የኢትዮጵያን መልማት እና መበልጸግ የማይፈልጉ እንደነበሩ አስታውሰዋል:: ትልልቅ (ሜጋ) ፕሮጀክቶች ሲጀመሩ ለማደናቀፍ ከመሞከር ጀምሮ ሀገሪቱን ለማጥፋት እስከ መዛት የደረሰ ሙከራ ማድረጋቸውን አንስተዋል:: ኢትዮጵያ ጠል የሆኑ እና ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ግንኙነት የሌላቸውን ሀገራት በአጋርነት በመጠቀም ሀገሪቱን ለማዳከም ከመታተር ጀምሮ ባይሳካላቸውም ሁለት ጊዜ ቀጥተኛ ወረራ እንደፈጸሙ አስታውሰዋል::

የግብጽ መሪዎች ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ በእንግሊዛውያን  እንዲገደሉ ማድረግን ጨምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት ሁለንተናዊ መዳከም ውስጥ  እንዲገባ ከጥንት ጀምሮ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር አስታውሰዋል::

የኢትዮጵያን ዕድገት የማይፈልጉት ግብጾች በተለይ ኢትዮጵያ ሕዳሴን ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ባስቀመጠች ማግሥት የሀገሪቱ መሪ ሆነው የመጡት ሙርሲ ኢትዮጵያን ለማዳከም ሰፊ እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን ያስታውሳሉ:: ከኢትዮጵያ ጋር ኩርፊያ ውስጥ የገባችውን ኤርትራ በማስታጠቅ ውጊያ ማስጀመር፣ የአረብ ሊግ አባል የሆነችው ጅቡቲ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን የወደብ አገልግሎት እንድታቆም ማድረግ፣ ለኦጋዴን ነጻ አውጪ ድርጅት የመሣሪያ ድጋፍ በማድረግ ሀገሪቱን በማስጠቃት ኢትዮጵያ በውስጥ ችግር እንድትወጠር ማድረግ ላይ እንደሠሩ ተናግረዋል::

የግብጽ መንግሥት ለኤርትራ ከኢትዮጵያ መገንጠል እና ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር እንድትርቅ በሰፊው መሥራቱን ይናገራሉ:: ለዚህ ደግሞ የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒሥትር  እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት  ዋና ጸሐፊ የነበሩትን ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ (ግብጻዊ) ዋና ተዋናይ አድርገዋቸዋል::

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየመን፣ በጅቡቲ እና አካባቢዎቹ  የባሕር ላይ ውንብድና ለመስፋፋቱ ምክንያቱ የኤርትራ ደካማ አሥተዳደር ነው፤ ቀይ ባሕር በኢትዮጵያ ቁጥጥር  ስር በነበረበት ወቅት ግን ቀጣናው አስተማማኝ ሰላም እንደነበረው አስታውሰዋል::

ኘሮፌሰር አደም ኢትዮጵያ ያለ አግባብ ያጣችውን ቀይ  ባሕር የማስመለስ እንጂ የጦርነት ፍላጎት  እንደሌላት አስገንዝበዋል:: ኤርትራም በሰላማዊ መንገድ ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን እንድትጠቀም በማድረግ የሀገሯን ምጣኔ ሀብት ለማሳደግ ትኩረት እንድተሰጥ ነው ሙያዊ ምረ ሐሳብ የሰጡት::

ኢትዮጵያ ባልተገባ የፖለቲካ ሸፍጥ  እና ዓለም አቀፍ ሕግን ባልተከተለ መልኩ  የባሕር በር ማጣቷን ምሁሩ ገልፀዋል:: ጠንካራ  የዲኘሎማሲ ሥራዎችን ማከናወን፣  ሕዝቡም በታላቁ የዓባይ ግድብ ላይ  ያደረገውን ርብርብ በዚህም ላይ ሊያጠናክር  እንደሚገባ አስገንዝበዋል:: በሃይማኖት፣ በብሔር እና  በዘር አለመከፋፈል፣ በሀገሪቱ በየትኛውም  አካባቢ ያሉ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገዶች በመፍታት አንድነታችንን መመለስ እንደሚገባ ገልጸዋል::

በተመሳሳይ ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት መጠናቀቅ በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና  መንግሥት አጀንዳ የሆነው የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻርም የሚደገፍ እንደሆነ የሕግ ምሁራን አረጋግጠዋል:: በዓለም አቀፍ ሕግ የሦስተኛ ዲግሪ ምሁር እና የአማራ ክልል የፍትሕ እና የሕግ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ደሴ ጥላሁን (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ መሆኑን ያስቀድማሉ:: ኢትዮጵያ በታሪክ ወደነበራት የባሕር በር እንድትመለስ ጥያቄው ላለፉት ከ30 ዓመታት በላይ እንደ አይነኬ እና አደገኛ ሆኖ ሲታይ መቆየቱን ያስከትላሉ::

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በታሪኳ የባሕር በር የነበራት ሀገር መሆኗ፣ በጂኦ ፖለቲካም ከቀይ ባሕር ያልራቀች (ከአሰብ ወደብ ከ60 ኪ.ሜ ባነሰ ርቀት መገኘታችንን ልብ ይሏል) በመሆኗ ጥያቄው በየትኛውም መመዘኛ አግባብነት ያለው ለመሆኑ ማስመስከሪያ አድርገው አንስተዋል:: በየዓመቱ ለወደብ ኪራይ የምታወጣው ወጪ ከፍተኛ መሆኑ እና እየገነባች ላለው ግዙፍ ኢኮኖሚ የሚመጥን ወደብ ማስፈለጉን ተጨማሪ ምክንያት አድርገው አንስተዋል::

የሕዝብ ቁጥር በፍጥነት መጨመር እና የባሕር በር ያጣችበት መንገድ ኢትዮጵያ ያላትን ዓለም አቀፍ ሕግ የጣሰ መሆኑ ሌላው ለጥያቄው ተገቢነት ማረጋገጫ በማድረግ ያነሳሉ:: በያኔው ዘመን ውክልና የሌላቸው አካላት የብሔራዊ ጥቅምን የሚያክል ትልቅ ጉዳይ አሳልፎ የሚሰጡ ስህተቶችን መፈጸማቸውንም ጠቁመዋል:: ይህንንም ስህተት በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት በዓለም አደባባይ ሕግን መሠረት አድርጎ በሰላማዊ መንገድ በመሞገት ለጥያቄው እልባት መስጠት እንደሚቻል ነው ያስታወቁት::

በአጠቃላይ ዓለም አቀፍ ሕጉ ኢትዮጵያ የነበራትን ማስመለስ እና እየገነባችው ያለውን ኢኮኖሚዋን በአግባቡ መሸከም የሚችል ተጨማሪ ወደቦችን መጠቀም እንደምትችል የሚፈቅድ እንደሆነ አስረድተዋል::

ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን ያጣችው ሕጋዊነትን ባልተከተለ አካሄድ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒሥትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል:: ለዚህም አስረጂ ምክንያች አንስተዋል፤ በወቅቱ የነበሩ ተቋማት በጉዳዩ ላይ እጃቸውን አለማስገባታቸውን፣ ካቢኔው አለማወቁን፣ ተወካዮች በጉዳዩ ላይ አለመወያየታቸውን፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ውሳኔ ስለማሳለፉ ማረጋገጫ ሰነድ አለመገኘቱን ያነሷቸው መሠረታዊ ምክያቶች ናቸው::

ኢትዮጵያ በታሪክ ለቀይ ባሕር ቅርብ በነበረችበት ዘመን ከዓለም ኀያላን አንዷ ነበረች ብለዋል:: ከ30 ዓመት በላይ ከቀይ ባሕር የራቀችው ኢትዮጵያ ዳግም ወደ ቀይ ባሕር እንዴት ትቅረብ የሚለው ጥያቄ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሐሳብ ሊሆን እንደሚገባም አንስተዋል:: የኢትዮጵያ መንግሥት ኢትዮጵያን በታሪክ ወደነበራት የባሕር በር ለለመለስ የሚከተለው መንገድ ሰላማዊ አማራጭ መሆኑንም አንስተዋል::

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የህዳር  8  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here