ሀገራችን ኢትዮጵያ ለእንስሳት ሀብት ልማት ተስማሚ የአየር ንብረት እና ሰፊ ብዝኃ ህይወት ያላት ሀገር መሆኗ ይታወቃል። ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብቷ ከአፍሪካ ቀዳሚ ናት። 61 ነጥብ 59 ሚሊዮን የዳልጋ ከብት፣ 32 ነጥብ 85 ሚሊዮን በጎች፣ 36 ነጥብ 80 ፍየሎች፣ 48 ነጥብ 13 ሚሊዮን ዶሮዎች፣ 3 ነጥብ 73 ሚሊዮን ግመሎች፣ 9 ነጥብ 23 አህዮች እና 6 ሚሊዮን 792 ሺህ 719 የንብ ቀፎዎች ያሏት ሀገር መሆኗን የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ መረጃ ያመላክታል።
ይሁን እንጂ በዘርፉ ምርት እምብዛም ተጠቃሚ አይደለችም። ካላት የእንስሳት ሀብት አንፃር የአርሶ እና የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነትም ሆነ ሀገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ዝቅተኛ እንደሆነ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ መረጃ አክሏል። ለዚህም ከሚጠቀሱት ዋነኛ ምክንያቶች መካከል የሀገር በቀል ዝርያዎች የሚሰጡት ምርት ዝቅተኛ መሆን እና በቂ የተሻሻሉ ዝርያዎች አለመኖር፣ በጥራትም ሆነ በብዛት የእንስሳት መኖ አለመዘጋጀት፣ የእንስሳት ጤና አገልግሎት ሽፋን በሚጠበቀው ደረጃ አለማደግ፣ ዘመናዊ እና ገበያ ተኮር የእንስሳት እርባታ አለመስፋፋት እንዲሁም የእንስስሳት ምርት እና ተዋፅኦ የማቀነባበር እና እሴት የመጨመር ክህሎት እና ዕውቀት ዝቅተኛ መሆን ተጠቃሽ ናቸው።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ካሏት ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት አኳያ ማግኘት የነበረባትን ጥቅም ማግኘት እንድትችል የእንስሳት ዝርያዎችን በማሻሻል የእንስሳት ምርታማነትን ማሳደግ ይጠበቅባታል። አሁን ላይ መንግሥት የእንስሳት ሀብትን ከሌሎች የውጭ ንግድ መስኮች ጋር ተወዳዳሪ ለማድረግ በትኩረት እየሠራ ነው ተብሏል። ከሥራዎቹ መካከልም የእንስሳት ዝርያን ማሻሻል አንዱ ነው።
የአማራ ክልል ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት ባለ ጸጋ ነው። ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ከሚያበረክታቸው የግብርና ውጤቶች መካከልም አንዱ የእንስሳት ምርት ነው።
የዘርፉን ጥቅም ለማሳደግ ታዲያ ዝርያ ማሻሻል ላይ አተኩሮ መሥራት ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ባለሙያዎች ምክረ ሐሳባቸውን ያቀርባሉ። ለአብነት የወተት ምርትን ብናነሳ የአካባቢ ዝርያ ላሞች በአንድ ቀን በአማካኝ የሚሰጡት ወተት አንድ ነጥብ ሰባት ሊትር ሲሆን የውጭ ዝርያዎች ደግሞ ከ30 እስከ 40 ሊትር ይሰጣሉ። እነዚህ ሁለት ዝርያዎች ሲዳቀሉ ደግሞ በአማካኝ ከ10 እስከ 12 ሊትር ወተት በአንድ ቀን መስጠት እንደሚችሉ ነው ባለሙያዎች የሚያስረዱት። ከዚህ በተጨማሪም አርቢዎች ጥጃ በማስወለድ በፍጥነት አድገው የተሻለ የገቢ ምንጭ ያስገኛሉ።
ዝርያ ማሻሻል ሲባል ቁጥራቸው አነስተኛ በሆኑ እንስሳት ከፍተኛ ምርት ማግኘት ማለት ነው። በመሆኑም ያለን የእንስሳት ሀብት የቁጥር ብዛት ብቻ ሳይሆን ጥራት እና ምርታማነት ላይ ሊሠራ ይገባል።
በአማራ ክልል ከ1982 ዓ.ም ጀምሮ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን የክልሉ እንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ጽ/ቤት የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ባለሙያው አቶ አሕመድ አልቃድር ለበኩር ጋዜጣ ተናግረዋል። ሥራውም እየተሻሻለ እና እያደገ መጥቷል ብለዋል። እንደ ባለሙያው ማብራሪያ አሁን ላይ በክልሉ ካለው የዳልጋ ከብት ውስጥ ከሦስት እስከ አራት በመቶው ዝርያውን ማሻሻል ተችሏል። ቁጥሩም ከ800 ሺህ በላይ ደርሷል።
ይህን ተግባር አጠናክሮ ለማስቀጠል ግን እንቅፋት ገጥሟል ይላሉ አቶ አሕመድ። ለዝርያ ማሻሻል ሥራው መሠረት የሆነው የፈሳሽ ናይትሮጅን ማምረቻ ማሽን ማርጀት እና ብልሽት አንዱ ፈታኝ ሁኔታ ነው። ሆኖም በቂ ምርት አምርቶ ወደ ወረዳዎች ለማሠራጨት እንቅፋት እየሆነ መምጣቱን ገልፀዋል። ችግሩን ለመፍታት ጽ/ቤቱ እየሠራ ሲሆን የፈሳሽ ናይትሮጂን ማሽን በባሕር ዳር እና በደሴ በአዲስ ለመትከል አቅዶ እየሠራ መሆኑን አመላክተዋል።
የመብራት መቆራረጥ የፈሳሽ ናይትሮጅን ሥራውን እያስተጓጎለ ያለ ሌላው ችግር መሆኑን ባለሙያው አንስተዋል። የሚመረተውንም ቢሆን በተገቢው መንገድ ለማጓጓዝ በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት እና የበጀት እጥረት እንቅፋት ሆኗል።
ሕገ ወጥ የክልስ እንስት ጥጆች እና ላሞች ንግድ፣ እየተከሰተ ያለው ድርቅ እና ወቅታዊ ችግሩ በእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ላይ አሉታዊ ተፅዕኖው እያሳደረ መሆኑን አንስተዋል። በዚህም ምክንያት መዳቀል ያለባቸው ሳይዳቀሉ ይቀራሉ፣ የመኖ እጥረት ይከሰታል፣ መመረት ያለበት የወተት ምርት ሳይመረት ይቀራል፣ አለፍ ሲልም የእንስሳቱ ህይወት ያልፋል።
አቶ አሕመድ ችግሮቹ በሚከሰቱበት ወቅት እንስሳቱን ወደ ተሻሉ አካባቢዎች በማዛወር መታደግ ይገባል ብለዋል። አጋር አካላት ሕገ ወጥ የክልስ እንስሳትን ንግድ በመከላከል የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱም ጠይቀዋል። በተመሳሳይ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ለማቅረብ መታቀዱን ያነሱት ባለሙያው የእንስሳት አዳቃይ ስልጠናም በፊደራል ደረጃ እንዲሰጥ ፈቃድ ተገኝቷል ብለዋል።
በአማራ ክልል ያለውን የእንስሳት ዝርያ በማሻሻል ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ (ዘርፉን ለማዘመን) አስፈላጊ ቴክኖሎጂዎች መሟላት ይገባል። አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስገባት በርካታ ቁጥር ያላቸውን ላሞች በአንድ ወቅት በማዳቀል በርካታ ጥጆች እንዲወለዱ የሚያደርግ የሆርሞን አቅርቦት እየተከናወነ ይገኛል።
የእንስሳት ዝርያን የመጠበቅ እና የማስፋፋት ሥራ እየተከናወነ ሲሆን የውጭ ዝርያዎችን ከአካባቢው ዝርያዎች ጋር አዳቅሎ የተሻለ ምርት እንዲሰጡ እየተደረገ ነው። ለእርባታ አገልግሎት የሚውሉ ጊደሮችን እና ላሞችን ወደ ማድለብ ማስገበት አይገባም። በዚህ ጉዳይ ባለሙያዎች ግንዛቤ እንዲፈጥሩ እየተሠራ ነው ብለዋል። መድለብ ያለባቸው እንስሳት በተለያዩ ምክንያት መውለድ የማይችሉ መሆን እንዳለባቸውም አመላክተዋል። እንስሳትን ለእርሻ፣ ለስጋ እና ለወተት ተብሎ በመለየት ማርባት ይገባል ብለዋል።
የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ተግባር የተቀናጀ ሥራን ይጠይቃል። የጤና፣ የመኖ እና የእርባታ (የዝርያ ማሻሻል) ባለሙያዎች ተቀናጅተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል። በየደረጃው ያለው አመራርም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ፈሳሽ ናይትሮጅንን ጨምሮ ለእንስሳት ዝርያ ማሻሻል የሚያገለግሉ ግብዓቶችም በወቅቱ መቅረብ አለባቸው።
የፈሳሽ ናይትሮጅን ማምረቻዎቹ በባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደሴ እና ደብረ ብርሃን የሚገኙ መሆናቸውን ለአሚኮ የተናገሩት የባሕር ዳር ሰው ሠራሽ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ጥሩነህ ሙሴ ናቸው። አንዳንዶቹ አሁን ላይ በእርጅና ምክንያት ከሥራ ውጭ መሆናቸውን ጠቁመዋል። በመጠንም በቂ አይሁን እንጂ ማሽኖቹ ፈሳሽ ናይትሮጅን እያመረቱ ይገኛሉ። በሙሉ አቅማቸው እንዲሠሩ እና ተጠቃሚው በሚፈልገው መልኩ እንዲሆን ልዩ ትኩረት ይሻልም ብለዋል። ዳይሬክተሩ እንዳሉት ነባር ማሽኖችን ከመጠገን ጎን ለጎን አዳዲስ ማሽኖችን ለማስገባት (ከፊደራል መንግሥት ጋር በመቀናጀት) ጥረት እየተደረገ ነው። በቅርቡ አዲስ ማሽን ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የተናገሩት ዳይሬክተሩ ይህም ያለውን ችግር የሚያሻሽል መሆኑን ተስፋ ሰጭ ነው ብለዋል።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም