የህዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም
ቱር ደ ፍራንስ ከታላላቅ ውድድሮች ዢሮ ኢታሊያ እና ቮኤልታ ኤ እስፓኝን መካከል አንዱ ነው:: ይህ የብስክሌት መድረክ እድሜ ጠገብ ሲሆን እ.አ.አ 1903 የስፖርት ጋዜጦችን ለማሻሻጥ ታስቦ መጀመሩን የስፖርቱ የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ:: በሂደትም ሕግ እና ደንብ ወጥቶለት፣ ቅርጽ እየያዘ እና ዙሮች እና የሚሸፍኑት ኪሎ ሜትሮች እየጨመሩ ውድድሩ አሁን ካለበት ደረጃ ላይ ደርሷል::
ቱር ደ ፍራንስ ባጠቃላይ 21 ዙሮች አሉት:: ውድድሩን ለማጠናቀቅም እስከ 24 ቀናት ይፈጃል:: ተወዳዳሪዎቹ በአጠቃላይ በእነዚህ ዙሮች እና ቀናት ሦስት ሺህ 500 ኪሎ ሜትሮችን የሚሸፍኑ ይሆናል:: በመድረኩ የሚፎካከሩት ብስልክሌተኞች አስቸጋሪውን የአየር ጸባይ እና መልከአም ምድር የሚቋቋሙ እንደ አለት ጠንካራ መሆን ይጠበቅባቸዋል:: በየዓመቱ የሚከናወነው ይህ ግዙፍ የብስክሌት መድረክ ለአውሮፓውያን ተወዳዳሪዎቻቸው የተሰጠ እስኪመስል በተደጋጋሚ ነግሠዋል:: በተለይ ፈረንሳያውያን፣ ጣሊያናውያን እና ስፔናውያን በዚህ መድረክ በተደጋጋሚ ስማቸው ተጠርቷል:: ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ጀርመን፣ አሜሪካ እና ሌሎች ሀገራትም በዘርፉ እየተፎካከሩ እንደሆነ የቢቢሲ ስፖርት መረጃ ያመለክታል::
አህጉራችን አፍሪካ ግን ለዚህ ውድድር ሩቅ መሆኗን ጭምር መረጃው ያትታል:: ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጎረቤታችን ኤርትራ በዘርፉ በየመድረኩ የሚያንጸባርቁ ባለተሰጥኦ ብስክሌተኞችን ለዓለም እያስተዋወቀች ትገኛለች:: ብስክሌት መጋለብ ትልቁ የኤርትራውያን መገለጫ ባህል ነው:: ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ቅኝ የገዟቸው ጣሊያኖች ይህን ተግባር እንዳወርሷቸው መረጃዎች አስነብበዋል:: አሁን ላይም በአስመራ ጎዳናዎች ብስክሌት ትልቁ የመጓጓዣ ዘዴ እና አማራጭ እንደሆነ የቢቢሲ ስፖርት መረጃ ይመሰክራል:: ይህ አማራጭ መጓጓዣነትም ቀስ በቀስ ወደ ስፖርትነት ተቀይሮ ድንቅ ብስክሌተኞችን ለማፍራት በቅቷል::
የኤርትራ ብስክሌተኞች ካለፉት ዐስር ዓመታት ወዲህ በዓለም አቀፍ መድረኮች ውጤት እያስመዘገቡ እና ስማቸው እየናኝ መጥቷል:: ኤርትራም በብስክሌት መድረክ ስሟ ተደጋግሞ መጠራት ጀምሯል:: እ.አ.አ በ2015 ኤርትራዊው ዳንኤል ተክለሀይማኖት በግዙፉ የብስክሌት መድረክ ቱር ደ ፍራንስ የተሳተፈ የመጀመሪያው አፍሪካዊ በመሆን ስሙ በታሪክ ሰፍሯል:: የዳንኤል ስኬት ቢኒያምን እና ኬቨንን ለመሳሰሉ ብስክሌተኞችም መንገድ ጠርጓል::
በአስመራ ከተማ ተወልዶ ያደገው ቢኒያም ግርማይ ኃይሉ የቱር ደ ፍራንስን ውድድር በቴሌቭዥን መስኮት እየተከታተለ እንዳደገ ይናገራል:: ቀስ በቀስም ለብስክሌት ስፖርት ያለው ፍቅር እንደ ጨመረ እና ስፖርቱን እንደተቀላቀለ ከቢቢሲ ስፖርት ጋር በነበረው ቃለ ምልልስ ተናግሯል:: በ2012 በፈረንጆች ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ብስከሌት ሻምፒዮና መሳተፍ እንደ ጀመረ የግል የታሪክ ማህደሩ ያሳያል:: በ2019 እ.አ.አ በኢኳቶሪያል ጊኒ በተካሄደው የትሮፒካል አሚሳ ቦንጎ ውድድር ሦስተኛ ደረጃን የዞ በማጠናቀቅ የመጀመሪያ ድሉን አስመዝግቧል፡፡
ትልቅ ጽናት፣ ብርታት እና ጥንካሬ በሚጠይቀው ዘርፍ በ2022 እ.አ.አ የዢሮ ኢታሊያን ውድድር በማሸነፍ የመጀመሪያው አፍሪካዊ መሆን ቻለ:: በ2024ቱ የቱር ደ ፍራንስ ውድድርም ሦስተኛውን፣ ስምንተኛውን እና 12ኛውን ዙር በማሸነፍ አዲስ ክብረ ወሰን አስመዝግቧል:: የ24 ዓመቱ ኤርትራዊ በቱር ደ ፍራንስ ያሸነፈ የመጀመሪያው አፍሪካዊም መሆን ችሏል:: በአጠቃላይ በውድድሩ 387 ነጥቦችን በመሰብሰብ የውድድሩን አረንጓዴ መለያ( Green Jersey ) ያሸነፈ የመጀመሪያው ጥቁር ብስክሌተኛ መሆኑ የሚታወስ ነው:: በመድረኩ ብቸኛው ጥቁር ተወዳዳሪ ሆኖ የቀረበው ኤርትራዊው ብስክሌተኛ፤ ዝነኛው የቱር ደ ፍራንስ ውድድር ለአውሮፓውያን ብቻ እንዳልሆነ አሳይቷል:: የአፍሪካ የብስክሌት ንጉሡ ያስመዘገበው ድንቅ ውጤትም በሀገሩ አዲስ የብስክሌት አቢዮት እንዲቀሰቀስ አድርጓል:: ለወትሮም የብስክሌት ስፖርት ይዘወተር በነበረው የአስመራ ጎዳናዎች ትልቅ መነቃቃትን ፈጥሯል:: ወጣት ብስክሌተኞች ዘርፉን እንዲቀላቀሉ ምክንያት ሆኗል::
ኬቨን ተክለ ማሪያም በአስመራ ከተማ የሚኖር የመጪው ዘመን ድንቅ ታዳጊ ብስክሌተኛ ነው:: የ17 ዓመቱ ኬቨን “ የማይቻል ነገር እንደሌለ ቢኒያም ሁሉንም አድርጎ አሳይቶናል” ሲል ከቢቢሲ ስፖርት ጋር በነበረው ቆይታ ተንግሯል:: “ህልሜ ቢኒያም የሠራውን ገድል መድገም ሳይሆን የተሻለ ሥራ መሥራት ነው” ሲልም ተደምጧል:: ውጤታማ ለመሆንም ጠንክሬ እየሠራሁ ነው ብሏል::
በዓለም አቀፍ ውድድሮች ቢኒያም ያሳካውን የትኛውም አፍሪካዊ ባለማደረጉ ኬቨንን እና ለመሳሰሉ ኤርትራዊ ታዳጊ ብስክሌተኞች ትልቅ መነቃቃትን ፈጥሯል:: ኬቨን ተክለማሪያም ከአንድ ወር በፊት በኬኒያ ኢልዶሬት በተደረገው በአፍሪካ የብስክሌት ሻምፒዮና ሁለት ወርቅ ሜዳሊያ ማሸነፉ አይዘነጋም:: የዚህን ታዳጊ ስኬትም በርካታ ሚዲያዎች በ2018 በፈረንጆች ቢኒያም ግርማይ በሩዋንዳ በተደረገው የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮና ላይ ካስመዘገበው ውጤት ጋር አመሳስለውታል:: ቢኒያም በሩዋንዳ በተደረገው የአፍሪካ የብስክሌት ሻምፒዮና ላይ ሦስት ወርቆችን ማምጣቱን የታሪክ ማህደሩ አስነብቧል::
ብስክሌተኛው ቢኒያም በፈረንጆች 2018 በዢሮ ኢታሊያ ያሳየውን ድንቅ ብቃት ዘንድሮም በቱር ደ ፍራንስ በመድገም አሸናፊ በመሆን የአረንጓዴው መለያ ተሸላሚ ሆኗል:: በ2024 ባስመዘገበው አጠቃላይ ውጤት ደግሞ ለ2024ቱ ለዝነኛው ሽልማት ቬሎ ዲኦር ዕጩ መሆን ችሏል:: በዚህ ሽልማት ዕጩ የሆነ የመጀመሪያው አፍሪካዊም መሆን ችሏል:: የሽልማት ስነ ስርዓቱም በዚህ ወር መጨረሻ እንደሚከናወን አዘጋጆች አሳውቀዋል:: የብስክሌት አሰልጣኙ ዮናስ ዘካሪያስ ቢኒያም በዓለም አቀፍ መድረክ እያሳየ ባለው ድንቅ ብቃት ምክንያት በርካታ አዳዲስ ብስክሌተኞች እየወጡ መሆኑን ተናግሯል::
ሊጠናቀቅ ከሁለት ወራት ያነሰ እድሜ በቀረው የ2024 የውድድር ዘመን ኤርትራ በድንቅ የብስክሌት ስፖርተኞቿ አማካይነት በአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮናን በበላይነት ማጠናቀቋ አይዘነጋም:: ሀገሪቱ በዘርፉ አሁን እየሠራች ባለቸው አስደናቂ ሥራ በቀጣይ አምስት ወይም ስድስት ዓመታት ውስጥ በዓለም ላይ እጅግ ዝናቸው የናኝ ብስክሌተኞችን ልታሳየን እንደምትችል የቢቢሲ ስፖርት መረጃ ያመለክታል::
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የህዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም