የእሳተ ገሞራ ብሔራዊ ፓርክ

0
9

በሩዋንዳ ሰሜናዊ ክልል የመጥፋት አደጋ ያንዣበበባቸው ጐሬላዎች መጠበቂያ ቀጣና ነው:: ፓርኩ በኮንጐ የቬሩንጋ ብሔራዊ ፓርክ እና ከኡጋንዳው ማጋሂንጋ ጎሬላ ብሔራዊ ፓርክን ይዋሰናል::

በብሔራዊ ፓርኩ  አስሪ ሁለት የጐሬላ መንጋዎች ወይም ቡድኖች መገኛ በመሆኑ ጥበቃ የሚደረግለት የጐብኚዎች መዳረሻ ሆኗል::

የብሔራዊ ፓርኩ ስፋት 160 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ተለክቷል:: በፓርኩ ቀጣና የካሪሲምቢ፣ ቢሶክ እና ሙሃቡራ የተሰኙ ተራራዎች ይገኛሉ:: በተራራዎቹ ላይ ጐብኚዎች ወጥተው ዙሪያውን መቃኘት ስለሚያስችላቸው በአብዛኞቹ ተመራጭ  ቀጣና ነው::

የሩዋንዳው የእሳተ ገሞራ ብሔራዊ ፓርክ ጐሬላዎችን ለመጐብኘት ከሌሎቹ አዋሳኞች ጐብኚዎችን የበለጠ መሳብ ችሏል:: ለዚህም ከኪጋሊ አውሮኘላን ማረፊያ እስከ ፓርኩ የሦስት  ሰዓት የተሽከርካሪ ጉዞ በኋላ መደረሱ እና የተጠናከረ ጥበቃ መደረጉ ነው በምክንያትነት የተጠቀሰው::

በ1990ዎቹ በአገሪቱ የነበረው የርስ በርስ ጦርነት እና አደን በቱሪዝም እንቅስቃሴው ላይ አጥልቶበት ቆይቷል:: ሆኖም ከ2005 እ.አ.አ ወዲህ ለሚወለዱ የጐሬላ ግልገሎች ስም የማውጣት ስነስርዓት እንደ ታላቅ በዓል  የማስተዋወቅ ስራ በመስራቱ ዘርፉ መነቃቃቱን ድረገፆች አስነብበዋል::

በፖርኩ ከጐሬላዎች ባሻገር ባለ ወርቃማ ቀለም ጦጣዎች፣ ነጠብጣባማ ወይም ዥንጉርጉር ጅብ ከዓዕዋፍም 178 ዝርያዎች እንደሚገኙ ተመዝግቧል::

በፓርኩ ጐብኚዎች ቀደም ብሎ ኘሮግራም አስይዘው በቁጥር የተወሰኑቱ  ብቻ  የጐሬላ መንጋዎችን ቀርበው እንዲመለከቱ እንደሚያደርግ ወይም ፈቃድ እንደሚሰጥ በወጣው ደንብ አስተዋውቋል- የፓርኩ አስተዳደር:: ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ቮልካኖሱ ናሽናልፓርክ፣ ቮልካኖስ ናሽናል ፓርክ ሩዋንዳ እና ቪዚት ሩዋንዳ ድረገፆችን ተጠቅመናል::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here