የእሳት ስጋት በሰሜን ዋልታ

0
37

በሰሜን ዋልታ (አርክቲክ) የዓየር ንብረት ለውጥ ባስከተለው የሙቀት መጨመር የዓፈር ርጥበት ተመናምኖ ቁጥቋጦዎችን ማቀጣጠሉ ቀጣናውን ለሰደድ እሳት ወደ ተመቻቸ የቃጠሎ ዘመን መሸጋገሩን እንደሚያመላክት ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ አስነብቧል::

የአላስካ ዩኒቨርሲቲ በመረጃ ምንጭነት እንዳስነበበው ከአምስት ሀገራት የተውጣጡ ተመራማሪዎችን ያካተተ ቡድን በርካታ ሳይንሳዊ ስልቶችን አጣምሮ  ናሙናዎችን በቁፋሮ መሰብሰብ ችሏል:: በውጤቱም በቅርብ ዓመታት የእሳት ቃጠሎ መከሰት እና መስፋፋት ከሙቀት መጨመር ጋር መያያዙን ነው ያረጋገጠው::

በቀጣናው ግማሽ ሜትር ጥልቀት ከወንዞች እና ኃይቆች ስር ከሚገኝ መሬት ንብብር ናሙናዎችን በመውሰድ ቅሪቶችን አጥንቷል፣ ሳይንሳዊ ትንተናንም ተግባራዊ አድርጓል- የጥናት እና ምርምር ቡድኑ:: በዚህም የቅሪቶቹ ንብብር መቼ እና እንዴት እንደተፈጠረ የቆየበትን ጊዜ መነሻ አድርገው ለድምዳሜያቸው በማስረጃነት ተገልግለውበታል- ተመራማሪዎቹ::

በጥናት እና ምርምሩ ውጤትም ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በቀጣናው  የሰደድ እሳት ከፍተኛ ጭማሪ እያሳየ መምጣቱን አረጋግጠዋል:: ከ1950ዎቹ ጀምሮም እስከ 2000 የዓየር ንብረት ባስከተለው የሙቀት መጨመር ቃጠሎው  መባባሱን ነው መገንዘብ የቻሉት::

ከተሰበሰበው ናሙና በ2015 እ.አ.አ አፈሩ እየደረቀ ሲሄድ የሰደድ እሳት መከሰት እየጨመረ መከሰቻ ቀጣናውም እየተሰፋፋ መምጣቱንም ነው ያረጋገጡት::  በሳተላይት የተሰበሰበው መረጃ ከ1960ዎቹ፣ 1990ዎቹ እንዲሁም ከ2000 እስከ 2010ቹ የሰደድ እሳት በክልሉ በተደጋጋሚ መስተዋሉን አመላክቷል::

በመጨረሻም በመስክ እና በሳተላይት የተሰበሰበው መረጃ ትንተና ውጤት ተመራማሪዎች ቡድን ስራአስኪያጅ ራንዲ ፉልዌበር የሰደድ እሳት የበለጠ ተጠናክሮ ሊከሰት እንደሚችል ማረጋገጣቸውን  ነው በማደማደሚያነት ያስገነዘቡት::

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የጥር 18  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here