ኢራን ለመጀመሪያ ጊዜ በእስራኤል ግዛት ላይ ጥቃት ፈፅማለች። ባለፈው ቅዳሜ ምሽት እኩለ ሌሊት ላይ እስራኤል በአየር ድብደባ ማስጠንቀቂያ ተናውጣለች። ነዋሪዎቹ መጠለያ እንዲፈልጉ ሲታዘዝ እና የአየር መከላከያ ሲንቀሳቀስ ፍንዳታ ተሰማ። በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ በርካታ ቦታዎች ከኢራን በተላኩ ድሮኖች እና ሚሳኤሎች የሌሊቱ ሰማይ አብርቷል፤ ይሁንና እስራኤል ክልል ከመድረሳቸው በፊት ብዙ ድሮኖች እና ሚሳኤሎች በእስራኤል የመከላከያ ጥይት ተመትተው ወድቀው ነበር። የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ኢራን እስራኤልን ለማጥቃት የላከቻቸው ሦስት መቶ ሚሳኤሎች እና ድሮኖች 99 በመቶ ያህሉ የእስራኤልን መሬት ሳይረግጡ ነው አየር ላይ የጋዩት::
ኢራን በግዛቷ ሆና በእስራኤል ላይ ያደረሰችው የአየር ጥቃት በተቃናቃኞቹ የቀጣናው ኃይሎች መካከል ያለው ግጭት መባባሱን አመላካች እንደሆነ ነው እየተገለጸ ያለው::
እስራኤልን ለማጥቃት ከተላኩት መካከል ቢያንስ 110 የባላስቲክ ሚሳኤሎች ይገኙበታል። ከእነዚህ ውስጥ በጣም ጥቂቶቹ ወደ እስራኤል እንደደረሱ የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ የሆኑት ሪር አድም ዳንኤል አጋር በቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል። ይሁንና ቢቢሲ እነዚህን አኃዞች በራሱ እንዳላረጋገጠ ነው የዘገበው::
ባለፈው ቅዳሜ ምሽት የኢራን አብዮታዊ ዘብ ጠባቂዎች ኮርፕስ አይ አር ጂ ሲ (IRGC) እንደገለጸው የባላስቲክ ሚሳኤሎች የተተኮሱት በዝግታ ከሚንቀሳቀሱት አውሮፕላኖች ከአንድ ሰዓት ገደማ በኋላ ሲሆን ይህም እስራኤልን በተመሳሳይ ጊዜ ለመምታት ነበር።
የአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስቴር ከኢራን፣ ከኢራቅ፣ ከሶሪያ እና ከየመን የተወረወሩ በደርዘን የሚቆጠሩ ሚሳኤሎችን እና አውሮፕላኖችን እንደያዙ ተናግሯል። በሊባኖስ የሚገኘው የኢራን ድጋፍ ያለው የሄዝቦላ ቡድን እስራኤል ከሶሪያ በተቆጣጠረችው በጎላን ኮረብታዎች በሚገኝ የእስራኤል ወታደራዊ ሰፈር ሁለት ሮኬቶችን እንደተኮሰ ገልጿል።
ዘጠኝ ሀገራት ተሳትፈውበታል በሚባለው የኢራን ሰሞነኛ ጥቃት ከኢራን፣ ከኢራቅ፣ ከሶሪያ እና ከየመን ሚሳኤሎች ተተኩሰዋል። እስራኤል፣ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ዮርዳኖስ ደግሞ ጥቃቱን በማክሸፍ ተሳትፈዋል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይሎች እንደሚሉት የኢራን ጥቃት 170 የበረራ፣ 30 የክሩዝ እና 120 የባላስቲክ ሚሳኤሎችን ያካተተ ነበር። ከነዚህ ውስጥ 99 በመቶ የሚሆኑትን በአየር መከላከያ ተከላክለዋለች።
ኒው ዮርክ ታይምስ በበኩሉ እንደገለጸው ኢራን እና እስራኤል ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ድብቅ የጥቃት ታሪክ አላቸው:: የአካባቢው ተቀናቃኞች በቅርቡ በሶሪያ በኢራናውያን ወታደራዊ አዛዦች የተገደሉበትን ጥቃት ጨምሮ ለበርካታ ዐሥርተ ዓመታት አንዳቸው በሌላኛው ላይ እጅ ሲቀሳሰሩ ቆይተዋል።
ቀደም ሲል እስራኤል እና ኢራን ኃላፊነትን ባይወስዱም ለዓመታት በሌላ ጦርነት ውስጥ በስውር ይካፈሉ ነበር። በየብስ፣ በባሕር፣ በአየር እና በበየነ-መረብ አማካኝነት እርስ በእርስ ጥቃት ሲያደርሱ ቆይተዋል:: እነዚህ ጥቃቶች እ.አ.አ. ባለፈው ጥቅምት ወር 2024 ሐማስ በአቅራቢያው በሚገኙ የእስራኤል ማኅበረሰቦች ላይ በሰነዘረው ጥቃት እና እስራኤል በአጸፋው በፍልስጤም ግዛት በጋዛ እያካሄደች በምትገኘው ጦርነት በእጅጉ ተባብሷል።
እስራኤል በ1948 ላይ ከተመሠረተች በኋላ ከግብፅ በመቀጠል እውቅና በመስጠት ሁለተኛዋ እስላማዊት ሀገር ኢራን ነበረች:: ሁለቱ ሀገራት እ.አ.አ እስከ 1979 ኢራን ውስጥ የእስልምና አብዮት እስኪካሄድ ድረስ ተባባሪዎች ነበሩ። ከዚያ በኋላ ግን ኢራን የእስራኤልን የመኖር መብት እንደማትቀበል አሳወቀች፤ እናም እንድትወገድ ትፈልጋለች። የሀገሪቱ ከፍተኛ መሪ አያቶላ አሊ ካሜኒ ከዚህ ቀደም እስራኤልን “ከስር ነቅለው እንደሚያጠፉ እና “የካንሰር ዕጢ” በማለት መጥራታቸው ይታወሳል።
የፖለቲካ ተንታኞች ኢራን ሰሞኑን በእስራኤል ላይ የፈጸመችው የቦምብ ድብደባ እ.አ.አ. ሚያዝያ 1 ቀን 2024 ላይ በሶሪያ ዋና ከተማ ደማስቆ በሚገኝ የኢራናውያን ቆንስላ ሕንፃ ላይ ለተፈጸመው የአውሮፕላን ጥቃት ምላሽ ነው ይላሉ።
ኢራን ለደረሰባት ጥቃት እስራኤልን ተጠያቂ ታደርጋለች፤ ይህንንም ሉዓላዊነቷን እንደ መጣስ አድርጋ ተመልክታዋለች። እስራኤል ድርጊቱን እንደፈጸመች ሀሳብ ባትስጥም ጥቃቱን እስራኤል እንደፈጸመችው ግን በሰፊው ይታሰባል። ከፍተኛ የኢራን ጦር ጄኔራሎችን ጨምሮ በጥቃቱ 13 ሰዎች እንደሞቱ ይታወቃል::
ቢቢሲ እንደዘገበው ኢራን በኢራቅ፣ በሶሪያ እና በዮርዳኖስ በአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ በሮኬት ጥቃት የሰነዘሩትን በርካታ የሺያ ሚሊሻዎች ትደግፍ ነበር። አሜሪካ በበኩሏ በዮርዳኖስ በሚገኝ አንድ ወታደራዊ የጦር ሰፈር ውስጥ ሦስት ወታደሮቿ ከተገደሉ በኋላ አጸፋውን መልሳለች ።
በየመንም ኢራን የሀገሪቱን ሕዝብ በብዛት ለሚቆጣጠረው የሀውቲ ታጣቂ ቡድን ድጋፍ ታደርጋለች። ሀውቲዎች በጋዛ ለሐማስ ድጋፍ ለማሳየት በእስራኤል ላይ ሚሳኤሎችን እና ድሮኖችን ተኩሰዋል። በተጨማሪም በባሕር ዳርቻዋ አቅራቢያ የንግድ መርከቦችን አጥቅተዋል:: አሜሪካ እና እንግሊዝ በምላሹ የሀውቲ ዒላማዎችን መትተዋል።
በበርካታ ግጭቶች መካካል ተሳታፊ የሆነችው ኢራን እ.አ.አ. ጥቅምት 7 ቀን 2024 በእስራኤል ላይ ጥቃት የሰነዘሩትን ሐማስን ጨምሮ ለፍልስጤም የታጠቁ ቡድኖች (ሃማስ) የጦር መሣሪያ እና ሥልጠናም ትሰጣለች።
ቢቢሲ የእስራኤልን እና የኢራንን ወታደራዊ አቅም እንዳነጻጸረው ከሆነ ኢራን በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ከእስራኤል በጣም ትበልጣለች፤ 90 ሚሊዮን የሚጠጋ የሕዝብ ብዛት ያላት ሲሆን ከእስራኤል ዐሥር እጥፍ ገደማ ትበልጣለች:: ነገር ግን ይህ እንደ ታላቅ ወታደራዊ ኃይል አይተረጎምም ይላል ቢቢሲ በዘገባው::
ኢራን በሚሳኤሎች እና በድሮኖች ላይ ከፍተኛ ወጪ አድርጋለች። የራሷ የሆነ ሰፊ የጦር መሣሪያ አላት:: ነገር ግን ዓላማዋን ለሚያስፈጽሙላት ማለትም በየመን ለሚገኙት ሀውቲዎች እና በሊባኖስ ለሄዝቦላ ከፍተኛ መጠን ያለው የጦር መሣሪያ እያቀረበች ነው። የጎደላት ዘመናዊው የአየር መከላከያ መሣሪያዎች እና ተዋጊ አውሮፕላኖች ናቸው ።
በተጨማሪም ሩሲያ ከዩክሬን ጋር በምታደርገው ጦርነት ቴሕራን ለሞስኮ ለሰጠችው ወታደራዊ ድጋፍ ሩሲያ በምላሹ የሚሻሻሉትን ለማሻሻል ከኢራን ጋር ትብብር በማድረግ ላይ ትገኛለች ተብሎ ይታመናል:: ኢራን ጥቃት የሚሰነዝሩባቸው ድሮኖችን አቅርባ በአሁኑ ወቅት ሩሲያ የጦር መሣሪያዎቹን ራሷ ለማምረት እየጣረች እንደሆነ ተዘግቧል።
በአንጻሩ ደግሞ እስራኤል በዓለም ላይ እጅግ የተራቀቁ የአየር ኃይሎች ካሏቸው ሀገሮች አንዷ ነች። በአይ ኤስ አይ ኤስ (ISIS) ወታደራዊ ሚዛን ሪፖርት መሠረት እስራኤል “F-15s፣ F-16s” እና የቅርብ “F-35” ስውር ጄትን ጨምሮ ቢያንስ 14 አውሮፕላኖች አሏት:: በተጨማሪም እስራኤል በጥላቻ በተሞሉ ክልሎች ውስጥ ጥቃት የማካሄድ ልምድ አላት ይላል ቢቢሲ::
እስራኤል የራሷ የኒውክሌር መሣሪያዎች እንዳሏት ቢታሰብም ሆን ተብሎ ግልጽ አልሆነም::
ኢራን ደግሞ የኒውክሌር መሣሪያ እንደሌላት ብትናገርም በሌሎች ሀገራት ዘንድ ግን እንዳላት ትታማለች:: ይሁንና የኒውክሌር መሣሪያ የታጠቀች ሀገር ለመሆን ሲቪል የኒውክሌር ፕሮግራሟን ለመጠቀም ጥረት እያደረገች መሆኑን ትክዳለች።
ኢራን እ.አ.አ. በ2015 ከዓለም ኃያላን መንግሥታት ጋር የተፈፀመውን የኒውክሌር ስምምነት በመጣስ ከሁለት ዓመት በላይ ዩራኒየምን ወደ 60 በመቶ ገደማ በግልጽ ስታበለጽግ ቆይታለች።
እስራኤል ኢራን በእስራኤል ላይ ጥፋት ለማድረስ ቃል የገቡ የውክልና ኃይሎችን እንደምትረዳ ታምናለች:: ሐማስን እና የሊባኖስ የሺያ ጦረኞች ቡድንን ሄዝቦላን በገንዘብ እና በጦር መሣሪያ በማስታጠቅ እንዲሁም የኒውክሌር ቦምብ ለመገንባት እየሞከረች እንደሆነች ታምናለች ሆኖም ኢራን ይህንን ትክዳለች:: በሩሲያ እና በዩክሬን መካል በሚካሄደው ጦርነትም ሩሲያ የኢራንን የጦር መሣሪያዎች መጠቀሟም ተነግሯል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል ከኢራን በኩል ለደረሰባት ጥቃት ምላሽ እንደምትሰጥ ተናግራለች:: ሆኖም አጸፋው ወደ ቀጣናዊ ጦርነት እንዳይስፋፋ በመስጋት ሁለቱም ሀገራት ከአጋሮቻቸው ተማጽኖ እየደረሰባቸው ነው::
አልጀዚራ እንደዘገበው የእስራኤል የጦር ካቢኔ በእስራኤል ላይ ታይቶ የማይታወቅ ቀጥተኛ ጥቃት ከተሰነዘረበት ጊዜ አንስቶ በኢራን ላይ የሚወሰደውን ዲፕሎማሲያዊ ግፊት ለማሟላት በተደጋጋሚ ተሰብስቧል። የእስራኤል ጦር አዛዥ ኸርዚ ሃሌቪ “ወታደራዊ ምላሽ እርግጠኛ ነው” ብለዋል::
የሩሲያዉ ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸው ሁለቱም ወገኖች በመካከለኛው ምሥራቅ ላይ አስከፊ መዘዝ ከሚያስከትል አዲስ ግጭት ከሚቀሰቅስ እርምጃ እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
ፑቲን በኢራን ጥቃት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በሕዝብ ፊት በሰጡት አስተያየት፤ በአሁኑ ወቅት በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው አለመረጋጋት ዋነኛ መንስኤ ቀጣይ የሆነው የእስራኤል እና የሐማስ ግጭት ነው፤ ቭላድሚር ፑቲን ሁሉም ወገኖች ምክንያታዊ የሆነ ገደብ እንደሚያሳዩ እና በመላው ክልል ላይ አደገኛ ውጤት የሚያስከትል አዲስ ግጭት እንዳይፈጠር እንደሚከላከሉ ተስፋቸውን ገልጸዋል። ፑቲን ከሰሞኑ ከኢራኑ ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ራይሲ ጋር በስልክ መወያታቸውንም አልጀዚራ ዘግቧል::
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢራን እና የእስራኤል ወቅታዊ ውጥረት ለዮርዳኖስም መትረፉ እየተነገረ ነው:: ዮርዳኖስ ኢራን ወደ እስራኤል የተኮሰቻቸውን ከ300 በላይ ድሮኖች እና ሚሳኤሎች በማክሸፉ ሂደት ትልቅ ድርሻ እንደነበራት ነው የተነገረው።
ፋርስ የዜና አገልግሎት እንደዘገበው የኢራን ሚሳኤሎች የዮርዳኖስን የአየር ክልል አቋርጠው የሚያልፉ በመሆናቸው ሉዓላዊነቷን ለማስከበር እርምጃውን መውሰዷን ገልጻለች።
“የሕዝባችንን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ማንኛውንም ጥቃት ለመመከት እንሥራለን” ያሉት የሀገሪቱ ንጉሥ አብዱላህ ሁለተኛ እርምጃው እስራኤልን ከጥቃት ለመጠበቅ የተፈጸመ አለመሆኑን ተናግረዋል።
ይሁንና ኢራን በሶሪያ ለተፈጸመባት ጥቃት አጻፋ ነው ያለችውን ጥቃት በመመከት የተሳተፈችውን ዮርዳኖስን “ቀጣይ ዒላማ ትሆናለች” ስትል አስጠንቅቃለች::
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም