የእሷ ቀን

0
107

በ2017 ዓ.ም በሀገሪቱ ለ49ኛ፣ በአማራ ክልል ደግሞ ለ30ኛ ጊዜ “ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል!” በሚል መሪ ሐሳብ ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን /march-8/ እየተከበረ ይገኛል፡፡

ቀኑ በክልሉ በሁሉም አካባቢ የማህፀን ጫፍ በር ካንሰር ቅድመ ምርመራን ጨምሮ በተለያዩ ዝግጀቶች እየተከበረ ነው፡፡ በቦንድ ግዥ፣ ሴቶችን በገቢ ማስገኛ ሥራዎች በማሰማራት፣ የደም ልገሳ በማድረግ፣ የሴቶች የልማት ሕብረትን በማጠናከር፣ በትምህርታቸው ጎበዝ ሴት ተማሪዎችን በመሸለም እና በማበረታታት፣ የሕፃናት ማቆያ የግንባታ ቦታ በመረከብና በመሳሰሉ ተግባራት እየተከበረ እንደሚገኝ ከክልሉ ሴቶች ሕጻናትና ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ የማሕበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

የአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናትና ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ምጥን ብርሃኑ ለአሚኮ እንደገለጹት የዘንድሮ መሪ ቃል  መልዕክት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለመ ነው፡፡ በዓሉ ሴቶች ያሉበትን ሁኔታ በመገምገም ለቀጣይ አንድ ዓመት ተግባራዊ ለውጥ የሚያመጡ ሥራዎችን ለማከናወን ውሳኔ የሚተላለፍበት እና አቅጣጫ የሚቀመጥበት እንደሆነም ነው ያብራሩት።

ምንም እንኳን የሴቶችን ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት  ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ ቢሠራም አሁንም ክፍተቶች እንዳሉ ነው የተናገሩት፡፡  በሴቶች ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ ፈጣን እና ቀጣይነት ያለው ለውጥ ለማምጣት በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባም ወ/ሮ ምጥን  አስገንዝበዋል፡፡

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) በበኩላቸው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን አስመልክተው በሰጡት  ጋዜጣዊ መግለጫ

የቀኑ መከበር የሴቶችን ሁለንተናዊ የትግል እንቅስቃሴ ውጤት ለመዘከር፣ ሰፋፊ ንቅናቄዎችን ለማድረግና ለማህበረሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር እንደሚያስችል ጠቁመዋል፡፡

መንግስት የሴቶችን መብት ለማስጠበቅ፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ብሎም የአመራርና ውሳኔ ሰጪነት ሚናቸውን ለማሳደግ እየወሰደ ባለው ጠንካራ ርምጃ አበረታች ለውጦች መምጣታቸውንም ሚንስትሯ  ገልጸዋል።

 

የሴቶችን አደረጃጀት በማጠናከር ግንባር ቀደሞችን  ከመፍጠር ጎን ለጎን የቁጠባ ባህልን በማሳደግ እና የብድር አገልግሎትን በማመቻቸት በገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ መደረጉንም አብራርተዋል።

ሴቶች በተለያዩ የሥራ መስኮች ላይ ተሳትፏቸውን በማጠናከር በሰላም ግንባታ እና ግጭት አፈታት ላይ ያላቸውን ጉልህ ሚና  አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም ከመሥሪያ ቤቱ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

ቀኑን በመላ ሀገሪቱ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት መደረጉን የገለጹት ሚንሥትሯ በዓሉ እስከ መጋቢት 30 ቀን 2017 ድረስ በተለያዩ ዝግጅቶ እንደሚከበርም ጠቁመዋል።

የሴቶች ቀን (ማርች 8 ) መሠረቱ  ፓለቲካዊ ዓመፅ  ቢሆንም በዓለም ላይ የተንሰራፋውን የተዛባ የሥርዓተ-ፆታ ኀይል ሚዛንን ለማስተካከል በተለያዩ  ጊዜያት እና ቦታ በድጋፍ ሰልፍ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች  በማከናወን በየዓመቱ ይከበራል። በዕለቱ ሴቶች በማኅረበሰቡ የደረሰባቸውን ጭቆና ተቋቁመው  በፖለቲካውና  በምጣኔ  ሀብቱ  ያገኙትን  ትሩፋት በሴቶች ቀን (በማርች 8) ይዘክራሉ፡፡

የሴቶች ቀን(ማርች 8) መከበር የጀመረው እ.አ.አ በየካቲት 1908 በኒውዮርክ ከተማ ነበር፡፡ በወቅቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የልብስ ስፌት ሴት ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ በማድረግ በከተማው ውስጥ በመዘዋወር የሥራ ሁኔታቸው ማሻሻያ እንዲደረግበት በመጠየቅ ለመጀመሪያ ጊዜ  አደባባይ ለተቃውሞ ወጡ፡፡

በካሊፎርኒያ ሳንታ ባርባራ ዩኒቨርሲቲ የሴቶች ጥናት ፕሮፌሰር  ኢሊን ቦሪስ “እንደ ዛሬው ሁሉ እነዚህ ሴቶች ባልተደራጁ የሥራ ቦታዎች ከወንዶች አቻዎቻቸው እኩል እየሠሩ ነግር ግን ዝቅተኛ ደመወዝ የሚከፈላቸው እና ጾታዊ ትንኮሳ ይደርስባቸው ነበር” ሲሉ ለታይም መጽሔት ተናግረዋል።

 

እንደ ቢቢሲ ዘገባ በወቅቱ ከደመወዝ እና ከሥራ ማስተካከያው ባሻገር በዋናነት ደግሞ ሴቶች የመምረጥ መብት እንዲፈቀድላቸው ሲጠይቁ ነበር፡፡ በወቅቱ  በአሜሪካ ሴቶች  መምረጥም ሆነ መመረጥ አይችሉም ነበር፡፡

ተቃውሞው ለአንድ ዓመት የዘለቀ ሲሆን ከዓመት በኋላ የአሜሪካ ሶሻሊስት ፓርቲ ዕለቱን ብሔራዊ የሴቶች ቀን ብሎ ሰይሞታል፡፡ ይህ በሆነ በሁለተኛው ዓመት በዴንማርክ፣ ኮፐንሐገን ከ17 ሀገራት በተውጣጡ አንድ መቶ ሴቶች በታደሙበት ጉባኤ ላይ ክላራ ዚክተን የተባለች ጀርመናዊት የሶሻሊስት አራማጅ ፖለቲከኛ በዓሉ በአሜሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ሁሉ እንዲከበር ሀሳብ አቀረበች፤ ሀሳቡ ተቀባይነት አገኘ፡፡

በአውሮፓዊያኑ በ1908 በዩናይትድ ኪንግደም (እግሊዝ) በዓሉ የሚከበርበት ቀለም ይፋ የተደረገ ሲሆን ሐምራዊ፣  አረንጓዴ እና ነጭ ቀለማት የበዓሉ ቀን ማድመቂያ  ሆነዋል፡፡ ሐምራዊ ቀለም ፍትሕንና ክብርን፣ አረንጓዴ   ልምላሜና ተስፋን እንዲሁም ነጭ  ንጽህናን ይወክላሉ፡፡

እ.አ.አ. ከ1975 ጀምሮ የተባበሩት መንግሥታት ይፋዊ በዓል ከሆነ ጀምሮም በዓለም   በየዓመቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ መሪ ቃሎች ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በሚል  የብዙ ሀገራት   ብሔራዊ በዓል ሆኖ ቀጥሏል።

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የመጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here