በአማራ ክልል የእብድ ውሻ በሽታን ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናውኑ መሆኑን የክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡ በኢንስቲትዩቱ የክልሉ የአንድ ጤና ምልከታ የሙያተኞች ቡድን ሰብሳቢ አቶ ሐብታሙ አለባቸው እንደገለጹት በክልሉ የእብድ ውሻ በሽታን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚያስችል ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ከዘጠኝ ወር በፊት ለክልሉ ምክር ቤት እንዲጸድቅ ቀርቧል፡፡
አቶ ሐብታሙ እንደሚሉት የተሠራው ሥራ በቂ ባይሆንም ከእንስሳት እና አሳ ሀብት ልማት ጽ/ቤት ጋር ባለቤት ያላቸውን ውሾች የመከተብ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ክትባቱ በገጠር እና በከተማ በዘመቻ መልክ እንደሚሰጥ ነው የተናገሩት፡፡ የአንድ ጤና ምልከታ ማስተባበሪያ ምክር ቤት እና የሙያተኞች ቡድን ተቋቁሞም ባለድርሻ አካላትን በተደጋጋሚ በማግኘት በጋራ መሥራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የጋራ ውይይት እየተደረገ ነው ፡፡
ባለቤት የሌላቸው ውሾች ለእብድ ውሻ በሽታ የበለጠ ተጋላጭ ቢሆኑም ባለቤት ያላቸውም ለበሽታው የመጋለጥ እድላቸው ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ነው የተናገሩት፡፡ በበሽታው ላለመያዝ ዋስትና የሚሆነው የውሻው መከተብ ብቻ ነው የሚሉት ባለሙያው ውሻዎችን ለማስወገድ ጥቅም ላይ የሚውለው ኬሚካል ወደ ሀገር እንዳይገባ በመከልከሉ ግን ባለቤት የሌላቸውን ውሾች ለማስወገድ በአሁኑ ጊዜ ምንም አይነት እርምጃ እየተወሰደ አይደለም፡፡ ስለዚህ መፍትሔ የተደረገው ባለቤት የሌላቸው ውሾች እንዳይራቡ ሴት ውሻዎችን ማምከን ሲሆን ይህን አማራጭ ለመጠቀም ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ውይይት መጀመሩን አሳውቀዋል፡፡
አቶ ሀብታሙ ክትባትን በማስመልከት በሰጡን መረጃ እስካሁን ባለው ሁኔታ በመንግሥት የጤና ተቋማት ብቻ የሚገኝ ሲሆን የዕብድ ውሻ በሽታ የድህረ ተጋላጭነት ክትባት በሁለት አይነት መንገድ እንደሚሰጥ ነው የጠቆሙት፡፡ አንደኛው “የነርቭ ቲሹ” ክትባት ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረትና ምንም አይነት የመድሃኒት እጥረት የለበትም፡፡ ይሁንና የጤና ተቋማት መድኃኒቱ ከማለቁ በፊት ወቅቱን ጠብቀው ባለማምጣታቸው እና ማምጣት ሲፈልጉ ደግሞ የጸጥታ ችግር እና የአውሮፕላን ትኬት መጥፋት አንዳንዴ እጥረት እንዲከሰት ያደርጋል፡፡ ሁለተኛው ክትባት የሕብረ ህዋሳት ክትባት (ሴል ካልቸር) የሚባል እና ከውጭ ሀገር የሚገባ በጥራትም ሆነ በውጤታማነቱ የተሻለው ነው፡፡ ይሁንና የመድኃኒቱ እጥረት እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡
አቶ ሐብታሙ እንዳሉት በአማራ ክልል ከሐምሌ 1/ቀን 2016 ዓ.ም እሰከ ግንቦት 17 ቀን 2017 ዓ.ም ስድስት ሺህ 670 ሰዎች በተጠረጠረ የእብድ ውሻ የተነከሱ ሲሆን 76 ሰዎች የእብድ ውሻ በሽታ ምልክቶቹ ታይቶባቸዋል፡፡ ምልክቱ ከታየባቸው ውስጥ 34ቱ ለሕልፈት ተዳርገዋል፡፡ አሃዛዊው መረጃ እንደሚያመላክተው አሁን ያለው የእብድ ውሻ በሽታ ካለፉት ጊዜያቶች ጋር ሲነጻጸር ጨምሯል፡፡
በመጨረሻም በውሻ የተነከሰ ሰው የተነከሰበትን ቦታ እና አካባቢውን በሳሙና፣ በንጹህ ውኃ እና በፀረ- ተህዋሲያን ኬሚካል ለ15 ደቂቃ ማጠብ እንደሚገባ እና በበሽታው በተጠቃ እንስሳ የተነከሱ ሰዎችን በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም በመውሰድ ሕክምና እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም