የእናቶች ሀሴት

0
266

ወ/ሮ መቅደስ አማረ በኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኀይል ባሕርዳር ዲስትሪክት በጽሕፈት ሙያ ተቀጥራ በማገልገል ላይ ናት:: የአንዲት ልጅ እናት የሆነችው ወ/ሮ መቅደስ ልጇን ለማሳደግና የመንግስት ሥራዋን በተገቢው መንገድ ለማከናወን ለሁለት ዓመታት ፈታኝ ሁኔታ ገጥሟት ነበር::   እነዚያን ጊዜያት ስታስታውስ በመንግሥት የተፈቀደውን የአራት ወር የወሊድ ፈቃድና ከዓመት ረፍቴ አንድ ወር ጨምሬ ልጄ አምስት ወር ሲሞላት ለሞግዚት ሰጥቼ ሥራ ገባሁ:: በወቅቱ አካሌ እንጅ ሙሉ ሀሳቤ ከልጄ ጋር ነበር::

“እንኳንም ዘንቦብሽ…” እንደሚባለው ለዛውም ሞግዚቷን ሦስት ወር እንደቆየች ቤተሰቦቿ ወሰዱብኝ:: በዛ ወቅት የማደርገውን አጣሁ:: ሥራ እንዳልተው ልጄን የማሳደጉ ኀላፊነት የኔ ብቻ ስለነበር ለወተት፣ ለሳሙና… መግዣ የትም አላገኝ:: የነበረኝ አማራጭ አዝሎ መግባት ብቻ ሆነ:: ከስምንት ወሯ ጀምሮ አዝዬ ቢሮ መግባት ጀመርሁ:: በዛ ላይ  አዝያት ስጽፍ ቁሚ፣ ተቀመጭ እያለች ታስቸግረኝ ነበር:: ሲርባት ደግሞ በአብዛኛው ከስምንት ሰዓት በኋላ ወደ ቤት እሄዳለሁ:: በዚህም በሥራዬም ውጤታማ አልነበርሁም:: ሠራተኛ ማስግባት ባስብም ደመወዜ ዝቅተኛ በመሆኑ አንድ ሺህ እና ከዛ በላይ መክፈል ከባድ ሆነብኝ:: በመጨረሻ በተገቢው ሰዓት ስለማልገባ፣በምፈለግ ሠዓትም ስለማልገኝ  ደመወዜ እንዳይሰጠኝ ሁሉ ተጽፎብኝ ነበር::

በዚህ ፈተና ውስጥ እያለሁ ግን መስሪያ ቤታችን የእናቶችን ችግር በመረዳት የልጆች ማቆያ ከፈተልን:: እኔም ማቆያው ከተከፈተ በኋላ ልጄን ያለምንም ሀሳብ የማውልበት ማቆያ አገኘሁ:: ዛሬ ልጄን ከሠራተኛ ጋር ብተዋት እንኳ ባጃጅ ይገጫት ይሆን? እሳት ይበላት ይሆን?… የሚል ስጋት ያድርብኝ ነበር:: በማዋያው ግን ህጻናት ጤንነታታቸው ተጠብቆ በእንክብካቤ ስለሚውሉ ጠዋት አንድ ሰዓት ከ30 አስረክቤ 11 ሰዓት ተረክቤ ወደ ቤቴ እሄዳለሁ:: ልጄን ለማሳደግ ግን ብዙ ተፈትኛለሁ:: አሁን እኔ ሳልሸማቀቅ፣ ተቋሜን ሳልጐዳ የሥራ ሰዓቴን ለሥራ እያዋልሁ ነው በማለት ያሳለፈችውን ፈተና ዛሬ ላይ አምባ እየተናነቃትም፣ እየሳቀችም አጫውታናለች::

እኛም ዲስትሪክቱ እናቶች ተረጋግተው ሥራቸውን እያከናወኑ፣ የነገ ሀገር መሪዎች፣ የኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ የሚሆኑት ሕጻናት ተገቢውን የተመጣጠነ ምግብ በሠዓቱ አግኝተው እንዲያድጉ ለማስቻል አንደኛ ፎቅ ባዘጋጀው የሕጻናት ማቆያ ተገኝተን ነበር:: ወደ ማዕከሉ ለመግባት በመጀመሪያ እግራችን ወይንም እስከነጫማችን የምንሸፍንበት ላስቲክ /ፊስታል/ ለአፍና አፍንጫችን ጭንብል/ማስክ/ አድርገን  ወደ እንግዳ መቀበያው ዘለቀን:: ከዛም እጃችን በሳኒታይዘር አጽድተን በሕፃናቱ ተንከባካቢ ነርስ የሙቀት ልኬታ ተደረገልን::

ከዚህ ሁሉ በኋላ የሞግዚቶች የልብስ መቀየሪያና የጽዳት መጠበቂያ፣ ሻወርና መፀዳጃ ቤት፣ ሙሉ ወለሉ በምንጣፍ የተሸፈነ የሕጻናቱን እይታ የሚስቡና ዕውቀት የሚያስጨብጡ ስዕሎች፣ ፊደላት፣ የተለያዩ መጫዎቻዎች የሚገኙበት የሕጻናቱ ማዋያ፣ ድንገተኛ ህመም ሲሰማቸው የሚታዩበት፣ የኤሌክትሪክ ዘመናዊ ምድጃዎች፣ ፍሪጆች፣ ኩባያዎች…  የምግብ ማብሰያ/ኪችን፣ የልጆች ምግብ መደርደሪያ፣ ከአንድ ዓመት በላይ እና በታች ያሉ ሕጻናት የሚተኙባቸው የተለያዩ ክፍሎችን በቅደም ተከተል ጐበኘን::

በዚህ ቦታ በመልካም እንክብካቤ በማዋያው ያሉ ህጻናት ልጆች እናታቸውን ሲያዩ እምብዛም እንዲይዟቸው አይጓጉም:: እንደታዘብነው ሞግዜቶቻቸው ከእናት ያልተናነሰ እንደሚንከባከቧቸው ነው::

በዲስትሪክቱ የፋይናንስ አገልግሎት ሠራተኛ  ወ/ሮ ውብአንች አቲከም በሕጻናት ማቆያው ልጆቻቸውን ከሚያውሉ እናቶች መካከል ሌላዋ ናት:: የሦስት ልጆች እናት የሆነችው ወ/ሮ ውብአንች እንደምትለው ሁለቱን ልጆቿን ለሠራተኛ ሠጥታ ሥራ ከገባች በኋላ ይወድቁ ይሆን? በሰዓቱ በልተው ይሆን? ሰውነታቸው ሞቆ ይሆን?… እያለች  በሥራ  ገበታዋ ላይ አካሏ እንጅ ሙሉ ሀሳቧ ከቤት ስለሚሆን ውጤታማ ሥራ አትሠራም ነበር::

ዛሬ ልጇን በማቆያ ማዕከል በማዋል የመንግሥትን የሥራ ሰዓት ሳታባክን በሰዓት ገበታ በሰዓት ትወጣለች:: የሁለት ዓመት ልጇ ቁጥር፣ ፊደል… መለየት ጀምራለች፤ ተረት ሲነበብላቸው አዳምጣ የሰማችውን መናገር ችላለች:: በአጠቃላይ ማዋያው ለልጇ እድገትም፣ ለእርሷ ሥራም ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላታል::

“ልጄ 11 ወር ሲሞላው ነው ማዕከሉ ሥራ የጀመረው:: ከእርሷ በፊት ሁለት ልጆች አሉኝ:: በፊት ሥራ እየሄድሁ ተደውሎልኝ ከታክሲ ወርጀ ሁሉ እመለስ ነበር:: ሲታመመብኝ አቀራለሁ:: ይህ ሲሆን የሚረዳ አለቃም አይኖር:: በተደጋጋሚ ልጄ ታሞብኝ ነው ማለትም ከባድ ነበር” ያለችን ደግሞ ሌላዋ የዲስትሪክቱ ሰራተኛ ወ/ሮ ሞሚና ይብሬ ናት::

ወ/ሮዋ አሁን ላይ ልጇን በማቆያው ካስገባች በኋላ እንደድሮው የሚያሳስቡት ነገር የለም:: ጠዋት በሰዓቱ ትገባለች፣ በምሳ ሰዓት ምግቧን ከበላች በኋላም ትርፍ ሥራ ትሠራለች:: ከአለቃ ጋር በሰዓት ጭቅጭቅ ቀርቷል:: እነርሱን የገጠማቸውን እድል ለሌሎች  መንግሥት ሠራተኞች ተመኝታለች::”

በፌዴራል ገቢዎች ሚኒስቴር የባሕርዳር ቅርንጫፍ ባላደረባ ወ/ሮ ማአዛ ማሞ ተቋማቸው የሕጻናት ማቆያ በማዘጋጀቱ የእድሉ ተጠቃሚ ለመሆን በቅታለች:: የመንግሥት ሠራተኛ ሆኖ ልጅ ማሳደግ ለእናቶች ፈተና እንደሆነ የመጀመሪያ ልጇን በሠራተኛ ስታሳድግ ተገንዝባለች::  ያን ጊዜ ዛሬ ስታስታውስ፤  “እናተነት በጣም ከባድ ነው::

በሥራ ቦታዬ አዘውትሬ አልገኝም ነበር፤ ይህ ደግሞ በጣም ያሳቀቅ ነበር:: የሥራ መግቢያ ሰዓት ሲያልፍብኝ መቆጣጠሪያ ደብተሩ ይነሳ ይሆናል በሚልም እጨነቅ ነበር:: አሁን ሁለተኛ ልጀን ስወልድ ማቆያ በመከፈቱ በጠዋት ተነስቼ የሚያስፈልገውን አሟልቼ በሰርቪስ ወደ ሥራየ እገባለሁ:: ዛሬ ቢሮ ተፈልጌ አልጠፋም፤ አልሳቀቀም::

ልጄም በማቆያው በጥሩ ሁኔታ ይያዝልኛል፤ ዛሬ ከቤቴ ትቼው የምመጣ ሀሳብ የለኝም:: በሥራዬም ውጤታማ ነኝ:: በውጤቴም/ውጤት ተኮር/ ከቀደሙ የአምስትና ስድስት ቁጥር ብልጫ አለው” በማለት ነው  ትናንትና ዛሬን በንጽጽር የገለፀችው::

በአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማህበራዊ  ጉዳይ ቢሮ  የሕጻናት መብትና ደኅንነት ማስጠበቅ ዳይሬክተር አቶ አሻግሬ ዘውዴ እንዳሉት ደግሞ በሁሉም ተቋማት የህጻናት ማቆያ ቢዘጋጅ የነገ ሀገር ተረካቢ ሕጻናት ጤንነታቸው ተጠብቆ እንዲያድጉና ሴቶች በሙሉ አቅማቸው በተሠማሩበት ሙያ ሥራ ሳይበድሉ ውጤታማ ይሆናሉ:: ይህም ሴቶች ለሀገርም፣ ለተቋምም የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ ምንም ትክ የለውም ይላሉ:: ይሁንና እስካሁን ባለው ጊዜ በክልሉ ማቆያ ያላቸው ተቋማት ከስምንት አይበልጡም:: በ2015 ዓ.ም ግን አዋጁን በየሁሉም ተቋም ለማስተግበር ጥረት እየተደረገ ነው::

እኛም የህጻናት ማቆያ ባዘጋጁ ተቋማት ከሚሠሩ  ሴት ሠራተኞች ጋር ባደረግነው ቆይታ በፊት የደረሰባቸውን እንግልት እና አሁን ያገኙትን የአእምሮ እርካታ ተገንዝበናል:: በመሆኑም የህጻናት ማቆያ ያላዘጋጁ መሥሪያ ቤቶች አዋጁን ቢተገብሩ የሴት ሠራተኞችን ሙሉ አቅም ከመጠቀም ባለፈ ጤንነቱ የተረጋገጠ ዜጋ በመፍጠር ሀገርን ማሳደግ ነውና “ሴቶችን እናብቃ!”የሚለው አባባል ከቃል አልፎ ይተግበር መልዕክታችን ነው::

(ሙሉ ዓብይ)

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here