“እናት ትኑር ሁሌም ትሂድ አጎንብሳ፣
ሕመም ታክማለች በእጆቿ ደባብሳ!” ይህ የእናትን ሕያው ፍቅር ለመግለጽ የተደረደረ ስንኝ ነው። ማንም ከአብራኳ የወጣ ሁሉ ምትክ የለሽ ይላታል – እናትን። እናት ስለ ልጇ የማትሆነው ስለሌላትም ሁሉም ነገር ናት በሚል ነው የምትሞገሰው። “እናት አልባ ቤት በርሃ ነው” የሚለው የኢትዮጵያዊያን ብሂልም የዚህ ማሳያ ነው።
በምንም የማይለካውን የእናትን ውለታ ለመዘከር ታዲያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በየዓመቱ የእናቶች ቀን ተከብሮ እንዲውል ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል። እ.አ.አ ከ1907 ጀምሮ በየዓመቱ የሚከበር ሲሆን ግንቦት ወር በገባ በሁለተኛው እሁድ ነው ተከብሮ የሚውለው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀው የእናቶች ቀን በየዓመቱ ተከብሮ እንዲውል የተወሰነው እናቶች ለዓለማችን የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ለማስታወስ ነው። “ሁሉም ቀናት የእናቶች ናቸው” ሲል የሚጠቅሰው የድርጅቱ መረጃ በየዓመቱ እንዲከበር መወሰኑ ደግሞ በቀኑ የእናቶችን ውለታ ይበልጥ ለመዘከር እንደሆነ ያስገነዝባል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በእናቶች መካከል ልዩነት ባይኖርም በዓለም አቀፍ ደረጃ የበለጠ ተፅዕኖ ፈጣሪ እናቶች መኖራቸውን በማንሳት ጀግና እናቶች ሲሉ የሚያሞካሿቸው በርካታ ናቸው። እኛም የዘንድሮውን የእናቶች ቀን መነሻ በማድረግ የተወሰኑትን ተፅዕኖ ፈጣሪ እናቶች እናነሳለን።
አበበች ጎበና
ብዙዎች አበበች ጎበናን “የሁሉም እናት፣ የድሆች እናት” ሲሉ ነው የሚጠሯቸው። “አፍሪካዊቷ ማዘር ቴሬዛ”ም ይሏቸዋል – ኢትዮጵያ ያፈራቻቸው በጎ አድራጊዋ እናት ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሕጻናትን ተንከባክበው ለቁም ነገር አብቅተዋል።
የጀግናዋን እናት ክብርት ዶክተር አበበች ጎበና የሕይወት ታሪክ በተመለከተ ሰዋሰው ከተሰኘ የመረጃ ምንጭ ያገኘነው መረጃ እንደሚያስገነዝበው በ1972 ዓ.ም በሀገራችን ተከስቶ በነበረው ድርቅ ምክንያት ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ ሕጻናትን ለመንከባከብ “አበበች ጎበና የሕጻናት ክብካቤ እና ልማት ማሕበር”ን መሠረቱ።
ከሕጻናት እንክብካቤ ተግባራቸው ባለፈም በበርካታ መልካም ማሕበራዊ ተግባሮቻቸው ይታወቃሉ። ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ መስጠታቸውን ሰዋሰው ጠቅሷል።
አበበች ጎበና እንደ እናት ለሌላው ኖረው ያለፉ ጀግና እናት ስለመሆናቸውም የተመሰከረላቸው ናቸው። በመልካም ተግባራቸውም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ተሰጥቷቸዋል።
ዶክተር ካትሪን ሃምሊን
ዶክተር ኤሊኖር ካትሪን ሐምሊን ትውልዳቸው አውስትራሊያ ቢሆንም መልካም ተግባራቸው ግን በኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ ይገኛል። ለሳምንታት ቆይተው ወደ ኢትዮጵያ እንደመጡ የሚነገርላቸው ዶክተር ካትሪን ሃምሊን ከ60 ዓመታት በላይ ኖረዋል። ሃምሊን ፊስቱላ ሆስፒታልን ከኒውዚላንዳዊው ባለቤታቸው ዶክተር ሬጂናልድ ሃምሊን ጋር መሥርተው ከ60 ዓመት በላይ አገልግለዋል።
የጽንስና ማህጸን ባለሙያዋ ዶክተር ካትሪን ሃምሊን በፊስቱላ ችግር የሚሰቃዩ በርካታ ሴቶች ፈውስ አግኝተው ጤናማ ኑሮ እንዲገፉ በማስቻል ባለውለታ ናቸው። በኢትዮጵያ ከ60 ሺህ በላይ በፊስቱላ የተጠቁ ሴቶችን ከሥነ ልቦናዊ እና አካላዊ ቁስለት ማዳን እንደቻሉ ከሃምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል ድረ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ዶክተር ካትሪን ሃምሊን ለሌሎች የኖሩ ጀግና እናት ናቸው። በዚህ መልካም ተግባራቸውም ዓለም ሲዘክራቸው ይኖራል።
ካቲ ሂድብ
የዓለማችን ጀግና እናት በመባል የሚታወቁት ካቲ ሂድብ ወላጅ አልባ ህጻናትን ለመርዳት ባደረጉት ጥረት ይታወሳሉ። ይህች እናት በተለይም በዚምባብዌ፣ ህንድ፣ ቦስኒያ፣ ሜክሲኮ፣ ቦሊቪያ እና ዩጋንዳ ወላጅ የሌላቸውን ህጻናት በማሳደግ የዓለማችን ባለውለታ እንደሆኑ ይነገራል።
ዋሪስ ድሬ
ሶማሊያዊቷ ዋሪስ ድሬ ሌላኛዋ ከዓለማችን ጀግና እናቶች አንደኛዋ ናት። በተለይም በ13 ዓመቷ የህጻንነት ዕድሜዋ የቀረበላትን ጋብቻ በመሸሽ ያሳለፈቻቸው ውጣ ውረዶች ከባድ እንደ ነበሩ በእርሳቸው የተቋቋመው ‘ዴዘርት ፍላወር ፋውንዴሽን’ (desert flower foundation) የተባለው ድርጅት አስነብቧል።
ብዙ አስቸጋሪ የሕይወት ምዕራፎችን በማለፍም ስኬታማ ሞዴል ለመሆን የበቃች ሲሆን በዓለም ላይ ያለዕድሜ ጋብቻን እና የሴት ልጅ ግርዛትን የሚያስቀሩ ሥራዎችን በማከናወን ትታወቃለች።
ሳራህ ብሪድላቭ
የዓለማችን የመጀመሪያዋ በጥረቷ ሚሊየነር የሆነችው ጥቁር ሴት ሳራህ ብሪድላቭ ሌላኛዋ የምድራችን ጀግና እናት ናት።
ይህች እናት የባሪያ ንግድ ሰለባ የነበረች ሲሆን “የወደፊት ሕይወቴ የባሰ አስቀያሚ ሳይሆን ከድህነት መውጣት አለብኝ፣ ለልጆቼም የተሻለ ሁኔታ መፍጠርም አለብኝ” በሚል ወደ ሚሊየነርነት የተሸጋገረች መሆኗ በእናቶች ጉዳይ መረጃዎችን የሚያጋራው ‘ውሜንስ ሂስትሪ ዶት ኦርግ’ (www.womenshistory.org) ላይ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል። ወደ ንግድ ገብታ በጥረቷ ስኬታማ በመባል የብዙ እናቶች አርዓያ መሆኗንም መረጃው አክሏል።
ኢሬና ሴንድለር
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከሁለት ሺህ 500 በላይ አይሁዳዊያንን ከእልቂት የታደጉት ፖላንዳዊቷ ኢሬና ሴንድለር ደግሞ ሌላዋ የዓለማችን ጀግና እናት ናቸው። ‘ዘ ዩናይትድ ስቴትስ ሆሎኮስት ሙዚየም’ (The United States Holocaust Memorial Museum) እንዳስነበበው ኤሬና ሴንድለር በተለይ የአይሁዳያን ባለውለታ ናቸው።
አይሁዳዊያንን ከናዚ እልቂት የታደጉት እኒህ እናት በዚህ መልካም ድርጊታቸው ብዙ መከራን ተቀብለዋል። ከዚህ ባለፈም እንዲገደሉ ተፈርዶባቸው ነበር። ይሁን እንጂ ተዓምር በሚያስብል መንገድ ከሞት ተርፈው በፖላንድ መንግሥት የጀግና ሜዳሊያ ለመሸለም በቅተዋል።
ሜሪ ኩሪ
የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ሜሪ ኩሪ በአደጋ ምክንያት ባሏን ብታጣም ሁለት ልጆቿን ከማሳደግ ጎን ለጎን በኬሚስትሪ ዘርፍ በሠራችው ምርምር የኖቤል ሽልማትን ማግኘት ችላለች።
የእናት ፍቅር በዘመን የማይጠወልግ፣ የማያረጅ፣ የማይደበዝዝ፣ ዘላለም አብሮ የሚኖር ዘላለማዊ የሰውነት ልኬት ነው። መልካም የእናቶች ቀን!::
(ጌትሽ ኃይሌ)
በኲር የግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም