በእንስሳት ሃብቷ በቀዳሚነት የምትጠቀሰው ኢትዮጵያ ተጠቃሚነቷ ግን ዝቅተኛ ነው፤ ኢትዮጵያ ባላት እንስሳት ልክ ተጠቃሚ እንዳትሆን በምክንያትነት ከሚጠቀሱት መካከል ደግሞ የእንስሳት አያያዟ ዘመናዊነትን የተላበሰ አለመሆኑ በዋናነት ይጠቀሳል። አሁን ላይ ታዲያ ለእንስሳት ልማቱ ዘርፍ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው፡፡ በዚህም አርሶ እና አርብቶ አደሩ የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችን እና የጤና አጠባበቃቸው እንዲሻሻል በማድረግ ተጠቃሚነቱን እንዲያሳድግ እየተሠራ ያለው እንደ አብነት የሚታይ ነው።
በኢትዮጵያ በእንስሳት ሃብቱ በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሰው የአማራ ክልል ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ከሚያበረክታቸው የግብርና ውጤቶች መካከል አንዱ የእንስሳት ምርት ነው። ክልሉ ለዳልጋና ለጋማ ከብቶች፣ ለዶሮ፣ ለዓሳ እና ለንብ ሃብት ልማት እጅግ ምቹ የአየር ንብረት አለው። የክልሉ ሕዝብም ከእርሻ ሥራ ጎን ለጎን የእንስሳት እርባታን የሚያስኬድ በመሆኑ ከፍተኛ የቁም እንስሳትን በማርባት ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ ያቀርባል።
ከክልሉ እንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው አማራ ክልል ከ63 ሚሊዮን 669 ሺህ በላይ የእንስሳት ሃብት ባለቤት ነው፤ ይህም ከጠቅላላው የሀገሪቱ የእንስሳት ብዛት አንድ ሦስተኛውን ድርሻ ይይዛል።
ጽ/ቤቱ እንዳስታወቀው ክልሉ ዘርፉን በተሻለ ደረጃ ምርታማ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችን ተደራሽ ማድረግ፣ የመኖ አቅርቦቱን ማሻሻል እና የእንስሳት ጤናን መጠበቅ ደግሞ የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማሻሻል እየተሠሩ ከሚገኙ ተግባራት መካከል ይጠቀሳሉ።
በጽ/ቤቱ የእንስሳት ጤና አገልግሎት ማስፋፊያ ባለሙያው አቶ አሰፋ ረዳኢ ለበኩር እንደተናገሩት በክልሉ በርካታ የእንስሳት ሃብት መኖሩን ጠቅሰው የእንስሳት ሃብቱን ውጤታማ እና ጤናማ ሊያደርጉ የሚችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው። በጤናው ዘርፍ የአገልግሎት ተደራሽነት እንዲሰፋ በማድረግ ተጠቃሚነትን ማሳደግ ደግሞ ዋነኛው ተግባር ነው ብለዋል።
መሻሻል እየታዬ መሆኑን ያነሱት ባለሙያው በቀበሌ ሁለት የእንስሳት ጤና ባለሙያዎች እንዲመደቡ በማድረግ አርሶ አደሮች በቅርበት ሆነው የእንስሳትን ጤና እንዲከታተሉ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። የጤና ባለሙያዎቹ ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር፣ ቀድመው በሽታን በመከላከል እና ለእንስሳቱ ሕክምና በመስጠት እያደረጉት ያለው ሥራ የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ባለሙያው እንዳሉት የእንስሳት ጤና ጥበቃ ሥራ በመንግሥት ብቻ ሳይሆን በግል እንዲሰጥ የተፈቀደበት አሠራር አለ። የግል የእንስሳት ጤና ተቋማትን በማካተት መመሪያ ተዘጋጅቶ በየደረጃው እንዲሠሩ እየተደረገ ነው። ይህም የእንስሳትን ጤናን ለመጠበቅ እና የሕክምና ቁሶችን ለመግዛት የነበረውን ችግር አቃሏል። በክልሉ በአጠቃላይ 759 የእንስሳት ጤና ክሊኒኮች እና 543 የእንስሳት መድኃኒት ቤቶች በድምሩ 1302 የግል የእንስሳት ጤና ተቋማት የእንስሳቱን ጤናን ለመጠበቅ የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ መሆኑንም ባለሙያው አስረድተዋል። አገልግሎቱ በጥራት እንዲከናወንም መንግሥት የበኩሉን ድጋፍ እና ክትትል እያደረገ መሆኑን አክለዋል።
ሌላው ባለሙያው ያነሱት መልካም ጅምር አስጊ የሆኑ የእንስሳት በሽታዎችን በመለየት እና በመከላከል በኩል የተገኘውን አበረታች ለውጥ ነው፤ ለውጤቱ መምጣት ደግሞ በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች አማካኝነት ግንዛቤ በመፍጠር፣ ቅድመ መከላከል ክትባት በመስጠት እና መሠል ተግባራት መከናወናቸው ነው።
ከዚህ በተጨማሪም የማሕበረሰቡን ጤና የሚጎዱ በሽታዎችን በተለይ ከእንስሳት ወደ ሰው በቀላሉ ሊተላለፉ የሚችሉ በሽታዎችን ለመከላከል በቅንጅት እየተሠራ ነው። ለአብነትም የአባ ሰንጋ እና ውሻን ሊያሳብድ የሚችሉ በሽታዎችን ለመከላከል የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውን አንስተዋል፤ በእነዚህ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ላይ የተጀመረው ሥራም ተጠናክሮ ይሠራል ብለዋል።
ባለሙያው አቶ አሰፋ ለእንስሳት ሃብት ተጠቃሚነት መሻሻል ያነሱት ሌላው ተግባር ክትባትን ነው፤ ይህም እንስሳት በበሽታ እንዳይጠቁ የሚያስችል የቅድመ መከላከያ ተመራጭ መንገድ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ እንስሳቱ የሚያድሩበትን እና የሚውሉበትን ቦታ የተሻለ እና ምቹ ማድረግ የሚገባ ተግባር መሆኑን አስገንዝበዋል።
የእንስሳት ጤና ግብዓቶችን ለማድረስ በክልሉ የተፈጠረው ግጭት ፈተና ሆኗል፤ ባለሙያዎች ታዲያ ችግሩን በመቋቋም የሚጠበቅባቸውን ሙያዊ ኃላፊነት እየተወጡ መሆኑን በማንሳት ምስጋና አቅርበዋል።
ባለሙያው አክለውም የእንስሳትን ጤና ለመጠበቅ ጥናት ተጠንቷል፤ በዚህም መሠረት የራሱ የሆነ ተዘዋዋሪ በጀት እንዲመደብለት ተደርጓል። ይህም የመድኃኒት እና የሕክምና ቁሳቁስ ለመግዛት ሚናው ከፍተኛ ነው። ሃብቱን ለተባለለት ዓላማ እንዲውል ደግሞ ጥብቅ ክትትል እና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከተገኙት መልካም ውጤቶች ባሻገር ዘርፉ አሁንም ችግሮች እንዳሉበት ባለሙያው ተናግረዋል፤ የእንስሳት ጤና ተቋማት ቢገነቡም ባለሙያ አለመቅጠር፣ በተለያዩ ምክንያቶች ባለሙያዎች ሙያቸውን ሲለቁ ቶሎ ያለመተካት እና ለእንስሳት ጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ ሥልጠናዎች መቀዛቀዝ እየታዩ ያሉ ክፍተቶች መሆናቸውን ባለሙያው ያነሷቸው ችግሮች ናቸው። በቀጣይ ታዲያ ችግሮቹን መሠረት በማድረግ እንደሚሠራ በማንሳት የሚመለከታቸው ሁሉ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
እንደ ሀገር የእንስሳት ጤናን ለመጠበቅ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወነ ይገኛል። 26ኛው የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት የአፍሪካ አህጉራዊ ጉባኤ “የእንስሳት ጤና ለምግብ እና ስነ-ምግብ ዋስትና መረጋገጥ እና ለሕብረተሰብ ጤና” በሚል መሪ ሐሳብ ከጥር 27-30/2017 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ መከበሩ ደግሞ አንዱ ማሳያ ነው።
በጉባኤው በአፍሪካ የእንስሳት ጤና አገልግሎት፣ ድንበር ዘለል የእንስሳት በሽታዎችን መቆጣጠር እና መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ብሎም ከበሽታ ነፃ የሆነ አህጉር ለመፍጠር የሚረዱ ውይይቶች መደረጋቸውን ከግብርና ሚኒስቴር የማሕበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። በዚህም ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት እና በአህጉር ደረጃ ካሉ ሀገራት ጋር ድንበር ዘለል የእንስሳት በሽታዎችን ለመቆጣጠር እና የገበያ ተደራሽነትን ለማስፋት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተመላክቷል።
በጉባኤው በሌማት ትሩፋቱ እየተሠሩ ያሉ (የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል፣ መኖ፣ የእንስሳት ጤና) እና በሕብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ዙሪያ በስፋት ውይይቶች ተደርገዋል። የእንስሳት ሕክምና አገልግሎት እንዲጠናከር በእንስሳት እና በእንስሳት ተዋጽኦ ንግድ ዘርፍ ያሉ የጤና አጠባበቅ ሕግጋት መከበር ላይ እንደዚህ ያሉ ጉባኤዎች ከፍተኛ ሚና እንደሚኖራቸው የተነሳ ሲሆን ትብብሩም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ተብሏል። የእንስሳትን ጤና መጠበቅ የሕብረተሰቡን የምግብና ስነ-ምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ብሎም ዘርፉን ለማነቃቃት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው በጉባኤው በስፋት ተብራርቷል።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም