ሀገራት ለ2026ቱ የዓለም ዋንጫ የመጨረሻውን የማጣሪያ መርሀግብር አድርገዋል፤ እያደረጉም ነው:: የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን ለ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ትኬት ከቆረጡት መካከል አንዱ ሲሆን ሁሉንም የማጣሪያ ጨዋታ በማሸነፍ ነው ያጠናቀቀው:: የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ቶማስ ቱህል ለሰርቢያ እና አልባኒያ ጨዋታዎች የመረጡት የ25 ተጫዋቾች ስብስብ ሀገሪቱ ለዓመታት ስትጋፈጥ የቆየችውን አንድ ስር የሰደደ ችግር በግልጽ አሳይቷል፤ የባህላዊ አጥቂዎች ወይም “የዘጠኞች ቁጥር አጥቂዎች” እጥረትን።
በቡድኑ ውስጥ ብቸኛው ግልጽ እና ተፈጥሯዊ አጥቂ የ32 ዓመቱ ሀሪ ኬን መሆኑ እንግሊዝ ምን ያህል በአንድ ተጫዋች ላይ እንደምትደገፍ የሚያሳይ አስደንጋጭ ምልክት ነው።
በቀጣዩ የዓለም ዋንጫ እና በተለይም ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት ሀሪ ኬንን የሚተካ ግልጽ አማራጭ አለመኖሩ ለ”ሦስቱ አናብስት” ትልቅ ስጋት እንደሚሆን ከወዲሁ ግልጽ ነው። ሀሪ ኬን በ110 ጨዋታዎች 76 ግቦችን በማስቆጠር የእንግሊዝ የምንግዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ነው። ቡድኑ ውስጥ ሌሎች አጥቂዎች ቢኖሩም የሀሪኬንን ያህል ውጤታማ አጥቂ ግን የለም:: የአስቶንቪላው አጥቂ ኦሊ ዋትኪንስ፣ የቶተንሃሙ አጥቂ ዶሚኒክ ሶላንኬ እና የቼልሲ ተስፈኛ ሊያም ዲላፕ በተደጋጋሚ የጉዳት ሰለባ የሚሆኑ ተጫዋቾች ናቸው:: ቡድኑ ውስጥ እንደ ማርከስ ራሽፎርድ፣ ጃሮድ ቦወን፣ ፊል ፎደን እና አንቶኒ ጎርደን ያሉ ሁለገብ አጥቂዎች መኖራቸውም ይታወቃል:: እነዚህ ተጫዋቾች የዘጠኝ ቁጥር አጥቂዎች ባይሆኑም አስፈላጊ ሆነው ሲገኝ ግን የመጫወት ብቃት እንዳላቸው አያጠያይቅም:: ይሁን እንጂ ይህ ጊዜያዊ ችግሩን ከመሸፈን የዘለለ መፍትሔ እንደማይሆን የቢቢሲ ስፖርት መረጃ አመልክቷል::
ታዲያ የእንግሊዝ ዘጠኝ ቁጥር አጥቂዎች ለምን ደበዘዙ? እና ለምንድነው ሀገሪቱ እንደ ቀድሞው ዘጠኝ ቁጥር አጥቂዎችን ማፍራት ያልቻለችው? የአሁኑን የአጥቂ እጥረት በደንብ ለመገንዘብ እ.አ.አ የ1990ዎቹ ወርቃማ አጥቂዎችን ማስታወስ እንደሚገባ ቢቢሲ ስፖርት ያስነብባል:: የፕሪምየር ሊጉን የመጀመሪያ ዓመታት መለስ ብለን ስናስታውስ እ.አ.አ በ1992/93ቱ የመጀመሪያ የውድድር ዘመን 20 የሚሆኑ የእንግሊዝ አጥቂዎች 10 እና ከዚያ በላይ የሊግ ግቦችን ማስቆጠራቸውን መረጃዎች ያስረዳሉ::
ይህ ቁጥር ከቅርብ ዓመታት ጋር ሲነጻጸር የሰማይ ያህል የራቀ ነው። እ.አ.አ በ1993/94 የውድድር ዘመን አንዲ ኮል ለኒውካስል 34 ግቦችን አስቆጥሯል:: በቀጣዩ ዓመት ደግሞ አለን ሺረር ለብላክበርን ሮቨርስ በተመሳሳይ 34 ግቦችን ከመረብ አገናኝቷል:: እ.አ.አ የ1990ዎቹ የእንግሊዝ እግር ኳስ በድንቅ የዘጠኝ ቁጥር አጥቂዎች የተሞላ ነበር። ከአለን ሺረር እና አንዲ ኮል በተጨማሪ እንደ ሌስ ፈርዲናንድ፣ ኢያን ራይት፣ ቴዲ ሼሪንግሃም፣ ሮቢ ፋውለር፣ ክሪስ ስተን እና ዴቪድ ሂርስት ያሉ ተጫዋቾች በርካታ ግቦችን አስቆጥረዋል:: እ.አ.አ ከ1998ቱ የዓለም ዋንጫ በፊት እንግሊዝ የምትመካባቸው አስደናቂ የዘጠኝ ቁጥር አጥቂዎች እንደነበሯት ቢቢሲ ስፖርት ያመለክታል።
እነዚህ አጥቂዎች የተለያዩ የጨዋታ ዘይቤዎች የነበሯቸው ቢሆንም አንድ የሚያመሳስላቸው ነገርም ነበር፤ ሁሉም በየሳምንቱ ለክለቦቻቸው በቋሚነት ይጫወቱ ነበር። ይህም ልምድ እንዲያገኙ እና ብቃታቸውን እንዲያዳብሩ አስችሏቸዋል። በወቅቱ አብዛኞቹ ቡድኖች በሁለት አጥቂዎች (4-4-2) የአሰላለፍ ስልት ስለሚጠቀሙ እንግሊዛውያን አጥቂዎች የመሰለፍ እድላቸው ሰፊ እንደነበር መረጃው ያትታል። ይህ ወርቃማ ዘመን ታዲያ ከአሁኑ ጋር ሲነጻጸር የእንግሊዝ አጥቂዎች ቁጥር እና ጥራት ምን ያህል እንደቀነሰ በግልጽ ያሳያል።
ባለፈው የውድድር ዘመን በፕሪምየር ሊጉ በእንግሊዝ አጥቂዎች የተቆጠሩት 67 ግቦች ብቻ ሲሆኑ ይህም እ.አ.አ በ2020/21 ከተቆጠረው በግማሽ ያንሳል:: በዚህ የውድድር ዘመን ደግሞ ቁጥሩ ሊቀንስ እንደሚችል ገና ከወዲሁ ቢቢሲ ስፖርት ግምቱን አስቀምጧል:: በዚህ ዓመት እስካሁን እንግሊዛውያን አጥቂዎች ያስቆጠሩት 11 ግቦችን ብቻ ሲሆን በዚህ ከቀጠሉ በውድድር ዘመኑ መጨረሻ የሚያስቆጥሩት 38 ግቦችን ብቻ ይሆናል። ይህም ከ30 ዓመታት በፊት አንዲ ኮል እና አለን ሺረር ብቻቸውን ካስቆጠሩት በትንሽ ግብ ብቻ የሚበልጥ ይሆናል::
በእንግሊዝ በሄራዊ ቡድን ውስጥ የዘጠኝ ቁጥር አጥቂዎች እጥረት በድንገት የተከሰተ ሳይሆን ለረጅም ጊዜ ሲንከባለል የመጣ ችግር ነው:: እንደ ቢቢሲ ስፖርት ተንታኙ ክሪስ ስተን መረጃ አጥቂዎች በፕሪምየር ሊጉ በቂ የመጫወት እድል አለማግኘታቸው ነው። “አሁን ላይ ክለቦች ከየትኛውም የዓለም ክፍል ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ተጫዋቾች ስለሚያመጡ ለእንግሊዛውያን አጥቂዎች የመሰለፍ እድሉ ጠቧል“ ይላል:: ዘንድሮ ከሦስት በላይ የሊግ ጨዋታዎችን በቋሚነት የጀመሩት ዌልቤክ፣ ዋትኪንስ እና ካልቨርት ሌዊን ብቻ መሆናቸው የክሪስ ስተን ሀሳብ ትክክል መሆኑን ያሳያል።
ሌላኛው ቁልፍ ምክንያት የቡድኖች የአጨዋወት ስርዓት መቀየር ነው ይላል የእግር ኳስ ተንታኙ። “በእኔ ዘመን አብዛኞቹ ቡድኖች በሁለት አጥቂዎች ይጫወቱ ነበር” ሲል ክሪስ ስተን ያስረዳል። “አሁን ግን በሁለት አጥቂዎች የሚጫወቱት በጣም ጥቂት ቡድኖች ናቸው። እንደ ማንቸስተር ሲቲ እና አርሰናል ያሉ ታላላቅ ቡድኖች እንኳን በአንድ “ትልቅ ዘጠኝ ቁጥር” ላይ ቢመሰረቱም አጥቂዎቹ ግን እንግሊዛዊ አይደሉም ሲል ይናገራል።
የፕሪሚየር ሊጉ የምንግዜም ኮከብ ግብ አስቆጣሪ የሆነው አለን ሺረር ደግሞ ችግሩ ከታች ከወጣቶች አካዳሚ እንደሚጀምር ያምናል:: “ታዳጊዎች ሲሰለጥኑ በፊት አጥቂነት መጫወት አይፈልጉም” ሲል ለ ዘ ሬስት ኢዝ ፉትቦል ፖድካስት ተናግሯል። አጥቂው ብዙ ጊዜ ኳስ ስለማይነካ ታዳጊዎች የፊት አጥቂነት ሚናን መቀበል እንደማይፈልጉም አለን ሺረር ተናግሯል::
ሺረር እንደሚለው ወጣት ተጫዋቾች ብዙ ጊዜ ኳስን በሚያገኙበት እና ፈጠራቸውን በሚያሳዩበት የክንፍ መስመር ወይም የአማካይ ስፍራ የበለጠ ይማረካሉ። ታዲያ ይህ የአመለካከት ለውጥ ሀገሪቱ ዘጠኝ ቁጥር አጥቂዎችን እንዳታፈራ ትልቅ እንቅፋት ሆኗል ብሎ የቀድሞው የብላክበርን ሮቨርስ ግብ አነፍናፊ አለን ሺረር ያምናል:: የዘመናዊ እግር ኳስ አጥቂዎች ከቀድሞዎቹ የተለዩ ናቸው:: እንደ ቡካዮ ሳካ ያሉ የክንፍ ተጫዋቾች ከቀድሞዎቹ የበለጠ ግቦችን እያስቆጠሩ ነው:: ነገር ግን የፊት መስመሩን ብቻውን መምራት የሚችል፣ አካላዊ ጥንካሬ ያለው እና በተጋጣሚ የግብ ክልል ውስጥ አደጋ የሚፈጥር አጥቂ መኖር የራሱ የሆነ ትልቅ ጠቀሜታ አለው::
በዚህ የውድድር ዘመን በፕሪሚየር ሊጉ እስካሁን የተጫወቱት ስምንት የእንግሊዝ አጥቂዎች ብቻ ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥ ከ26 ዓመት በታች የሆነው ብቸኛው ተጫዋች የ22 ዓመቱ ዲላፕ ነው:: ይህም እንግሊዝ ተተኪ አጥቂዎችን ለማፍራት ምን ያህል እንደተቸገረች ነው:: ከዲላፕ ጀርባም ተስፋ የሚሰጥ አዲስ ትውልድ ያለ አይመስልም:: የእንግሊዝ ከ21 ዓመት በታች ቡድን ባለፈው ክረምት በአውሮፓ ዋንጫ የተሳተፈው ያለሁነኛ አጥቂ እንደነበር አይዘነጋም:: ቡድኑ በቅርቡም ያካተተው አንድ አጥቂ ብቻ ሲሆን እሱም የማንቸስተር ሲቲው ዲቪን ሙባማ ነው፤ ሙባማ እስካሁን በፕሪምየር ሊጉ ግብ አላስቆጠረም:: አሁኑ ላይ በሻምፒዮንሺፑ ክለብ ስቶክ ሲቲ በውሰት እየተጫወተ ይገኛል::
የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን በሌሎች የሜዳ ክፍሎች በሚጫወቱ ባለተሰጥኦዎች የተሞላ ነው:: እንደ ጁድ ቤሊንግሃም፣ ዲክላን ራይስ እና ቡካዮ ሳካ ያሉ ወጣት ኮከቦች ቡድኑን በየትኛውም ውድድር ላይ ተፎካካሪ እንደሚያደርጉት ይታመናል:: እንግሊዝ ለ2026ቱ የዓለም ዋንጫም ቀዳሚ ግምት ከተሰጣቸው ሀገራት መካከል ትጠቀሳለች:: ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ተስፋ በአንድ ተጫዋች ጫንቃ ላይ ያረፈ ይመስላል- ሀሪ ኬን ላይ።
የፊት መስመሩ ጥልቀት ማጣት የቡድኑ ትልቁ ድክመት ሆኗል:: ለዓለም ዋንጫው በሚደረገው ዝግጅት ወቅት ኬን ጉዳት ቢገጥመው ምን ሊፈጠር ይችላል? ማን ነው የእርሱን ቦታ ተክቶ በቋሚነት ግቦችን የሚያስቆጥረው? ኦሊ ዋትኪንስ ከጉዳቱ አገግሞ ጫናውን መቋቋም ይችላል? ወይስ ቱህል ያለ ዘጠኝ ቁጥር አጥቂ ለመጫወት ይገደዳሉ? እነዚህ ጥያቄዎች አንግሊዛውያን መስማት የማይፈልጓቻ ከባድ ጥያቄዎች ናቸው::
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የህዳር 15 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


