የእግር ኳሱ ንጉሥ

0
138

ብዘዎች የእግር ኳስ ንጉሥ እያሉ ይጠሩታል፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ለ13 ዓመታት አገልግሏል፤ በ1954 ዓ.ም ሦስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ ስታነሳ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች ነበር፤ የካፍ የመጀመሪያው ኢንስትራክተርም ነው፤ በአውሮፓ ታላላቅ ክለቦች የእናስፈርምህ ጥያቄም ቀርቦለት ነበር፤ ከተጫዋችነት እስከ አሰልጣኝነት ወርቃማ ጊዜ ያሳለፈው- መንግስቱ ወርቁ።

በቴክኒክ ክህሎቱ የላቀ፣ ፈጣን እና ለተከላካይ አስቸጋሪ፣ ምንም እንኳ የገዘፈ ተክለ ቁመና እና ረጅም ቁመት ባይኖረውም በአየር ላይ ኳስን በሚገባ የሚጠቀም ድንቅ አጥቂ ነበር። ጠንካራ የአሸናፊነት መንፈስን የተላበሰ አስደናቂ አጥቂ ነበርም ይሉታል። የፊት አውራሪው የመንግስቱ ወርቁ ታሪክ ከዚህ ይጀምራል።

መንግስቱ በ1932 ዓ.ም በቀድሞው በጌምድር ጠቅላይ ግዛት ቋራ ወረዳ ነው የተወለደው። ቤተሰቦቹ ያወጡለት ስምም “አሻግራቸው” እንደነበር በአንድ ወቅት ከሊብሮ ጋዜጣ ጋር በነበረው ቃለምልልስ ተናግሯል። አባቱ ፊታውራሪ ወርቁ የፀረ ፋሽስት አርበኛ ስለነበሩ  እናቱን ወይዘሮ እማዋይሽ አብተውን ፍሽስቶች ያስሯቸዋል። ህጻኑ መንግስቱም ከእናቱ መለየት ስለማይችል አብሮ ለእስር መዳረጉን የታሪክ ማህደሩ ያስታውሰናል። ታዲያ በዚህ ወቅት ፋሽስቶች “አንተ መንግስት መሆን ነው የምትፈልገው!?” በማለት መንግስቱ የሚል ስያሜ እንደሰጡት በቃለምልልሱ ያስታውሳል።

አባቱ ፊታውራሪ ወርቁ ስንቄ በጠላት መስዋዕት ከሆነ በኋላ በንጉሥ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ትዕዛዝ ወደ አዲስ አበባ ማቅናቱንም የግል የታሪክ ማህደሩ ያስነብበናል። በ1940 ዓ.ም መድሀኒዓለም የመጀመሪያ ትምህርት ቤት በመግባት ትምህርቱን መከታተል ጀመረ።

መንግሥቱ በቀለም ትምህርቱ ጎበዝ ከሚባሉት ተማሪዎች መካከል አንዱ ነበር። ከትምህርቱ ጎን ለጎን በትምህርት ቤት በሚከናወኑ ስፖርታዊ ውድድሮች ንቁ ተሳታፊ እንደነበር የቀድሞው ኳሰኛ ታሪክ ያስረዳል። እግር ኳስ፣ ቮሊቦል፣ ሩጫ እና ቅርጫት ኳስ በመሳተፍ ሁለገብ ስፖርተኛ የነበረ ቢሆንም የበለጠ ነፍሱ የምትወደው ስፖርት ግን እግር ኳስ እንደነበር መረጃዎች አመልክተዋል።

በወቅቱ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ባልተመዘገበው ጉለሌ ቡድን ተብሎ በሚጠራው ጀማሪ ክለብ አባል ሆኖ ይጫወትም ነበር። ቡድኑ ከፈረሰ በኋላ ግን በ1949 ዓ.ም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድንን መቀላቀሉን ከሰዋሰው ዶት ኮም ያገኝነው መረጃ ያስነብባል። ፈረሰኞቹ ወደ ድሬድዋ አቅንተው ከጥጥ ማህበር ጋር ባደርጉት ጨዋታ አዲሱ የእግር ኳስ ኮከብ የመጀመሪያ ጨዋታውን አከናውኗል። በመርሀግብሩ ተቀይሮ በመግባት የማሸነፊያ ሁለት ግቦችን ከመረብ አገናኝቷል። ከዚህ በኋላ የአንጋፋው ክለብ ደጋፊዎች ደጋግመው የሚሰሙትን የእግር ኳስ ገድል በፈረሰኞቹ ቤት ፈጽሟል።

በወቅቱ ለእግር ኳስ ተጫዋቾች ክፍያ እና ጥቅማ ጥቅም ባለመኖሩ ህይወታቸውን የሚመሩበት ሥራ ግድ ይላቸው ነበር። ታዲያ መንግስቱ በአቪዬሽን ኤሌክትሪክ የሙያ እና ቴክኒክ ምሩቅ በመሆኑ በመብራት ኃይል ተቀጥሮ ይሠራ እንደነበር የታሪክ ማህደሩ ይነግረናል። መብራት ኃይል፣ እየሠራ ለምን ለቅዱስ ጊዮርጊስ ይጫወታል? የሚል ጥያቄም በሥራ ባልደረቦቹ ይነሳበታል። ይህንን ጉዳይ ይበልጥ የሚያባብስ  አጋጣሚ ብዙም ሳይቆይ ድጋሚ ይፈጠራል።

መብራት ኃይል ከቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫውተው ፈረሰኞቹ በመንግስቱ ወርቁ ሀትሪክ ታግዘው አራት ለአንድ ያሸንፋል። “የእኛን ደሞዝ እየበላ እንዴት መብራት ኃይል ላይ ግብ ያስቆጥራል?” የሚል ተጨማሪ ውዝግብ በክለቡ አባላት እና በድርጅቱ ሠራተኞች ተነስቷል።

ቅዱስ ጊዮርጊስን ለቆ ለመብራት ኃይል እንዲጫወትም ከጥሩ ማማለያ ጋር ቢቀርብለትም ለክለቡ ታማኝ በመሆኑ አሻፈረኝ ብሏል። በውሳኔው መጽናቱን የተገነዘቡ የድርጅቱ ኃላፊዎች ሊያገኝ የነበረውን የደረጃ እድገት እና የውጪ ሀገር የትምህርት እድል እንዳይሰጠው ውሳኔ አስተላልፈዋል። በመጨረሻም ሥራውን ለቆ ሙሉ ጊዜውን ክፍያ እና ጥቅማ ጥቅም ለማያገኝበት እግር ኳስ ራሱን አሳልፎ ሰጠ።

የቀድሞው ግብ አነፍናፊ በእግር ኳስ ህይወቱ ከፈረሰኞች መለያ ውጪ የሌላ ክለብ መለያ ሳይለብስ ነው የእግር ኳስ ህይወቱን የቋጨው። በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ለ16 ዓመታት ያህል በመቆየት ከክቡር ይድነቃቸው ተሰማ ቀጥሎ ፈረሰኞችን ያገለገለ ተጫዋችም ነው።  ከ1958 እስከ 1963 ዓ.ም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ዋንጫን፤ በ1965 እና 1966 ዓ.ም ደግሞ የጥሎ ማለፍ ዋንጫን ከፈረሰኞች ጋር አሳክቷል።

የአፍሪካ ዋንጫ በመጣ ቁጥር የአህጉሪቱ ታላቅ የእግር ኳስ መድረክ መስራች የሆነችው ኢትዮጵያ እንዳለፉት ዓመታት በውድድሩ ደብዛዋ ሳይጠፋ ብዙ የሚነገርላት ታሪክ ሠርታለች። በእግር ኳሱ ዓለም ጀግኖችን ፈጥራ በአፍሪካ ዋንጫ ብዙ የተባለላቸውን የእግር ኳስ ኮከቦችን አበርክታለች። ከእነዚህ ጀግኖች መካከል አንዱ መንግስቱ ወርቁ ነው። ከ2ኛው እስከ 7ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ድረስ በአጥቂ መስመር ተሰልፎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አገልግሏል።

መንግስቱ ወርቁ ሲነሳ በ1954 ዓ.ም በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የተደረገው ሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ አብሮ ይወሳል። በውድድሩ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን እንድታነሳ ካደረጉት ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው። እስከ 1998 ዓ.ም በተደረጉት የአፍሪካ ዋንጫዎች አስር ግቦችን በማስቆጠር የአፍሪካ ዋንጫ ኮከብ ግብ አግቢ እንደነበር አይዘነጋም።

መንግስቱ ወርቁ ከወርቃማ የተጫዋችነት ዘመኑ ባሻገር በአሰልጣኝነት ዘመኑ በርካታ ክለቦችን እና ብሔራዊ ቡድኑን ጭምር አሰልጥኗል።

የእግር ኳስ ችሎታና ልምድ ብቻውን ጥሩ አሰልጣኝ እንደማያደርግ የተረዳው መንግስቱ  ከዓለም አቀፉ የእግር ኳስ የበላይ አስተዳዳሪ (ፊፋ) የተለያዩ ስልጠናዎችን በመውስድ ወደ አሰልጣኝነት ሙያው ገብቷል። በ1965 ዓ.ም በአዲስ አበባ፤ በ1968 ዓ.ም በግብጽ አሌክሳንደሪያ፤ በ1969 ዓ.ም በምእራብ ጀርመን የእግር ኳስ ከፍተኛ ስልጠና  በመውሰድ አጠናቋል።

በ1970 ዓ.ም በጀርመን ፤ በ1972 ዓ.ም ፊፋ ኮካኮላ አካዳሚ በኬንያ ያዘጋጀውን የአሰልጣኝነት ስልጠናም ወስዷል። በዚህም በአፍሪካ የመጀመሪያው የካፍ ኢንስትራክተር መሆን ችሏል። መንግስቱ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን ማሰልጠን የጀመረው በ1968 ዓ.ም ኢትዮጵያ ባዘጋጀችው የ10ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ረዳት አሰልጣኝ በመሆን ነበር።

በ13ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ እንድትሳተፍ አድርጓል። ከብሄራዊ ቡደኑ በተጨማሪም ቅዱስ ጊዮርጊስን፤ መብራት ኃይልን፤ ኢትዮጵያ መድንን አሰልጥኗል። እነዚህን ክለቦች ባሰለጠነበት ወቅት ባስመዘገባቸው ውጤቶች  የአዲስ አበባ  ቡድን ምርጥ አሰልጣኝ በመሆን በሥራው  የተዋጣለት አሰልጣኝ መሆኑን አስመስክሯል።

መንግስቱ ወርቁ ከስምንት ቁጥር ጋር የተለየ ቁርኝት አለው። የሚለብሰው መለያ ስምንት ቁጥር እንደነበር ይነገራል፤ የመኪና ታርጋውም መጨረሻ ላይ ስምንት ቁጥር ነበረው፤ ሆቴል ሲያድር የሚተኛውም ስምንት ቁጥር አልጋ ቤት እንደነበር በቃለ ምልልሱ ተናግሯል። ብዙውን ጊዜ የግል ህይወቱ ሳይቀር ከስምንት ቁጥር ጋር የተቆራኘች እንደነበር  መረጃዎች ያሳያሉ። ታዲያ በዚህ ሁሉ ምክንያት በፈረሰኞቹ ቤት ስምንት ቁጥር ሌላኛው የመንግስቱ ወርቁ መጠሪያ ስም ነበር ማለት ይቻላል። ክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስም የቀድሞው የእግር ኳስ ኮከብ ህይወቱ ካለፈ በኋላ ለክብሩ ሲል መለያውን በክብር እንዲቀመጥ አድርጓል።

መንግስቱ በአውሮፓ ክለቦች ተፈልጎ እንደነበር በአንድ ወቅት በሊብሮ ጋዜጣ ተናግሯል። በክቡር ይድነቃቸው ተሰማ አሰልጣኝነት ብሄራዊ ቡድኑ ለወዳጅነት ጨዋታ ወደ ፈረንሳይ ባቀናበት ወቅት መንግስቱ ሜዳ ውስጥ በሳየው ድንቅ ብቃት በአውሮፓ ክለቦች እይታ ውስጥ ይገባል። የግሪኩ ኦሎምፒያኮስ፣ በቱርክ ኤስ ዮዝ እና የፈረንሳይ ክለቦች ጭምር ዐይናቸውን አሳርፈውበት እንደነበር በቃለ ምልልሱ ይናገራል።

ኢትዮጵያዊውን ኮከብ ለማስፈርም ይበልጥ ፍላጎት አሳይቶ የነበረው ግን የሴሪ ኤው ክለብ ኤስሚላን ነበር። ኤስሚላን ሁለት መቶ ሺህ ዶላር ለዝውውሩ በመመደብ ብዙ ርቀት መጓዙን የቀድሞ አጥቂው ተናግሯል። ይሁን እንጂ ኤስሚላን በኢትዮጵያ ላይ ግፍ እና መከራ ያደረሰው የጣሊያን ክለብ መሆኑ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ዝውውሩ ተቀባይነት እንዲያጣ አድርጎታል። የ20ኛው የክፍለ ዘመን የኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ዝውውርም በዚህ መልኩ ከሽፏል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ሲነሳ፤ ስሙ ከኳስ ጋር ሁሌም የሚጠራው መንግስቱ ወርቁ፤ በተወለደ በ70 ዓመቱ በ2003 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። የአፍሪካ ዋንጫ በመጣ ቁጥር ግን ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ እግር ኳስ ባበረከተው የላቀ አስተዋጽኦ ሲታወስ ይኖራል። (ስለሺ ተሾመ)

በኲር የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here