የእግር ኳስ ተጫዋቾች እረፍታቸውን እንዴት ያሳልፉ?

0
55

የኢትዮጵያ የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ የ2017 የውድድር ዓመት ተጠናቋል። በተመሳሳይ የ2017 ዓ.ም የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ እና በየደረጃው ያሉ የሊግ እርከን ውድድሮችም የተጠናቀቁ ሲሆን አሁን ተጫዋቾች እረፍት ላይ ናቸው። በያመቱ የክረምት ወራት ሲቃረብ ብዙ የስፖርት ውድድሮች ተጠናቀው የእረፍት ጊዜ ይሆናል። ይህ የእረፍት ጊዜ ተጫዋቾች ከደረሰባቸው የአጥንት ስብራት፣ ከጡንቻ እና ከጅማት ጉዳቶች የሚያገግሙበት፣ የደከመ ሰውነታቸውን እና አዕምሯቸውን የሚያድሱበት ወቅት መሆኑን የፊፋ መረጃ ያመለክታል።

የእረፍት ወቅት ተጫዋቾች ከውድድር ነፃ የሚሆኑበት፣ ለመዝናናት ካልሆነ በቀር መደበኛ ውድድር ውስጥ የማይገቡበት ወቅት መሆኑን በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በስፖርት ሳይንስ አካዳሚ መምህር፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የስነ ምግብ ባለሙያ እና የመቻል ስፖርት ክለብ የስነ ምግብ አማካሪ  የሆኑት ዳንኤል ክብረት (ዶ.ር) ከአሚኮ በኵር ጋዜጣ ስፖርት ዝግጅት ክፍል ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

የእረፍት ወቅት ተጫዋቾች ዓመቱን ሙሉ ከነበረባቸው ድካም አገግመው ለቅድመ ውድድር የሚዘጋጁበት ሲሆን ከውድድር እና ልምምድ ርቀው የሚቆዩበት ወቅት ነው። ተጫዋቾች በውድድር ወቅት የነበረባቸውን ድካም፣ የፈሳሽ እጥረት (Nutrient) የማስተካከያ መልካም አጋጣሚ ነው። ከድካማቸው ለማገገም አመጋገባቸውን የሚያስተካክሉበት፣ ማሳጅ እና ሳውና ባዝ በመጠቀም ራሳቸውን የሚጠብቁበት ጭምር ነው- የእረፍት ወቅት።

 

ሌላው እና ወሳኙ ነገር ደግሞ ተጫዋቾች ዓመቱን ሙሉ የነበረባቸውን ደካማ ጎን ማለትም የአካል ብቃት የሚያስተካክሉበት መልካም አጋጣሚ ነው። በአጠቃላይ ተጫዋቾች ለቀጣይ ዓመት ራሳቸውን የሚያዘጋጁበት ጭምር ነው። በእረፍት ወቅት ተጫዋቾች አዕምሯቸውን እና አካላቸውን በተገቢው መንገድ ማሳረፍ እንዳለባቸው የስነ ምግብ ባለሙያው ዳንኤል ክብረት(ዶ.ር) ተናግረዋል።

ተጫዋቾች ሙሉ በሙሉ ኃይል ሰጪ (ካርቦሀይድሬት) ምግቦችን ማቆም እንደሌለባቸውም ባለሙያው ይመክራሉ። በውድድር ወቅት ከሚወስዱት መጠን በግማሽ እንዲቀንሱ ግን የስነ ምግብ ባለሙያው ያሳስባሉ። በምትኩም የሚወስዱት የገንቢ ምግቦች  መጠን  መጨመር አለባቸው ነው የተባለው። ከድካም ለማገገም የሚያግዙ ምግቦችን ለምሳሌ ዓሣን፣ ቁንዶ በርበሬ እና እርድን የመሳሰሉ ቅመማቅመሞች ቶሎ ለማገገም አስተዋጽኦ እንዳላቸውም ተጠቅሷል። እንዲሁም ቶሎ ከድካም ለማገገም የሚወስዱትን የፈሳሽ መጠን መጨመር አለባቸው- የባለሙያው አስተያየት ነው። ይህን ለማስተካከልም የግንዛቤ ፈጠራ  ሥራ መሠራት አለበት ነው ያሉት።

 

በእረፍት ወቅት ተጫዋቾች ከስልካቸው ጋር ያላቸውን ቁርኝት በመቀነስ ተገቢውን እንቅልፍ መተኛት ይኖርባቸዋል፤ ይህ ካልሆነ ከድካማቸው በሚገባ እንዳያገግሙ እንቅፋት ይሆናቸዋል ነው የተባለው። በውድድር ወቅት የሚታየው አቋም በእረፍት ወቅት በተገነባ ሰውነት እንደሆነ የስነ ምግብ ባለሙያው ያስረዳሉ። ታዲያ ዓመቱን ሙሉ በወጥ አቋም ለመጫወት የእረፍት ወቅትን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል ባይ ናቸው ዳንኤል (ዶር)። ይህን የድህረ ውድድር ወቅት በአግባቡ ካልተጠቀሙ ግን በውድድር ወቅት ተጫዋቾች ጥሩ አቋም ለማሳየት ይቸገራሉ:: እናም በዚህ የእረፍት ወቅት ተጫዋቾች  አመጋገባቸውን፣  እና ፈሳሽ አወሳሰዳቸውን ማስተካከል እንዳለባቸው የስነ ምግብ ባለሙያው ይመክራሉ።

 

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ  የእግር ኳስ አመጋገብ በሀገራችን ገና ተግባራዊ እየሆነ ያለ ሳይንስ ነው። የእግር ኳስ አመጋገብ የተጫዋቾችን አቅም የሚጨምር እንደሆነ የተናገሩት  ዳንኤል (ዶ.ር) ውጤታማ የሚሆነው ግን አመጋገብ፣ ፈሳሽ አወሳሰድ እና የማገገሚያ ስልቶች ተቀናጅተው በአግባቡ ተግባራዊ ሲደረጉ እንደሆነ ገልጸዋል።  ወቅቱን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የቴክኒክ ክህሎታቸውን ለማዳበር ሊጠቀሙበት ይገባል፤ ከዚህ በተረፈ ግን ተጫዋቾች የእረፍት ጊዜያቸውን ለማገገሚያነት ብቻ እንዲጠቀሙበት ይመከራል ብለዋል- የስነ ምግብ ባለሙያው።

ለእግር ኳስ አመጋገብ ትኩረት ተሰጥቶ ከተሠራ በአሠልጣኞች የሚፈለገውን የልምምድ ጫና ተጫዋቾች እንዲቀበሉ ያስችላል። ይህ ደግሞ ተጫዋቾች በብቃት ረጅም ጊዜ እንዲጫወቱ ያስችላቸዋል፤ በተጫዋችነት ዘመናቸውም መድረስ ከሚገባቸው ቦታ እንዲደርሱ ያግዛቸዋል። እግር ኳስ ባደገባቸው አምስቱ ታላላቅ ሊጎች ይህንን ሳይንስ በሚገባ ተግባራዊ በማድረጋቸው ተጫዋቾቻቸው ያላቸውን አቅም አውጥተው እየተጠቀሙ መሆኑንም ባለሙያው አስረድተዋል ።

 

የወንዶችም ሆነ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ተጫዋቾች ረዥም ጊዜ ውድድር ላይ በመቆየታቸው የተጠራቀመ ድካም እና ጉዳት ሊኖርባቸው  እንደሚችል ይጠበቃል። ታዲያ ከዚህ ድካም እና ጉዳታቸው  የሚያገግሙት የእረፍት ጊዜያቸውን በአግባቡ ሲጠቀሙበት መሆኑን የስነ ምግብ ባለሙያው ዳንኤል ክብረት (ዶር) ይናገራሉ። የእረፍት ወቅቱን በተገቢው መልኩ ከተጠቀሙ አካላቸው ብቻ ሳይሆን አዕምሯቸውም እንደሚታደስ  ጭምር ተናግረዋል- የስነ ምግብ ባለሙያው።

ተጫዋቾች በእረፍት ወቅት የሚሠሩት ልምምድ እንደየአቅማቸው መለያየት ይኖርበታል። ተጫዋቾች የሰውነት ውቅራቸውን፣ የሚጫወቱበትን ቦታ እና በዓመት ውስጥ የሚያደርጓቸውን የጨዋታ ብዛት ከግምት ውስጥ በማስገባት አመጋገባቸውን ማስተካከል አለባቸው ተብሏል። በእረፍት ወቅት ተጫዋቾች ሙሉ በሙሉ ማረፍ እንደሌለባቸውም የስነ ምግብ ባለሙያው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

 

“ከሰባት እስከ ዐስር ቀናት ሙሉ እረፍት ሊያደርጉ ይገባል፤ በሌሎች ቀናት ግን ልምምዶችን መሥራት ይጠበቅባቸዋል” ነው ያሉት ዳንኤል (ዶር)። ለማገገም የሚጠቀሟቸው ምግቦች ሁሉንም ተጫዋቾች ያማከለ ሲሆን ሌሎች ዓይነት አመጋገቦች ግን እንደየተጫዋቾች ይለያያል። ተጫዋቾች ከሙሉ የእረፍት ጊዜያቸው ከተመለሱ በኋላ አካል ብቃት ላይ ትኩረት አድርገው መሥራት እንዳለባቸው ተጠቁሟል። ከዚህ በተጨማሪ የጥንካሬ እና የመተጣጠፍ ሥራዎችን መሥራትም ይጠበቅባቸዋል።

 

በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ስፖርት እረፍት ሲባል ልምምድ ማቆም ብቻ መሆኑን የሚገነዘቡ ጥቂት አይደሉም። ይሁን እንጂ ተጫዋቾች በእረፍት ጊዜያቸው ከእግር ኳስ ጋር የተያያዘ ሥራ መሥራት እንደሌለባቸው የስነ ምግብ ባለሙያው ያስገነዝባሉ። በጅምናዚየም የሚሠሩትን ጨምሮ ከንክኪ ነፃ የሆኑ እና ለጉዳት የማያጋልጡ  ቀለል ያሉ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎችን ግን ማድረግ ይችላሉ ተብሏል። “ማረፍ የሚገባቸውን በትክክል ካለረፉ በውድድር ወቅት በተለይ እግራቸውን በቀላሉ የመጎዳት እድላቸው ሰፊ ነው” ብለዋል።

በሀገራችን በእረፍት ወቅት ተጫዋቾች መደበኛ ባልሆኑ ፉትሳል እና መሰል ውድድሮች ላይ ሲያዝወትሩ ይስተዋላል። ይህ ደግሞ ተጫዋቾችን የበለጠ ለጉዳት የሚያጋልጣቸው በመሆኑ ከእነዚህ ውድድሮች መራቅ ይኖርባቸዋልም ነው የተባለው። ለሰውነታቸው የሚያስፈልጋቸውን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና ሌሎች የጅምናዚየም ሥራዎች መሥራት እንዳለባቸው ግን ዳንኤል ክብረት (ዶር) ይናገራሉ።

 

ለአብነት የሜዳ ቴኒስ ተጫዋቾች በእረፍት ወቅታቸው እንዲያዘወትሩ የሚመከሩት ስፖርት ነው። በእግር ኳስ ስፖርት የተጫዋቾች አመጋገብ ጋር በተገናኘ እንደሀገር ብዙ መሠራት እንዳለበት የሚጠቁሙት የስነ ምግብ ባለሙያው ዳንኤል ክብረት (ዶር) በተጫዋቾች ዘንድ የፕሮፌሽናል አስተሳሰብ ችግር ይስተዋላልም ብለዋል።

በ2018 አዲሱ የወንዶች የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 20 ክለቦች እንደሚሳተፉ አወዳዳሪው አካል አሳውቋል። ታዲያ የክለቦች ቁጥር መጨመር ተጫዋቾች በርካታ ጨዋታዎችን እንዲያደርጉ ያስገድዳቸዋል። ይህ ደግሞ በተጫዋቾች ላይ የጨዋታ መደራረብ እና ጫና ያሳድራል ተብሎ ይጠበቃል። እናም ተጫዋቾች ጉዳት እንዳይገጥማቸው እና ከፍተኛ ድካምን መቋቋም እንዲችሉ ከወዲሁ የእረፍት ጊዜያቸውን በአግባቡ መጠቀም ያሰፈልጋቸዋል በሏል የስነ ምግብ ባለሙያው።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የሐምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here