የእግር ኳስ ተጫዋቾች ዋነኛዉ ችግር

0
127

የአፍሪካ ሀገራትን የሊግ ደረጃ ያወጣው ቲም ፎርም የተባለው ድረገጽ የኢትዮጵያን ፕሪሚየር ሊግ ከደካማዎች ተርታ አስልፎታል። ምንም እንኳ ከፍተኛ መዋለ ንዋይ እየፈሰሰበት ቢሆንም ከአፍሪካ ሀገራት የእግር ኳስ ሊጎች መካከል 26ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ተጫዋቾቹ  በሙያቸው  ብቁ (professional) አለመሆን  ለእግር  ኳሱ  እድገት    አንደኛው መሰናክል ተደርጎም ይወሰዳል። አንድ ተጫዋች በሙያው ብቁ (professional) ስለመሆኑ ከሚገለጽባቸው መገለጫዋች ውስጥ ደግሞ ሜዳ ውስጥ እና ከሜዳ ውጪ የሚያሳየው ባህሪ አንዱ ነው። ይህም በሀገራችን ዋነኛው ችግር ሆኖ በተደጋጋሚ ይነሳል።

በሙያቸው የበቁ (profissional) የእግር ኳስ ተጫዋቾች ሥራቸውን ያከብራሉ፤ ለሙያቸውም ይታመናሉ፤ ለለበሱት መለያም የሚዋደቁ ናቸው። በሜዳ ውስጥም ሆነ ከሜዳ ውጪ ከዓላማቸው ዝንፍ የማይሉ እንደ አለት የጠነከረ ስብዕና ያላቸው እንደ ሆኑ የፊፋ ዶት ኮም (Fifa.com) መረጃ ያመለክታል። ምንም እንኳ በጥናት ላይ የተደገፈ ባይሆንም በሀገራችን በሁሉም የሊግ እርከን የሚጫወቱ ተጫዋቾች ከደረጃ በታች መሆናቸውን በርካታ የዘርፉ ባለሙያዎች ያምናሉ።

 

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ለሙያቸው የተገዙ እና ያደሩ፣ ሜዳ ውስጥም ከሜዳ ውጪም ጥሩ ስነምግባር ያላቸው እና በሙያቸው ብቁ የሆኑ የእግር ኳስ ተጫዋቾች እንዳሉ ሁሉ በተቃራኒው ለሙያቸው ያልታመኑ ስነ ምግባር የጎደላቸው ተጫዋቾች መኖራቸው አያጠያይቅም።

በኢትዮጵያ  በሁሉም የሊግ እርከኖች የሚገኙ ተጫዋቾች ሜዳ ውስጥ እና ከሜዳ ውጪ በሚያሳዩት ያልተገባ ባህሪ ብዙ ጊዜ ስቴዲየሞች ወደ ጦር ሜዳነት ተቀይረው የተመለከትንበት አጋጣሚ ጥቂት አይደለም። በሁሉም የሊግ እርከን የሚገኙ  ዳኞች በተጫዋቾች ተደብድበዋል፣ተዋክበዋል፤ በአጠቃላይ ኢ ሰባዊ ድርጊት ተፈፅሞባችዋል:: በማስፈራራት ውሳኔያቸው ላይም ተጽዕኖ ተደርጎባቸዋል። ይህ ደግሞ በራሳቸው እና በቤተሰባቸው ላይ  ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጉዳት በማድረስ የራስ መተማመናቸው እንዲሸረሸር አድርጓል።

ይሁንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተጫዋቾች በዘርፉ ተጠቃሚ መሆናቸው እና ባለፉት አምስት ዓመታት በቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭት መተላለፉ ግን በትንሹም ቢሆን ሜዳ ላይ የተጫዋቾች ስነ ምግባር እንዲሻሻል ማድረጉን  ከአሚኮ በኵር ጋዜጣ የስፖርት ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉት የስፖርት ሳይንስ ባለሙያው  አቶ አማን ሞላ  አልሸሸጉም።

 

ክለቦች የሚተዳደሩባቸውን ደንቦች እና ሕጎች በተገቢው መንገድ ተፈጻሚ አለማድረጋቸው  ተጫዋቾች ሜዳ ውስጥ እና ከሜዳ ውጪ ሙያውን የሚጻረር ተግባር እንዲያከናውኑ ግን አሁንም ዕድል ሰጥቷቸዋል::  ከዚህ በፊት ክለቦች በሜዳቸው እና ከሜዳቸው ውጪ ጨዋታዎችን ያከናወኑ በነበረበት ወቅት ተጫዋቾች ከፍተኛ የስነ ምግባር እና የባህሪ ችግር ይስተዋልባቸው እንደነበር ባለሙያው አስታውሰዋል። በሜዳቸው መሸነፍ የማይፈልጉ ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች፣ የቡድን መሪዎች እና ደጋፊዎች ተጫዋቾችን ለጸብ ያነሳሳሉ። ዳኛን በማዋከብ ውጤት ለማስቀየር እንደሚሞክሩ የስፖርት ባለሙያው ተናግረዋል። ከታች ባሉ የሊግ እርከኖችም ቢሆን ተመሳሳይ ድርጊቶች ይፈጸሙ እንደነበር አስታውሰዋል::

 

የዳኛ ውሳኔ መቃወም እና ጨዋታ ካለቀ በኋላም ዳኞችን ማዋከብ በሕጉ መሰረት ከባድ ቅጣት የሚያስከትል ቢሆንም ተጫዋች፣ አሰልጣኞች፣ የቡድን መሪዎች እና ደጋፊዎች ግን በተደጋጋሚ ይህንን ሲያደርጉ አይስተዋልም። የዳኛን ውሳኔ በቃል ወይም በምልክት መቃወም እና ማዋከብ ቢጫ ካርድ ያሰጣል። ዳኛን መማታት እና አጸያፊ ስድብ መሳደብ ደግሞ ቀይ ካርድ እንደሚያሰጥ የጨዋታ ሕጉ ያትታል።

 

ክለቦች ባልተገባ መንገድ ሜዳ ላይ ዋጋ የሚያስከፍል  የስነ ምግባር ችግር ያለባቸውን ተጫዋቾች እንዲታረሙ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ሕጎችን ለማስፈጸምም በደንብ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል ባለሙያው። ለአብነት ተጫዋቾች በጥፋት ምክንያት ቅጣት ሲደርስባቸው ቅጣቱን ክለቦች ነው የሚከፍሉት። ይሁን እንጂ ተጫዋቾችን በስነ ምግባር ለማነጽ በቀጥታ ቅጣቶችን እነርሱ ላይ ማሳረፍ እንዳለባቸው ባለሙያው አቶ አማን ይነገራሉ።

እግር ኳሱ ባደገባቸው በአውሮፓ  ሀገራት ተጫዋቾች ከታክቲክ እና ከቴክኒክ ስልጠናዎች እኩል የጨዋታ ሕጎችንም እንዲሰለጥኑ እና እንዲገነዘቡ ይደረጋሉ ያሉት የዘርፉ ባለሙያው፤ ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ግን የጨዋታ ሕጎችን ባለማወቃቸው ነው ጥፋት የሚፈጽሙት ብለዋል።

 

ታዲያ ችግሩን ለመቅረፍ አወዳዳሪው አካል ለክለቦቹ እና ለተጫዋቾቹ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሥራት እንደሚኖርባቸው ባለሙያው አስገንዝበዋል። ተጫዋቾች የጨዋታ ሕጎችን (laws of the Game) ማወቅ እንደሚገባቸው እና ቅድመ ዝግጅት ስልጠና ላይ በደንብ ሊሠሩ ይገባል ነው የተባለው።

በሌሎቹ ሀገራት የእግር ኳስ ዳኝነት ሙያ እንደ አንድ መደበኛ ሥራ እንደሚሠራ ይታወቃል። በኢትዮጵያ ግን ከቀደሙት ጊዜያት ጀምሮ እንደ ተደራቢ ሥራ ተይዞ ጎን ለጎን መሠራቱ  በሀገራችን  ለሙያው ትኩረት አለመሰጠቱን ያሳያል። እናም የሀገራችን ዳኞች በቻሉት መጠን ዘመኑ የሚጠይቀውን የዳኝነት ዕውቀት መያዝ አለባቸው፤ ራሳቸውን በየጊዜው በማብቃትም  የሚሠሯቸውን ስህተቶች መቀነስ እንደሚችሉ አቶ አማን አጽንኦት ሰጥተዋል።

 

ተጫዋቾች ሜዳ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከሜዳ ውጪም የሚያሳዩት ጥሩ ያልሆነ ባህሪ እና ስነ ምግባር የእግር ኳስ ህይወታቸውን ይጎዳል። ከእነርሱ አልፎ የክለባቸውን ስም እና ዝና ያጎድፋል። አልኮል መጠጣት፣ የምሽት ቤቶችን ማድመቅ እና አላስፈላጊ አስተያየቶችን መስጠት በተጫዋቾች ዘንድ ከሜዳ ውጪ የሚታዩ የስነ ምግባር ጉድለቶች ናቸው። በተጨማሪም ከደጋፊዎች እና ጋዜጠኞች ጋር እሰጣ ገባ ውስጥ መግባትም ተጫዋቾች ከሜዳ ውጪ የሚታይባቸው የስነ ምግባር ጉድለቶች ናቸው።

ከሜዳ ውጪ ጥሩ ስነ ምግባር ያላቸው ተጫዋቾች በአሰልጣኞቻቸው፣ በቡድን አባሎቻቸው፣ በደጋፊዎች እና በስፖንሰር አድራጊ ድርጅቶች እምነት የሚጣልባቸው ይሆናል። ታዲያ ተጫዋቾች በሙያቸው ረዘም ላለ ጊዜ ለመቆየት፣ መልካም ስማቸውን ለመጠበቅ እና በእግር ኳስ ህይወታቸው ስኬታማ ለመሆን ሜዳ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከሜዳ ውጪም ራሳቸውን መጠበቅ ይኖርባቸዋል-የባለሙያው አስተያየት ነው።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የሐምሌ 21 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here