የከሸፈዉ የሰላም ስምምነት

0
13

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ የፕሬዚዳንትነት መንበሩን ሲቆናጠጡ አሳካቸዋለሁ ብለው ከወጠኑት የመቶ ቀናት ዕቅዳቸው አንዱ ደም አፋሳሹን የሩሲያ – የዩክሬን ጦርነትን ማስቆም ነበር:: ሆኖም ያሰቡት ሳይሆን ወራት ተቆጥረው አንድ ዓመት ሊሞላ ቀናት ቀርተዋል፤ ጦርነቱ  እንዲቆም ያደረጉት ተደጋጋሚ ጥረትም  አልተሳካም።

 

ትራምፕ ሰላም ወርዶ የሰዎች ሞት እንዲቆም ይፈልጋሉ፤ እናም ግጭቱ በጠረጴዛ ዙሪያ  እንዲፈታ   በተደጋጋሚ ፍላጎታቸው እንደሆነ የሁለቱንም ተፋላሚ ወገኖች በአካል እና በስልክ አግኝተው አወያይተዋቸዋል:: ልኡካናቸውን እየላኩም አነጋግረዋቸዋል:: ከወራት በፊት ከሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋርም በአሜሪካዋ አላስካ ግዛት በአካል ተገናኝተው መክረዋል:: ሆኖም ጠብ ያለ ነገር ሳይኖር ጦርነቱ እየተባባሰ ነው::

በተመሳሳይ በፕሬዚዳንት ትርምፕ የቀረበው 28 ነጥቦችን ያካተተው የሰላም ዕቅድ ጦርነቱን ለማስቆም ተስፋ ተጥሎበት ነበር፤ ተፋላሚዎቹም አወንታዊ ምላሽ ነበር የሰጡት:: በአሜሪካ የሚመራው የሰላም ሃሳብ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴም ፈጥሮ ነበር። ኪየቭ፣ ሞስኮ፣ አቡ ዳቢ እና ጄኔቫ ሁሉም ቁልፍ በሆኑ የአሜሪካ፣ የሩሲያ እና የዩክሬን ባለሥልጣናት መካከል ስብሰባዎችን አስተናግደዋል። ሁሉም የሰላም ዕቅድ ዝርዝሮችን ሲያወጡ ነበር።

እንደ ሮይተርስ ዘገባ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እና የዶናልድ ትራምፕ የቅርብ ሰው ጃሬድ ኩሽነር ጋር በሞስኮ ተገናኝተዋል። የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ እንደገለጹት ሩሲያ ጦርነቱን ለማስቆም በአሜሪካ የታቀዱትን ውስን ሀሳቦችን ተቀብላለች፤ ሌሎችን ግን ውድቅ አድርጋለች። እስካሁንም ስምምነት አልተደረሰም።

ትራምፕ በበኩላቸው ስቲቭ ዊትኮፍ እና ያሬድ ኩሽነር ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ጥሩ ውይይት እንዳደረጉ ተናግረዋል። “ፑቲን አንዳንድ የአሜሪካ ሀሳቦችን ተቀብሏል። ምንም እንኳን ስብሰባዎቹ ጥሩ ውጤት ባያስገኙም” ማለታቸውን ብሉምበርግ ዘግቧል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ እንደተናገሩት ደግሞ የኪየቭ ተደራዳሪዎች ከአውሮፓ መሪዎች ጋር በክሬምሊን ስብሰባ ውጤት ላይ ለመወያየት በቅርቡ በብራሰልስ ይገናኛሉ። በመቀጠልም ከፍተኛ ተደራዳሪ ሩስቴም ኡሜሮቭ እና የጦር ኃይሉ አዛዥ አንድሪ ህናቶቭ በዋሽንግተን ከአሜሪካ ልዑካን ጋር ለመገናኘት እንደሚዘጋጁ አስታውቀዋል።

ሾልኮ የወጣ የተባለ በአሜሪካ የተዘጋጀው ባለ 28 ነጥብ የሰላም ዕቅድ ዩክሬንን እና የአውሮፓ አጋሮቿን አስደንግጧል ተብሏል። ጡረተኛው የአሜሪካ ጦር ከፍተኛ መሪ የነበሩት ሌተናል ጄኔራል ቤን ሆጅስ “ዕቅዱ ሩሲያ ያቀረበችውን ከፍተኛ ፍላጎት ያካተተ ነው:: ዩክሬንን ኔቶን እንዳትቀላቀል ከልክሎ ግዛቷንም ለሞስኮ የሰጠ እና የኪየቭን ጦር ብዛት የሚገድብ” ብለውታል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሩሲያ ዩክሬን ጦርነትን ለማስቆም ባቀረቡት ዕቅድ ላይ የዩክሬን አጋሮች ስጋታቸውን ከገለጹ በኋላ “የአሜሪካ ዕቅድም ሊቀየር ይችላል” ማለታቸው የሚታወስ ነው።

የአውሮፓ፣ የካናዳ እና የጃፓን መሪዎች ዕቅዱ ፍትሐዊ እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት አስፈላጊ ነገሮች እንዳሉት ዕምነታቸውን ገልጸዋል፤ ይሁንና  በዩክሬን ላይ ስለሚደረጉ የድንበር ለውጦች እና ገደቦች ስጋታቸውን በመጥቀስ ተጨማሪ ሥራ እንደሚያስፈልገው ተናግረው ነበር።

ዩክሬን እና አጋሮቿ የሰላም ዕቅዱ ላይ ማሻሻያ አንዲደረግ ግፊት ሲያደርጉ ነበር። በሌላ በኩል ከማሻሻያው በፊት የነበረውን ዕቅድ ሩሲያ ተቀብላው ነበር። የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ የአሜሪካ እና የዩክሬን የደኅንነት ባለሥልጣናት በጄኔቫ ስዊዘርላንድ ተገናኝተው በጉዳዩ ዙሪያ ተወያይተዋል። ከውይይቱም በኋላ በዕቅዱ ላይ ለውጥ መጥቷል። ሩሲያ ግን አልተቀበለችውም::

ሮይተርስ እንደዘገበው የሰላም ድርድሩ በቀጠለበት በዚህ ወቅት በሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ጥቃቶች ቀጥለዋል። ሆጅስ ከኤቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ “የትራምፕ አስተዳደር ዩክሬንን ለመርዳት በጭራሽ አላሰበም” ሲሉ ወቅሰዋል።

የምዕራባውያን መሪዎች  ፑቲን ዩክሬንን ከወረሩ በኋላ በሩሲያ ፍላጎት ላይ ለመደራደር መገደዳቸውን አሳስበዋል። ዎል ስትሪት ጆርናል እንደዘገበው የአሜሪካ ባለሥልጣናት በአሜሪካ፣ ሩሲያ እና ዩክሬን መካከል የንግድ ስምምነቶችን ማረጋገጥ የሰላም ድርድሩ ቁልፍ አድርገው ይመለከቱታል።

መረጃው እንደሚጠቁመው የአውሮፓ መሪዎች ሞስኮ የበለጠ እንድትስማማ ግፊት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል፤  ዩክሬንን በመደገፍም ጦርነቱን ለማበረታታት ተንቀሳቅሰዋል። ኪየቭ እና የአውሮፓ አጋሮቿ እንደሚያምኑት፣ የሰላም ስምምነት ቢፈጠርም እንኳ ወደ ፊት ሩሲያ እንደገና ጥቃት እንዳትሰነዝር ለማድረግ በጣም ውጤታማው መንገድ ዩክሬን የኔቶ አባል እንድትሆን ማድረግ ነው።

ሩሲያ ደግሞ እንዲህ ዓይነቱን ሀሳብ አጥብቃ ትቃወማለች።  ትራምፕም ኪየቭን ወደ ሕብረቱ የማስገባት ፍላጎት እንደሌላቸው ደጋግመው ሲገልጹ ነበር።

የአውሮፓ ኮሚሽን እ.አ.አ በ2026 እና 2027 የዩክሬንን የገንዘብ ፍላጎት ለመሸፈን የተያዙትን የሩሲያ የባንክ ንብረቶች ለመጠቀም እና ለመበደር ሁለት ሀሳቦችን አቅርቧል። ዩክሬን በሩሲያ ጦርነት ላይ የምታደርገውን ትግል ለመደገፍ፣ ወታደራዊ እና መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለመሸፈን 90 ቢሊዮን ዩሮ (159 ቢሊዮን ዶላር) ትፈልጋለች። የኮሚሽኑ እርምጃም ለዚህ አገልግሎት ነው::

የሕግ ፕሮፖዛሎች በአብዛኛው በቤልጂየም ውስጥ በሚገኙ የሩሲያ ንብረቶች ላይ የተመሠረተ “የማካካሻ ብድር” እና እነዚህን የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ወደ ሩሲያ የመመለስ ክልከላን ያካትታል። ይህን በተመለከተ አስተያየት የሰጡት ሆጅስ “አውሮፓ ጦርነቱን ለመሸከም መዘጋጀቷን የሚያሳይ ምልክት ነው” ብለዋል።

ሆጅስ አክለውም “አውሮፓውያን በመጨረሻ ከእንቅልፋቸው ነቅተው ፕሬዚደንት ትራምፕ ወይም የአሜሪካ አስተዳደር ሊታደጋቸው እንደማይችል አውቀውታል” ይላሉ። ይሁንና ቤልጂየም የአውሮፓ ሕብረት የታገዱትን የሩሲያ ንብረቶችን ለዩክሬን ለመጠቀም ያቀደውን ውድቅ አድርጋለች። ሩሲያ ዕቅዱን “ስርቆት” ስትል ገልጻዋለች።

ይህ በእንዲህ እያለ አውስትራሊያ ለዩክሬን የ95 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ልታደርግ መሆኑ ተነግሯል። በተጨማሪም በሩሲያ መርከቦች ላይ ማዕቀብ እንደምትጥል እና ጡረታ የወጡ ወታደራዊ ሄሊኮፕተሮችን ለዩክሬን ለመስጠት እያሰበች መሆኗን አሳውቃለች። ጦርነቱ እ.አ.አ በየካቲት 2022 ከጀመረ ወዲህ አውስትራሊያ ለዩክሬን ያደረገችው አጠቃላይ የመከላከያ ድጋፍ አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር ደርሷል።

አውስትራሊያ እና ኒውዚላንድ ለኪየቭ ወታደራዊ ዕርዳታን የሚያመቻቹ የመጀመሪያዎቹ የኔቶ አባል ያልሆኑ ሀገሮች ናቸው።

አውስትራሊያ የኔቶ አባል ባትሆንም መሪዎቿ በየጊዜው ከኔቶ ስብሰባዎች የሚጋበዙት ከጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ እና ኒውዚላንድ ጋር የኢንዶ-ፓሲፊክ ፎር (IP4) ቡድን አካል በመሆኗ ነው።

በሌላ በኩል የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን “አውሮፓ ጦርነትን የምትፈልግ ከሆነ ሩሲያ ዝግጁ ናት” ማለታቸውን ቲበአር ቲ ወርልድ ዘግቧል።

ፕሬዝዳንት ፑቲን አክለውም “የአውሮፓ ሀገራት ከሩሲያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማቋረጣቸው ከሰላም ድርድር ራሳቸውን ዘግተዋል” ብለዋል።

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የህዳር  29  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here