የከተማችንን ውበት አታጉድፉ!

0
137

“ከአበቦች ሁሉ መአዛሽ ማራኪ ነው ፀአዳ ቀለመ ደማቋ በጣም ውብ ነሽ አንች ፅጌረዳ

ከአበቦች አንች ተመርጠሻል ያየሽ ሁሉ ባንች ህይወቱን ያድሳል

ልዩ ነው ከሌሎች ያንች አፈጣጠር ተዘርዝሮ መች እንዲህ ያልቃል ባጭር  ፅጌረዳ ስለአንች አፈጣጠር”

በሚል የኢትዮጵያ ሙዚቃ ንጉሥ ጥላሁን ገሠሠ አቀንቅኗል። በዚህ ሙዚቃ ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ ፅጌረዳ በሚል ባህርዳር ከተማን የገለጻት መስሎ ይሰማኛል። ልክ እንደ አበቦች ንግሥት ፅጌረዳ ሁሉ፤ ባህርዳር ከተማም የከተሞች ንግሥት ብላት የተሳሳትሁ አይመስለኝም። ምክንያቱም እኔ ብቻ ሳልሆን ዓለም የመሰከረላት ውብ ከተማ ናት።

በቅርቡ አዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ወደሆነ አንድ ወዳጄ ዘንድ ስልክ ደወልሁ። የተለመደውን “ሰላም ሰነበትህ” ሠላምታ ተለዋወጥን፤ ወቅታዊ ሁኔታውን አንስተን መረጃ ተለዋወጥን። የዘመድ አዝማዱን ደህንነትም ተጠያየቅን።

በሰላምታችን መገባደጃ “ባህርዳር እንዴት ናት?” እሚል ጥያቄ አቀረበልኝ። ሰላም ናት! እስካሁን ሁሉም ነገር በነበረው ሁኔታ ቀጥሏል፤ ለየት የሚለው በዋናው የከተማዋ ጎዳናዎች ላይ የኮሪደር ልማት እየተከናወነ  ነው የሚል ምላሽ ሰጠሁ። “እውነት! ባህርዳር ከተማ የኮሪደር ልማት ጀመረ?” እሚል አግራሞት አዘል ጥያቄን አስከተለ። አዎ! ያውም በተፋጠነ ሁኔታ አልሁት። “ይገርማል! ለባህርዳር ከተማ ተፈጥሮ ካደላት ውበት ላይ ኮሪደር ልማት ከታከለበት እማ የቀደመ ውበቷ ይበልጥ ይደምቃል። ደስ የሚል ተግባር ነው። መጥቼ እስካያት ጓጓሁ” ብሎ ወጋችን ተቋጨ።

ለዚህ የትዝብት ፅሑፌ ተዛማጅ ሆኖ እንጂ የእኔ እና የወዳጄ ስልክ ልውውጥ ቀድሞ መምጣት ትኩረት የሚሻ ሆኖ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ዋናው ትኩረቴ በዚች ውብ ባህርዳር ከተማ ውበት እና ውበቷን እያጎደፉ ባሉ አንዳንድ ድርጊቶች ዙሪያ ይሆናል።

ባህርዳር ከተማ የታሪካዊ፣ ባህላዊ እና ተፈጥሯዊ መስህብ ሃብቶች ባለቤት ናት። በጉያዋ ያሉት የጣና ሃይቅ ገዳማት እምቅ ሃይማኖታዊ እንዲሁም ታሪካዊ ሰነዶች እና ቅርሶችን ይዘዋል። በተፈጥሮ ልግስና አባይ እና ጣና ተጎራብተው ባህርዳርን አድምቀዋታል።

በከተማዋ ውስጥ ለውስጥ የተገነቡት የአስፋልት፣ ኮብልስቶን እና እግረኛ መንገዶች እንዲሁም በየመንገዶች ዳርቻ የተተከሉት ዘንባባዎች የውበቷ መገለጫ ናቸው።

በማስተር ፕላን እየተመሩ የተገነቡት የመኖሪያ እና ኢንዱስትሪ መንደሮች የባህርዳርን ውበት ከዓመት ዓመት እንዲደምቅ አድርገውታል። ባለኮከብ ሆቴሎች እና ደረጃቸውን የጠበቁት አገልግሎት ሰጭ ተቋማትም እየተበራከቱ የመጡባት ውብ ከተማ ናት።

የዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እና እግር ኳስ ስቴዲየም ባለቤት ናት ውቢቷ ባህርዳር ከተማ። ተፈጥሮ በለገሰቻት እና ከዓመት ዓመት  ውበቷን ይበልጥ ለማዘመን በተከናወኑ ተግባራት ውጤት የባህርዳር ከተማ ውበት እየደመቀ ቀጥሏል።

ባህርዳር ከተማ እያስመዘገበች ካለው የእድገት ግስጋሴ ጋር ተያይዞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለኑሮ ምቹ ከተማ እና የማደግ ተስፋ ካላቸው 10 የዓለም ከተሞች መካከል አንዷ ሆና እ.አ.አ 2002 በዩኒስኮ መመረጧ ይታወሳል። የትምህርት ከተማ በሚልም እ.ኤ.አ 2017 በዩኔስኮ የተመረጠች ውብ ከተማ ናት ባህርዳር።

በኢትዮጵያ ከሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች አንዷ ባህርዳር ከተማ ናት። ለኮንፈረንስ ቱሪዝምም ተመራጭ ከተማ ናት። የጠቃቀስኳቸው የባህርዳር ከተማ ውበት መገለጫዎች ይበልጥ እንዲደምቁ ለማስቻልም የኮሪደር ልማት ሥራ አየተከናወነ ነው። እሰይ የሚያስብልም ሆኗል።

ስለባህርዳር ከተማ ውበት ከዚህም በላይ አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል። ነገር ግን ዋናው የዚህ ፅሑፍ ትኩረት አይደለም። ይልቁንስ ይህን ውበት የሚያጎድፉ ተግባራት ተበራክተዋልና  በጥልቀት ለመዳሰስ እሞክራለሁ።

ዘወትር ከሰኞ እስከ ዓርብ በየቀኑ ሁለት ጊዜ ለስራ የደርሶ መልስ ጉዞ የማደርግበት ጎዳና የትዝብቴ ቀዳሚ መስመር ሆኗል። በተለምዶ የተባበሩት እየተባለ ከሚጠራው ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እና ራዲዮ ባህርዳር ቅርጫፍ ቢሮ ድረስ ያለው መስመር ለባህርዳር ከተማ ውበት እንደ እንከን የሚታዩበት አንዱ አካባቢ ነው። ይህ መስመር በከተማዋ ዋነኛ ተብለው ከሚጠቀሱት የአስፋልት መንገዶች መካከል አንዱ ነው።ነገር ግን ለተሽከርካሪ እና ለነዋሪዋ ተገቢውን አገልግሎት እየሰጠ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የከባድ መኪና ተሽከርካሪዎች የፓርኪግ አገልግሎት መስጫ ሆኗል። መንገዱን የአካባቢው ወጣቶች ለፓርኪግ አገልግሎት መስጫ አድርገውታል።

በጣና ክፍለከተማ ቀበሌ 16 የሚካለለው ይህ ጎዳና ሥርዓት ባጣ መልኩ ለከባድ መኪናዎች መቆሚያ አገልግሎት መዋሉ ብቻ አይደለም ችግር ሆኖ የሚገለጸው። የተሽከርካሪዎቹ ጎማ ስር ሥነምግባር የጎደላቸው ግለሰቦች መጸዳጃ ቤት እስኪመስል በሽንት ፍሳሽ መንገዱ እንዲሞላ ያደርጉታል።

በዚህ ጎዳና በሚቆሙ ትልልቅ ሃገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎች ስር የሚፈጸምን የጎማ ስር ሽንት ማስወገድ ጸያፍ ተግባር እንዲባባስ ያደረጉት ደግሞ በጎዳናው ግራና ቀኝ የተከፈቱት መጠጥ ቤቶች ናቸው ። መጠጥ ቤቶቹ መጸዳጃ ቤት ስለሌላቸው ተገልጋዩ ከጠጣ በኋላ በአቅራቢያው ከቆሙ ተሽከርካሪዎች ስር ሽንቱን ያራግፋል። ይህ መጥፎ ተግባር የሚፈጸመው በወንዶች ነው። ሴቶችን አይመለከትም።

የከተማውን አንዳንድ ጎዳናዎች ውበት የሚያሳጣው ተግባር ጎማ ስር የሚሸና ሽንት ብቻ አይደለም። በየአካባቢው መሃል ከተማ ላይ የወተት ላሞች እርባታ ይካሄዳል። እንስሳቱ አስፋልት መንገዱን ያድሩበታል። ጎዳናው የእንስሳት ተረፈ ምርት መጣያ ሆኗል። የመንገዱን መጥፎ ሽታ ይበልጥ የጎላ እንዲሆን አድርጎታል።

ከባህርዳር ከተማ ዋና አውራ መንገድ በመነሳት ወደ ድባንቄ መድሃኒዓለም አቅጣጫ በሚደረግ ጉዞም የመንገዱ ግራና ቀኝ በዘፈቀደ በተጣለ ቆሻሻ ተሞልቶ መመልከት የተለመደ ሆኗል።

የተለያዪ ውጋጅ ቆሻሻ በተሽከርካሪ ተጭኖ በዚህ የከተማዋ ጎዳና ይራገፋል። የሚጣለው ቆሻሻ ከመጥፎ ጠረኑ ባሻገር ለዓይን ደስ አይልም፡፡

ከገጠር መንገድ አቅጣጫ ተነስቶ ይህን ዋና የአስፋልት መንገድ የሚቀላቀለው ጎዳናም ተመሳሳይ ተግባር የሚፈጸምበት አካባቢ ነው። በዚህ መስመር ደግሞ በተለይ የባጃጅ አሽከርካሪዎች ባጃጃቸውን አቁመው ሲጸዳዱ መመልከት የተለመደ አስነዋሪ ተግባር ሆኗል።

በከተማዋ ጣና ክፍለከተማ ፅ/ቤት አፍንጫ  ስር የሚስተዋለው ተግባርም አንዱ የትዝብቴ ማረፊያ ነው። በክፍለከተማው የተለያዩ አካባቢዎች የሚሰማሩ ደንብ አስከባሪዎች የስራ ስምሪት መነሻ እዚሁ ፅ/ቤት ነው። ነገር ግን የአካባቢውን ውበት የሚያጎድፍ ተግባር በፅ/ቤቱ አቅራቢያ ይፈጸማል። ሃይ የሚል ግን የለም። ቆሻሻ በዘፈቀደ ይጣላል። መሸት ሲልም የአካባቢው ነዋሪ የሚጸዳዳው ከክፍለከተማው ፊት ለፊት ባለ ሜዳ ላይ ነው።

በዚህ አካባቢ በከተሞች ልማት ፈንድ እና በአንድ ረጅ ድርጅት የተገነቡ መጸዳጃ ቤቶች አሉ። ነገር ግን እነሱን ችላ ብሎ ሜዳ ላይ መጸዳዳት ከመልካም ስነምግባር ያፈነገጠ ተግባር ነው። የከተማዋን ውበትም አጉድፏል።

“ምነው! ባህርዳር ዳግማዊ ሚኒልክ እና ጣና ክፍለከተሞች ብቻ ናቸው?” የሚል ጥያቄን ሳታነሱ እኔው የምልከታ ጉዞዬን ልቀጥል ወሰንኩ። ወደ ሽንብጥ ክፍለከተማ ተጓዝኩ። በዚህ ክፍለከተማ በርካታ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ይገኛሉ። ከነዚህ መካከል የክልሉ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ አንዱ ነው። የቢሮው መዝናኛ ክበብ ለሰራተኞቹ እና ለውጭ ደንበኞች አገልግሎት ይሰጣል። የተሟላ መጸዳጃ ቤት ግን የለውም። የክበቡ ደንበኞችም ከበሉና ከጠጡ በኋላ እዚያው አካባቢ ሜዳ ላይ ይጸዳዳሉ/ሽንታቸውን/ ያስወግዳሉ። እዚሁ ቢሮ ጎን የክልሉ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ቢሮ ይገኛል። እነዚህ ሁሉ ተቋማት ባሉበት አካባቢ የሚደረግ ህገወጥ ተግባር ደግሞ ሌላኛው የባህርዳርን ከተማ ውበት የሚያጎድፍ ነው።

እያንዳንዱን የባህርዳር ከተማ አካባቢ በጥልቀት ለመዳሰስ አስቸጋሪ ነው። አብነቶችን እየጠቀስኩ ከክፍለከተማ ክፍለከተማ ጉዞዬ ቀጥሏል። አባ ፋሲሎ ክፍለከተማ ተገኝቻለሁ። የዚህ ክፍለከተማ ከፊል ክልል ጣና ሃይቅን ያካልላል። በሃይቁ አቅራቢያ ያለው ቀደምት የአስፋልት መንገድ ደግሞ የባህርዳርን ውበት ዘወር ዘወር ብለው ከሚመለከቱበት ጎዳና መካከል አንዱ ነው። ይሁን እንጂ እዚህም ውበትን አጉዳፊ ነገር ይስተዋላል።

የጣናን ዳርቻ ተጎራብተው የተገነቡ መዝናኛ ቦታዎች እና ዘመናዊ ሆቴሎች በዚህ አካባቢ ይገኛሉ። በነዚህ የሚገለገሉት ደግሞ ለጉብኝት አልያም በስብሰባ ምክንያት ወደከተማዋ ጎራ ያሉ ናቸው። በመሆኑም የሚመለከቱት ሁሉ የተዋበ ቢሆን መልካም ነበር። ግን አልሆነም። በጨጨሆ የባህል ምሽት ቤት እና በሠርፀ ድንግል ትምህርት ቤት መካከል በጣም መጥፎ ሽታን የታቀፈ ተፋሰስ አለ። የከተማዋ ውበት እዚህም ጎሎ ይታያል።

የባህርዳር ከተማን ውበት እያጎደፉ ያሉ ሁሉንም ተግባራት መዘርዘር አንባቢን ማሰልቸት ይሆናል። እንዲያው ለመጠቆም ያህል ከፓሊ ቴክኒክ ወደ ባህርዳር ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ አቅጣጫ፣ ከፓሊ ቴክኒክ ባህርዳር ዮኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ/ዊዝደም/ መስመር፣ ከዋናው ገበያ አዲሱ መናኸሪያ አቅጣጫ ያሉት እና ሌሎችም አካባቢዎች ለፍሳሽ ማስወገጃ ታስበው በየመንገዱ ግራና ቀኝ የተገነቡ ተፋሰሶች የሽንት መሽኛ እና የቆሻሻ መጣያ ሆነዋል። ይህን መሰል ድርጊት የከተማዋ ውበት ላይ አሉታዊ ጫና አንዳያሳድሩ ክትትል ያስፈልገዋል፡፡

ታላቁን የአባይ ወንዝ ተሻግሬ ግሽ አባይ ክፍለከተማ ደርሻለሁ። ለአብነት ህዝብ በብዛት የሚውልበት የአካል ተሃድሶ ማዕከል የቆርቆሮ አጥርን ተከልሎ በርካታ ህገወጥ ሽንቱን ይሸናል። በዚህ የተነሳ የአጥሩ ቆርቆሮ በሽንት ተበልቶ ከጥቅም ውጭ ሆኗል። የቆሻሻው ሽታም አካባቢውን በክሎታል።

“እና! ምን ይሁን?” ከመባሉ በፊት እኔው ቀድሜ፤ መሆን ይገባዋል ብየ የማስበውን ልጠቁም። በመጀመሪያ ሁላችንም የከተማዋ ነዋሪዎች ለባህርዳር ከተማ ውበት ተቆርቋሪ ልንሆን ይገባል። በተገኘው ቦታ ሁሉ ከመጸዳዳት እንቆጠብ። ውበቷን የሚያጎድፍ ተግባር እንዳይፈጸምም አጥፊዎችን በጋራ እንከላከል። አለዚያ የባህርዳር ከተማ ውበት የተሟላ ሊሆን አይችልም።

በየክፍለከተማው ደንብ በማስከበር ተግባር ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎችም፤ ህገወጥ የመንገድ ላይ ንግድን ከመቆጣጠር ባለፈ የባህርዳር ከተማ ውበት አምባሳደር ሊሆኑ ይገባል።

የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ደግሞ ባህርዳር ውበቷ ይበልጥ እንዲጎላ ለማስቻል እያከናወነ ካለው የኮሪደር ልማት እና ሌሎች ተግባራት ጎን ለጎን፤ ያላትን ውበት ለሚያጎድፉ አስጸያፊ ሁኔታዎች ትኩረት ሊሰጥ ግድ ይላል። ይህን በማድረግ በመልካም ሁኔታ የተከናወነው ተግባር ሁሉ በጽዳት ጉድለት እንዳይበላሽ ከወዲሁ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።

በየቦታው የሚከናወን የፓርኪግ አገልግሎት ስርአት ሊበጅለት ግድ ይላል። አለበለዚያ መኪናዎች በፓርኪግ ሰበብ በየቦታው የሚቆሙ ከሆነ ህገ ወጦች ጎማቸው ስር ሽንታቸውን እያፈሰሱ የከተማዋ ውበት ላይ ጫና ያሳድራል።

በከተማዋ በዘፈቀደ መንገድ የሚከናወን የወተት ላሞች እርባታም ስርዓት ሊበጅለት ይገባል። ቀደም ብሎ የተከናወኑ ተግባራት መኖራቸው አሌ ባይባልም፤ አሁንም አውራ ጎዳናዎችን የከብቶች መዋያ እና ማደሪያ ማድረግ ግን ተገቢ አይደለም። የእኔ ምልከታ በዚሁ ተቋጨ። ይህ የግል ሃሳብ ማንጸባረቂያ ገጽ ደግሞ የሁላችን ነው። እናንተም ያላችሁን ሃሳብ ጻፉበት አላለሁ። ቸር ይግጠመን።

(ጥላሁን ወንዴ)

በኲር የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here