የከንቲባ ችሎት

0
278

በባሕር ዳር ከተማ አቫንቲ ብሉናይል ሆቴል አዳራሽ ውስጥ ተገኝተናል:: በቦታው የመገኘታችን ምክንያት ደግሞ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት የሕዝብ መድረክ ሲያዘጋጅ ነዋሪው ከሚሰጠው አስተያየት እና በአገልግሎት አሰጣጡ ዙሪያ ባደረገው  ጥናት ችግር መኖሩን አረጋግጧል፤ ይህን ተከትሎም ከተማ አስተዳደሩ የሕዝቡ ችግር በጊዜ እየተመለሰ አይደለም የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል::  ችግሮቹን ለማቃለልም የከተማው ከንቲባ በሰብሳቢነት የሚመሩት እና ችግር   የሚነሳባቸው የተቋም ኃላፊዎች እና ቡድን መሪዎች ተገኝተው ምላሽ የሚሰጡበት  ሳምንታዊ የከንቲባ ችሎት አቋቁሟል::

እኛም በሁለተኛ ሳምንት ለሁለተኛ ጊዜ  በሚካሄደው የከንቲባ ችሎት  ተገኝተን ነበር:: ከተሰበሰቡት በርካታ ባለጉዳዮች  ጠጋ ብለን ጉዳያቸው ምን እንደሆነ አንዱን ባለጉዳይ ጠየቅናቸው::  “አይ አንቺን ቁሜ ሳነጋግር ወረፋ ያልፈኛል” በማለት ጉዳያቸውን ቶሎ ለማስፈፀም ባላቸው ጉጉት ምላሽ ሳይሰጡን ጆሯቸውንም፣ ዐይናቸውንም፣ ፊታቸውንም ሥም ዝርዝር ወደ ሚፅፈው ሰዉ  አዞሩ::

አብረዋቸው የነበሩ ሌላው የዘንዘልማ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር በለጠ ያዜ ግን  “ተው እንጅ እንንገራቸው ‘በሽታውን ያልተናገረ መድኀኒት የለውም’ እንደሚባለው  ጉዳያችንን ይወቁት  እንጂ” በሚል ቆም ብለው  አነጋገሩን::

አርሶ አደር በለጠ በከንቲባ ችሎት የመገኘታቸው ምክንያት ሦሰት ሄክታር ከሩብ (13 ቃዳ) የእርሻ መሬታቸው በመንግሥት ለልማት ተፈልጎ ከተወሰደባቸው አርሶ አደሮች አንዱ ናቸው:: “የስምንት ልጆች አባት ነኝ:: ከአንዱ በስተቀር ሌሎች ልጆቼ ከ18 ዓመት በላይ በመሆናቸው በሕጉ መሰረት ትክ ቦታ ላገኝ ይገባኝ ነበር፤ ግን እስካሁን ምላሽ አላገኘሁም የሚል ያልተፈታ  ቅሬታ ይዘው ለሁለተኛ ጊዜ በባሕር ዳር ከተማ በሚደረገው የከንቲባ ችሎት ተገኝተው ያልተፈታላቸውን ችግር ለማቅረብ ነው::

ሌላው አርሶ አደር ጥጋብ አድማስ ደግሞ በልማት ሰበብ የመኖሪያ ቤታቸው ጭምር ተወስዶባቸው ትክ አግኝተዋል:: “ነገር ግን  ልጆቼ ትክ ቦታ አላገኙም፤  ያለአግባብ 500 ካሬ መሬት ተነስቶብኛል:: ወደ ሚመለከተው አካል ተመላልሼ  ተወስኖልኝ ነበር:: ይሁን እንጅ   በ2015 ዓ.ም ወደ አፈፃፀም ቢመራልኝም የሚመለከተው ክፍል ‘መረጃው ጠፍቷል’ በሚል እንደገና ግልባጭ ይዤ እንዳቀርብ  ታዛዤ  በየሚመለከተው ቦታ ሁሉ ብሄድም ጉዳዬን ሰምቶ ምላሽ የሚሰጠኝ  አጥቼ ነበር::  አሁን በተፈጠረው መድረክ ላይ ግን ችግሬን አቅርቤ ለሁሉም  መፍትሄ እንደማገኝ አስቤያለሁ” በማለት አዲስ በተቋቋመው የከንቲባ ችሎት ተስፋ መሰነቃቸውን ነው የነገሩን::

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ አስራት ሙጨ እንደገለፁት  ከንቲባ ችሎት የተቋቋመው የሕዝብ መድረክ ሲዘጋጅ እና በጥናትም ሲታይ አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ችግር መኖሩ ተረጋግጧል፤ እንደከተማም ብዙ ችግሮች ይነሳሉ::  ለአብነት ጉዳይ አስፈጻሚ ባለጉዳዩ በቀጥታ ሳይሆን ሀብት ያለው ካለአግባብ በደላላ በአጭር ጊዜያት ያስፈጽማል::  በተለይ አርሶ አደሩ እና አቅመ ደካማው ድሀ ግን እንግልት ስለሚደርስበት ጥያቄው  በጊዜ እየተመለሰ እንዳልሆነ በተገኘው ማስረጃ ተመስርቶ ወደ ሥራ ተገብቷል::

በችሎቱ ችግር የሚነሳባቸው የተቋም ኃላፊዎች እና  ቡድን መሪዎች ተገኝተው በከንቲባው ሰብሳቢነት እየተመራ ባለጉዳይ ችግሩን አቅርቦ ተቋማት ምላሽ የሚሰጡበት መሆኑን የጽ/ቤት ኃላፊዋ ተናግረዋል::   በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ በአገልጋይ እና ተገልጋይ መካከል የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ይፈታል የተባለው የከንቲባ ችሎትም  የመጀመሪያው  የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም  መጀመሩን ኃላፊዋ ጠቁመዋል::

ኃላፊዋ ስለ ችሎቱ አተገባበር እንዳስረዱን  ሁሉም  የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት  አመራር ከተገልጋዮቻቸው ፊት ይቆማሉ፤ በመጀመሪያ ችሎት  የቦታ ካርታ (ሰነድ) ማረጋገጫ ጥያቄ የሚሉ እና መሰል ፍርድ ቤት ያልያዛቸውን ጉዳዮች በመመልከት ሰፊ ውይይት ይደረጋል። የመሬት ፣ የካሳ ጉዳዮች ፣ የአገልጋይ እና ተገልጋይ ችግሮች፣ ተወስነው የአፈፃፃም ችግር ያለባቸው ይቀርባሉ:: ይህን ተከትሎ የሚመለከታቸው የሕግ አካላት፣ አመራር እና ባለጉዳዮች እንዲሁም ሌሎች ታዛቢዎች በተገኙበት ችግሮች እየቀረቡ እንዲፈቱ ከንቲባ ኮሚቴው ከዚህ ቀደም ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት  ለበርካታ ጊዜያት እየተንከባለሉ መፍትሄ አልባ የሆኑ ጉዳዮች ይታያሉ።

ለሁለት ቀናት በተካሄደው በዚህ ችሎት የታዩ በርካታ ጉዳዮች ከመሬት ጋር የተያያዙ መሆናቸውን እና በእነዚህም ጉዳዮች ግልፅ ክርክር እና ውይይት እንደተደረገባቸው  ወ/ሮ አስራት ጠቁመዋል::

በሰብሳቢው በክቡር ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በሚመራው ችሎት  ግልፅ በሆኑ ቅሬታዎች ላይ የአፈፃፀም ውሳኔ እንዲሰጣቸው የአስተያየት አቅጣጫ በማስቀመጥ፣ ውስብስብነት ያላቸው ጉዳዮችን ደግሞ በቀጣይ መጣራት ያለባቸው መረጃዎች ተጣርተው እና ተጠናክረው እንዲቀርቡ እና አፋጣኝ ፍትሕ እንዲሰጣቸው  ለየካቲት 25 ቀጠሮ ተሰጥቶ እንደ ነበር አስታውሰዋል::

ወደ ፊት በችግሮች ዙሪያ  ተቋማቱ ወደ ተጠያቂነት ስለሚሄዱ መነቃቃት ስለሚኖር አገልግሎት ፈላጊው  ተገቢውን መስተንግዶ በየደረጃው እንደሚያገኝ የከንቲባ ጽ/ቤት ኃላፊዋ  አስረድተዋል:: በማህበረሰቡ በኩል ደግሞ ቀድሞ ውሳኔ ያገኙ ፣ የቆዩ እና ውሳኔ ያገኙ  ሁነቶችን ፣ ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ የያዙትን ደግሞ የማይሆን መሆኑን ተረድተው ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ (ይዘው እንዳይመጡ) ያደርጋል::

በቀጣይም ሁሉም ችግር በየሳምንት በሚካሄድ ችሎት ብቻ በአንድ ጊዜ ስለማይፈታ ሰው ሲበዛ  ሌላ የመልካም አስተዳደር ችግር እንዳይፈጥር ችግሮችን ለይቶ ለየተቋማቱ በመስጠት ወደ ከንቲባ ችሎቱ ሳይመጣ በየአቅራቢያው የሚከፈትበት መንገድም እንደሚፈጠር ኃላፊዋ ጠቁመዋል::

በሌላ በኩል የቆየውን የአገልግሎት ችግር ችሎቱ በከተማ አስተዳደር ብቻ ሳይሆን ቀበሌ ሳይፈታ ክፍለ ከተማ የሚፈታበት መንገድ እያደገ መምጣት እንዳለበትም መወሰኑን ኃላፊዋ ጠቁመዋል::

“የከንቲባ ችሎቱ ሲጀመር በማህበረሰቡ  በሳምንት አንድ ቀን ይካሄድ የሚል ሃሳብ ነበር ፤ በተገልጋዩ ደግሞ ሁለት ቀን ይደረግ የሚል ጥያቄ አለ:: ተገልጋይ እየበዛ ከሄደ  ግን በሳምንት ሁለቴ የሚካሄድበት ዕድሉ ክፍት ነው :: “ ያሉት ወ/ሮ አስራት፣ ጉዳዩ ያለው ታች ስለሆነ በቀበሌ ሁለት ቀን እንዲሁም በክፍለ ከተማ በሳምንት አንድ ቀን የሚያደርጉበት ነው:: የመልካም አስተዳደር ችግር ትልቅ ፈተና እንደሆነ ያነሱት ወ/ሮ አስራት፣ ችግሮችን ለይቶ ለየተቋሙ በመስጠት ችግሮቹ ችሎቱ ላይ ሳይውሉ ሳያድሩ  የሚፈታበት መንገድ በመፍጠር ይሠራል:: በተጨማሪም ችግር ሁነው አላሠራ ያሉ ነገሮች በተለይ በመሬት ዙሪያ  ያሉ መመሪያዎችን ሁሉ እስከመለወጥ ድረስ የሚሄድበት ዕድል እንዳለው ገልፀዋል::

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here