ዓለም አቀፉ የረሀብ መረጃ ጠቋሚ እንደሚያመላክተው ዓለም ስምንት ቢሊዮን ህዝቦቿን ለመመገብ በቂ ምግብ የምታመርት ቢሆንም 733 ሚሊዮን ሰዎች ማለትም ከአስር ሰዎች መካከል አንዱ በየቀኑ ይራባል:: በአፍሪካ ደግሞ ከአምስት ሰዎች አንድ ሰው የዕለት ጉርሱን ማግኝት አይችልም። እንዲሁም በዓለም ዙሪያ ሁለት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ወይም 35 በመቶ ሰዎች ለጤናማ አመጋገብ የሚረዳቸውን ምግብ የመግዛት አቅም የላቸውም:: ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሀገሮች ደግሞ 71 ነጥብ አምስት በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ናቸው ለጤናማ አመጋገብ የሚረዳቸውን ምግብ ማግኘት የማይችሉት:: ከፍተኛ ገቢ ባላቸው ሀገሮች ይህ አሃዝ ወደ ስድስት ነጥብ ሦስት በመቶ ዝቅ ብሏል።
ዓለም አቀፍ የረሃብ መረጃ ጠቋሚ እንደሚያመላክተውበተጠናቀቀው የአውሮፓዊያኑ 2024 በ 36 ሀገሮች ውስጥ የረሃብ መጠን በከባድ ደረጃ ላይ ይገኛል ።
እ.አ.አ ከ2019 ጀምሮ የረሃብ ችግር ያለባቸው ሰዎች ቁጥርም በ152 ሚሊዮን ገደማ ጨምሯል። ለረሃብ መስፋፋትና መበራከት ጦርነት እና የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ናቸው:: ለአብነትም የሱዳን ጦርነት አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውሶችን በማስከተል እና በደም አፋሳሽነቱ የሚጠቀሰው የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ከተጀመረ ሁለት ዓመታት ሊቆጠሩ ነው::
እ.አ.አ. ሚያዝያ 15/ 2023 ሥልጣን ለመጨበጥ በሚጣጣሩ ተቀናቃኝ ጄኔራሎች መካከል የተቀሰቀሰው ጭካኔ የተሞላበት ግጭት ከ14 ሚሊዮን በላይ የሱዳን ሕዝብን ቤት እና ንብረታቸውን ጥለው እንዲሰደዱ አድርጓል። በስደተኛ አስተናጋጅ ሀገሮች ላይም የምግብ እጥረትን አባብሷል። ጦርነቱ ከሦስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ ሱዳናዊያንን ወደ ጎረቤት ሀገራት ማለትም ወደ ቻድ፣ ግብጽ እና ደቡብ ሱዳን እንዲሰደዱ አድርጓል። በሱዳን ጦር እና (አር ኤስ ኤፍ) በፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች (RSF) መካከል በተነሳው ጦርነት ሱዳን ከፍተኛ ችግር ውስጥ ትገኛለች::
ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ከባድ ውጊያ የቀጠለ ሲሆን በሁሉም አቅጣጫ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕጎች እየተጣሱ ነው:: በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል፤ እንዲሁም ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ የጾታ ጥቃት በጣም ተስፋፍቶ ይገኛል:: በተጨማሪም የጤናና የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ መዋቅሮች ፈራርሰዋል ። በዚህም አብዛኛው ህዝብ የጤና አገልግሎት ማግኘት አልቻለም፤ ህፃናት ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነዋል::። ንጹህ ውኃና የንጽህና አጠባበቅን ጨምሮ አስፈላጊ በሆኑ አገልግሎቶች ላይ ከሚደርሰው መፈራረስ ጋር በተያያዘ እንደ ኮሌራ ያሉ ገዳይ በሽታዎች በፍጥነት እየተዛመቱ ነው ።
ቀደም ሲል በወጡ ሪፖርቶች የመኖሪያ ቤቶች እና የሲቪል መሰረተ ልማቶች ወድመዋል፤ ዋና ከተማዋ ካርቱም እንዳልነበር ሆናለች :: በጦርነቱ ዘግናኝ ግፍና በደል ተፈጽሟል እየተፈፀመም ነው። ዜጎችን የማሰቃየት እና ብሄርን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ተደርገዋል:: ያለልዩነት ጥቃቶች ሰላማዊ ዜጎችን እየገደለ ነው። ሱዳን ዛሬ በዓለም ትልቁ የመፈናቀል ቀውስ የሚስተናገደባት ሀገር ሆናለች:: የቱርኩ የዜና ወኪል አናዶሉ እንደ ዘገበው በጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሃን እና በቀድሞ ምክትላቸው በሞሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ በሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች መካከል የሥልጣን ሽኩቻ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ ወደ 25ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ተገድለዋል ::
ከሰሞኑ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኩል በወጡ ሪፖርቶች ደግሞ ከ24 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ ህዝብ ማለትም ከሀገሪቱ ግማሽ ያህሉ የሱዳን ህዝብ ከፍተኛ የምግብ እጥረት አጋጥሞታል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አጋር የሆነው በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ረሃብን የሚከታተለው አይ ፒ ሲ የተባለው መርሃ ግብር ነው ይህንን ያረጋገጠው::
የአይፒሲ (IPC) የረሀብ ሪፖርት ኮሚቴ (FRC) እንሚያመላክተው ረሃቡ ደረጃ አምስት ላይ የደረሰ ሲሆን የሰሜን ዳርፉር፣ ዘምዘም ካምፕ እና የምዕራብ ኑባ ተራራ ክፍሎች በርሃቡ በከፍተኛ ሁኔታ ተጎድተዋል:: ከታህሳስ 2024 እስከ ሚያዚያ 2025 ባለው ጊዜም የኡም ካዳዳ፣ ሜሊት፣ ኤል ፋሸር፣ እና አል ላይት የሰሜን ዳርፉር ቀበሌዎችም ተጨማሪ ርሃቡ እንደሚስፋፋባቸው ነው የተገለጸው። በተጨማሪም በሌሎች 17 አካባቢዎች የሚገኙ የውስጥ ተፈናቃዮች ለረሃብ መጋለጣቸው ነው የተነገረው:: ጉዳት ከደረሰባቸው አካባቢዎች መካከል የካርቱምና የአል ጃዚራ ግዛቶችም ይገኙበታል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በፍጥነት እየተባባሰ የመጣው የረሀብ ሁኔታ በጥልቅ እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል:: ጉተሬዝ እንዳሳሰቡት ጦርነቱ በፍጥነት ካልቆመ የረሀብ አደጋውን ለመቅረፍ የሚደረገውን ጥረት ማለትም የእርዳታ ቁሳቁሶችን እና የድርጅቱን ሰራተኞች እንቅስቃሴ ያስተጓጉላል:: ዋና ጸኃፊው እንዳሉት በ2025 በሱዳን ያለውን ቀውስ ለመታደግና በጎረቤት ሀገራት ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ እንዳይባባስ በአፋጣኝ ጦርነቱን ማቆም እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።
እንደሚታወቀው ረሀብ የምግብ እጥረት ብቻ ሳይሆን የጤና፣ የመተዳደሪያና የማህበራዊ መዋቅሮች መበላሸት ነው። መላው ማኅበረሰብ በተስፋ መቁረጥ ስሜት እንዲዋጥ ያደርጋል። በዘገባው እንደተመላከተውም ምንም እንኳ ከአማካይ በላይ የሚዘንበው ዝናብ ለግብርና ሥራዎች አጋዥ ቢሆንም ያልተቋረጠው ግጭት የግብርና እንቅስቃሴዎችን በእጅጉ አስተጓጉሏል። አርሶ አደሮች ማሳቸውን ጥለው እንዲሰደዱ አስገድዷቸዋል።
አይ ፒ ሲ በተለይ በግጭት ቀጠናዎች አስተማማኝ፣ ያላንዳች እንቅፋትና ዘላቂ ሰብአዊ ዕርዳታ እንዲደርስ፣ እንዲሁም በርካታ ዘርፎችን ያቀነባበረ ሰብዓዊ ዕርዳታ በከፍተኛ ደረጃ እንዲደርስ ጠይቋል። ሪፖርቱ ችግሩ እንዳይባባስ ሊከላከል የሚችለው ጥላቻን ወዲያውኑ ማስወገድ ብቻ እንደሆነ አጉልቶ ያሳያል ።
በተያያዘም በሱዳን ሰሜን ዳርፉር ግዛት በዛምዛም ካምፕ ረሃብ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተረጋገጠ ከአራት ወራት በኋላ፣ በመላ ሀገሪቱ ለሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የምግብና የምግብ አቅርቦት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስተጓጎለ መምጣቱን የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) እና ዩኒሴፍ (UNICEF) አስጠንቅቀዋል።
ድርጅቶቹ እንደገለጹት በአፋጣኝ ያለ ምንም እንቅፋት ሰብዓዊ እርዳታና አጣዳፊ የሆነ ዓለም አቀፋዊ ድጋፍ ካልተደረገ በ2025 የረሀቡ አደጋ ይበልጥ እየተዛመተ ይሄዳል። የሚሊዮኖችን ሕይወት፣ በአብዛኛው የህጻናትን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ይሆናል::
ለቀውሱ ዋነኛ መንስኤ ያደረጉትም ግጭት፣ መፈናቀልና ሰብዓዊ እርዳታ ማግኘት የተገደበ መሆኑ ነው። ከአምሰት ወራት በፊት ረሀብ ለመጀመሪያ ጊዜ በተረጋገጠበት በሰሜን ዳርፉር ዛምዛም ካምፕ ውስጥ አንዳንድ ሰብዓዊ የምግብ እርዳታዎች ቢደርሱም ሁኔታዎች አሁንም የከፉ ናቸው። ለረጅም ጊዜ የዘለቀው ዓመፅና የኢኮኖሚ ችግር የገበያዎችን ሁኔታ አናውጦታል፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ አድርገዋል እንዲሁም ዋነኛ የሸቀጦች ዋጋ ለአብዛኞቹ ሰዎች የማይቀመስ እንዲሆን አድርገዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም የምግብ ዋስትናና የተመጣጠነ ምግብ ዳይሬክተር የሆኑት ዣን ማርቲን ባውር በሱዳን ውስጥ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ረሀብ እየተከሰተ መሆኑን ገልጸዋል:: “ሰዎች ለወራቶች ምግብ ማግኘት የሚችሉበት አጋጣሚ በጣም አነስተኛ በመሆኑ እየደከሙ ነው” ብለዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም በሱዳን ውስጥ እጅግ ረሃብ የከፋባቸውን አካባቢዎች ለመድረስ አስቸጋሪ የሆኑ ቦታዎች ላይ ቋሚ እና የማያቋርጥ የምግብ እርዳታ ለማድረግ ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል::
የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም በቅርቡ በጦርነት በፈራረሰችው ሱዳን ውስጥ በረሃብ አደጋ ለተጠቁ ከ800ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች የምግብ እርዳታ ሰጥቷል። ይህ በእንዲህ እያለ በሱዳን ጦር የሚመራው መንግሥት ይህ ሪፖርት ከመውጣቱ በፊት ከኮሚቴው ጋር ትብብሩን ማቋረጡን ሮይተርስ ዘግቧል። የሱዳን የግብርና ሚኒስትር አቡ በከር አል በሽሪ ሪፖርቱ “የሱዳንን ሉአላዊነት የሚጋፋ እና አሳማኝ መረጃዎችን ያልያዘ” በሚል ውድቅ ማድረጋቸው ነው የተነገረው። የግብርና ሚኒስትሩ ከሰሞኑ ታህሳስ 23 2024 ቀን በፃፉት ደብዳቤ አይ ፒ ሲ የሱዳንን ሉዓላዊነትና ክብር የሚያዳክሙ አስተማማኝ ያልሆኑ ሪፖርቶችን እያወጣ ነው ::
አለማቀፉ የረሃብ ገምጋሚ ኮሚቴ (ኤይ ፒ ሲ) በበኩሉ ለሱዳናውያን የከፋ ረሃብ ውስጥ መግባት የሀገሪቱ ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሉን ተጠያቂ አድርጓል:: አይ ፒ ሲ በምዕራባውያን ሀገሮች የሚደገፍና በ19 ትላልቅ ሰብዓዊ ድርጅቶችና መንግሥታዊ ተቋማት የሚተዳደር ገለልተኛ አካል ነው ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደገለጸው ደም መፋሰሱን የሚያቆም፣ ለድርድር ስምምነት መንገድ የሚጠርግ፣ የተኩስ አቁም ስምምነት የሚያካሂድ እና የሱዳንን አንድነት የሚያስጠብቅ በሱዳን የሚመራ ተአማኒ የሆነ የፖለቲካ ሂደት ያስፈልጋል ። ይህ ካልሆነ ግን የዚህ ጦርነት መዘዙ ለሱዳን እና ለአካባቢው ሁሉ ከባድ ይሆናል::
በሌላ በኩል አናዶሉ እንደዘገበው ከሰሞኑ ጄኔራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን ሀገሪቱ ከብሪታንያ ቅኝ ግዛት ነፃ የወጣችበትን 69ኛ ዓመት አስመልክቶ በሱዳን መንግሥት ቴሌቪዥን ብቅ ብሎ ፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሎችን ይዞ ወደ ቅድመ-ጦርነት ሁኔታ መመለስ አይቻልም ብለዋል:: ይሁን እንጂ “ጦርነቱን የሚያቆምና ሰላማዊ ሰዎች በሰላም ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ የሚያደርግ ማንኛውም እውነተኛ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።”ሁኔታው ከሚያዝያ 15 ቀን 2023 በፊት ወደነበረበት ሁኔታ ሊመለስ አይችልም። እነዚህን ነፍሰ ገዳዮች፣ ወንጀለኞች እና ደጋፊዎቻቸውን በሱዳን ህዝብ መካከል እንደገና መቀበል አንችልም” ብለዋል አል-ቡርሃን ስለ አርኤስኤፍ በማስመልከት ሲናገሩ:: አክለውም የሱዳን ህዝብ በአርኤስኤፍ ሚሊሺያዎች ለግድያ፣ ለረሃብ፣ ለመፈናቀል ለመብት ጥሰት ተዳርጓል ብለዋል።
በጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሀን እና በቀድሞ ምክትላቸው በሞሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ በሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች (አር ኤስ ኤፍ ) መካከል የሥልጣን ሽኩቻ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ ወደ 25ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ተገድለዋል ፤እንዲሁም ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል። በሁለቱ ተቀናቃኞች መካከል ተኩስ አቁም ለማድረግ በአሜሪካ፣ በሳዑዲ አረቢያ እና በበርካታ ሀገሮች የተደረገው ጥረትም እስካሁን አልተሳካም።
(ሳባ ሙሉጌታ )
በኲር የጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም