የካሳ አከፋፈል ሥርዓት

0
570

በሕገ-መንግስሥቱ አንቀጽ 40 ንኡስ ቁጥር ስምንት መርህ ተግባራዊ ለማድረግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 455/97 በአንቀጽ ሰባት ላይ የካሳ መሰረት እና መጠን ሰፍሯል:: በዚህ ርእስ ስር በአንቀጽ ስምንት የማፈናቀያ ካሳ በሚል ርዕስ ስር ሁለት ዓይነት የካሳ ክፍያዎች እንዳሉ ተደንግጓል::

ካሳ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ከነባር ይዞታው ለሚለቅ ሰው በቅድሚያ ተመጣጣኝ ምትክ ክፍያ እና ቦታ የማግኘት ሕገ- መንግሥታዊ መብት ስላለው እነዚህ ሕጎች እንደወጡ ያትታል:: በሕጉ በአንቀፅ ሰባት መሰረት የካሳ መሰረት ሆኖ የሚወሰደው እንዲለቅ በሚመለከተው አካል የተወሰነበት ባለይዞታ በመሬቱ ላይ ለሚገኘው ንብረት እና በመሬቱ ላይ ላደረገው ቋሚ ማሻሻል የሚከፈል  ነው::

በሚለቀቀው የመሬት ይዞታ ላይ ለሚገኝ ንብረት የሚከፈል ካሳ ንብረቱን ባለበት ሁኔታ ለመተካት የሚያስችል እንደሆነ በመርሁ ላይ ሰፍሯል::  በመሬት ላይ ለተደረገ ቋሚ መሻሻል የሚከፈለው ካሳ መሰረቱ በመሬቱ ላይ የዋለው ገንዘብ እና የጉልበት ዋጋ የሚተካ የካሳ መጠን ነው:: እንዲለቅ እየተደረገ ያለው ንብረት መልሶ በመትከል አገልግሎት ለመስጠት የሚችል በሚሆንበት ጊዜ ከፍ ብለው ከተጠቀሱት ንብረቱን ባለበት ሁኔታ የሚተካ ካሳ እና በመሬቱ ለተደረገ ቋሚ መሻሻል የወጣ ገንዘብን እና የጉልበት ዋጋ በካሳ መልክ ከሚከፈለው በተጨማሪ የንብረቱ ማንሻ፣ የማጓጓዣ እና መልሶ ለመትከል የሚጠይቀውን ወጪ እንዲሸፍን የሚከፈለው ካሳ ነው::

ይህም ማለት ለሁሉም ሰው ከይዞታው በመልቀቁ ምክንያት በመሬቱ ለሚገኝ ንብረት ካሳ የማግኘት መብት እንዳለው የሚያረጋግጥ ነው:: ለተደረገ ቋሚ መሻሻል እና መልሶ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ የሚከፈል ካሳ ግን እንደየ ሁኔታው እና የንብረቱ ዓይነት እየታየ የሚከፈል ካሳ ነው:: በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ሁለት የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ ለሚነሳው ቤት የሚከፈለው አነስተኛ የካሣ መጠን እንደየ ክልል ፣ እንደ አዲስ አበባ እና ድሬደዋ ተጨባጭ ሁኔታ የተለያየ ነው::

ሁሉም አካባቢዎች  በሚያወጡት ደረጃ /ስታንዳርድ/  መሰረት ቢያንስ ዝቅተኛውን የቤት ደረጃ ሊያስገነባ የሚችል መሆን አለበት::

በሌላ በኩል በመሬት ይዞታው ላይ ለተደረገ ቋሚ ማሻሻል የሚከፈል ካሣም በመሬቱ ላይ የዋለውን ገንዘብ እና የጉልበት ዋጋ የሚተካ ክፍያ በአካባቢው ወቅታዊ ዋጋ ተሰልቶ ይሆናል::

 

የልማት ተነሽ ካሳ እና ምትክ ቦታ

በቋሚነት ስለሚነሳ የገጠር መሬት ባለይዞታ የሚሰጥ ካሳ እና ምትክ ቦታ በተመለከተ የመሬት ይዞታውን በቋሚነት እንዲለቅ የሚደረግ የገጠር መሬት ባለይዞታ እንደ አካባቢው ሁኔታ ከተወሰደበት መሬት ተመጣጣኝ ምርት የሚያስገኝ ምትክ መሬት ይሰጠዋል::

ተመጣጣኝ ምትክ መሬት የሚሰጠው ከሆነ መሬቱን ከመልቀቁ በፊት በነበሩት ሦስት ዓመታት ውስጥ በየዓመቱ ከመሬቱ ሲያገኝ ከነበረው ከፍተኛውን የአንድ ዓመት ገቢ በወቅታዊ ዋጋ ተሰልቶ የልማት ተነሽ ካሳ ይከፈለዋል ማለት ነው:: ተመጣጣኝ ምትክ መሬት የማይሰጠው ከሆነ መሬቱን እንዲለቅ ከመደረጉ በፊት በነበሩት ሦስት ዓመታት ውስጥ ከመሬቱ ሲያገኝ የነበረውን ከፍተኛ ዓመታዊ ገቢ በ15 ተባዝቶ የልማት ተነሽ ካሳ መከፈል እንዳለበት ሕጉ ያስቀምጣል ::

ለምሳሌ በአማራ ክልል በተሻሻለው የክልሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 58 ንዑስ አንቀጽ ሰባት እና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባወጣው ደንብ ቁጥር 472/2012 ዓ.ም  አንቀጽ 48 ንዑስ አንቀጽ አንድ ስር በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት  መመሪያ ቁጥር 44/2013ን አውጥቷል ::

በጊዜያዊነት ለሚለቀቅ መሬት የሚከፈል የልማት ተነሽ ካሣ በማንኛውም ሁኔታ በዘላቂነት ከሚከፈል የልማት ተነሽ ድጋፍ መብለጥ የለበትም:: የዚህ ንዑስ አንቀፅ ዝርዝር አፈፃፀም ይህን አዋጅ ለማስፈጸም በወጣው ደንብ ይወሰናል::

 

በጊዜያዊነት ስለሚነሳ

የገጠር መሬት ባለይዞታ የሚሰጥ የልማት ተነሽ ድጋፍ ካሳ የሚባለው ይዞታውን ለተወሰነ ጊዜ እንዲለቅ ለሚደረግ የገጠር መሬት ባለይዞታ ከሆነ መሬቱ ከመለቀቁ በፊት በነበሩት ሦስት ዓመታት ውስጥ ያገኘው ከፍተኛ ዓመታዊ ገቢ መሬቱ እስከሚመለስ ድረስ ባለው ጊዜ ታስቦ የልማት ተነሽ ድጋፍ ካሣ ይከፈለዋል::

የሚከፈለው የልማት ተነሽ ካሣ መሬቱ የነበረውን ምርታማነት ለመመለስ የሚወስደውን በአካባቢ የግብርና ተቋም የሚወሰን ተጨማሪ ጊዜ ታሳቢ ማድረግ አለበት:: መሬቱ ተመልሶ በፊት ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት መስጠት የማይችል ከሆነ ደግሞ በቋሚነት እንደለቀቀ ተቆጥሮ የልማት ተነሽ ካሳ ወይም ምትክ ቦታ ይሰጠዋል:: መሬቱ በጊዜያዊነት በተለቀቀበት ጊዜ የተከፈለ የልማት ተነሽ ካሣ በቋሚነት እንደለቀቀ ተቆጥሮ ከሚከፈል ካሳ ተቀንሶ ለተነሺው ልዩነቱ ይሰጠዋል::

 

በቋሚነት ለሚነሳ

ከቦታው በቋሚነት ለሚነሳ የከተማ መሬት ባለይዞታ ምትክ ቦታ ወይም መኖሪያ ቤት በግዥ እንዲያገኝ ይመቻቻል:: የሚሰጠው ምትክ ቦታ ከሆነ በቦታው ቤት እስኪገነባ ለሁለት ዓመት የሚኖርበት ቤት ያለኪራይ ይሰጠዋል ወይም ለፈረሰበት ቤት በወቅታዊ የኪራይ ግምት ተሰልቶ የሁለት ዓመት የልማት ተነሽ ካሣ ይከፈለዋል:: የሚሰጠው ምትክ ቤት ከሆነ ለፈረሰበት ቤት በወቅታዊ የኪራይ ግምት ተሰልቶ የአንድ ዓመት የልማት ተነሽ ካሣ ይከፈለዋል::

የልማት ተነሽ ካሣ መጠን ቢያንስ የአካባቢውን ዝቅተኛ የቤት ኪራይ ለመከራየት ከሚያስችል ያነሰ መሆን የለበትም::ተነሺዎች በነበሩበት አካባቢ ለነበራቸው የማህበራዊ ትስስር መቋረጥና ለሚደርስ የሥነ-ልቦና ጉዳት ማካካሻም ይከፈላቸዋል::

የሚለቀቀው የሊዝ ይዞታ ከሆነ የሚሰጠው ምትክ ቦታ ከተለቀቀው መሬት በደረጃ እና በስፋት ተመጣጣኝ መሆን አለበት:: ይህንን ለመፈፀም የማይቻል ከሆነ አማራጭ የአፈፃፀም ሁኔታ እንደየ ከተሞቹ ተጨባጭ ሁኔታ በመመሪያ የሚወሰን ይሆናል::

 

ገቢ በመቋረጡ ስለሚከፈል የኢኮኖሚ ጉዳት ካሣ

ለሕዝብ ጥቅም ተብሎ ቦታ እንዲለቀቅ ከመደረጉ ጋር በተያያዘ ከይዞታው ሳይነሳ በጊዜያዊነት ወይም በዘላቂነት ሲያገኝ የነበረው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለተቋረጠበት ሰው የጉዳት ካሳ ይከፈላል:: የካሳውን መጠንና ዓይነት ለመወሰን ከመቀጠር፣  ከንግድ፣ ከኪራይ፣ ከእርሻ ውጪ መሬትን በመጠቀም የሚገኝ ገቢ እና የመሳሰለው ዓመታዊ የተጣራ ገቢን ታሳቢ ሊያደርግ ይችላል::

 

ከገጠር ወደ ከተማ ለተካለለ የከተማ አካባቢ ባለ ይዞታ

ከገጠር ወደ ከተማ በተካለለ የአርሶ አደር ይዞታ ከመኖሪያ ቤቱ ለሚነሳ ባለይዞታ በክልል፣ በአዲስ አበባ እና በድሬደዋ ካቢኔ የሚወሰን ሆኖ የከተማውን ደረጃ/ስታንዳርድ/ በመጠበቅ ከ አምስት መቶ ሜትር ካሬ ያልበለጠ የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ መሰጠት አለበት::

ዕድሜው 18 ዓመት እና በላይ ለሆነው የባለይዞታውን ገቢ በመጋራት አብሮ የሚኖር አርሶ ወይም አርብቶ አደር ልጅ የቦታ ስፋቱ የከተማውን አነስተኛ የመሬት ይዞታ ደረጃ የሆነ ለመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ መሰጠት አለበት:: ለመኖሪያ የሚሰጠው ጠቅላላ የቦታ መጠን ከነበረው የመኖሪያ ይዞታ በላይ መሆን የለበትም:: የመኖሪያ ይዞታ መጠን የባለ ይዞታው መኖሪያ ቤት ያረፈበትና የአጥር ግቢውን ይጨምራል::

 

ንብረት ስለመገመት

እንዲለቀቅ በሚፈለግ መሬት ላይ ለሚገኝ ንብረት ካሣ የሚወጣውን ሀገር አቀፍ ቀመር መሠረት በማድረግ በተመሰከረለት የግል ድርጅት ወይም ግለሰብ አማካሪዎች ይገመታል::

የካሣውን መጠን የሚገምት የተመሰከረለት የግል ድርጅት ወይም የግል አማካሪዎች ከሌሉ ራሱን የቻለ በመንግሥት በተቋቋመ ተቋም ይገመታል::

የካሣውን መጠን የሚገምት ድርጅት ከሌለ የሚለቀቀው መሬት እንደሚገኝበት አካባቢ የሚመለከተው የወረዳ ወይም የከተማ አስተዳደር ተገቢው ሙያ ያላቸው አባላት የያዘ ገማች ኮሚቴ በማቋቋም የሚገመት ይሆናል::

የሚነሳው ንብረት የተለየ እውቀት የሚጠይቅ ሲሆን ደግሞ አግባብ ባለው የመንግሥት ወይም የግል ድርጅት ሊገመት ይችላል::

የሚነሳው ንብረት የመንግሥት መሠረተ ልማት ወይም የአገልግሎት መስመር ከሆነ የካሣ ግምቱ የሚዘጋጀው በንብረቱ ባለቤት ይሆናል::

የካሣ ግምት የሚሰላበት ነጠላ ዋጋ ቢበዛ በየሁለት ዓመቱ መከለስ አለበት።

ይህም ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት ፣ ካሣ የሚከፈልበት እና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ለመወሰን የወጣ አዋጅ በቁጥር 1161/2011 አንቀጽ 11 እስከ 17 በግልጽ ተደንግጓል።

የመረጃ ምንጮቻችን ስክሪብድ ዶት ኮም፣ አቢስኒያ ሎው እና ሎው ኢትዮጵያ ኮሜንት ናቸው::

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here