የኢትዮጵያ ወራት ከሕዝቡ ባህል፣ ትውፊት እና ታሪክ ጋር የየራሳቸው ቦታ አላቸው። በተለይ ደግሞ ታሪክ ሲወሳ የካቲት እና ግንቦት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ትላልቅ ታሪካዊ ክስተቶችን ይዘው ይገኛሉ። የየካቲትን በመጀመር ታሪክን ወደ ኋላ እንዳስስ።
የካቲት አድዋን የመሰለ የድሎች ድል ያስመዘገብንበት ወር ነው፣ ከ40 ዓመታት በኋላ የካቲት ወር ላይ አድዋ ላይ የተሸነፈው ፋሺስት ጣሊያን የአዲስ አበባውን ጭፍጨፋ በመፈፀም የበቀል ግፍ ፈፀመ። ግራዚያኒን ለመግደል የተወረወረው ቦምብ ግራዚያኒን ቢያቆስለውም አልገደለውም። ነገር ግን በዚህ የጀግኖች አርበኝነት የተደናገጠው ጣሊያን ምላሽ በሚል በመቶ ሺዎች ንፁሃን ኢትዮጵያውያን ላይ የወሰደው የጭካኔ እርምጃ በታሪክ ውስጥ የማይሽር ጠባሳን አኑሯል። በዚህ ወቅት ለሕዝባቸው መበደል ጨፍጫፊውን ያወገዙት፣ ለነፃነት ሲሉ በግፈኛው ተገድለው ሰማእት የሆኑት የታላቁ የአቡነ ጴጥሮስ ገድል የተከወነው በዚህ በየካቲት ወር ነበር።
ፋሽስቱን በአርበኝነት ይፋለሙትና መቀመጫ መቆሚያ ያሳጡት የጦር አዝማቾች ራስ ደስታ ዳምጠው እና ደጃዝማች በየነ መርዕድ በጀግንነት የፋሺስት ኢጣልያ ሠራዊትን በዝዋይ አካባቢ ሲፋለሙ ህይወታቸውን የገበሩበት ክስተት የተመዘገበ የካቲት 16 ቀን 1929 ዓ.ም ነበር።
በግራዚያኒ የሚመራው የፋሽስቱ ጦር ከእነዚህ የጦር መሪዎች አርበኞች ጋር ሲፋለም የማታ ማታ ድል ቀናው። ሁለቱም ኢትዮጵያውያን አዝማቾች ሕይወታቸውን በዚህ ዕለት ነበር። ፋሽስቶቹ ራስ ደስታን ከያዟቸው በኋላ በጥይት ደበደቧቸው፡፡ እነርሱ ሞተው ህይወት ለእኛ የሰጡንን ጀግኖቻችን እንዲህ ሞተውም ሲዘከሩ ይኖራሉ።
የካራማራው ድል ኢትዮጵያን መዳፈር መሪር ዋጋ እንደሚያስከፍል ዳግም የተረጋገጠው የኢትዮጵያ ሠራዊት በሶማሊያ ወራሪ ሠራዊት ላይ የካራማራን ድል የተቀናጀው በየካቲት ወር ነበር። የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም። ታላቋን ሶማሊያ ለመመስረት የዚያድ ባሬ ሰራዊት ኢትዮጵያን ወረረ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ልክ እንደ አድዋው የሀገሩን ዳር ድንበር ለማስከበር ወደ ድንበር ገሰገሰ።
በኢትዮጵያውያን የአየር ኃይልና የምድር ጦር ልዩ ወታደራዊ ቅንጅት የዚያድባሬ እብሪት ካራማራ ላይ የተነፈሰበት ወርሃ የካቲት ከአድዋ ድል በተጨማሪ ኢትዮጵያውያን ለነፃነት ውድ መስዋእትነት ከፍለው ታሪክ የፃፉበት ሌላው የድሎች ድል ነው።
በሌላም ረገድ የግራኝ አህመድን መጨረሻ ያረጋገጠው የመጨረሻው ፍጥምጥም የተከወነው የካቲት 23 1535 ዓ.ም መሆኑ የየካቲትን ታሪክ ብዙነት ያጠናክረዋል። ዐፄ ገላውዲዎስ ከፖርቹጋል ሰራዊት ጋር በመተባበር የግራኝ አህመድን ጦር ድል ነስተውታል፤ ግራኝ አህመድም በዚሁ እለት ዘንተራ በተባለ ሜዳ ላይ በተደረገው ከባድ ጦርነት ላይ ተገድሏል።
የሚንስትሮች መታገት
የካቲት ወር በኢትዮጵያ የአብዮት ፍንዳታ፣ የወታደሩ አመጽ ተስፋፍቶ አዲስ አበባ የሚገኙ የ4ተኛ ክፍለ ጦር፤ የጦር ሠራዊት፤ ዓየር ኃይል እና የዋና መሥሪያ ቤት ወታደሮች በከተማው ‘ቁልፍ’ ቦታዎችን በቁጥጥራቸው ሥር አዋሉ። ብዙዎችን የአክሊሉ ሀብተ-ወልድን ሚኒስቴሮች አስረው ያዙ። ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አቶ እንዳልካቸው መኮንን ለጠቅላይ ሚኒስትርነት እና ጄኔራል አቢይ አበበን የመከላከያ ሚኒስትር አድርገው ሾሙ። በወቅቱ አዲስ አበባ ላይ ሊካሄድ ተዘጋጅቶ የነበረው የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ስብሰባ በረብሻው ምክንያት ተሰርዞ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል።
የካቲት ወር ሌላ ድንቅ ታሪካዊ ክስተት የተስተናገደበት ትልቅ ወር ነው። ንግሥት ዘውዲቱ በአባታቸው በዐፄ ምኒልክ ዙፋን እንዲቀመጡ ከተደረገ በኋላ በጳጳሱ ተቀብተው ዘውድ የጫኑበት ታሪካዊ ወር ነው። በተያያዘም በዚሁ ወር የካቲት 4 ቀን 1909 ዓ.ም ልዑል ራስ ተፈሪ መኮንንም ታላቁን የሰሎሞን ኒሻን ተሸልመው ለአልጋ ወራሽነት የሚገባው ክብር እና ስርዓተ ጸሎት የተደረገበት ነበር።
የካቲት 1685 ዓ.ም ላይ የዐፄ ኢያሱ አድያም ሰገድ ልጅ ንጉሥ ዳዊት፣ ዐፄ ዳዊት አድባር ሰገድ ተብለው ዘውድ ጭነው ነግሠዋል። የካቲት 1790 ዓ.ም ላይ ደግሞ የ12 ዓመቱ ልጅ ሠርፀ ድንግል፣ አባታቸው ዐፄ ሚናስ ሲሞቱ መለክ ሰገድ ተብለው ነገሡ። ዐፄ ሠርፀ ድንግል የመንግሥት ሥራቸውን የሚሠሩት በእናታቸው በእቴጌ አድማስ ሰገድ ሥሉስ ኃይላ አማካይነት እንደነበር ታሪክ ያስረዳል።
ደጃዝማች ካሳ ኃይሉ ደረስጌ ማርያም ላይ የካቲት 5 ቀን 1847 ዓ.ም አቡነ ሰላማ ቀብተዋቸው ዘውድ ጭነው ዓፄ ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተባሉ። በሌላ ታሪክ የካቲት 12 የዐፄ ቴዎድሮስ ባለቤት እቶጌ ተዋበች መራሂት ኢትዮጵያ ተብለው የእቴጌነት አክሊል በእጨጌው አማካይነት በራሳቸው ላይ የደፉበት ወርም ነበር።
የካቲት ወር የታላላቆች ውልደት ዜና እረፍት የተከሰተበትም ነው። በየካቲት ወር 1889 ታላቁ የአድዋ ጦርነት የጦር አዝማች ራስ አሉላ እንግዳ(አባ ነጋ) ከዚህ አለም በሞት የተለዩበት ወር ነው። የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ባለቤት እቴጌ መነን አስፋው በዚህ ወር በተወለዱ 73 ዓመታቸው አረፉ። በየካቲት ወር 1555 ዓ.ም ላይ ኢትዮጵያን ለአራት ዓመታት በንጉሥነት የመሯት ዐፄ ሚናስ (ቀዳማዊ አድማስ ሰገድ) ያረፉበት ነው፡፡ ዐፄ ሚናስ የዐፄ ገላውዴዎስ ወንድምና የዐፄ ልብነ ድንግል ልጅ ነበሩ።
እውቁ ኢትዮጵያዊ የፊልም ሊቅ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ የተወለዱት በየካቲት ወር 1938 ዓ.ም በጎንደር ከተማ ነው።
ግንቦት እና የኢትዮጵያ ታሪክ
የእምባቦ ጠርነት
በታሪክ ድርሳናት እንደሰፈረው ደም አፋሳሽ ጦርነቶች የታዩበት ግንቦት, የንጉሥ ምኒልክ (በኋላ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ) እና የንጉሥ ተክለሃይማኖት ጦር እምባቦ ላይ ከባድ ውጊያ አድርጓል።
የደብረሊባኖስ እልቂት
የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ዘርፎ መነኮሳቱን በግፍ የጨፈጨፈውም በግንቦት ወር ነበር።
የግንቦቱ መፈንቅለ መንግሥት
ማክሰኞ ግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም የሀገሪቱ ምርጥ ጄኔራሎች እርስ በእርስ ጦርነት እየተሠቃየች ላለች ሀገራቸው መፍትሔ ያሉትን የሚተገብሩበት ቀን ነበር።
ይህ ወቅት የኢትዮጵያ ወታደሮች እና አመራሮቻቸው በጦርነት የተማረሩበት ወቅት ነበር። ከጀኔራሎቹም በላይ በእነመንግሥቱ ኃይለማርያም ይሁንታን ያገኘ ካድሬ ስለወታደራዊ ስትራቴጅ ለመተንተን የሚቃጣበት እና ጀኔራሎቹን ያማረረበት ወቅት እንደነበር እማኝነታቸውን ይሰጣሉ። በገፈፋና በግድ ጦር ሜዳ ይቀላቀሉ የነበሩ ወታደሮች በቁርጠኝነት ይዋጋ የነበረውን ሠራዊት መንፈስ እንደቀየሩት ታሪክን የኋሊት በማስታወስ፣ ይህ ሁሉ ውጥንቅጥ ያሳሰባቸው የጦሩ መሪዎች ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ከሥልጣን ካልተወገዱ ኢትዮጵያ የገባችበት ችግር ሊፈታ እንደማይችል አመኑ፤ መፈንቅለ መንግሥት ለማካሔድም እንደወጠኑ ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ፣ ‘አብዮቱና ትዝታዬ’፣ በተሰኘ መጽሐፋቸው ፅፈውታል።
አዲስ አበባና አስመራም የመፈንቅለ መንግሥት መሪዎቹ ማዕከል ሆኑ። ሆኖም የአዲስ አበባው ማታ ላይ እንዲሁም አስመራው ደግሞ ከአንድ ቀን በኋላ ግንቦት 9 ቀን 1981 ከሸፈ። አዲስ አበባ ውስጥ ሙከራውን ያደረጉት ጀኔራሎች ራሳቸውን ገደሉ፣ ተገደሉ፣ ታሰሩ። አስመራ ላይ ደግሞ ግንቦት 9 ቀን 1981ዓ.ም የ102ኛ አየር ወለድ ክፍለ ጦር በምሥራቅና በሰሜን የገጠማትን ጦርነት ሲመሩ የኖሩትን ጀኔራሎችን በማይታሰበው አረመኔያዊ ድርጊት አስመራን የደም አበላ አደረጋት።
በአጠቃላይ በመፈንቅለ መንግሥቱ ከ137 በላይ የጦሩ አመራሮች ታሰሩ። ከእነዚህ መካከልም 28 ጀኔራሎች፣ ከ20 በላይ ኮሎኔሎች፣ ከ20 በላይ ሻለቃዎች፣ ከ20 በላይ ሻምበሎች ይገኙበታል። ገንጣይ አስገንጣይ የሚባሉት ሳይቀሩ አንዳንዶቹ “የኢትዮጵያ መንግስት ቀኝ እጁን በግራ እጁ ቆረጠ!” ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ “ኢትዮጵያ የጦር መሃንዲሶቿን ገደለች፣ በላች” ብለው ጽፈውታል።
ግንቦት የታላላቅ ሰዎች ውልደት እዘና ዜና እረፍት ተመዘገበበት ወር ነው፡፡ ከመሪዎች የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚደንት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለ ማሪያም ፤ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ፣ ተወለዱበት ነው፡፡
በኢትዮጵያ የመጀመሪው አጭር ልብ ወለድ “የጉለሌው ሰካራም” ደራሲው ተመስገን ገብሬ ተወለደው በግንቦት ወር ነው፡፡ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ የሞቱት በዚህ ወር ነበር፡፡
በርካታ የታሪክ መፅሃፍት ደራሲው እና ጋዜጠኛው ጳውሎስ ኞኞ ያረፈውም በዚህ ወር ነበር፡፡
(መሠረት ቸኮል)
በኲር የግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም