ለአስር ደቂቃ ያህል ጠንካራ ወይም ከበድ ያለ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መስራት ደቂቅ ህዋሳትን ወደ ደምስር በመልቀቅ የተዳከሙ ዘረመል ወይም “ዲ ኤንኤ” በመጠገን የካንሰር እድገትን መግታት እንደሚያስችል ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡
በእንግሊዝ የኒውካስትል ዩንቨርሲቲ ተመራማሪዎች ባደረጉት ጥልቅ ጥናት እና ክትትል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጥቃትን በደም ስር ውስጥ የሚገኙ ህዋሳትን በማንቀሳቀስ እና ፍጥነታቸውን በመጨመር የተጐዳውን በመጠገን የካንሰር እድገትን እንደሚገታ ማረጋገጥ ችለዋል፡፡
የአካል ብቃት እንቅስቃሴው የደቂቅ ህዋሳት (ሞሎኪል) ቁጥርን ከመጨመሩ ባሻገር በደም ስር ውስጥ ዝውውራቸው እንዲጨምርም ያስችላል፡፡ ይህ በራሱ በተጠቃ አካል አቅራቢያ የሚገኝ እብጠትን በመቀነስ በደም ስር ውስጥ ጤናማ ዝዉውርን ያሰፍናል ነው ያሉት ተመራማሪዎቹ፡፡
የተመራማሪዎቹ ቡድን መሪ ዶ/ር ሳም ኦሬንጅ በጥናት እና ምርምሩ ስለተገኘው ግንዛቤ ሲያስረዱ የካንሰር ሴሎች እድገት እንዴት እንደሚገታ፣ እንደሚጠገን እና አንቀሣቃሽ ኃይል እንዴት እንደሚጠቀሙ በውል በመረዳት ለአዲስ ህክምና ወይም ፈውስ ለመሻት ተስፋ ሰጪነቱን ነው ያረጋገጡት፡፡
የምርምር ቡድኑ አባላት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በህዋስ ውስጥ የኃይል ቋቱ “ማይቶኮንዶሪያ” ህዋሳት አባላት እንቅስቃሴያቸው እንዲጨምር “ኦክስጂን” በብቃት እንዲጠቀሙ ማስቻሉን መገንዘባቸውንም ነው ያብራሩት፡፡
በመጨረሻም ተመራማሪዎቹ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በአንጀት ካንሰር የመያዝ አደጋን 20 በመቶ እንደሚቀንስ ነው ግምታቸውን ያስቀመጡት፡፡ ለዚህም ብስክሌት መንዳት፣ የአትክልት ስፍራ መኮትኮት፣ ማፅዳት እና የመሳሰሉ እንቅስቃሴዎች እንደሚመከሩ ነው ያስገነዘቡት፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የጥር 11 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


