የክለቦች ሽሚያ እና የተጫዋቾች መዳረሻ

0
164

በእግር ኳሱ ዓለም ኢትዮጵያን ጨምሮ በአውሮፓ እና በሌሎች አብዛኞቹ ሀገራት የተጫወች ዝውውር የሚፈፀመው በክረምት እና በጥር ወቅት ነው:: የጥር የተጫዋቾች ዝውውር ክለቦች የቡድናቸውን ክፍተት ወይም ቀዳዳ ለመሸፈን የሚጠቀሙበት በውድድር ዓመቱ አጋማሽ የሚከናወን ዝውውር ነው::

ይህ የዝውውር ወቅት ለአንድ ወር ብቻ የሚቆይም ነው:: በክረምቱ የተጫዋቾች ዝውውር ግን ክለቦች አዲስ የረዥም ጊዜ  ዕቅድ የሚነድፉበት፣ እንደገና ቡድናቸውን የሚያደራጁበት እና ለዝውውር በርካታ መዋዕለ ንዋያቸውን የሚያፈሱበት በመሆኑ በርካታ ተጫዋቾች የሚዘዋወሩበት ወቅት ነው::

ክለቦች በክፍያ ወይም የውል ስምምነታቸውን የጨረሱትን ተጫዋቾች በነፃ ያስፈርማሉ:: የዘንድሮው የአውሮፓ የተጫዋቾች የዝውውር ወቅት ሰኔ ሰባት ቀን 2016 ዓ.ም ተከፍቷል:: ነሐሴ 27 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ስካይ ስፖርት አስነብቧል:: ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም በአምስቱ ታላላቅ ሊጎች  የሚገኙ ክለቦች የሚፈልጓቸውን ተጫዋቾች የሚያስኮበልሉ ይሆናል::

ተጫዋቾችም ህልማቸውን ለመኖር ህልማችን ናቸዉ ወደሚሏቸው ክለቦች መዳረሻቸውን ያደርጋሉ:: ባሳለፍነው ዓመት በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር ወቅት በአምስቱ ታላላቅ ሊጎች የሚገኙ ክለቦች በአጠቃላይ ከአራት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ፓውንድ ገንዘብ በላይ ወጪ ማድረጋቸውን ጎል ዶት ኮም አስነብቧል::

ታላላቆች የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች አርሴናል፣ ቸልሲ፣ ሊቨርፑል፣ ማንቸስተር ሲቲ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ እና ቶትህናም ሆትስፐርስ በድምሩ ከአንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ውጪ አድርገዋል:: እንደ ጎል ዶት ኮም መረጃ ጁዲ በሊንግሀም ከቦርሺያ ዶርትመንድ ወደ ሪያል ማድሪድ፣ ሀሪኬን ከቶትህናም ወደ ባየርን ሙኒክ እና ሞይሰስ ካይሴዶ ከብራይተን ወደ ቸልሲ  ባሳለፍነው ክረምት ከተፈፀሙ ታላላቅ ዝውውሮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው::

ኪሊያን ምባፔ ምንም እንኳ በነፃ ዝውውር ከፓርሰን ዥርማ ወደ ሪያል ማድሪድ ቢያቀናም ከተጠባቂ የዘንድሮ ዝውውሮች መካከል እንዱ እንደነበር አያጠያይቅም:: እኛም የተለያዩ የአውሮፓ ጋዜጦችን እና መጽሔቶችን ዋቢ በማድረግ በዘንድሮው የክረምቱ የዝውውር ወቅት ይፈጸማሉ ተብለው የሚጠበቁ ዝውውሮችን እንዳስሳለን::

የስፔኑ ኃያል ክለብ ብራዚላዊውን ታዳጊ ኢንድሪክንም ከፓልሜራስ በይፋ ማስፈረሙ አይዘነጋም:: አዲሱን የጋላክቲኮ ስብስብ እየፈጠሩ የሚገኙት ፕሬዝደንት ፍሎረንቲኖ ፔሬዝ በአልፎንሶ ዴቪስ ፍላጎት ካሳዩ ውለው አድረዋል:: የ23 ዓመቱ የግራ ተመላላሽ በስፍራው ካሉ ምርጥ የአውሮፓ ባለተሰጥኦዎች መካከል ስለመሆኑ አያጠያይቅም::

ካናዳዊው ተከላካይ በ2025 እ.አ.አ ነው ከባቫሪያኑ ክለብ ባየርን ሙኒክ ጋር የተፈራረመው ውል የሚጠናቀቀው:: ሪያል ማድሪድ በዚህ ክረምት የመሀል ተከላካይ ለማስፈረም ዕቅድ ባይኖረውም የግራ ተመላላሹን ማጣት እንደሌለባቸው ግን ፍሎረንቲኖ ፔሬዝ ያምናል::

እናም ሎስባልንኮዎች አልፎንሶ ዴቪስን ለማስፈረም አንድ ተጫዋች የዝውውሩ አካል ለማድረግም አስበዋል:: የጀርመኑ ክለብም ተጫዋቹን በቀጣይ ዓመት በነፃ ላለማጣት በዚህ ክረምት ይሸጠዋል ተብሎ ይጠበቃል:: ሪያል ማድሪድ ለዝውውሩ ከ30 ሚሊዮን ፓውንድ ገንዘብ በላይ አያወጣም ተብሏል:: ዴቪስ ሳንቲያጎ ቤርናቢዮ ከደረሰ የፌርላንድ ሜንዲ ጥሩ ተፎካካሪ ይሆናልም ተብሎ ይገመታል::

በዚህ ክረምት ክለቡን ይለቃሉ ተብለው ከሚጠበቁ ተጫዋቾች መካክል ተካቷል፤ ቪክቶር ኦስሜህን:: ናይጀሪያዊው ግብ አነፍናፊ በ2022/23 የውድድር ዘመን ከኔፕልሱ ክለብ ናፖሊ ጋር የሴሪኤውን ዋንጫ ማንሳቱ ይታወሳል:: የ25 ዓመቱ የፊት መስመር ተሰላፊ ከናይጀሪያ ሌጎስ ተነስቶ በጀርመን ቡንደስ ሊጋ እና በፈረንሳይ ሊግ አንድ ጎልብቶ በጣሊያን ሴሪኤ ያንፀባረቀ ድንቅ አጥቂ ነው::

ናፖሊን ከተቀላቀለበት 2020 እ.አ.አ ጀምሮ በ133 ጨዋታዎች ተሰልፎ 176 ግቦችን አስቆጥሯል:: ኦስሜህን ናፖሊ ከ33 ዓመታት በኋላ የሴሪኤውን ዋንጫ ሲያሳካ ግንባር ቀደም መሪ ተዋናይ ከነበሩ ኮከቦች መካከል አንዱ እንደነበር አይዘነጋም:: በ2023 የአፍሪካ ኮከብ ተጫዋች ሲሆን በፈረንሳይ ዓመታዊ የተጫዋቾች ሽልማት ምርጥ አስር ውስጥ የገባ የመጀመሪያው ናይጀሪያዊም ነው::

ኦስሜህን በፍጥነቱ፣ በአጨራረሱ እና ለቡድን ጓደኞቹ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ክህሎቱ ይታወቃል:: በአየር ላይ ኳሶች የበላይነት በመውሰድም የሚታወቅበት ብቃቱ ነው:: የጣሊያኑ ክለብ ይህንን ድንቅ አጥቂ በክለቡ ለማቆየት ጥረት እያደረገ ቢሆንም ተጫዋቹ ግን ልቡ መሸፈቱን መረጃዎች ወጥተዋል::

ታላላቅ የእንግሊዝ ክለቦችም ዐይናቸውን አሳርፈውበታል:: አርሴናል፣ ቸልሲ እና ማንቸስተር ዩናይትድ ደግሞ ፈላጊዎቹ ናቸው:: ናይጄሪያዊው ኮከብ በ2023 ታህሳስ ወር አዲስ የሦስት ዓመት ውል ከናፖሊ ጋር መፈረሙ የሚታወስ ነው:: ታዲያ ኦስሜህን ለማስፈረም የሚፈልግ ክለብ 111 ሚሊዮን ፓውንድ የውል ማፍረሻውን መክፈል እንደሚጠበቅበት ናፖሊ ማሳወቁ ተዘግቧል::

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በጀርመን ቡንደስሊጋ ከታዩ ምርጥ ባለተሰጥኦ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው፤ ጀርመናዊው የ21 ዓመቱ የጨዋታ አቀጣጣይ ፍሎሪያን ዊርትዝ:: የ21 ዓመቱ ኮከብ ባየርን ሊቨርኩሰን ለመጀመሪያ ግዜ የቡንደስ ሊጋውን ዋንጫ እንዲያነሳ ከፍተኛውን ድርሻ ከተወጡት ተጫዋቾች መካከል ይጠቀሳል:: ጀርመን የአውሮፓ ዋንጫውን ለማንሳት ከምትተማመንባቸው ተጫዋቾች መካከልም አንዱ ነው::

ወጣቱ ባለተሰጥኦ በባየርን ሊቨርኩሰን ቤት ቀሪ የሁለት ዓመታት ውል ቢኖረውም ታላላቅ የአውሮፓ ክለቦች የዝውውር ራዳር ውስጥ ገብቷል:: ሪያል ማድሪድ፣ ባየርን ሙኒክ፣ ማንቸስተር ሲቲ፣ ሊቨርፑል፣ ቸልሲ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ እና ኒውካስትል ዩናይትድ ተጫዋቹን ለማስኮብለል በባይ አሬና ስቴዲየም ሰማይ ስር እያንዣበቡ መሆናቸውን የዘጠና ደቂቃ መረጃ ያሳያል:: ባየርን ሊቨርኩሰንም ከተጫዋቹ ዝውውር 130 ሚሊዮን ፓውንድ ገንዘብ ማግኝት እንደሚፈልግ ተዘግቧል::

ኒውካስትል ዩናይትድ የፈረንጆች አዲስ ዓመት 2024 ከገባ በኋላ አስደንጋጭ የገንዘብ ኪሳራ እንደደረሰበት መረጃዎች አመልክተዋል:: በሳውዲ ባለሀብቶች የሚዘወረው ክለብ ከፍተኛ የገንዘብ ቀውስ ውስጥ መግባቱን ተከትሎ በዚህ ክረምት ተጫዋች ለመሸጥ ይገደዳል:: ክለቡ በሳውዲ ባለሀብቶች ከተያዘ ጀምሮ ምንም እንኳ ሜዳ ላይ መነቃቃት ቢታይበትም የገንዘብ ኪሳራ ገጥሞታል::

ችግሩን ለመቅረፍም ከፍተኛ ገንዘብ የሚያወጣለትን አንድ ተጫውች ለመሸጥ አስቧል:: እንደ ጎል ዶት ኮም መረጃ ብራዚላዊው አማካይ ቡሩኖ ጉማሬሽ ነው ጄምስ ፓርክ ሊለቅ የሚችለው:: የ26 ዓመቱ የመሀል ሜዳ ሞተር በቴክኒክ ችሎታው፣ ታታሪነቱ እና ፈጠራው በስፍራው በዓለም ላይ ካሉ ምርጥ ተጫዋቾች ውስጥ አንዱ አድርጎታል:: አማካዩ እ.አ.አበ2022 ነበር ከፈረንሳዩ ክለብ ሊዮን ኒውካስትል ዩናይትድን የተቀላቀለው::

በሁለት ዓመታት የጄምስ ፓርክ ቆይታውም ኒውካስትል ዩናይትድን ተፎካካሪ አድርጎታል:: ጉማሬሽ በኒውካስትል ዩናይትድ ቤት ቀሪ የሁለት ዓመት ከግማሽ ውል ቢኖረውም በዚህ ክረምት እንደሚለቅ ይጠበቃል:: የተጫዋቹ ውል ማፍረሻ የተቀመጥው የጊዜ ገደብ ባለፈው ሳምንት መጠናቀቁ አይዘነጋም፡፡ አርሴናል እና ማንቸስተር ዩናይትድ የተጫዋቹ ፈላጊዎች ሲሆኑ የሰሜን ለንደኑ ክለብ አማካዩን ለማስፈረም በሚስጥር ገፍቶ መሄዱን የእንግሊዝ ጋዜጦች አስነብበዋል::

ሌልኛው የባየርን ሙኒኩ አማካይ ጆሹዋ ኪምሚችም ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ አሊያን ዛሬናን ይለቃል ተብሎ ይጠበቃል:: የ29 ዓመቱ ጀርመናዊ በ2015 ነበር ከሌላኛው የቡንደስ ሊጋ ክለብ አርቢ ላይብዚንግ የባቫሪያኑን ክለብ የተቀላቀለው:: ሁለገብ እንደሆነ የሚነገርለት ኪምሚች ተከላካይ፣ የተከላካይ አማካይ፣ የመሀል አማካይ እና የጨዋታ አቀጣጣይ ጭምር ነው:: የተጫዋቹ የውል ስምምነት በቀጣይ ዓመት ነው የሚጠናቀቀው::

የጀርመኑ ኃያል ክለብም ቀጣይ ዓመት በነፃ ላለማጣት ዘንድሮ የመውጫ በሩን ይከፍትለታል ተብሎ ይጠበቃል:: ሁለገቡን ባለተሰጥኦ አርሴናል፣ ባርሴሎና፣ ሊቨርፑል፣ ማንቸስተር ሲቲ እና ሪያል ማድሪድ ይፈልጉታል:: እንደ ዘጠና ደቂቃ መረጃ በቤርናቢዮ በሊንግሀም፣ ሞድሪች፣ ካማቪንጋ፣ ቫልቨርዴ፣ ዲያዝ፣ ቾአሚኒ፣ሴባዮስ እና ጉለርን የመሳሰሉት የመሀል ሜዳ ኮከቦች በስፍራው መኖራቸው ተጫዋቹ ሎስብላንኮዎችን የመቀላቀሉን ዕድል ያጠበዋል::

የአሰልጣኝ የርገን ክሎፕ ተተኪ የሆነው የአንፊልዱ አለቃ አርኔ ስሎት ከሰኔ ወር ጀምሮ ሥራውን በይፋ ጀምሯል:: አሰልጣኙ በመርሲሳይዱ ክለብ ስኬታማ ጊዜ ያሳለፉትን ሙሀመድ ሳላህ፣ ቨርጂል ቫንዳይክ እና ትሬንት አሌክስ አርኖልድን የማቆየት ትልቅ ኃላፊነት ተጥሎበታል:: በተለይ ደግሞ ግብጻዊው ኮከብ ሙሀመድ ሳላህ ከሊቨርፑል ጋር ለመለያየት እያሰበ ይገኛል:: የ32 ዓመቱ ግብ አዳኝ በቀዮቹ ቤት ያለው የውል ስምምነት የሚጠናቀቀው በ2024/25 እ.አ.አ ነው::

በጥብቅ በሳውዲ ፕሮ ሊግ ክለቦች የሚፈለገው ሳላህ የዝውውር ወቅቱ ሳይጠናቀቅ ወደ ሳውዲ አረቢያ ይጓዛል ተብሎ ይጠበቃል:: ባሳለፍነው የክረምቱ የዝውውር ወቅት በርካታ የሳውዲ ክለቦች ረብጣ ሚሊዮን ገንዘቦችን ይዘው ተጫዋቹን ለማስኮብለል ሞክረው እንደነበረ አይዘነጋም:: ሙሀመድ ሳላህ በ2017 እ.አ.አ አንፊልድ ሮድ ከደረሰ በኋላ የየርገን ክሎፕ ዋነኛ የማጥቂያ መሳሪያ ሆኖ አገልግሏል:: ከክለቡ ጋርም የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ እና የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ማንሳቱ ይታወሳል::

በተመሳሳይ በአንፊልድ ሮድ የኡራጋዊው አጥቂ ዳርዊን ኑኔዝ እጣ ፈንታም አጠያያቂ ሆኗል:: በ2022 የውድድር ዘመን ከቤኔፊካ 85 ሚሊዮን ፓውንድ ገንዘብ ወጥቶበት አንፊልድ የደረሰው ግዙፉ አጥቂ የተጠበቀውን ያህል መሆን አልቻለም:: በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በ54 ጨዋታዎች 18 ግቦችን ብቻ በማስቆጠሩ ለብዙ ትችቶች ተጋልጧል::

የአጨራረስ ችግር አለበት፣ በርካታ የግብ ዕድሎችን ያመክናል ተብሎ በደጋፊዎች የሚተቸው አጥቂው በአንፊልድ ደስተኛ አለመሆኑ ተሰምቷል:: በኢንስታግራም ገጹ በሊቨርፑል መለያ ያጋራቸውን ሁሉንም ምስሎች ማጥፋቱ ደግሞ ይበልጥ የተጫዋቹን የአንፊልድ ቆይታ ጥያቄ ውስት ከቶታል:: ይሄንን መረጃ የሰማው የካታለኑ ክለብ ባርሴሎና የ24 ዓመቱን አጥቂ ጉዳይ በትኩረት እየተከታተለው ይገኛል:: ባርሴሎና ኡራጋዊውን አጥቂ የረዥም ጊዜ የሮበርት ሎዋንዶስኪ ተተኪ ለማድረግ ዕቅድ እንዳለው ጎል ዶት ኮም አስነብቧል::

በአውሮፓ ምድር በርካታ ኮከቦችን በማፍራት ከሚታወቁት የእግር ኳስ አካዳሚዎች የቤኔፊካ የእግር ኳስ አካዳሚ ከቀዳሚዎች ተርታ ይሰለፋል:: ጃኦ ፊሊክስ፣ ኤንዞ ፈርናንዴዝ፣ ዳርዊን ኑኔዝ፣ ሩቤን ዲያዝ፣ ጎንካሎ ራሞስ እና ኤደርሰን ሞራየስን የመሳሰሉ ባለተሰጥኦ አፍርቷል:: የዚህ አካዳሚ ፍሬ የሆነው ጃኦ ኔቭስም በታላላቅ የአውሮፓ ክለቦች ዕይታ ውስጥ ገብቷል::

የ19 ዓመቱ ባለተሰጥኦ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት የቤኔፊካን ዋናውን ቡድን ስብሮ በመግባት አስደናቂ ብቃቱን አሳይቷል:: ድንቅ ብቃቱን የተመለከቱት ፓርሰን ዥርማ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ቸልሲ እና ሊቨርፑል የመሀል ሜዳው ባለተሰጥኦ ለማስኮብለል ፍላጎት ያላቸው ክለቦች ናቸው:: የላንክሻየሩ ክለብ ማንቸስተር ዩናይትድም መቶ ሚሊዮን ፓውንድ ገንዘብ አውጥቶ ተጫዋቹን የማስፈረም ከፍተኛ ፍላጎት አለው ነው የተባለው:: አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ በዚህ ክረምት የመሀል ስፍራ ተጫዋች ማስፈረም ዋናው ዕቅዳቸው መሆኑ ተዘግቧል::

የብሬንት ፎርዱን አጥቂ ኢቫን ቶኒን ለማስፈረም የለንደን ክለቦች አርሴናል፣ ቸልሲ እና ቶትህናም ፍላጎት ማሳየታቸውን መረጃዎች አመልክተዋል:: ብሬንትፎርድም መቶ ሚሊዮን ፓውንድ ገንዘብ የመሸጫ ዋጋው መሆኑን ይፋ አድርጓል::

የክሪስታል ፓላሱን የክንፍ ተጫዋች ማይክ ኦሊሴንም በርካታ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ዐይናቸውን አሳርፈውበታል:: ባየርን ሙኒክ፣ ቸልሲ እና ኒውካስትል ዩናይትድ ደግሞ በዝውውር ገፍተው ጥያቄ እያቀረቡ ያሉ ክለቦች መሆናቸውን እውቁ ጋዜጠኛ ፋብሪዚዮ ሮማኖ አስነብቧል::

እንደ ጣሊያናዊው ጋዜጠኛ መረጃ ሰማያዊ ለባሾች የ22 ዓመቱን ተጫዋች የግላቸው እንደሚያደርጉ ተማምነዋል:: ቸልሲዎች የ24 ዓመቱን ተከላካይ ትሬቨህ ቻሉባህን እና 25 ሚሊዮን ፓውንድ ገንዝብ ለማቅረብ ዕቅድ መያዛቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ ማን ወደ የትኛው ክለብ ያመራል? ከአምስቱ ታላላቅ ሊጎች የትኛው  ክለብ ስኬታማ ዝውውር ይፈጽማል? ጊዜ የሚፈታው ይሆናል::

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here