የክልሉን ሰላም ለመመለስ ሁሉን አቀፍ ርብርብ ያስፈልጋል

0
165

ከሁለት ዓመታት በላይ በዘለቀው የሰሜኑ ጦርነት የአማራ ክልል ከ522 ቢሊዮን ብር በላይ ቁሳዊ ውድመት እንደደረሰበት በአማራ ክልል በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ማቋቋም እና ግንባታ ፈንድ ጽ/ቤት በጥናት ማረጋገጡን አስታውቆ ነበር። በዚህ ጦርነት የጎበጠው ክልሉ ታዲያ ከሐምሌ 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለዳግም ግጭት መዳረጉ ችግሩን አባብሶታል። አንድ ዓመትን የተሻገረው ግጭቱ ሚሊዮኖችን ከትምህርት ገበታ አስቀርቷል፣ የጤና አገልግሎትን አስተጓጉሏል፣ የሰዎችን እንቅስቃሴም ገድቧል። ይህ ሁሉ ተደማምሮ ታዲያ የክልሉን ነዋሪዎች ለሰብዓዊ ቀውስ አጋልጧል። ምጣኔ ሀብታዊ ውድመትንም አስከትሏል። ለአብነትም የዕድገት መሠረት የሆነው ዓመታዊው የግብር አሰባሰብ አፈጻጸም (የ2016 ዓ.ም) 55 በመቶ በታች ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የክልሉን ሰላም ለመመለስ ተደጋጋሚ ሙከራዎች ቢደረጉም የክልሉን ሰላም ማስፈን አልተቻለም፣ አሁንም ድረስ አውዳሚው ግጭት እንደቀጠለ ነው። የክልሉን ሰላም ለማስፈን የሰላም ካውንስል (ምክር ቤት) መቋቋሙ ደግሞ ተስፋ የተጣለበት ነበር። ይሁን እንጂ “መንግሥት እና ፋኖን ለማቀራረብ ያደረኩት ጥረት ውጤት ማምጣት አልቻለም” ማለቱን ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል። በሂደቱም እንቅፋት እንደገጠመው አክሏል።

የብዙ ሀገራት ታሪክ እንደሚያስረዳው በተለያዩ ምክንያቶች አውዳሚ ጦርነትን አስተናግደዋል። ለአብነትም የወቅቱ  የዓለማችን  ኃያል  አሜሪካ የጦርነት ታሪክ አላት። የጥቁሮች መብት በከፍተኛ ደረጃ የተነፈገባት ሀገርም ነበረች። ይህንን ጥቁር ታሪክ ለመቀየር “ህልም አለኝ” በማለት ትግሉን የጀመረው ማርቲን ሉተር ኪንግ ባቀጣጠለው ዐቢዮት ታዲያ እኩልነት በተግባር እንዲተረጎም አደረገ። ሀገሪቱ ያሳለፈችውን የጦርነት ታሪኳንም  እንደ ትምህርት ቤት በመቁጠር ወደ ዕድገት ጎዳና መስፈንጠሪያ አድርጋዋለች። ለዚህ ዋናው መሠረትም መንግሥታት በተለዋወጡ ቁጥር የማይለዋወጡ ዘመን አይሽሬ ተቋማትን መገንበቷ ነው። ይህም የሕግ የበላይነትንና በተግባር እንዲተረጎም አድርጎታል።

በተመሳሳይ ብሔርተኝነት ባመጣው ጦስ አንድ ሚሊዮን ገደማ ዜጎቿን ያጣችው ሩዋንዳ በአሁኑ ወቅት በተሻለ ዕድገት ላይ ትገኛለች። በሀገሪቱ ተንሰራፍቶ የነበረው ብሔርተኝነት በአሁኑ ወቅት ጸያፍ ሆኗል። ማውራትም ከባድ ቅጣትን ያስከትላል።

በሌላ በኩል ከብሔር ፌደራሊዝም ፈጥነው ያልወጡ ሀገራት የከፋ አደጋ ገጥሟቸዋል። እስከ መፈራረስም ደርሰዋል። ለዚህ ደግሞ ዩጎዝላቪያ ተጠቃሽ ናት።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአማራ ክልል የተከሰተውን ግጭት ጨምሮ ኢትዮጵያ የገጠማት ፈተና ብሔርተኝነት የወለደው ነው። የብሔር ፌደራሊዝምን አስኳል አድርጎ የተቀረጸው  ሕገ መንግሥት ደግሞ የችግሩ ማዕከል ነው ሲሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ሐሳብ ያነሳሉ። በመሆኑም ከጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት የጸዳ እና ሁሉን አካታች ሕገ መንግሥት ወደ ሥራ ማስገባት ለሀገራዊ ችግሮች ፍቱን መድኃኒት ነው ሲሉ ይሞግታሉ።

በጦርነት ውስጥ የነበሩ ሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው የሕግ የበላይነትን ማስፈን፣ ዘመን ተሻጋሪ ተቋማትን መገንባት፣ የውይይት ባሕልን ማዳበር፣ ቁርጠኛ ፖለቲካዊ ውሳኔ ሰጪነት፣ ለሚገጥማቸው ችግር ወንድማማችነትን እና ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር የይቅርታ ባሕልን ማዳበራቸው ዋናዋናዎቹ የችግራቸው መሻገሪያ ስልቶች ናቸው።

በተመሳሳይ በርካታ ሀገራት አፍራሽነቱን በመረዳት ብሔር ተኮር የፖለቲካ እንቅስቃሴን እስከ ማገድም ደርሰዋል፡፡

በአማራ ክልል የተቋቋመው የሰላም ምክር ቤት ምንም እንኳን እስካሁን ውጤት ባያመጣም ጥረቱን ግን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በበኩላቸው መንግሥት ከታጠቁ ኃይሎች ጋር ንግግር እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ችግሩን በውይይት እና በድርድር ለመፍታት እየተሠራበት መሆኑን በቅርቡ በተካሄደው የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ መናገራቸው ይታወሳል።

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here