የአማራ ክልል ምክር ቤት ባካሄደው 6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 10ኛ መደበኛ ጉባዔ የክልሉን ጥቅል በጀት መርምሮ አፅድቋል፡፡ በዚህም መሠረት የአማራ ክልል መንግሥት የ2018 በጀት ዓመት ጥቅል በጀት 225 ቢሊዮን 453 ሚሊዮን 779 ሺህ 237 ብር ሆኖ ፀድቋል።
የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኃላፊ ጥላሁን መሐሪ (ዶ/ር) የሕዝብን አንገብጋቢ ችግሮችን ታሳቢ በማድረግ የካፒታል በጀት ድልድል መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
የድህነት ተኮር ሴክተሮች የበጀት ድርሻቸው የተሻለ እንዲሆን ተደርጎ መሠራቱን ያነሱት ዶክተር ጥላሁን የዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና ሀገራዊ አቅጣጫዎች ከግምት ውስጥ ስለመግባታቸውም አክለዋል።
የበጀት ድልድሉ የወጭ ፍላጎትን እና ተጨባጭ ሙያዊ አስተያየቶችን ተጠቅሞ የቢሮዎችን፣ የወረዳዎችን እና የከተማ አሥተዳደሮችን ድርሻ ክፍፍል በመወሰን በአሥተዳደር እርከኖች መካከል የሚጠበቀው ፍትሕዊነት እንዲኖር ታሳቢ ያደረገ እንደሆነም አብራርተዋል።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የሐምሌ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም