የክረምት ስጋቶች

0
180

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው ከ1998 እስከ 2017 እ.አ.አ ድረስ አራት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሰዎች በመሬት መንሸራተት ምክንያት ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ከ18ሺህ በላይ ሰዎች ህይታቸው አልፏል። ገደላማ፣  ኮረብታማ፣ ሸለቆዎች፣ በሰደድ እሳት የተቃጠለ መሬት፣ የደን መመናመን፣ ወንዞች የሚገኙባቸው አካባቢዎች… ለመሬት መንሸራተት ተጋላጭ እንደሆኑ መረጃው ያሳያል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በሰው ሠራሽ ምክንያት የሚከሰቱትን አደጋዎች መከላከል እንደሚቻል ያብራራል።

ኢትዮጵያ በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሮ አደጋዎች ውስጥ እያለፈች ትገኛለች። በድርቅ፣ በጎርፍ አደጋ እና አልፎ አልፎ በመሬት መንሸራተት… እየተፈተነች ነው። በዚህ ምክንያትም መተኪያ የሌለውን የሰውን ህይወት ቀጥፏል፣ ለአካል ጉዳት ዳርጓል፣ ከሞቀ ቤታቸው አፈናቅሏል፣ ንብረታቸውንም አውድሟል። ለዚህም አማራ ክልልን ጨምሮ ሰሞኑን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን እና በሌሎች አካባቢዎች የደረሱት አደጋዎች ማሳያዎች ናቸው።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ጎፋ ዞን፣ ገዜ ጎፋ ወረዳ ድንገተኛ የመሬት ናዳ የደረሰው ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ነበር። ይህም በአሳዛኝ ሁኔታ የበርካቶችን ህይወት ነጥቋል። በሌላ በኩል በሲዳማ ክልል ባጋጠመው የመሬት መንሸራተት እና ደራሽ ውኃ የሞቱ ሰዎች መኖራቸውን የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታውቋል። በክልሉ ማዕከላዊ ሲዳማ ዞን ወንሾ ወረዳ ግሸሬ ጉዱ ሞና ሆም ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በጣለው ከባድ ዝናብ ነበር ሐምሌ 21 ቀን 2016 ዓ.ም በሰው ህይወት፣ እንስሳት እና በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰው። በተመሳሳይ በአማራ ክልል በደሴ ከተማ አስተዳደር አራዳ ክፍለ ከተማ 03 መንበረ ፀሐይ ቀበሌ በተለምዶ ታች ጀሜ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ያጋጠመው የመሬት መንሸራተት በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 3፡00 ጀምሮ ያለማቋረጥ የዘነበውን ዝናብ ተከትሎ የመሬት መንሸራተት አደጋው መከሰቱን አሚኮ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪ አቶ ከድር ሙሐመድ ተናግረዋል፡፡ በአደጋው የመኖሪያ ቤታቸው ላይ ጉዳት እንደደረሰበት ገልፀዋል።

በተመሳሳይ የክረምት መግባትን ተከትሎ ስጋት ከሚፈጠርባቸው አካባቢዎች መካከል የደቡብ ጎንደር ዞን አንዱ ነው። የክረምቱን መግባት ተከትሎ ታዲያ የጎርፍ ስጋት እንዳለባቸው በዞኑ በደራ እና በሊቦ ከምከም ወረዳዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት የተከሰተው የጎርፍ አደጋ በሰዎች፣ በሰብል ልማት እና በእንስሳት ላይ ጉዳት ሲያደርስ እንደቆየ አርሶ አደሮቹ ለበኩር ተናግረዋል፡፡ ዘንድሮም የጎርፍ አደጋ ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት ውስጥ እንዳለባቸው በማንሳት በተወሰኑ ቦታዎች ላይም ችግሩ ተከስቷል ብለዋል።

አሁን ላይ እየጣለ ያለው ከባድ ዝናብ በሰብላቸው ላይ ጉዳት እንዳደረሰባቸው በሊቦ ከምከም ወረዳ ቡራ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር በላይነህ ውቤ ለበኩር ጋዜጣ በስልክ ተናግረዋል። በክረምት ወቅት ሁልጊዜም የጎርፍ አደጋ ስጋት እንዳለባቸውም አንስተዋል፡፡

አርሶ አደር በላይነህ በበጋ ወራት መሬታቸውን ሲያርሱና ሲያለሰልሱ ቆይተው ማሳቸውን በሰብል ሸፍነው ነበር። ነገር ግን ከባድ ዝናብ እየጣለ በመሆኑ በጎርፍ ምክንያት ሰብላቸው ለጉዳት ተዳርጓል። የእንስሳት መኖ እጥረትም እንዳጋጠመ አስረድተዋል። በዚህ ዓመት የተከሰተው ከባድ ዝናብ ከዛሬ ዐሥር ዓመት በፊት አጋጥሞ እንደነበር አስታውሰዋል። “ከልፋቴ ባሻገር፤ ለዘር እና ለአፈር ማዳበሪያ ያወጣሁት ገንዘብ ከንቱ ቀረ” በማለት ነው የገጠማቸውን ችግር ያስታወሱት።

የጎርፍ አደጋውን ለመከላከል እየደለደሉ እና እየከተሩ ሥራቸውን ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን ከሠሩት  ሥራ በላይ የሆነ የጎርፍ አደጋ  አጋጥሟቸዋል፡፡  መንግሥትም የዘር እና የአፈር ማዳበሪያ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

ሌላው ሐሳባቸውን በስልክ ያካፈሉን የደቡብ ጎንደር ዞን ደራ ወረዳ ጅግና ቀበሌ ላይአጋም ጎጥ ነዋሪው አርሶ አደር ወለላው ተፈራ ናቸው። ከሁለት ተኩል ሄክታር በላይ መሬታቸውን በበቆሎ እና በሩዝ ሰብል ሸፍነዋል። የአፈር መከተር ሥራ ሲሠሩ መቆየታቸውንም ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን የክረምቱ ዝናብ ከባድ በመሆኑ በአፈር የተደለደለው አካባቢ እየተንሸራተተ ነው ብለዋል፡፡

ጎርፍ የመከላከል ሥራ እየሠሩ ቢሆንም ከአቅም በላይ ሊሆን ስለሚችል መንግሥት ከጎናቸው እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡ በተለይም የውኃ ማፋሰሻ  መሣሪያ በወቅቱ ይቅረብልን ብለዋል።

በፎገራ፣ ደራ እና ሊቦ ከምከም ወረዳዎች ላይ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን የተናገሩት ደግሞ የደቡብ ጎንደር ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ በላይ አስራደ ናቸው፡፡ የክልሉ መንግሥት በፈቀደው ዐሥራ አንድ ሚሊዮን ብር በጀት 25 ኪሎ ሜትር የጎርፍ ማፋሰሻ እና መከላከያ መከተሪያዎች ተሠርተዋል፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰብም በኬሻ አፈር በመሙላት የማሳውን ዳር እና የመኖሪያ ቤቱን አካባቢ እየገደበ እና እየከተረ መሆኑን ለበኩር ጋዜጣ በስልክ አስታውቀዋል፡፡

ኃላፊው እንዳሉት እነዚህ ወረዳዎች (ፎገራ፣ ደራ እና ሊቦ ከምከም) በተደጋጋሚ በጎርፍ ሲጠቁ ቆይተዋል። በተለይ ደግሞ  እስከ 2012 ዓ.ም ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ እንደነበር አስታውሰዋል። ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ ለማኅበረሰቡ በተሰጠው ግንዛቤ እና በተሠሩ ሥራዎች ጉዳቱን መቀነስ ተችሏል። ነገር ግን በዚህ ዓመት ስጋቱ ከፍ ያለ ነው ብለዋል። በጎርፍ ሊጠቁ የሚችሉ 23 ቀበሌዎች መኖራቸውንም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

በጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ ቀበሌዎች ማኅበረሰቡ ላይ ሊደርስ የሚችለውን የሰብል ምርት፣ የእንስሳት እና የማኅበራዊ ተቋማት ኪሳራ ታሳቢ በማድረግ ከክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ጋር በመሆን በበጋ ወራት የቅድመ መከላከል ሥራ ሲሠራ መቆየቱንም ተናግረዋል። የጎርፍ መጥለቅለቅ ቢፈጠር ከችግሩ ለመውጣት ጀልባዎች መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል። ነገር ግን ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶች መቅረብ እንዳለባቸው ጠይቀዋል። የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋ ሲፈጠር ማኅበረሰቡን የሚያነቁ በጎ ፈቃደኞች መኖራቸውንም አክለዋል፡፡ የጎርፍ አደጋ ቢከሰት ምላሽ የሚሰጥ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሠራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ኃላፊው እንደተናገሩት የአካባቢው ነዋሪዎች ሊከሰት ከሚችለው የጎርፍ አደጋ ራሳቸውን ለመጠበቅ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ በተለይም በጉማራ እና በርብ አካባቢ ጥንቃቄ ይሻል። ችግሩ ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን ስለሚችል የክልሉ መንግሥት ከወዲሁ በጀት መድቦ አስፈላጊ ዕቃዎችን ማቅረብ አለበት።

የጎርፍ አደጋ ስጋቱን ለመከላከል እና ለመቀነስ የክልሉ ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ያደረገው ቅድመ ዝግጅት ሥራ ጥሩ የሚባል መሆኑን የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አቶ ጥላሁን ደጀኔ ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡ በሊቦ ከምከም ስምንት ኪሎ ሜትር፣ በደራ 22 ኪሎ ሜትር እና በፎገራ ወረዳ አንድ ኪሎ ሜትር የጎርፍ መከላከያ ማፋሰሻ ተሠርቷል ብለዋል፡፡

በርብ እና ጉማራ ወንዞች መካከል በሚገኘው የፎገራ ወረዳ ተጨማሪ የጎርፍ መከላከያ ሥራ እንደሚፈልግ አስታውቀዋል። በአካባቢው ነዋሪዎች፣ በእንስሳት እና በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የክልሉ ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ በጥናት ላይ የተመሠረተ ቅድመ ዝግጅት መሥራቱን ዋና አሥተዳዳሪው ተናግረዋል።

እንደ ዋና አሥተዳዳሪው ገለጻ የቅድመ ዝግጅት ሥራው የአየር ትንበያውን በጥልቀት መገምገም፣ የጎርፍ አደጋ ስጋት ያለባቸውን አካባቢዎች መለየት፣ የአደጋ ስጋት ምላሽ ዕቅድ ማዘጋጀት፣ ሃብት ማሠባሠብ እና ግብዓቶችን ማቅረብ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡

በአንዳንድ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የወንዞች ሙላት፣ ቅጽበታዊ ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት የሚያስከትል ከባድ ዝናብ ስለሚኖር አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲደረግ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳስቧል፡፡

በተለይም በምዕራብ፣ በሰሜን ምዕራብ፣ በሰሜን፣ በሰሜን ምሥራቅና እና በመካከለኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ጠንካራ የዝናብ መጠንና ስርጭት እንደሚኖራቸው አሀዛዊ የትንበያ መረጃዎች ያመላክታሉ ብሏል፡፡

በመሆኑም ለወንዞች ሙላትና ለቅጽበታዊ ጎርፍ መከሰት እንዲሁም የመሬት መንሸራተት የሚያስከትል ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ስለሚኖር ከወዲሁ ማኅበረሰቡ እና የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ እና ዝግጅት እንዲያደርጉ አሳስቧል።

 

ማጠቃለያ

ከአሜሪካው ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ድረ ገጽ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው የመሬት መንሸራተት ክስተት የምንለው ከአንድ ተዳፋታማ አካባቢ ድንጋይ፣ አፈር ላይ ያሉ ደኖች፣ አፈር እንዲሁም ሌሎች ጥራጊዎች በፊት ከነበሩበት ወደ ቁልቁለት ቦታ ሲንሸራተቱ እና ስፍራውን ለቀው ሲሄዱ የሚከሰት ነው። ይህ ሂደት በድንገት ወይም ቀስ በቀስ ረዘም ላለ ጊዜ ሊከሰት ይችላል።

በተዳፋታማ አካባቢዎች ከፍተኛ ዝናብ መዝነብ፣ የበረዶ መቅለጥ፣ የመሬት መሸርሸር፣ የመሬት መንቀጥቀጥ እና እሳተ ገሞራ ደግሞ ዋና ዋና መንስዔዎች መሆናቸውን ዘርዝሯል። ይህም በተፈጥሮ ወይም በሰው ሠራሽ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል አብራርቷል።

የመረጃ ምንጩ አክሎም አደጋውን የመከላከያ ስልቶችን ጠቅሷል። የቅድመ መከላከል ሥራዎችን መሥራት፣ ጠንካራ ማፋሰሻዎችን መገንባት፣ ወቅታዊ የአየር ንብረት ትንበያ መረጃዎችን መከታተል እና መተግበር፣ ስጋቱ ከቅድመ መከላከል ሥራዎች በላይ ከሆነ ደግሞ አካባቢውን መልቀቅ የቢሆን ምክረ ሐሳቦች ናቸው።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር ሐምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here