የክፍለ ዘመን እርግማን ሲነሳ

0
162

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን የአውሮፓ እግር ኳስ የሰርክ ወግ የነበረ፣ ለ11 ዓመታት በባቫሪያኑ ክለብ ባየርሙኒክ ተይዞ የነበረውን የበላይነት የገታ፣ በአውሮፓ በተከታታይ 51 ጨዋታዎችን በማሸነፍ ክብረወሰን የጨበጠ፣ በታሪኩ የመጀመሪያውን የቡንደስ ሊጋ ዋንጫ ያሳካ ክለብ ነው- ባየር ሌቨርኩሰን። የዚህ ክለብ አሰልጣኝ ደግሞ ዣቢ አሎንሶ ኦላኖ ነው።

ባየር ሌቨርኩሰን 119 ዓመታት እድሜን ያስቆጠረ ክለብ ቢሆንም የቡንደስ ሊጋውን ዋንጫ ግን ከዚህ በፊት አያውቀውም። በቀይ እና ጥቁር መለያ የሚታወቀው የጀርመኑ ክለብ ምንም እንኳ ከዚህ በፊት የቡንደስ ሊጋውን ዋንጫ ለማንሳት ባይታደልም አምስት ጊዜ ተፎካካሪ በመሆን ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁን ግን የታሪክ ማህደሩ ያሳያል።

ይህም በቡንደስ ሊጋው ታሪክ ክብረወሰን ሆኖ ተመዝግቧል። በዚህ ምክንያት የተቀናቃኝ ክለብ ደጋፊዎች መሳለቂያ ሆኖ ቆይቷል። ዋንጫ የማያሸንፍ (ኔቨርኩሰን ) ተብሎም ቅጽል ስም ተሰጥቶ እንደነበረ ይታወቃል። አሁን ግን ታሪኩን ቀይሯል፤ የማይሸነፈው ( ኔቨር ሉዘር) ተብሎ ተወድሷል። ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ የዘለቀው የዋንጫ እርግማን ተነስቶ  ከቡንደስ ሊጋው ዋንጫ ጋር ተገናኝቷል።

የዣቢ አሎንሶው ቡድን በቡንደስ ሊጋው አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ በክበረወሰኖች ታጅቦ ነው ዋንጫውን ያነሳው። ባየር ሌቨርኩሰን የቡንደስ ሊጋው ሻምፒዮን የሆነው 90 ነጥቦችን በመሰብሰብ ነው። 28 ጨዋታዎችን ሲረታ በስድስቱ ብቻ ነጥብ መጋራቱ የሚታወስ ነው። 89 ግቦችን ደግሞ በተጋጣሚ መረብ ላይ አሳርፏል። በየጨዋታው በአማካይ ከሁለት ነጥብ ሁለት ግቦች በላይ አስቆጥሯል። ይህ ቁጥራዊ መረጃም በክለቡ ታሪክ አዲስ ክብረወሰን ሆኖ ተመዝግቧል።

በክለቡ 119 ዓመታት ታሪክ ዘንድሮ አነስተኛ ግቦች የተቆጠሩበት ሲሆን 24 ግቦች ብቻ ነው የተቆጠሩበት። አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ የቡንደስ ሊጋው ሻምፒዮን የሆነው ቡድን በአውሮፓ መድረክም በተከታታይ 51 ጨዋታዎችን ባለመሸነፍ አዲስ ክብረ ወሰን ጨብጧል። እ.አ.አ ከ1963 እስከ 1965 የፖርቹጋሉ ክለብ ቤኔፊካ 48 ጨዋታዎችን በተከታታይ በማሸነፍ ላለፉት 60 ዓመታት ክብረ ወሰኑን ይዞ መቆየቱን መረጃዎች ያሳያሉ።

የጀርመኑ ክለብ በዚህ ዓመት የቤኔፊካን ክብረወሰን በመሻገር አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል። በአውሮፓ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ባየር ሌቨርኩሰን በአታላንታ ሦስት ለባዶ ተሸንፎ ያለመሽነፍ ጉዞው መገታቱ የሚታወስ ነው። ባየር ሌቨርኩሰን በአጠቃላይ ካደረጋቸው 53 ጨዋታዎች 43ቱን አሸንፏል፤ በዘጠኙ አቻ ሲለያይ በአንዱ ብቻ ነው የተሸነፈው።

ከቡንደስ ሊጋው በተጨማሪ የዲኤፍቢ ፖካል (DFB-Pokal) ዋንጫን አሳክቷል። በአውሮ ሊግም እስከ ፍፃሜ ተጉዟል። ከሜዳው ውጪ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰባት ጨዋታዎችን ማሸነፍ የቻለውም በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ነበር።

የባየር ሌቨርኩሰን አዲስ የእግር ኳስ አቢዮት የተጀመረው እ.አ.አ በ2021/22 የውድድር ዘመን ነው። በወቅቱ ክለቡ ወደ ታችኛው የሊግ እርከን የመውረድ አደጋ ተጋርጦበት የነበረ ሲሆን ኃላፊዎች ክለቡን ለማትረፍም የቀድሞ አሰልጣኙን ጄራርዶ ሲኦኒን አሰናበቱት።

አሰልጣኝ ዣቢ አሎንሶም ስዊዘርላንዳዊውን አሰልጣኝ ጄራርዶ ሲኦኒን በመተካት አዲሱ የባየር ሌቨርኩሰን አለቃ በመሆን ሹመትን አግኝቷል። ስፔናዊው አሰልጣኝም ክለቡን ከመውረድ ታድጎታል። ዣቢ አሎንሶ በሪያል ሶሲዳድ ሁለተኛው ቡድን (ቢ ቡድን) ውስጥ ብቻ መሥራቱ እና በዋና አሰልጣኝነት ልምድ ያላካበተ በመሆኑ የ2022/23 የውድድር ዘመን ሲጀመረ ብዙዎች ስጋት አድሮባቸው እንደነበር መረጃዎች አመልክተዋል።

ይሁን እንጂ ግምቶችን ፉርሽ አድርጎ የሚታይ ለውጥ አምጥቶ አሳይቷል። በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ደግሞ ዓመቱን በስኬት ደምድሟል። የ42 ዓመቱ አሰልጣኝ በአንፊልድ ሮድ ከራፋ ቤኒቴዝ፣ በሳንቲያጎ ቤርናቢዮ ከሆዜ ሞሪንሆ እና በአሊያንዝ አሪና ከፔፕ ጓርዲዮላ ጋር አብሮ መሥራቱ ስኬታማ እንዲሆን አስችሎታል። “ከተለያዩ የዓለም ቁንጮ አሰልጣኞች ጋር መሥራቴ ብዙ አስተምሮኛል” ብሏል።

ከአሰልጣኝ የርገን ክሎፕ ጋር ቢሠራ ደግሞ የበለጠ ውጤታም ይሆን እንደነበረ ተናግሯል። የቀድሞው የመሀል ሜዳ ሰው በአጭር ጊዜ ውስጥ አስደናቂ ቡድን በመገንባት ውጤታማ መሆኑ ብዙዎችን አስደንቋል። በተጫዋችነት ዘመኑ አስደናቂ ዕይታ የነበረው፣ በጥልቀት እግር ኳስን የሚረዳ እና የሚገነዘብ ሀሳባዊ ተጫዋች የነበረ መሆኑ ለአሰልጣኝነቱ ህይወቱ እንዳገዘው ዘ ጋርዲያን አስነብቧል።

አሰልጣኝ ዣቢ አሎንሶ ከፔፕ ጓርዲዮላ ቀጥሎ የቡንደስ ሊጋ ክለብ ያሰለጠነ እና ዋንጫውን ያሳካ ሁለተኛው አሰልጣኝ ለመሆን በቅቷል።  አሎንሶ ተጫዋችም አሰልጣኝም ሆኖ የቡንደስ ሊጋውን ዋንጫ ያነሳ ዘጠንኛው ሰው ሆኖ ስሙን በጀርመን እግር ኳስ ታሪክ አስፍሯል። ከዚህ በፊት ሀንሲ ፍሊክ፣ ኒኮ ኮቫቺች፣ ማቲያስ ሰመር፣ ፍራንዝ ቤክናበወር እና ከመሳሰሉት ሌሎች የቀድሞ የእግር ኳስ ሰዎች ጋር ስሙን በደማቁ አጽፏል።

በአንድ ጨዋታ ከ200 በላይ ቅብብሎችን ካደረጉ ሦስት ተጫዋቾች መካከል ዣቢ አንዱ እንደነበር ጠቅሶ ቡድኑንም በዚያ መንገድ መገንባቱን መረጃው አመልክቷል። ዘንድሮ በቡድንደስ ሊጋው የባየር ሌቨርኩሰንን ያህል የኳስ ቅብብል ያደረገ ክለብ የለም። ቅብብሎቹ ደግሞ የተሳኩ፣ ዓላማ ያላቸው እና የተጋጣሚ ቡድንን እንቅስቃሴ የሚረብሹ ናቸው።

አሰልጣኝ አሎንሶ የባየር ሌቨርኩሰን መለያ የሆነውን የእግር ኳስ ባህል የጠበቀ የእግር ኳስ ፍልስፍና ተግባራዊ እንደሚያደርግም ይነገራል። በኳስ ቁጥጥር አጥብቆ የሚያምን እና በመልሶ ማጥቃት ተጋጣሚን ፋታ መንሳት የሚል መርህ አለው። 3-4-2-1 የስፔናዊው አሰልጣኝ ተመራጭ የጨዋታ አሰላለፍ ነው። ለዚህ ፍልስፍናው ደግሞ አጋዥ የሚሆኑ ድንቅ ባለተሰጥኦ ተጫዋቾችን በስብስቡ ይዟል።

በተለይ ደግሞ የክንፍ አጥቂዎች በኳስ ሽግግር ወቅት ትልቅ ሚና የነበራቸው ሲሆን አስፍተው በመጫወት በመልሶ ማጥቃት በተጋጣሚ ቡድን ላይ አደጋ በመጣል ስኬታማ ጊዜ አሳልፈዋል። ኳስን ከኋላ መስርቶ በጥብቅ መከላከል ኳስን ተቆጣጥሮ በመጫወት እና እንደ አስፈላጊነቱ በመልሶ ማጥቃት ተጋጣሚን ፍታ ማሳጣት በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ዣቢ አሎንሶ ሜዳ ላይ ተግባራዊ ሲያደርገው የነበረ የእግር ኳስ ሀሳብ ነው።

በ2022/23 የውድድር ዘመን መጨረሻ በርካታ ቁልፍ ተጫዋቾች ክለቡን ለቀው እንደነበረ አይዘነጋም። ስፔናዊው አሰልጣኝ ግን 90 ሚሊዮን ዩሮ ገደማ በማውጣት በርካታ ወሳኝ ተጫዋቾችን ማስፈረም ችሏል። ለአብነት ግራኒት ዣካን ከአርሴናል፣ ጆናስ ሆፍማንን ከቦርሺያ ሞንቼግላድባ፣ አሌክስ ግሪማልዶን ከቤኔፊካ እና ቪክተር ቦኒፌስን ከዩኒየን ሴንት ጊሊዮስ በማስፈረም ነው ዓመቱን የጀመረው።

የእነዚህ ድንቅ ባለተሰጥኦ የሜዳ ላይ ጥምረት በውድድር ዓመቱ መጨረሻ ፍሬ አፍርቶ ክለቡ በዋንጫ ታጅቦ እንዲያጠናቅቅ አስችሎታል። አዳዲስ ፈራሚዎች በግልም በቡድንም ስኬታማ እንዲሆኑ የአሰልጣኙ ሚና ላቅ ያለ እንደነበረ ጎል ዶት ኮም አስነብቧል። ተጫዋቾች በራስ መተማመናቸው ከፍ እንዲል እና በቡድኑ ዋስትና እንዲሰማቸው ማድረግ ችሏል ዣቢ አሎንሶ።

አሁን ላይ በአውሮፓ ከሚገኙ ድንቅ የጨዋታ አቀጣጣዮች መካከል አንዱ የሆነው ፍሎሪያን ዊርቲዝ በስፔናዊው አሰልጣኝ ስር ለማንጸባረቅ ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም። ተከላካዩ ጆናታን  ምንም እንኳ የላቀ ተሰጥኦ ቢኖረውም አሎንሶ ወደ ጀርመኑ ክለብ ከማቅናቱ በፊት ግን የአቋም መውረድ ገጥሞት ነበር። የተከላካዩን ድንቅ ብቃት የተረዳው አሎንሶ  ተሰጥኦውን አውጥቶ እንዲጠቀም አስችሎታል። ይህም አሰልጣኙ ተጫዋቾችን ወደ ኮከብነት የማሸጋገር አቅም እንዳለው ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።

የአሎንሶ ቀድሞ አሰልጣኞች ሰለ አዕምሮ ብስለቱ እና ታላቅነቱ ምስክርነት ሰጥተዋል። “ፈጣን ተማሪ ነበር፤ ነገሮችን የሚረዳበት መንገድም ያስደንቅ ነበር፤ ይህን ደግሞ ሜዳ ላይ አሳይቷል” ብሏል ራፋ ቤኒቴዝ። አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ ደግሞ “ጨዋታን ለመረዳት ከፍተኛ ጉጉት ነበረው፤ ለማሽነፍ ምን ማድረግ እንዳለበት ቀድሞ ያውቅ የነበረ ተጫዋች ነበር” ብሏል።

አሰልጣኝ ዣቢ አሎንሶ ኦላኖ በባየር ሊቨርኩሰን ቤት የፈፀመውን ገድል የተመለከቱት በተጫዋችነት ያሳለፈባቸው ሊቨርፑል እና ባየርሙኒክ ዐይናቸውን ቢያሳርፉበትም እርሱ ግን ክለቡን እንደማይለቅ ቀደም ብሎ ማረጋገጫ ሰጥቷል።

ዘጋርዲያንን እና ጎል ዶት ኮምን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here