የከተሞችን ደረጃ እና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ፣ መሠረተ ልማትን አቀናጅቶ በመጠቀም ዘላቂ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ፣ የአረንጓዴ ልማት ሽፋንን ለማሻሻል፣ የሥራ ዕድል መፍጠሪያ መስክን ለማስፋት፣ የሥራ ባህል እና የትብብር መንፈስን ለማዳበር ሀገራት በኮሪደር ልማት ላይ ትኩረት አድርገው ሠርተውበታል::የኮሪደር ልማት ሥራዎች ከተሞች ጽዱ እንዲሆኑ በማድረግ ጤናማ ማኅበረሰብ ለመፍጠር አበርክቶው ከፍተኛ መሆኑን በልማቱ በርካታ ዓመታት የሠሩ ሀገራት ተሞክሮ ያሳያል::
ሲንጋፖር በኮሪደር ልማት ሥራዎች ለብዙዎች በተሞክሮነት የምትጠቀስ ሀገር ናት::ሀገሪቷ በመንገድ መሠረተ ልማት፣ በሕንጻ ዲዛይን እና ደረጃ፣ ጽዳት እና ውበትን ለገቢ ምንጭነት በመጠቀም ረገድ ለብዙ ሀገራት በተሞክሮነት የምትነሳ ሀገር ናት፡፡
ሲንጋፖር የአረንጓዴ ልማት ትርጉም ሳያስፈልገው የተገለጠባት ሀገር ናት::መንገዶቿ፣ ተራራዎቿ፣ መልክዓ ምድሯ፣ ሕንጻዎቿ፣ መኖሪያ ቤቶች… ሁሉም ችግኞች ተተክለው ይታዩባታል::ሰው ሠራሽ ፏፏቴዎችም የሲንጋፖር መልኮች ናቸው:: እግረኛ መንገዶቿ ፀሐይን መከለል በሚችሉ ሼዶች የተሠሩ ናቸው::ይህም በአንድም ይሁን በሌላ ዜጎቿ ለከተማዋ ውበት ልዩ ትርጉም እንዲሰጡ አድርጓቸዋል፡፡
የሲንጋፖር የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ለከተማዋ ጽዱነት ከፍ ያለ ሚና አለው::ነዋሪዎቿም ለሀገራቸው ጽዱነት፣ ውብነት እና በዓለም ተምሳሌት የመሆን ዓላማ ማስቀደማቸው ውበቷ ለዜጎቿ እና ለሀገሪቱ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ሆኖ ብቅ ብሏል::
ከተማዋ እ.አ.አ በ2024 ከዜጎቿ ቁጥር በላይ በሚሆኑ ጎብኝዎች ተጎብኝታለች::የሀገሪቱ የሕዝብ ቁጥር 6 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሲሆን በተጠቀሰው ዓመት የጎበኛት ሕዝብ ቁጥር ግን 16 ነጥብ 5 ሚሊዮን መሆኑን የሀገሪቱ ቱሪዝም ቦርድ (www.stb.gov.sg) መረጃ ያሳያል::ከጥር እስከ መስከረም ባሉት ወቅቶችም 22 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ችላለች::ይህም የኮሪደር እና የአረንጓዴ ልማት ያስገኙላት በረከት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
ኢትዮጵያም የኮሪደር ልማትን የከተሞች ዕድገት መሰላል፣ የውበት ማስጠበቂያ፣ የኢኮኖሚ ምንጭ እና የሥራ ዕድል መፍጠሪያ መስክ አድርጋ እየሠራችበት ትገኛለች::የኮሪደር ልማቱ በሀገራችን አዲስ አበባም ተግባራዊ ተደርጎ በውጤታማነት ይነሳል::እንደውም የኮሪደር ልማቱ ከኢትዮጵያም አልፎ ለአፍሪካ ሀገራትም በተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑን የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሴሪል ራማፎሳ ተናግረዋል፤ “የሕብረታችን መቀመጫ አዲስ አበባ ውብ እና ጽዱ ሆናለች::በውብ መብራቶች ባሸበረቁት ጽዱ መንገዶቿ ነዋሪዎቿ እና እንግዶቿ ያለ ስጋት በነጻነት ይዝናኑበታል::የከተማዋ ውብ እና ጽዱ መሆን ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንድትሆን አስችሏታል፤ ለንግድ ሥራም ይበልጥ ምቹ ሆናለች” በማለት የልማቱን እንቅስቃሴ ጠቅሰዋል::
በአጠቃላይ አዲስ አበባ ለአፍሪካ ተምሳሌት የምትሆን ከተማ መሆኗን አንስተዋል::ሀገራቸውም ልክ እንደ አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿ ምቹ ከተማ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሠሩ ለአመራሮቻቸው አስታውቀዋል፡፡
ከሲንጋፖር እስከ አዲስ አበባ ተከናውኖ መልካም ውጤት እየተመዘገበበት ያለው የኮሪደር ልማት ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ ክልሎች ተግባራዊ በመደረግ ላይ ነው::የአማራ ክልልም የኮሪደር ልማትን በሰባት ከተሞች እያከናወነ ይገኛል፡፡
ተፈጥሮ ለከተማዋ የሰጠቻትን ውበት ገልጦ ለማውጣት፣ ጽዱ እና ለዜጎቿ የተመቸች ለማድረግ፣ ጎብኝዎቿንም በተሟላ መሠረተ ልማት ለመቀበል እና የቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘም የባሕር ዳር ከተማም ለኮሪደር ልማት ልዩ ትኩረት ሰጥታለች::የከተማዋ ነዋሪው ዓለማየሁ ፋንታ እንደሚሉት ባሕር ዳርን የማስዋብ እና ውብ የማድረግ ሥራ ጅማሮውን የሚያደርገው በ1958 ዓ.ም ነው::አቶ ዓለማየሁ ከተማዋ ከትናንት እስከ ዛሬ ያለችበትን ሁኔታ እንደሚያውቁ ተናግረዋል::እንደ እርሳቸው ማብራሪያ ከ59 ዓመት በፊት ባሕር ዳርን አረንጓዴ፣ ውብ፣ ጽዱ እና ለዜጎቿ የተመቸች ለማድረግ የተጀመረው ተግባር ዛሬ በኮሪደር ልማት ቀጥሏል::ልማቱ ባሕር ዳርን ከማስዋብ ባለፈ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ የኢኮኖሚ ምንጭን በማሳደግ ረገድ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል::በመሆኑም ሁሉም ልማቱን ሊደግፍ እንደሚገባ ጠይቀዋል::
በባሕር ዳር ከተማ 22 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ይከናወናል::የመጀመሪያው የኮሪደር ልማት ከደጅ አዝማች በላይ ዘለቀ አየር ማረፊያ እስከ ዓባይ ማዶ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ያለውን አካባቢ የሚያካልል ነው::ከመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን (ኢላ ማደያ) በአዲሡ ድልድይ አድርጎ የጎንደር መውጫ ነባሩን አስፋልት መንገድ የሚያገናኘው የኮሪደር ልማት ሌላኛው አካል መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው አስታውቀዋል፡፡
ከደጅ አዝማች በላይ ዘለቀ አየር ማረፊያ እስከ ዓባይ ማዶ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ከሚደርሰው የኮሪደር ልማት ውስጥ ከርእሰ መስተዳደር ጽ/ቤት እስከ ድሮው ግዮን ሆቴል የሚደርሰው ሦስት ኪሎ ሜትር ሥራ ወደ መጠናቀቅ ምዕራፍ መድረሱ ተመላክቷል::
የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ነባር መታወቂያ የሆኑ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች በስፋት የሚከናወኑበት ነው::የሕዝብ መዝናኛ አረንጓዴ ቦታዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑንም አቶ ጎሹ ጠቁመዋል::የድሮው ሕዳር 11 የአሁኑ ዘምባባ ፓርክ እና በቀደመ ሥሙ ዲፖ በአሁኑ ጣና መናፈሻን ለአብነት አንስተዋል::
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የኮሪደር ልማቱ የባሕር ዳርን የብስክሌት ከተማነት የሚመልስ እንዲሆን ተደርጎ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል::ከዋናው መንገድ ግራ እና ቀኝ ለእያንዳንዱ ሦስት ሜትር ስፋት ያላቸው እና ደረጃቸውን የጠበቁ የብስክሌት መንገዶች እየተሠሩ ነው::በተጨማሪም ኮሪደር ልማቱ ዜጎች ከትራፊክ አደጋ ደኅንነታቸውን ጠብቀው የሚጓዙባቸው የእግረኛ መንገዶችን ያካተተ ነው፡፡
የአውቶብስ እና የታክሲ መሳፈሪያ፣ የብስክሌት የአንድ ማዕከል መቆሚያ፣ የከተማዋን ጽዱነት ለማረጋገጥ አስፈላጊ በተባሉ ቦታዎች ሁሉ መጸዳጃ ቤቶችን መገንባት፣ በየመንገዶቹ ማረፊያ ቦታዎችን ማዘጋጀት የልማቱ አካል ሆነው እየተሠራባቸው መሆናቸው ተመላክቷል::እነዚህ ሁሉ ሥራዎች የሕዝቡን የመዝናኛ ቦታ ፍላጎት እጥረት ከመፍታት ባለፈ የኢኮኖሚ ምንጭ አማራጭ መፍትሔ ሆነው እንዲያገለግሉ ተደርጎ ይሠራል ተብሏል::
ባሁኑ ወቅት የኮሪደር ልማቱ የተቀናጀ መሠረተ ልማትን አካቶ እየተሠራም ይገኛል::የመብራት፣ የውኃ እና የቴሌ መስመር ዝርጋታዎች ከመሬት በታች ተቀብረው እንዲያልፉ ተደርጓል::ይህም የከተሞችን ደረጃ ከፍ ከማድረግ ባለፈ በየጊዜው ለተለያየ ዓላማ ተብሎ በሚከናወን ቁፋሮ የሚቆራረጥን የኀይል ቅርቦት በዘላቂነት ለመፍታት የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል::
የመንገድ መሠረተ ልማት ጥያቄዎች እንዲፈቱ የኮሪደር ልማቱ አጋዥነቱ ከፍተኛ ነው::ለአብነት በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ከኮሪደር ልማቱ በተጨማሪ ስፋታቸው ከ20 እስከ 40 ሜትር የሚደርሱ 22 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ ሰባት ከተሞች እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት በሥራ ዕድል ፈጠራም ከፍተኛ ሚና እያበረከተ ነው::በክልሉ ከ800 ሺህ በላይ ዜጎች በሥራ ፈላጊነት ተመዝግበው እንደሚገኙ የክልሉ ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ መረጃ ይጠቁማል::በቅርብ ጊዜ የተጀመረው የኮሪደር ልማትም ለ37 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉ ተመላክቷል::
የኮሪደር ልማት ሥራው ከባሕር ዳር በተጨማሪ በጎንደር፣ ወልዲያ፣ ደሴ፣ ኮምፖልቻ፣ ደብረ ብርሐን እና ደብረ ማርቆስ ከተሞችም እየተከናወነ ነው::
የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ሥራ ክልሉ ያለውን እምቅ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ የመስህብ ሐብት ይበልጥ ለጎብኝዎች በሚያስተዋውቅ አግባብ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል::በተጨማሪም ከተሞች በጎብኝዎች ዘንድ ተመራጭ እንዲሆኑ እና የረጅም ጊዜ መቆያ ሆነው ገቢያቸውን በእጥፍ እንዲያሳድጉ የሚያደርጉ ሥራዎችም ትኩረት ተደርጎባቸዋል፡፡
በባሕር ዳር ከተማ፣ ጎንደር፣ ደሴ፣ ደብረ ብርሐን ከተሞች እየተሠሩ ያሉ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ያላቸውን የመስህብ ሐብት ለማስተዋወቅ በሚያስችል አግባብ እየተከናወነ መሆኑን ርእሰ መስተዳደሩ ማሳያዎችን እያነሱ አስረድተዋል::የክልሉ ብሎም የሀገሪቱ መለያ የሆነው ጣና ሃይቅ ለዘመናት በሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ነገሮች ተከልሎ መልኩን አጥቶ መቆየቱን ርእሰ መስተዳደሩ ያነሳሉ::አሁን እየተሠራ ያለው ሥራ ሰው ወደ ጣና ለመሄድ እንዲያስብ ሳይሆን ራሱ ውበቱ እና ገጽታው ስቦ እንዲወስድ የሃይቁ ዳርቻ አልፎ አልፎ ለእይታ ክፍት ሆኗል::
በዚህም ከነባሩ (አሮጌው) ድልድይ እስከ ዲፖ ድረስ ጣና ሃይቅን ስምንት ቦታ መግለጥ መቻሉን ተናግረዋል::በሁሉም የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኝ የኅብረተሰብ ክፍል እኩል ተዝናኖት የሚያገኝበት የመዝናኛ ስፍራም እየተሠራ ነው::የባሕር ዳርን የዛሬ ላይ ለምለምነት እና መታወቂያነት ሊያስቀጥሉ የሚችሉ ችግኞችን መትከልም የኮሪደር ልማቱ አንድ አካል ተደርጎ በትኩረት እየተሠራበት እንደሚገኝ አስታውቀዋል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የመጋቢት 8 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም