ለምለሟን ኮንጎ የመያዝ የቤልጂየማውያን ፍላጎት የተነሳሳው ሄነሪ ሞርተን ስታንሌይ በተባለ አንድ ግለሰብ ነበር። በ1869 እ ኤ አ የአንድ ጋዜጣ ባለቤት በኮንጎ አንድ ስፍራ እንደጠፋ የሚገመተውን ዴቪድ ሊቪንግስተን የተባለን ሚሲዮን እና አሳሽ እንዲፈልግ የ28 ዓመቱን ወጣት ጋዜጠኛ ስታንሌይን ቀጥሮ ወደ አፍሪካ ምድር ይልከዋል።
የኮንጎን አፈር እንደረገጠ የኮንጎ ድንግል የተፈጥሮ ውበት እና የትየለሌ ሀብት የስታንሌይን ቀልብ ሰረቀው። ከራስ እስከ እግሯ የተሞላ የተፈጥሮ ሀብቷን በረብጣ ዶላሮች ሲያሰላው ራሱን ያዘ፤ ኮንጎን ለአውሮፓ ከበርቴዎች አጫርቶ ሊያተርፍባት ልቡ ቋመጠ። በመጀመሪያም ለእንግሊዝ መንግሥት ወደ ኮንጎ ግብዣ ቢያቀርንም አልተቀበሉትም። በመቀጠል ስታንሊይ ፊቱን ወደ ቤልጂየሙ ንጉሥ ሊዮፖልድ አዞረ። በኮንጎ ተፋሰስ አካባቢ በተፈጥሮ ሀብት የተሞላ ለም የሆነ ኮንጎ የተባለ ነፃ ለም መሬት መኖሩን በመንገር አማለለው። ንጉሡም ምራቁን እስኪውጥ ድረስ በመጎምዠት ተስማማ፤ ስታንሌይንም የእርሱ ወኪል አድርጎ ተዝቆ በማያልቅ ደመወዝ ቀጠረው።
የቤልጂየሙ ንጉሥ ዳግማዊ ሊዮፖልድ የሀገሩን የንግድ ድርጅቶች ወደ ኮንጎ እንዲሄዱ አበረታታቸው። በነፃ ንግድ ሽፋን ሊዮፖልድ የሀገሩን የተመረጡ የንግድ ድርጅቶች እና ኩባንያዎች አሳምኖ ወደ ኮንጎ ሄደው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ላካቸው። ከእነርሱም ጋር ባደረገው ውል መሰረት ከሚገኘው ሀብት አብላጫው ድርሻ ለእርሱ ይሆናል።
የቤልጂየም ኩባንያዎች ኮንጎ ገብተው ስራ እንደጀመሩ ብዙም ሳይቆዩ ሀብት እና ገንዘብ ወዲያውኑ ያፍሱ ጀመር፤ ንጉሥ ሊዮፖልድ ከኩባያዎቹ በሚጎርፍለት ገንዘብ ካዝናው ሞልቶ ተትረፈረፈለት። እናም ንጉሥ ሊዮፖልድ በኮንጎ ያለውን የግል ግዛቱን ወደ ማጠናከር ገባ። በሀገሪቱ የራሱን አስተዳደር መስርቶ ሀብት ማጋበሱን ገፋበት። የሀገሬውን ጉልበት በነፃ እየበዘበዘ ቀጠለ። ኮንጎ የንጉሥ ዳግማዊ ሊዮፖልድ የግል ርስት ሆነች።
ንጉሥ ሊዎፖልድ በዘረጋው የጭቆና አገዛዝ እምቢ! አልገዛም ያለውን የኮንጎ ህዝብ እጅ እና እግር በመቁረጥ እጅግ ዘግናኝ ኢሰብዓዊ በደል ፈጽሟል፡፡ ከሁሉም የሚከፋው ደግሞ በንፁሃኑ ሕዝብ ላይ የፈጸመው የዘር ማጥፋት ግፍ ነው፤ ሊዮፖልድ በኮንጓውያን ላይ የፈፀመው ጭፍጨፋ ናዚ በአይሁዳዊያን ላይ ካደረሰው እልቂት ይበልጣል፡፡ ኮንጎን የግል ንብረት አድረጎ በገዛባቸው ሁለት አሥርት ዓመት ብቻ ከአስር ሚሊዮን በላይ ኮንጓውያንን እንደጨፈጨፈ ይታመናል፡፡ ሕዝቡ ላይ የሚፈፀም የተቀናጀ የርሀብ፣ የአስገዳጅ የጉልበት ብዝበዛ እና ስልታዊ ጭቆናም የሚሊዮኖችን ህይወት ቀጥፏል።
እንዲህ አይነት የኮንጎ ህዝብ በጅምላ ለመጥፋት የመቃረቡን መርዶ የሚያሳብቁ መረጃዎች በአደባባይ እየወጡ የግፉን አሰቃቂነት ደፍረው ማጋለጥ ጀመሩ። የአዳም ሆችቦብ ስነህዝባዊ የጥናት ውጤት መጠነ ሰፊ የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈፀሙን ያሳያል። በ1883 ዓ.ም ላይ 20 ሚሊዮን የነበረው የሕዝብ ቁጥር በ1903 ዓ.ም ወደ 8.5 ሚሊዮን መውረዱን ያመላከተበት ዘግናኝ አህዛዊ ጥናት በኮንጎ ሕዝብ ላይ የደረሰውን ጭፍጨፋ ወደር የለሽነት ያረጋግጣል።
ሆኖም ኮንጎ ተዝቆ በማያልቅ የተፈጥሮ ፀጋ የታደለች ምድር ናት፡፡ በምድሯ የሞላው ወርቅ፣ አልማዝ፣ የዝሆን ጥርስ፣ መዳብ፣ ዩራኒየም፣ ኮባልት እና ሌሎች የከበሩ ማዕድናት ምዕራባውያን ያማልላል። በዚህ መሰረት ለብቻው የግል እርስት አድርጎ ኮንጎን የዘረፋት፣ ሕዝቧን ያሰቃየው የዳግማዊ ሊዮፖልድ ወንጀል ለዓለም ሲጋለጥ እና ከአለማቀፉ ማህበረሰብ ውግዘት እና ኩነናው ሲበዛበት ኮንጎን ለቤልጅየም መንግሥት ለማስረከብ ተገደደ።
ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ ይህ አማላዩና የበለጸገው የኮንጎ ምድር ከግለሰብ እጅ ወጥቶ በሀገረ ቤልጅየም የቅኝ ግዛት መንግሥት መዳፍ ስር ወደቀ፡፡ ከ1908 ዓ.ም ጀምሮ ማለት ነው ኮንጎ የቤልጅየም መንግሥት ቅኝ ግዛት ሆና እንድትቀጥል ተወሰነ። የአውሮፓ ትንሿ ሀገር ቤልጅየም በአፍሪካ በተፈጥሮ ሀብት እጅግ የበለጸገውን ሀገርና ሕዝብ “ቤልጅየም ኮንጎ” በሚል ስም እንድትገዛ ዕድል አገኘች፡፡
ሆኖም ለዓመታት በተከፈለው መስዋዕትነት ይህ በምድራችን የሚያስጎመዥ ከፍተኛ የተፈጥሮ ሃብት ክምችት ያለበት የኮንጎ ምድር ከቅኝ ገዥዋ ቤልጅየም ባርነት ነፃ ለመውጣት ልጆቿ ተደራጅተው መራር ትግል ውስጥ ገቡ፡፡ እንደ ፓትሪስ ሉሙምባ አይነት ለኮንጎ ነፃነት ሕይወታቸውን ለመገበር የቆረጡ ልጆች ተነሱላት። ትግሉን በጀግንነት መርተው ለነፃነት ያበቃ አርበኝነት የፈፀሙ የኮንጎ የቁርጥ ቀን ድንቅ አርበኞች።
በኮንጎ የነፃነት ታሪክ ውስጥ ፓትሪስ ሉሙምባ ሰፊ ድርሻ አለው። ኮንጎ ለዘላለም የማትረሳው ባለውለታዋ የአፍሪካም ኩራት ነው። ሐምሌ 2 ቀን 1925 ዓ.ም በሰሜን ምስራቅ ካሳይ ክፍለ ግዛት ካታኮ-ኮምቤ ከተማ ኦናሉአ በተባለ አካባቢ ተወለደ፡፡ ወላጆቹ በኮንጎ “ባቴተላ” ከተባለ ጎሣ ውስጥ ነው የሚመዘዙት፡፡ እድሜው ለትምህርት ሲደርስ በትውልድ ቀየው በሚገኙ የካቶሊክ እና የፕሮቴስታንት ትምህርት ተቋማት ውስጥ ትምህርቱን ተከታትሏል፡፡ በትምህርቱ ፈጣንና ባለ ብሩህ አዕምሮ እንደነበር ይነገራል፡፡
ነጮች በሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት ሲማር እያለ መምህሩ ሲሳሳት ወጣቱ ፓትሪስ መምህሩን በጥያቄ ይወጠረውና ሊያርመው ይሞክራል። ነገር ግን በዚያ ትምህርት ቤት መብት የነጭ በመሆኑ የተናቀ የመሰለው ነጭ መምህር ጥቁሩን ትንታግ ተማሪ እንዲባረር አደረገው። ፓትሪክም ተመልሶ አልመጣም። ትውልድ ቀየውን ትቶ የወቅቱ የኮንጎ መዲና ወደ ነበረችው ሊዮፖልድቪል ተሰደደ። ጥቂት ቆይቶም በፖስታ ቤት ውስጥ ተቀጥሮ መስራት ጀመረ። ትምህርቱንም በማታ መርሃ ግብር ተከታትሎ ጨርሷል።
ሉሙምባ የፖለቲካና ሕዝባዊ ተሳትፎውን አጠንክሮ በመቀጠል በ1955 ዓ.ም በመንግሥት ሰራተኞች በተቋቋመው የአንድ አካባቢያዊ ኮንጎሊዝ ንግድ ማህበራት ዩንየን ፕሬዚደንት በመሆን አገልግሏል፡፡ በዚሁ ተመሳሳይ ዓመት የቤልጅየም ቅኝ ተገዥ ተወላጆችን ማኅበር በመመስረት በጸረ ቅኝ ግዛት ትግል ንቁ ተሳታፊ መሆን ጀመረ፡፡
1958 ዓ.ም በመላው ኮንጎ የነፃነት ጥያቄ እየተቀጣጠለ የነበረበት ወቅት ነው፡፡ ሉሙምባ ከጓዶቹ ጋር በመሆን ታሪካዊውን የ”ኮንጎሊዝ ብሔራዊ ንቅናቄ” ፓርቲን መሰረተ፡፡ ኤም ኤን ሲ በኮንጎ የፓርቲዎች ታሪክ ውስጥ መላ ሀገሪቱን የሚሸፍን ለነፃነት የሚታገል የመጀመሪያው ሀገር በቀል የፖለቲካ ፓርቲ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ነው ፓትሪስ ሉሙምባ ፓርቲው ለነፃነት በሚያደርገው ትግል የጸረ-ቅኝ አገዛዝ ንቅናቄው ዋና መሪና የፓርቲው ሊቀመንበር ሆኖ ብቅ ያለው፡፡
ጥር 1959 ዓ.ም የኮንጎን ነፃነት ለመጠየቅ በሊዮፖልድቪል በተካሄደው ሕዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ አመፅ ተቀሰቀሰ፡፡ አመፁን እንደተለመደው የቤልጅየም ቅኝ አገዛዝ በወታደራዊ ኃይል ለመቀልበስ ተንቀሳቀሰ፡፡ ይሁን እንጅ ንጉሥ ዳግማዊ ሊዮፖልድ እና ቤልጅየም ላለፉት ሰማኒያ ዓመታት በኮንጎ ላይ የፈጸሙት የዘር ፍጅት እና የተፈጥሮ ሀብት ምዝበራ እንዲያበቃ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሳይቀር ተጽዕኖ ማድረግ ጀመረ፡፡
ቤልጅየም መጀመሪያ ላይ የኮንጎን ነፃነት ብትቃወምም፣ ነገር ግን በነፃነት ታጋዮች ትግል ብርቱነት እና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተጽዕኖ ምክንያት ድንገት ሃሳቧን ለመቀየር ተገደደች፡፡ ይሁን እንጅ ቤልጅየሞች ሙሉ በሙሉ የኮንጎን ነፃነት ማወጅ አልፈለጉም፡፡ በተቃራኒው በአምስት ዓመታት ውስጥ በሂደት የኮንጎን ነፃነት ለመስጠት እንዳሰቡ ለመላው የኮንጎ ሕዝብ አስታወቁ፡፡ ሆኖም እነ ሉሙምባ ቤልጅየሞች አሻንጉሊት መንግሥት አስቀምጠው አገዛዛቸውን ማስቀጠል የሚያስችላቸው ሴራ እንደሆነ ተገነዘቡ፡፡ ከዚህ መነሻነት የሉሙምባ ፓርቲ ከየትኛውም የይስሙላ ምርጫ ራሱን እንደሚያገል አስታወቀ፡፡ ይህንኑ ሃሳብ በርካታ የኮንጎ ዜጎች በመደገፍ ከምርጫው መታቀብን መርጠዋል፡፡ ሆኖም የቤልጅየም ባለስልጣናት ተቃውሞውን በኃይል ለማክሸፍ መሞከራቸው ምክንያት ሆኖ የነፃነት ትግሉ እንደገና አንሰራርቶ አመጽ ፈነዳ፡፡
ጥቅምት 30 ቀን 1960 ዓ.ም በፈነዳው አመጽ የቤልጅየም መንግሥት ትልቅ ስጋት ውስጥ ገባ፡፡ በርካታ ዜጎች ሲቆስሉ ወደ 26 ሰዎች ደግሞ ሞቱ። የሕዝቡ ቁጣ እየጨመረ በመሄድ ለቀናት የቤልጅየምን ቅኝ ገዢ መንግሥት አስጨነቀው። በዚህ የተነሳም በስታንሊቪል ከተማ ሕዝቡን ለአመፅ በማነሳሳትና ለ26 ኮንጓውያን ሞት ሉሙምባን በመወንጀል ዳግም ዘብጥያ ወረወሩት፡፡ የኮንጎሊዝ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ መሪው ሉሙምባ ዘብጥያ ቢወርድም ፓርቲው የጀመረውን በምርጫ ያለመሳተፍ አድማ በመተው በምርጫው ለመወዳደር ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ፡፡ በመሆኑም በታህሣሡ የስታንሊቪል አካባቢያዊ ምርጫ የሉሙምባ ፓርቲ አሸነፈ።
ፓርቲው በምርጫው ቢያሸንፍም ቅሉ መሪው ግን በእስር ላይ ነበር። በዚህ መካከል የኮንጎ እና የቤልጅየም ፖለቲከኞች የኮንጎ ነፃነት የሚታወጅበትን ቀን ለመወሰንና በሃገሪቱ በሚካሄደው አዲስ የፖለቲካ ለውጥ ዙሪያ ከሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመወያየት ጥር 20 ቀን 1960 ዓ.ም ብራስልስ ላይ ለውይይት ተጠሩ። የፓርቲው ተወካዮች መሪያቸው ሉሙምባ እንዲፈታ በተደጋጋሚ ቢጠይቁም ሰሚ ታጣ። ከቀናት በኋላ ግን ሉሙምባ ከእስር ተፈትቶ በብራስልሱ ውይይት ላይ እንዲገኝ ተደረገ። በዚህ ውይይትም ነበር ቤልጅየም የኮንጎ ነፃነት ሰኔ 30 ቀን 1960 ዓ.ም እንዲሆን ወሰነች።
ይህ በእንዲህ እያለ ግንቦት ወር 1960 ዓ.ም በኮንጎ ሀገራዊ ምርጫ ተደረገ። በሀገሪቱ የመጀመሪያ በሆነው በዚህ ታሪካዊ ሀገር አቀፍ ምርጫ የፓትሪስ ሉሙምባ ፓርቲ 90 በመቶ ብልጫ ድምጽ አገኘ፡፡ ከዚህ በኋላ ምርጫውን ያሸነፈው ፓርቲ መሪ ፓትሪስ ሉሙምባ አዲስ መንግሥት መሰረተ።
ፓትሪስ ሉሙምባ የአዲሷ እና የነፃዋ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነ፤ እንዲሁም ተቀናቃኙን ካሳቩቡ ስልጣን በማጋራት የሀገሪቱ ፕሬዚደንት አደረገው፡፡ ፓትሪስ ሉሙምባ በ35 ዓመት ዕድሜው በሀገሪቱ ታሪክ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ወደ ስልጣን የመጣ የመጀመሪያው መሪ ተብሎ በታሪክ መዝገብ ላይ ስሙ ሰፈረ፡፡
ሆኖም ለዓመታት የኮንጎ ቅኝ ገዢ ሆና የኖረችው ቤልጅየም በአልማዝና በወርቅ ማዕድናት ከበለፀገው እና ለም ከሆነው መሬት የምታገኘው ጥቅም እንዳይቋረጥ መስጋቷ አልቀረም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሀገር ወዳዶቹ፣ የነፃነት ታጋዮች እና የሕዝብ ተወካዮች በተገኙበት ደማቅ ሥነ ሥርዓት ሰኔ 30 ቀን 1960 ዓ.ም የኮንጎ ነፃነት በይፋ መታወጁ ነው፡፡ በዚህ ታሪካዊ እለት ኮንጎ እንደ አዲስ ሃገር ተፈጠረች፡፡
የዕለቱ የክብር እንግዳ ሆነው የተሰየሙት የቤልጂየሙ ንጉሥ ባዶዊን መርሀ ግብሩን በንግግር እንዲከፍቱ ተደረገ። ንጉሡ በንግግራቸው ላይ ኮንጎ ከቤልጅየም ነፃ መውጣቷን፣ ራሷን መቻሏን እና ወደ አዲስ አስተዳደር መሸጋገሯን አበሰሩ፡፡ ሆኖም ንጉሥ ባዶዊን በንግግራቸው የቀድሞው ንጉሥ ሊዮፖልድ እና ሀገራቸው ቤልጅየም የኮንጎን ሕዝብ ከባርነት አውጥተው በልማትና በስልጣኔ ጎዳና አስገብተው እንዳዘመኑት በድፍረት ተናገሩ፡፡
ይባስ ብሎም በቤልጅየም በጎ ፈቃድ ዛሬ ኮንጓውያን ነፃነታቸውን መጎናጸፍ እንደቻሉ አስረዱ፡፡ በኮንጎ ስልጣኔ የተስፋፋው በአባታቸው አጎት ዳግማዊ ሊዮፖልድ የአስተዳደር ዘመን መሆኑን የራሳቸውን መረጃ እያጣቀሱ አሞካሹ፡፡ “የቤልጅየምን የአስተዳደር መዋቅር አትለውጡ፡፡ ምንግዜም ለምክር ወደ እኛ ለመምጣት አትፍሩ፤ ምንጊዜም ከጎናችሁ ነን፡፡ ለዕድገትና ለስልጣኔ የሚረዳችሁን ዕውቀት እንለግሳችኋለን” በማለት ታዳሚውን ያበሳጨ ንግግራቸውን አጠቃለሉ፡፡
“ክብር ለብሔራዊ ነፃነት ተፋላሚዎቻችን!” አለ ሉሙምባ፣ “…ምንም እንኳ ዛሬ በእኩልነት ከተስተካከልናት ወዳጅ ሀገር ቤልጅየም ጋር የኮንጎን የነፃነት ቀን አብረን ብናከብርም ማንኛውም ኮንጎዊ ለዚህ ድል የበቃው በቤልጅየም ቸርነት ሳይሆን በሕዝቧ መራር ትግል፣ ለነፃነት ባፈሰሰው ደሙ፣ በከሰከሰው አጥንቱ፣ በከፈለው ውድ መስዋዕትነት መሆኑን መቼም አንዘነጋውም፡፡ በምግብ ዕጦትም ሆነ በእንግልት የተውነው ጦርነት በፍጹም አልነበረም፡፡ ዕለት ተዕለት በጽናት በመዋጋት በከፈልነው መስዋዕትነት እነሆ ነፃነታችንን ልንጎናጸፍ በቅተናል፡፡
“ትግላችን ለ80 ዓመታት በግዴታ የተጫነብን አሳፋሪ ባርነትና ግፍ እንዲቆም አግዟል፡፡ ሕዝባችን ነፃነቱን ከመቀዳጀቱ በፊት ቀንና ማታ መዋረዱን፣ መሸማቀቁንና መንገላታቱን እናውቃለን፤ ምክንያቱም እኛ ጥቁሮች ነን፡፡ ለመሆኑ ጨካኙን እና በዝባዡን ቅኝ አገዛዝ ስለተቃወሙ ብቻ በርካቶች በግፍ የታጎሩባቸው እስር ቤቶችስ፣ በርካታ ወንድሞቻችንን የቀጠፉት የተኩስ ዕሩምታዎችስ እንዴት ይረሳሉ? በቅኝ ግዛት የደረሰብን የህሊና ጠባሳስ መቼ ሻረልን?” አለ በኩራት ፊቱን ወደ ቤልጂየሙ ንጉሥ እያዞረ!
‹‹ወገኖቼ የዛሬውን የነፃነት መታሰቢያ ቀን ለዘላለም በልባችሁ አትማችሁ አኑሩት፡፡ በኩራት ወደ ልጆቻችሁ አስተላልፉትና የትግል ታሪካችንን ዘክሯቸው፡፡ አሁን የነፃይቱ ኮንጎ ሪፐብሊክ በመታወጁ መሬታችን የልጆቻችን ሆኗል፡፡ ማኀበራዊ ፍትህ በማስፈን የሀገሪቱ ልጆች በተፈጥሮ ሃብታችን ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንሰራለን፡፡›› በማለት ያቀረበው ንግግር የአዳረሹን ሕዝብ ብቻ አይደለም መላውን ዓለም አስደመመው።
የቤልጂየሙ ንጉሥ የሉሙምባን ንግግር በክብራቸው ላይ የተቃጣ የስድብ ውርጅብኝ አድርገው ስለቆጠሩት ተበሳጭተዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር በሉሙምባ ላይ አቂመው ወዲያዉኑ ወደ ሀገራቸው እንደተመለሱ ይነገራል፡፡ ቤልጅየምም እንደ ሀገር ሉሙምባን እንደ ዋና ጠላት ፈረጃ ቀን እስኪገጥማት ታደባው ጀመር፡፡ በቦታው የነበሩ አንዳንድ የምዕራቡ ዓለም ጋዜጠኞችም በሉሙምባ ጠንካራ ንግግር መደናገጣቸው አልቀረም፡፡ ትክክል እንዳልሆነም በየፊናቸው የተቹም አልጠፉም፡፡
የኮንጎዋዊያንን አንጀት ግን አርሷል።
በሌላ በኩል ይህን የዓለምን ጆሮ ጭው ያደረገ ታሪካዊውን የሉሙምባ ንግግር በመድረኩ የተገኘውንም ሆነ በኮንጎ መገናኛ ብዙኃን የተከታተለውን የሀገሩ ዜጋ ሁሉ በፊት የደረሰበትን ግፍ በማስታወስ ስሜቱ ተነክቶና ቁጭት ውስጥ አስገብቶት እንደነበር ይነገራል፡፡ በመሆኑም ሕዝቡ ከአስከፊ የቅኝ ግዛት ቀንበር ነፃ በመውጣቱ በሆቴልና መሰል የመዝናኛ ስፍራዎች ደስታውን በሀገርኛው ዳንስና ጭፈራ ሲገልጽና ሲፈነጥዝ አመሸ። ውሎ አድሮ ግን ይህ በመስዋዕትነት የተገኘው ነፃነት ዘላቂ ሊሆን አልቻለም፡፡
… ይቀጥላል
(መሠረት ቸኮል)
በኲር የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም