የኮንጎዉ የነፃነት ኮከብ

0
150

~ ካለፈው የቀጠለ

በኮንጎ የነፃነት ታሪክ ፓትሪስ ሉሙምባ ሰፊ ድርሻ አለው። ኮንጎም ለዘላለም የማትረሳው ባለውለታዋ መሆኑን በክፍል አንድ አስነብበናል። ቀጣዩ የመጨረሻ ክፍልም እንደሚከተለው ቀርቧል።

የነፃነት ታጋዩ ፓትሪስ ሉሙምባ ተዝቆ ከማያልቀው የማእድን ሀብት ያገለላቸው  ቅኝ ገዥዎች ሌላ ሴራ መጎንጎን ጀመሩ፡፡ የካታንጋ ግዛት አስተዳደሪ የመገንጠል ጥያቄ እንዲያነሳ ገፋፉት፡፡

ብዙም ሳይቆይ ሐምሌ 11 ቀን 1960 ዓ.ም በሀገሪቱ የተፈጠረውን ትርምስ መጠቀም የፈለገው የካታንጋው መሪ ሞይስ ቾምቤ፤ በተፈጥሮ ሃብት የበለፀገችውን ካታንጋን ይዞ መገንጠሉን  አስታወቀ፡፡ ለማዕከላዊው መንግሥት የሚከፍሉትን ግብር እና ማንኛውንም ግንኙነት ማቋረጣቸውንም በይፋ ገለጸ፡፡

ሌሎች በኮንጎ ግዛት ስር የነበሩ ክልሎችም ተገንጥለናል የሚል አዋጅ አስነገሩ፡፡ በዚህ ወቅት ኮንጎ ለአራት መንግሥቶች ተከፋፈለች፡፡ ሆኖም በካሳቩቡና ሞቡቱ ሴሴኮ የሚመራው ሊዮፖልድቪል እና በሉሙምባ ደጋፊዎች የቆመው ስታንሊቪል በጋራ የተባበረች ኮንጎን ለማስቀጠል ፍላጎት ነበራቸው፡፡

በሞይስ ቾምቤ የሚመራው የካታንጋው ግዛተ-መንግሥት መቀመጫውን በኤልዛቤትቪል በማድረግና የደቡብ ካሳይ ግዛት ደግሞ በአልበርት ካሎንጂ መሪነት መቀመጫውን በባክዋንጋ ከተማ በማድረግ የራሳቸውን መንግሥታት መሰረቱ፡፡ በተለይ እነዚህ ሁለቱ ክፍለ ግዛቶች በሃገሪቱ በተፈጥሮ ሃብት የበለጸገ መልካምድር አላቸው፡፡ ነገር ግን ከኮንጎ አንድነት ይልቅ በተቃራኒው የየራሳቸውን መንግሥታት ለመመስረት የሚሹ ግዛቶች ነበሩ፡፡

ቤልጂየሞችም ለሉሙምባ ዋነኛ ተቀናቃኝና የካታንጋን የመገንጠል እንቅስቃሴ ለሚመራው ሞይስ ቾምቤ ድጋፍ ለመስጠት ያለመ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመሩ፡፡ በዚህ ቅር የተሰኘው ሉሙምባ የቤልጂየምን አምባሳደር ከሀገር እንዲወጣ ትዕዛዝ በማስተላለፍ ከቤልጂየም ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ማቋረጡን አስታወቀ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ሉሙምባ ቤልጂየም በኮንጎ አመጽ እያፋፋመች መሆኑን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አመለከተ፡፡ የቤልጂየም ወታደሮች በሀገሪቱ አመጽ በማቀጣጠል፣ የመገንጠልና ሀገር የመበታተን ሴራ ውስጥ በመሳተፋቸው ሀገር ለቀው እንዲወጡና በምትኩም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲተካ፤ በካታንጋ አመጸኞች ላይ ደግሞ እርምጃ በመውሰድ ሀገሪቷን እንዲያረጋጉ ጠየቀ፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት በበኩሉ የሉሙምባን ጥያቄ በመቀበል በሀገሪቱ ቀውሱ እንዳይባባስ የቤልጂየም ወታደሮች ከኮንጎ ወጥተው በተባበሩት መንግሥታት ወታደሮች እንዲተካ ውሳኔ አሳለፈ። ነገር ግን ተግባራዊ ሳይሆን ቀረ።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በምዕራባውያንና በአፍሪካ ሀገራት ድጋፍ የተነፈገው ሉሙምባ በመጨረሻም ደፍሮ ፊቱን ወደ ምሥራቁ ዓለም በማዞር የቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረትን እርዳታ ጠየቀ፡፡ ይህ ሁኔታ ከፕሬዚደንቱ ጆሴፍ ካሳቩቡ፣ ከካቢኔ ሚኒስትሩ ጆሴፍ ዲ ዛየር ሞቡቱ እንዲሁም ከአሜሪካና ከቤልጅየም ጋር ይበልጥ አቃቃረው።

የሉሙምባ ሶቭየት ኅብረትን ድጋፍ የመጋበዝ ጥሪ የውስጥና የውጪ ጠላቶቹ ኅብረት ፈጥረው እንዲበረቱ መንገድ ጠርጓል፡፡ ከዚህ በኋላ ሉሙምባ ብቻውን ተነጥሎ ከዕለት ዕለት በወዳጆቹና በባልደረቦቹ እየተከዳ ሀገር ለማስተዳደር አቅም እስከማጣት ደርሷል፡፡ በመጨረሻም ተሳዳጅ መሆን ጀመረ፡፡

መስከረም 5 ቀን 1960 ዓ.ም ሉሙምባ በሀገሩ ለተፈጠሩ ችግሮች መፍትሄ በማፈላለግ ላይ እያለ ፕሬዚደንት ካሳቩቡ ከጌታው የቤልጅየም ጠቅላይ ሚኒስትር በቴሌግራም በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት በሀገሪቱ ሬዲዮ ጣቢያ ባደረገው ንግግር ሉሙምባና ስድስት ሚንስትሮች ከሥራ መታገዳቸውን አስታወቀ፡፡

የሥልጣን ጥመኛው ሞቡቱ ሴሴኮ ሉሙምባን “ለኮንጎ ሕዝብ ዕልቂት ጥፋተኛ ነው” በሚል ፈረጀው፡፡ ሉሙምባን በመደገፍ የሚታወቁት ማውሪስ ምፖሎና ጆሴፍ ኢኪቶ የተባሉ ፖለቲከኞችም ክስ ቀረበባቸው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ወዲያዉኑ ለካሳቩቡና ኮሎኔል ሞቡቱ መንግሥት እውቅና መስጠቱን አስታወቀ፡፡ ጆሴፍ ሞቡቱ ሴሴኮ በባልደረቦቹና በወዳጆቾቹ መከዳት ተነጥሎ ብቻውን የቀረውን ሉሙምባ በመኖሪያ ቤቱ እንዳለ በወታደሮቹ አሳገተው፡፡

ሀገሪቱ በወታደራዊው መሪ ጆሴፍ ሞቡቱ ቁጥጥር ስር ከወደቀች በኋላ የነፃነት ታጋዩ ሉሙምባ  የቤት ውስጥ እስረኛ እንዲሆን ተደረገ፡፡ ሉሙምባ በሞቡቱና በተባበሩት መንግሥታት ወታደሮች በቁም እስር ከቆየበት ከመኖሪያ ቤቱ እንዳያመልጥ ይጠበቅ ነበር፡፡

የፓትሪስ ሉሙምባ ለሁለት ወራት በተንኮል  መታሰር ያሳሰባት ሶቭዬት ኅብረት ሉሙምባ እንዲፈታ ለተባበሩት መንግሥታት ጥያቄ ብታቀርብም ሰሚ ጆሮ አላገኘችም፡፡ የኮንጎ የነፃነት ምልክት ተደርጎ የሚቆጠረው ሉሙምባ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት እንዳለው የሚያውቁት ቤልጂየምና አሜሪካ ሉሙምባን ከስልጣን በማውረድ ብቻ አልረኩም፡፡ በቶሎ ገድለው ለሌሎች የአፍሪካ የነፃነት ታጋይ መሪዎች መማማሪያ ለማድረግ ነበር የቋመጡት፡፡

ፓትሪስ ሉሙምባ ከታሰረበት ኪንሻሳ 2000 ኪሎ ሜትር በምትርቀው ኪሳንጋኒ (ስታንሊቪል) ከተማ የሞቡቱ ሴሴኮን መፈንቅለ መንግሥት በመቃወም የሉሙምባ ደጋፊዎች “የኮንጎ ነፃ ሪፐብሊክ” በሚል ስም አማራጭ መንግሥት መሥርተው ነበር፡፡ ይህ መንግሥት በወቅቱ የሶቭዬት ኀብረትንና የቻይናን ዕውቅናም አግኝቶ ነበር፡፡

ዙሪያውን በጠላቶቹ የተከበበው ሉሙምባ አንድ አማራጭ ብቻ ታየው፡፡ ይኸውም ጠንካራ ደጋፊዎቹ ወዳሉበት “ስታንሊቪል” በማምለጥ ሕዝቡን ለትግል ማንቀሳቀስ እንደሚችል ተሰማው፡፡ በመሆኑም ህዳር 27 ቀን 1960 ዓ.ም ከሚጠብቁት ወታደሮች እጅ አምልጦ በተዘጋጀለት መኪና ከሚስቱና ልጆቹ ጋር በድብቅ ጉዞ ጀመረ፡፡ ይሁንና ስለ ሁኔታው ሞቡቱ ሴሴኮ በደረሰው መረጃ መሰረት ከተባበሩት መንግሥታት ሄሊኮፕተር በመዋስ ታማኝ ወታደሮቹን በመያዝ ሉሙምባን ማደን ጀመረ፡፡ ሆኖም ከአራት ቀናት ፍለጋ በኋላ ታህሳስ 2 ቀን 1960 ዓ.ም ሉሙምባ የሳንኩሩን ወንዝ በመሻገር ላይ እያለ በሞቡቱ ወታደሮች በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡

የአያያዙ ነገር እንዲህ ነው! የነፃነት ታጋዩ ሉሙምባ ሚስቱንና ልጁን ተሰናብቶ በጀልባ ማምለጥ ሲጀምር ከአፍታ ቆይታ በኋላ ሚስቱና ልጁ በጥቁር ኮንጓውያን ወታደሮች በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡ ሆኖም ሉሙምባ በቅርብ ርቀት ሆኖ የሚደርስባቸውን ወከባና እንግልት እያየ መታገስ ባለመቻሉ ወደ ኋላ በመመለስ እጁን ሰጠ፡፡ ጥቁር ወታደሮቹ ሉሙምባን እንደያዙት በሰደፍና ባገኙት ነገር እየተቀባበሉ ክፉኛ ደበደቡት፡፡  እጁን ወደኋላ በገመድ አስረው መኪና ላይ በመጫን ወደ ኪንሻሳ መለሱት፡፡ ከዚያም ከኪንሻሳ 600 ማይል ርቀት ላይ ወደ ሚገኘው ታስቪል ወታደራዊ እስር ቤት ተላከ፡፡ በዚሁ እስር ቤት ለስድስት ሳምንታት እስር ላይ እያለ በርካታ ደብዳቤዎችን ለፖለቲካ መሪዎች፣ ለቤተሰቡ እና ለጓደኞቹ ሁሉ ሀገሪቱ ስላለችበት ሁኔታ እና የወደፊት የሀገሪቱ መፃኢ እድል አስመልክቶ ጽፏል፡፡

እንዲሁም ለተባበሩት መንግሥታት እየደረሰበት ካለው ስቃይ እንዲታደጉት የሚማጸን ደብዳቤ ልኮ ነበር፡፡

ጥር 13 ቀን 1961 ዓ.ም ፓትሪስ ሉሙምባ ከታሰረበት ታስቪል ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ የሚገኙ ወታደሮች በደሞዝ ማነስ ምክንያት አመጽ አስነሱ፡፡ ሉሙምባ እስር ቤት ሆኖ ከውጭ ደጋፊዎቹ ጋር በደብዳቤ ይገናኝ እንደነበር በመወራቱ እና በደጋፊዎቹ እርዳታ ሊያመልጥ እንደሚችል ስጋት በመፍጠሩ ሉሙምባ እና አብረውት የታሰሩ ሌሎች ሁለት ሚንስትሮቹን ከእስር ቤቱ በማውጣት በገዳይ ቡድኖች ታጅበው ወደ ካታንጋ ግዛት ተወሰዱ፡፡

የኮንጎ ነፃ አውጭ ታጋይ ፓትሪስ ሉሙምባን ከወታደራዊ ካምፕ እስር ቤት አውጥተው የሕይወት ዘመን ጠላቱ ለሆነው ሞይስ ቾምቤ የመስዋዕት በግ አድርገው በማቅረብ የመግደሉንም ኃላፊነት የካታንጋ ባለስልጣናት  እንዲወስዱ በማሰብ ወደ ኤልሳቤትቪል (ያሁኗ ሉቡምባሺ) ከተማ ወሰዱት፡፡ ፓትሪስ ሉሙምባ ከሁለቱ ተከሳሽ ጓዶቹ ጋር በአውሮፕላን በሚጓዝበት ወቅት በቤልጂየም ቅጥረኛ መኮንን ወታደሮች ለበርካታ ሰዓታት በደረሰበት ከባድ ድብደባ እና ስቃይ በጣዕረ ሞት ውስጥ ይገኝ ነበር፡፡

ከበርካታ መሳለቅ እና ድብደባ በኋላ በቤልጂየማውያን የካታንጋ ፖሊስ ኮሚሽነሮች አስተባባሪነት ሶስት አልሞ ተኳሽ ወታደሮች ተዘጋጁ፡፡ ጥር 17 ቀን 1961 ዓ.ም ፓትሪስ ሉሙምባና ጓዶቹ በምሽት ጥቅጥቅ ወዳለው የኮንጎ ጫካ ተወሰዱ፡፡ በጫካው ውስጥ ከደረሱ በኋላ የተዳከመ አካላቸውን ከተሽከርካሪ እየጎተቱ አውርደው ከሉሙምባ ጋር የተከሰሱ ሁለት ባለስልጣናትን በማስቀደም ከዛፍ ግንድ ጋር አስረው ተራ በተራ ገደሏቸው፡፡ ገዳዮቹ በመጨረሻም ፊታቸውን ያዞሩት የድርጊቱ ማሳረጊያ ወደ ሆነው የነፃነት ታጋዩ ፓትሪስ ሉሙምባ  ነበር።

ለደቂቃ እንኳ አቋሙ የማይዛነፈው ፓትሪስ ሉሙምባ እንደ ጓደኞቹ  ዛፍ ላይ በማሰር   በጥይት ደብድበው ገደሉት፡፡ አስገራሚው ነገር ደግሞ በግድያው የካታንጋው ግዛት መሪ ሞይስ ቾምቤ እና ሁለት ሚኒስትሮቹ በተመልካችነት መገኘታቸው ነበር።

… ይቀጥላል

(መሠረት ቸኮል)

በኲር የካቲት 17  ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here